Sunday, 21 July 2019 00:00

“የታሪክ ትምህርት ለሕሙም አዕምሮ ፍቱን መድኃኒት ነው”

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(1 Vote)

 “ቲተስ ሊቪ (Titus Livy) የተባለ የታሪክ ሊቅ “የታሪክ ትምህርት ለታመመ አእምሮ ፍቱን መድኃኒት ነው” ይላል፡፡ ሊቪ ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረና የሮማን እና የሮማውያንን ጥንታዊ ታሪክ የጻፈ የታሪክ ተመራማሪ ነው፡፡ የሉቪ አባባል ሙሉ ሃሳብ እንዲህ የሚል ነው “የታሪክ ጥናት ለሕሙም አዕምሮ ፍቱን መድኃኒት ነው:: ምክንያቱም ታሪክ ውስጥ ወሰን አልባ ልዩ ልዩ የሰው ልጅ ተሞክሮዎች ሁሉም ሰው ያያቸው ዘንድ ፍንትው ብለው ተሰንደው ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በዚያ የታሪክ መዝገብ ውስጥ ራስዎንና ሀገርዎን፤ ምሳሌዎችንና ማስጠንቀቂያዎችን እንዲሁም አርዓያ የሚሆኑ በጎ ነገሮችንና ፍጹም ሊወገዱ የሚገባቸው ጸያፍ ተግባራትን ያገኛሉ” ይላል ሊቪ፡፡ በዛሬዋ ጽሁፌ የማተኩረው በዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ነው፡፡ የጣሊያናዊውን የታሪክ ምሁር እድሜ ጠገብ አባባል የጽሁፌ መንደርደሪያና ማጠናከሪያ አድርጌ አስቀድሜ ያቀረብኩትም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
የፈላስፋው ሊቪን ዘመን ተሻጋሪ መልዕክት በወጉ የተገነዘቡ አንጋፋዎቹ የኢትዮጵያ ምሁራን፣ ስርዓተ ትምህርት ቀርጸው የታሪክ ትምህርት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡ በዚህም መሰረት በዛሬው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የታሪክ ትምህርት ክፍል (Department of History) የተከፈተው እ.ኤ.አ በ1964 ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የታሪክ ትምህርት ለሁሉም የዩኒቨርስቲው የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች በጋራ ትምህርትነት (Common Course) ይሰጥ ነበር፡፡ ይህም እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ ዘልቋል፡፡
ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ስልጣን እንደጨበጠ ከወሰዳቸው የመጀመሪያ እርምጃዎች አንዱ፤ “የትምክህተኞች ጎራ” ብሎ የፈረጀውን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ማፍረስ ነበር፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ 42 ተኪ የሌላቸው አንጋፋ ምሁራንን በማባረር ነበር እርምጃውን የጀመረው፡፡ ያን ካደረገ በኋላ “ኢትዮጵያ የ100 ዓመት ታሪክ ነው ያላት” የሚል ትርክት አመጣ፡፡ ኢህአዴግ በዚህ አልረካም፡፡ በምርጫ 97 ህዝቡ ከጫፍ እስከ ጫፍ በመንቀሳቀስ ኢህአዴግን በምርጫ ካርዱ ቀጣው፡፡ ይህንን ያየው ኢህአዴግ፤ “የትምክህት ጎራው አሁንም አለ ማለት ነው” በሚል ስሌት፣ ቀደምት ምሁራኑን ካባረር ከአስር ዓመታት በኋላ ሌላ ዘመቻ ከፈተ፡፡ የታሪክ ትምህርት በዩኒቨርስቲው እንደ አንድ የሙያ መስክ ይሰጥ እንጂ ለማንኛውም የዩኒቨርስቲ ተማሪ በጋራ ትምህርትነት (ኮመን ኮርስ) እንዳይሰጥ አገደ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ስልጣን ላይ ከወጡ ወዲህ በከፍተኛ ትምህርት ዙሪያ ከተወሰዱት ጠቃሚ እርምጃዎች አንዱ “የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚጠበቅባቸውን ዓላማ ለማሳካት እንዲችሉ የስርዓተ ትምህርት ክለሳ” ለማድረግ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት ጥናቶች መደረጋቸው ነው፡፡ እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው “ጥናቱ የሚደረገው በምን ጉዳይ ላይ ነው? ጥናቱንስ የሚያካሂደው ማን ነው?” የሚሉት ጥያቄዎች ናቸው፡፡
ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ቅርበት ያላቸው ምንጮቼ በላኩልኝ መረጃ መሰረት፤ ጥናቱ የተካሄደው “የአንደኛ ዓመት የጋራ ኮርሶች ሲለበስ” በሚል ጉዳይ ዙሪያ ነው:: “ኮመን ኮርስ” ሆነው ለሁሉም ተማሪዎች እንዲሰጡ ጥናት እንዲደረግባቸው የተመረጡት አስራ አንድ የትምህርት ዓይነቶች ናቸው፡፡ እነሱም፡- “ኢኮኖሚክስ፣ ኢንተርፕረነርሺፕ፣ እንግሊዝኛ፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ ሎጂክ፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ ሂሣብ፣ ስፖርት፣ ሳይኮሎጂ እና ቴክኖሎጂ” የተሰኙ የትምህርት ዓይነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ኮርሶች ለሁሉም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲሰጡ መታሰቡ መልካም ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ጥናት መደረጉም ችግር የለውም፡፡ ችግር የሚነሳው ጥናቱን ባደረጉት ዩኒቨርሲቲዎች አግባብነት ዙሪያ ላይ ነው፡፡
ከጋራ ትምህርት ዓይነቶች (ኮመን ኮርሶች) ውስጥ በታሪክ ትምህርት አዘጋጆች አግባብነት ላይ በዚህ ጽሁፍ ትኩረት አደርጋለሁ፡፡ የታሪክ ትምህርት ላይ ትኩረት ያደረግሁት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ታሪክን አለመማር ዛሬ በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ ችግሮች ምክንያት መሆኑን ምሁራን እየተናገሩ ስለሆነ ነው:: ዛሬ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች ከ“ብሔርተኝነት” ወደ “እብሪተኝነት” (from nationalism to irationalism ) የተሸጋገሩት እኮ የሀገራቸውን የፖለቲካ ታሪክ፣ የኢኮኖሚና የባህል ታሪክ፣ የማህበራዊ ግንኙነት ታሪክ በአግባቡ ባለማወቃቸው ነው እየተባለ ነው፡፡ ጠባብ ፖለቲከኞች “ከክልሌ ውጣ” የሚል ስውር ሴራ ጎንጉነው ህዝብን ያፈናቀሉት የባህል እሴቶቻችንን፣ የሃይማኖት እሴቶቻችንን፣ አብሮ የመኖር ትስስራችንን ባለመማራቸው ነው እያሉ ነው፤ የማህበራዊ ሣይንስ ተመራማሪዎች፡፡
የታሪክ ትምህርትን በተመለከተ ጥናት እንዲያደርጉ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተመረጡት “መቱ፣ ቡሌ ሆራ፣ አርሲ፣ አዲግራት፣ ወልቂጤ፣ ወልዲያ፣ ዋቻሞ፣ ደብረ ታቦርና ኦዳ ቡልቱም” ዩኒቨርስቲዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ዩኒቨርስቲዎች በቅርብ ዓመታት የተቋቋሙ፣ ልምድ የሌላቸው ዩኒቨርስቲዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ዩኒቨርስቲዎች ታሪክን የሚያስተምሩት ሌክቸረሮችን ከትልልቆቹ ዩኒቨርስቲዎች በውሰት እየወሰዱ ነው፡፡ እናም እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው መሰረታዊ ጥያቄ፤ “ዩኒቨርስቲዎቹ በቂ የታሪክ ምሁራንን ሳያፈሩ፣ በቂ ልምድ ሳይኖራቸው ጥናቱን እንዲያደርጉ የተመረጡበት መስፈርት ምንድነው?” የሚል ነው፡፡
የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች እንደ አመሰራረታቸው “የመጀመሪያ ትውልድ፣ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ ትውልድ” (First, second, third Generation) የሚል ደረጃ እንደተሰጣቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ደረጃ የተሰጣቸው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በበኩሌ የአመሰራረታቸውን ቅደም ተከተል ለማመላከት እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ተቋማት እንደ ሰው ናቸው:: የዛሬ 10 ዓመት የተመሰረተ ተቋም፤ዘንድሮ ከተመሰረተው የተሻለ ልምድና ተቋማዊ ከፍታ እንደሚኖረውም ይታመናል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከሁሉም የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ደረጃ አንጋፋ ነው፡፡ በአፍሪካ ደረጃ የሚፎካከረው ተቋም ስለሌለ “የሰሃራ በታች ሃርቫርድ” (The Harvard of Sub-Saharan Africa) ይባል ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራንም አንጋፋነታቸው አሌ የሚባል አይደለም፡፡ አንጋፋዎቹ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲና ዲላ ዩኒቨርስቲ እያሉ የታሪክ ትምህርትን ትናንት የተመሰረቱት እነ መቱ፣ ቡሌ ሆራ፣ አርሲ፣ አዲግራት፣ ወልቂጤ፣ ወልዲያ፣ ዋቻሞ፣ ደብረ ታቦር እና ኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲዎች ጥናት ለማድረግ ይመጥናሉ? አንጋፋዎቹ የታሪክ ምሁራን እነ ፕሮፌሰር ተሰማ ተኣ፣ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ፣… እያሉ ከባችለር ዲግሪ በላይ በማያስተምሩ አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች የሚያስተምሩ መምህራን ጥናት እንዲያደርጉ መመረጡስ አግባብ ነው? እንዲህ ያለው አካሄድ ትልልቆቹን ዩኒቨርስቲዎችና ቀደምት ምሁራንን ለማግለል የታለመ አይመስልም? ይሄ ደግሞ በ1984 የተጀመረው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ችግር ውስጥ የመክተት እኩይ እርምጃ ቀጣይ ምእራፍ አያስመስለውም? ታሪክን፣ ጂኦግራፊንና የመሳሰሉትን ትምህርቶች ሁሉም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲማሩ ማድረግ እንደ አሜሪካ ባሉ ባደጉትና በሰለጠኑት ሀገራት ዩኒቨርስቲዎች የተለመደ አሰራር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ጨለማ ውስጥ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ የራሷ ዩኒቨርስቲ አቋቁማ የታሪክ ትምህርት ታስተምር ነበር፡፡ “History of Ethiopia and the Horn” የተሰኘው ኮርስ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ በሁሉም ዘርፍ ለሚሰለጥኑ የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ ተማሪዎች በጋራ ኮርስነት ለግማሽ ምዕተ ዓመት መሰጠቱ ይታወሳል:: እንዲህ ዓይነቱ በብሔራዊ ታሪክ ቁልፍ ክንውኖች ላይ የተመሰረተ የጋራ ኮርስ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መስጠት በብዙ ሀገራት አካዳሚያዊ ታሪክ ውስጥ ነባር ተግባር ነው::
