Saturday, 20 July 2019 12:07

“ፋብሪካው ያንተ ነው፤ ያረፈበት ቦታ ግን ያንተ አይደለም”

Written by  አሰፋ አዳነ (ዶ/ር)
Rate this item
(3 votes)

 - “ለተፈፀመብን ግፍና እንግልት ህዝብ ይፍረደን”
     - “ፋብሪካውን ውሰዱት፤ መሬቱ ግን የሻጩ ነው”
           
    በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘውን ጌትእሸት ዲተርጀንትና ማሸጊ የፋብሪካን በህዳር ወር 2005 ዓ.ም ከገዙ በኋላ ከሻጩ ሻምበል ጌታቸው እሸቱ ጋር ያላሰቡት ውዝግብና እሰጣ ገባ ውስጥ መግባታቸውን የሚገልፁት የገዢው የዶ/ር በውቀቱ ታደሰ ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር አሰፋ አዳነ፤ በሻጭ በሻምበል ጌታቸውና በፍትህ ሥርዓቱ ከፍተኛ በደል ደርሶብናል የሚሉት ዶ/ር በውቀቱ ታደሰ አሁን በእስር ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል:: የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሀቁን ተመርኩዞ ቢፈርድላቸውም በይግባኝ ሰሚና በሰበር ሰሚ ችሎት እንደገና ያልተገባ ፍርድ ተፈርዶብናል ብለዋል፡፡ ለመሆኑ በፋብሪካው ሻጭና ገዢ መካከል የተፈጠረው ችግር ምንድነው አሁንስ ጉዳዩ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል ገዢው ዶ/ር በውቀቱን ለእስር የዳረጋቸውስ ምንድነው? በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ተበዳይ ነኝ ከሚሉት ገዢ ዶ/ር በውቀቱ ታደሰ ከፍተኛ አማካሪና የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አሰፋ አዳነ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡


    በላቦራ ኢንተርናሽናል ኃ.የተወሰነ የግል ኩባንያ ውስጥ ኃላፊነትዎ ምንድን ነው?
በድርጅቱ ውስጥ የዋና ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ዋና አማካሪ ነኝ፡፡ አጠቃላይ ሥራዎችን እከታተላለሁ፤ አማክራለሁ፡፡ በተጨማሪም የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢም ሆኜ አገለግላለሁ:: የድርጅቱ ዋና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር በውቀቱ ታደሰ ሲሆኑ፤ ም/ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ደግሞ ባለቤታቸው ወ/ሮ መሰረት በረደድ ናቸው፡፡ ኩባንያው የተመሰረተውም በሁለቱ ግለሰቦች ነው፡፡
እኔ እንግዲህ ከአማካሪነቱና ከቦርድ ሰብሳቢነቱም በተጨማሪ ዶ/ር በውቀቱ ሥራ ሲበዛባቸውና ጫና ሲያጋጥማቸው እሳቸውን በመተካት እንደ ማኔጂንግ ዳይሬክተርም እሰራለሁ፡፡
ኩባንያው የተቋቋመው መቼ ነው? የተሰማራበት የስራ ዘርፍስ ምንድን ነው?
ላቦራ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ የተቋቋመው በ1991 ዓ.ም ሲሆን፤ በዋናነት የተሰማራበት ስራ የተለያዩ እቃዎችን ከውጭ ማስመጣት ነው፡፡ አንዳንዴ የቅባት እህሎችን ኤክስፖርት ያደርጋል:: በአብዛኛው ግን የህክምና መሳሪያዎችን ለምሳሌ፡- ኤክስሬይ፣ አልትራሳውንድ፣ ኢንዶስኮፒና የተለያዩ የላብራቶሪ እቃዎችን እንዲሁም የላብራቶሪ ሪኤጀንቶችን ማስመጣትና ማከፋፈል ነው ዋና ሥራው፡፡
በ2005 በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘውን ጌት እሸት ዲተርጀንትና ማሸጊያ ፋብሪካን ከገዛችሁ በኋላ ከሻጭ ጋር ከፍተኛ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባታችሁን ተረድቼአለሁ፡፡ የዚህ ሁሉ ውዝግብ መንስዔው ምንድን ነው?
እንግዲህ “ጌትእሸት ዲተርጀንት ፋብሪካና ማሸጊያ” የተገዛው በ2005 ዓ.ም ነው፡፡ እርግጥ ነው ከግዢው በፊት ማለትም በ2003 ዓ.ም በአማካሪነት እንድንሰራ ባለቤቶቹ እነ ሻምበል ጌታቸው እሸቱ ጠይቀውን፣ እኛም ማኔጅመንቱንና ምርቱን ወስደን በራሳችን ገንዘብ ልንሰራ ውል ገብተን ነበር:: በዚህም መሰረት ይህንን ማኔጅመንት በተሻለ መልኩ ለማደራጀት የተሻለ ሰው ያስፈለጋል ብለን ስላመንን ከህንድ አቅራቢዎቻችን ውስጥ አንዱን ስናማክረው፤ “ይሄ ትልቅ ሀሳብ ነው” ብሎ ፋብሪካውን መጥቶ አየው፡፡ በጣም ጥሩ በሆነ ቦታ ለትራንስፖርት በሚያመች ሁኔታ ላይ ነው ፋብሪካው ያለው ይሄንን በደንብ እንሰራበታለን አለን፤ ከዚያም ውል አደረግን:: ልንሰራ ውል ስናደርግም ዝም ብለን አይደለም፡፡ ይሄ ከእኛ ጋር ሊሰራ የፈለገው የውጭ ድርጅት ወደ 200ሺህ ዶላር ገደማ በጌት እሸት አካውንት ገቢ አድርጓል፡፡ ይሄንን ከባንክ ስቴትመንቱ ማግኘት ይቻላል፡፡
እሺ ይቀጥሉ?
ከዚያ ያ ገንዘብ ከገባ በኋላ ምንም የተሰራ ነገር የለም፡፡  ፋብሪካው ብዙ የጐደሉት ነገሮች ስለነበሩ፤ ገንዘቡ እንደገባ እኛ በፈለግነው መንገድ ሥራ ለመጀመር የሚያመች አልነበረም:: በዚህ መሃል እያለን “እንዲያውም ለምን ፋብሪካውን አትገዙትም?” የሚል ጥያቄ ከባለቤቶቹ ቀረበልን፡፡ ጥሩ እንገዛዋለን አልንና፤ ሙሉ በሙሉ ፋብሪካውን ለመግዛት በ22.5 ሚሊዮን ብር ተስማማን:: ፋብሪካው ያረፈው በ3ሺህ 15 ካ.ሜ ቦታ ላይ ነው:: ፊት ለፊቱ ትንሽ የተቆፈረና ጅምር ህንፃ አለ፡፡ ይሄ ቦታ ደግሞ 8 ሺህ 290 ካሬ ሜትር ነው:: በአጠቃላይ 11ሺ 300 ካ.ሜትር አካባቢ ነው የገዛነው ከነፋብሪካው ከነቦታው ማለት ነው፡፡ በኋላ ስናየው ግን ትንሽ ችግር ነበረበት፡፡ ችግሩ ምንድን ነው ካልሽኝ፤ ቦታው ሁለት ካርታ ነው ያለ ነው፡፡ 3015 ካ.ሜ ለብቻ፣ ሌላው 8ሺህ 290 ካሬው ለብቻ ካርታ ነበረው፡፡ እኛ ይሄን አናውቅም፡፡ ሁለቱም ቦታ የተያያዘና የአንድ ሰው ነው:: በነገራችን ላይ ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ፋብሪካው ካረፈበት እስከ ዋናው አስፋልት ድረስ የሱው ይዞታ ነው፤ ግን ቦታውን እየቆራረጠ፣ ካርታ ለየብቻው እያስወጣ ነው የሚሸጠው፡፡ እኛ ይህንን አናውቅም፡፡ ቦታው የአንድ ሰው ነው በሚለው ነው፣ ፋብሪካው ያለበትንና የፊት ለፊቱን ማስፋፊያ ጨምረን በ22.5 ሚ ብር ለመግዛት የተስማማነው፡፡ ከዚያ ወደ አከፋፈል ስንገባ፣ በምን መልኩ ይከናወን ወደሚለው ሄድን ማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ፋብሪካው 7 ሚ ብር የባንክ እዳ ነበረበት:: ባንክ በዚህ እዳ ምክንያት ሁለቱንም ካርታዎች ይዟል፡፡ 3015 እና 8290፡፡ ብድሩንም የሰጠው ለነዚህ ለሁለት ካርታዎች ነው፡፡ ልማት ባንክ ስለሆነ ብድሩን የሰጠው ይህንን ጉዳይ ባንክ ሄደን አረጋገጥን፡፡ ስለዚህ ይሄ 7 ሚ ብር ከዛን ጊዜ ጀምሮ ወደ እኛ እንዲዞር ተስማማን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለሻጭ ቅድሚያ ክፍያ ብለን 2 ሚ ብር በካሽ ከፈልን:: ጠቅላላ 9 ሚ. ብር ከፈልን ማለት ነው:: በዚሁ ሂደት የባንክ ብድር የመክፈያው ጊዜ (ግሬስ ታይም) ደርሷል ሲለን፣ እንደገና 2.9 ሚ ብር እዚያው ከፈልን፡፡ በጠቅላላ 9 ሚ ብር ስንከፍል፣ ከ22.5 ሚ ብሩ ላይ የሚቀርብን 13.5 ሚ ብር ይሆናል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ፋብሪካው ያልከፈለውና የቆየ 800 ሺህ ብር ታክስ ነበረበት፡፡ ይሄንንም ከፈልን:: ደረሰኙ ከሰነድ ጋር ተያይዞ ይገኛል፡፡ ይሄ 800ሺህ ብር ግን በውሉ ውስጥ የተካተተ አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ 9 ሚ ብር ከፍለን፣ 13.5 ሚ. ብር እዳ ይዘን ፋብሪካውን ተረከብን፡፡
ካርታውንስ አብራችሁ ተረከባችሁ?
አልተረከብንም፤ ምክንያቱም ካርታው ያለው በልማት ባንክ እጅ ነው፡፡ ባንኩ ደግሞ የሚያውቀን እኛን ነው:: ስምም የሚዞረው ካርታው ከባንክ እጅ ሲወጣና ባንኩ ያበደረውን ብር ወስዶ ሲጨርስ ነው፡፡ ግን ካርታው ጌትሸት ዲተርጀንት ስለተሸጠና እኛ ስለከፈልን የ7 ሚሊዮን ብር እዳውን በሙሉ ስንከፍል የሚሰጠን ለእኛ እንጂ ለሻጭ አይደም:: ይህ ከሆነ በኋላ ፋብሪካውን ወደ መጠጋገን፣ የጐደሉ እቃዎችን ወደ ማሟላትና ጥሬ እቃ ወደ ማቅረብ ሄድን፡፡ እንዲሁም ጥሩ ብቃት ያላቸው ኬሚስቶችና ሌሎች ባለሙያዎችንም ቀጠርን:: በፊት በፋብሪካው ይሰሩ የነበሩትን ስናያቸው ብዙም ብቃት ያላቸው ስላልነበሩ ነው፣ ብቃት ያላቸውን የቀጠርነው:: ከዚያ ጥሬ እቃ አሟልተን ወደ ምርት ገባንና የመጀመሪያውን ዙር አምርተን፣ ወደ ሁለተኛው ዙር ስንገባ ያልታሰበ እዳ መጣ፡፡
ምን ዓይነት ዕዳ?
ሻጭ መጣና “እኔ‘ኮ የሸጥኩላችሁ ፋብሪካውን እንጂ ፋብሪካው ያረፈበትን 3015 ካ.ሜትር አይደለም ብሎ ቁጭ አለ፡፡
ቅድም ሲነግሩኝ ግን ፋብሪካው ያረፈው 3015 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው ብለውኝ ነበር…?