የሀገሩን ታሪክ፣ የሀገሩን መልክዓ-ምድራዊ ሁኔታ፣ የሀገሩን ኢኮኖሚ፣… ያላወቀ ዜጋ የተሟላ እውቀት፣ የተሟላ ሰብእና ሊኖረው እንደማይችል ስለሚታመን ነው እነዚህን ትምህርቶች ሁሉም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲማሯቸው የሚደረገው:: እነዚህ ኮርሶች “ብሄራዊ ንቃተ ኅሊናን” (National Consciousness) ለማሳደግ እንደሚረዱም ይናገራሉ፤ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይሰጥ የነበረው የታሪክ ትምህርት ይዘትን በተመለከተ ከቅድመ አክሱም ጀምሮ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ የተፈጸሙ ዋና ዋና ታሪካዊ ክንዋኔዎችን ለምሳሌ የአክሱምና ዛግዌ ስልጣኔ፣ የሰለሞናዊ መንግሥት ግንባታ፣ የመካከለኛው ዘመን እስላማዊ መንግሥታት ተዋጽዖና አስተዋጽዖ፣ የኢማም አሕመድ ኢብን ኢብራሒም (ግራኝ) ጂሐድ፣ የ16ኛው ክፍለ ዘመን የሕዝቦች እንቅስቃሴ (16th Century Population Movements)፣ ሀገር አቋራጭ የሲራራ ንግድ መስመሮችና የደቡብ ኢትዮጵያ ታሪክ (long-distance trade routes and the History of Southern Ethiopia) የዘመናዊት ኢትዮጵያን የመመስረት ሂደትና ተግዳሮቶቹን ወዘተ. ያካተተ፣ መሳጭና ተናግሮ አናጋሪ፣ አመራማሪና አስተማሪ ኮርስ እንደነበር ኮርሱን የወሰዱ ሁሉ የሚመሰክሩት ሀቅ ነው::
ሁላችንም የትናንት ዉጤቶች ነን:: ወደ ፊት ለመዝለል ወደ ኋላ መንደርደር የግድ ነው:: መምጫችንን ሳናውቅ ዛሬያችንን ጠንቅቀን ማወቅና ነጋችንን መተንበይ ከባድ ነው:: ታሪክ ትናንትናን መሰረት አድርገን ዛሬን የምናይበት፤ ነገን የምንተነብይበት የዕውቀት ዘርፍ ነው፡፡ “History is the study of the past to understand the present and forecast the future” እንዲሉ ፈረንጆቹ፤ ትናንት የዛሬ መስታዋት የነገ ነፀብራቅ ነው:: በትናንት፣ በዛሬና በነገ መካከል ጥብቅ ሳይንሳዊ ቁርኝት አለ:: ነገ ላይ ነገ ዛሬ ይሆናል፤ ዛሬም ትናንት ይሆናል::
ይህ አመራማሪና አስተማሪ “ታሪካዊ” የታሪክ ትምሕርት፣ምርጫ 97ን ተከትሎ ውዥምብር ዉስጥ በገባው ኢሕአዴግ፣ “በከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት ዉስጥ የተቀበረ አደገኛ ፀረ-መንግሥት አካዳሚያዊ ቦምብ” ተብሎ በመፈረጁ፣ እንደ ቅንጅት መሪዎች፣ ግዞት ተፈርዶበት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ስርዓተ ትምሕርት ዝርዝር ውስጥ በአሳዛኝ ሁኔታ እንዲወገድ ተፈረደበት:: በዚህም ምክንያት ለታሪክ ባይታዋር የሆነ ድንዙዝ ትውልድ (A generation that surffers from historical amnesia) ተፈጠረ፡፡ እነሆ! ዛሬ ታሪካዊ ስህተትም እየሰራ ነው፡፡
እናም ሀገራችን ከምንም በላይ የአስተሳሰብ አብዮት (Mental Revolution) ያስፈልጋታል ተብሎ በሚታሰብበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ ይህን “ታሪካዊ” የታሪክ ኮርስ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ስርዓተ ትምሕርት ለመመለስ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኖንስቴር የተወሰደው “ታሪካዊ” እርምጃ ይበል የሚያሰኝ ነው:: ይሁን እንጂ ጥናቱ አግባብ በሌለው ባለሙያ፣ ልምድ በሌለው ዩኒቨርስቲ እንዲጠና አድርጎ በሁለት ቀናት “ቫሊዴሽን ዎርክ ሾፕ” (ሐምሌ 11 እና 12) ለማጽደቅ ከየዩኒቨርስቲው ተሰባሰቡ ብሎ ጥሪ ማድረግና መጣደፍ ከልማቱ ጥፋቱ የሚበልጥ መሆኑን አስረግጨ ለመናገር እወዳለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው:- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 5941 times