ትክክል ነው፤ ፋብሪካው ያረፈበት ቦታ በካርታውም እንደሚታየው፤ 3015 ካ.ሜ ቦታው ላይ ነው፡፡ ይሄ ብዙዎችን ግራ የሚያጋባ ሆነ:: በጣም አስቸጋሪ የሆነው፣ ፋብሪካው አየር ላይ አልተገነባም፤ ይሄንን ፋብሪካ ነቅለን ወደ ሌላ ጥግ አስጠግተን አንሰጠው ነገር፣ ለሰሚ ግራ የሚያጋባ ችግር ነው የገጠመን፡፡ “እኔ የሸጥኩት ፋብሪካውን ነው፤ መሬቱን ስላልሸጥኩላችሁ እዚህ ማምረትም ሆነ መቀመጥ አትችሉም” ብሎ ከጥበቃ አቅራቢ ኤጀንሲዎች፣ የጥበቃ ሰራተኞችን አምጥቶ፣ እኛ ከፋብሪካው ጋር የተረከብናቸውን የራሱን የጥበቃ ሰራተኞች አባርሮ በቁጥጥሩ ሥር አዋለው:: እኛ ይሄንን ሰምተን ቦታው ላይ ስንሄድ፣ “አትገቡም ተመለሱ” ተባልን፡፡ “እኛ የጥበቃ ኤጀንቶች ነን፤ ሃላፊነት ወስደናል አናስገባችሁም” አሉን፡፡
ከዚያ በኋላ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ለመወሰን በማኔጅመንት ደረጃ ቁጭ ብለን ተነጋገርን:: ምናልባት ይሄ ሰውዬ (ሻጩ) ቦታው አጓጉቶት ዋጋ ሊጨምር ፈልጐ ሊሆን ይችላል ተባባልን፡፡ ውላችን ላይ ምን ተቀምጧል? በሻጭና በገዢ መካከል ችግር ቢፈጠር በ3ኛ ወገን ያልቃል የሚል አለና፣ ጉዳዩን በውሉ መሰረት፣ ሽማግሌ ልከን እልባት እናብጅለት በማለት ሽማግሌ ላክን፡፡
በሽምግልናው እኛ ምን አልን፤ “ግዴለም ብዙ ወጪ አውጥተናል፤ ብዙ ሂደት ተጉዘናል፤ ግን ይሄ ነገር ይቅርብን፤ እናም የባንኩን እዳ 7 ሚ ብር ወደ እኛ አዙረናል፤ ከዚህም መሃል 2.9ሚ ብር ለባንክ ከፍለናል፤ እንደገና 2 ሚ ብር ደግሞ ቅድሚያ ክፍያ ከአጠቃላይ 4.9 ሚ ብር ከፍለናል:: እሱን መልስልን፤ ውሉም ይፍረስና ንብረትህን ውሰድ:: ከማደስና እቃ ከማሟላት ውጭ ያደረግነው ነገር የለም” አልን፡፡ ነገር ግን እሱ “ይሄማ አይሞከርም” አለን፡፡
ሻጭ የሰጡት ምክንያት ምን ነበር?
ምንም ምክንያት አላቀረበም፤ ግን “ጭቅጭቅ አልፈልግም፤ በቃ ውጡ” የሚል ምላሽ ሰጠ፡፡ ከሽምግልና በኋላ ማድረግ ያለብን፣ ወደ ክስ መሄድ ነው፡፡ ነበር ወደ ምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አዳማ ሄድን፡፡ የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳያችንን በደንብ አየ:: የከፈልንበትን ደረሰኝ መረመረ፤ ቦታው ድረስ መጥተውም ጉዳዩን ተመለከቱ፡፡ እኛ ክስ ስናቀርብ ሻጭ ያቀረበው የክስ መቃወሚያ፤ 1ኛ ውሉ ህጋዊ ስላልሆነ ይፍረስልኝ 2ኛ እዚያ ግቢ ውስጥ የቆሙ ያረጁ ትሮሊ አውቶቡሶች ነበሩ፡፡ እነዚህ አውቶቡሶች እስከ ዛሬ በየቀኑ ብሰራባቸው አገኝ የነበረውን ጥቅም ስላሳጡኝ፣ በየቀኑ የሚያስገቡት ገንዘብ በነዚህ አመታት ታስቦ ይከፈለኝ፡፡ 3ኛ ውሉ ይፀናል የሚባል ከሆነ፣ በተዋዋልነው መሰረት፣ ገዢ የቀረበትን 13.5 ሚ ብር በአንድ ጊዜ ይክፈለኝ የሚል ነው፡፡
እነዚያ በፋብሪካው ግቢ ውስጥ የቆሙትን አውቶቡሶች ሻጭ እንዲያነሳ ጥያቄ አላቀረባችሁም ነበር? ሌላው ደግሞ ቀሪውን 13.5 ሚ. ብር በስንት ጊዜ ልትከፍሉ ነበር ከሻጭ ጋር የተስማማችሁት?
በጣም ጥሩ፤ ቀሪውን 13.5 ሚ ብር እየሰራን በአራት አመት ከፍለን ልናጠቃልል ነው በውላችን ላይ የተስማማነው:: በየአመቱ 3.75 ሚ ብር እየከፈልን እናጠቃልላለን ብለን፣ እሱም ተስማምቶ፤ በውሉ ላይ ተቀምጧል፡፡ ሌላው አውቶቡሶቹን በተመለከተ ላነሳሺው፣ ከአንድም አምስት ጊዜ ንብረቱን እንዲያነሳ በደብዳቤ ጠይቀነዋል:: እነዚህን አውቶቡሶች በአስቸኳይ እንዲያነሳ በተደጋጋሚ ወትውተናል:: ሆኖም ፈቃደኛ ሆኖ ማንሳት አልቻለም፡፡    
ለዚህም በተደጋጋሚ የተፃፉለት ደብዳቤዎች በማስረጃነት ይገኛሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ፣ ፍ/ቤት ሻጭ በክስ መቃወሚያነት ያቀረበውን፣ የእኛንም የክስ ጭብጥ ግራ ቀኝ ካየ በኋላ ፍርድ ሰጠ፡፡ ፍርዱ ምን ይላል፤ አንደኛ ውሉ በውልና ማስረጀ የተፈፀመ ስለሆነ የፀና ይሆናል፡፡ ሁለተኛ፤ በግቢው ውስጥ የቆሙ አውቶቡሶች እንዲነሱለት ገዢ በተደጋጋሚ በደብዳቤ የጠየቀና ምላሽ ያልሰጣችሁ በመሆኑ አሁንም መረጃ ባቀረባችሁ ጊዜ ከሸጣችሁት ንብረት ውጭ ያለውን መውሰድ የምትችሉ መሆኑን፣ ሶስተኛ፤ በውሉ መሰረት፤ በአሁኑ አመት ቀሪውን 13.5 ሚ ብር ገዢ እየሰራ ሊከፍላችሁ በውሉ የተስማማችሁ በመሆኑ አሁንም በውሉ መሰረት 3.75ሚ ብር እየተከፈለ ማለቅ ያለበት መሆኑን በአጠቃላይ ግን ውሉ የፀና ይሆናል በሚል ነው ፍርድ ቤቱ የፈረደው፡፡
ከፍርዱ በኋላ ፋብሪካውን ተረከባችሁ… ወይስ?
እኛማ በአፈፃፀም ፋብሪካውን ተረከብን፡፡ ነገር ግን ሻጭ በጣም ቅር ተሰኘ፤ ይግባኝም ጠየቀ፡፡ በይግባኝ ሰሚው መረጃ ሲጠየቅ፣ በስር ፍርድ ቤት እስከ ፍርድ የሄደው ፋይል ነው የሚቀርብለት፡፡ በዚህ  መሰረት፤ ቀርበን ክርክር ስናደርግ ቆየን አዳዲስ ተጨማሪ መረጃዎችንም አቀረብን፡፡ በነገራችን ላይ 2.9 ሚ ለባንክ ከ7 ሚ ብር ላይ ዕዳውን ከፍለን ነበር ብዬሻለሁ፡፡ ከዛ በኋላ ደግሞ ተጨማሪ 2.9ሚ በድምሩ 5.8 ሚ ብር የባንክ እዳ ከፍለናል፡፡ ከባንክ ዕዳው 1.2 ሚ አካባቢ ነበር የሚቀርብን፡፡ ይሄንን ሁሉ አደረግን ልማት ባንክም ይሄንን ያህል እዳ ከፍለዋል፡፡ ቦታውን በተመለከተ ፋብሪካው 3015 ካሬ ሜትር ላይ አርፏል ፊት ለፊቱ 8ሺህ 290ካሬ ሜትር አብሮት እንዳለ የቢሾፍቱ ከተማ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽ/ቤት በፃፈልኝ ደብዳቤ መሰረት አረጋግጫለሁ ብሎ በአባሪነት ጽፎልናል:: ይህን ሁሉ አቅርበን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት፣ በመጀመሪያ ውሉ የፀና ይሆናል ይላል፡፡ ቀጥሎ ነገር ግን ከተዋዋላችሁት 22.5ሚ ብር ለባንክ 2.9ሚ፣ ለሻጭ 2 ሚ ብር ከፍላችኋል፡፡ ጠቅላላ 4.9 ሚ ሲቀነስ ከ22.5 ሚ 17.5 ሚ ቀሪ አለባችሁና መክፈል አለባችሁ የሚል ፍርድ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ፈረደብን፡፡
ወደ እናንተ የዞረው 7 ሚ. ብር የባንክ እዳስ?
ፍርድ ቤቱም ተሳስቷል ብዬ የማምነው እዚህ ላይ ነው:: 17.65 ሚ ለሻጭ ክፈሉት፤ ፋብሪካውን ውሰዱ፤ ነገር ግን ፋብሪካው ያረፈበት መሬት የእሱ ነው፡፡ ተባልን:: ፋብሪካውን አንስታችሁ በፌስታል ክተቱና ውሰዱ ካልተባልን በስተቀር እንዴት ይሆናል?! አሳፋሪ ነገር ነው የተፈፀመብን:: ይሄም ብቻ አይደለም፡፡ 17.65 ብሩንም ከነወለዱ በአንዴ ክፈሉ ተባልን፡፡ በተጨማሪም ግቢው ውስጥ ለአመታት የቆሙት አውቶብሶች በቀን ሊሰሩ ይችሉ የነበረው ታስቦ በቆሙበት አመታት ለአመት ተባዝቶ፣ 39 ሚ ብር ስለሚመጣ፣ ይሄንንም ክፈሉ የሚል ፍርድ ነው የተፈረደብን፡፡ እንዲህ አይነቱን አይን ያወጣ ፍርድ ተመልከቺ፡፡ ይሄ ሁሉ ግፍ በአንድ ዜጋ ላይ እንዴት ይሆናል ብለን ግራ በመጋባት ወደ ሰበር ሄድን፡፡ ለምን? ግማሽ ቅሬታ አለን፡፡ ግማሽ ያልኩበት አንደኛ ውሉ የፀና ይሆናል ማለታቸው ያጽናናል፡፡ ሁለተኛ፤ ከፊት ለፊቱ ያለውን 8290 ካ.ሜ ቦታ አልነኩብንም:: ስለዚህ ግልጽ ማስረጃ አለን፡፡ በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የተፈፀመብን መሰረታዊ የህግ ስህተት ስላለ ሰበር ሰሚ ችሎት ያስተካክለዋል ብለን ወደ ሰበር ሄድን፡፡  ሰበር ላይ ትልልቅና በርካታ ዳኞች አሉ ጉዳዩን ከስር መሰረቱ አጣርተው ያለውን ነገር ያስተካክሉታል የሚል እምነት ይዘን ነበር የሄድነው::
የሰበር ሰሚ ችሎቱ ውሳኔም እናንተ ላይ ነው የፈረደው?
አዎ! እዛ አመልክተን መዝገቡን ከ1-2 ወር ለሚደርስ ጊዜ አጠኑት” ካጠኑት በኋላ እኔ ሰበር ችሎትን ሁሌ እከታተላለሁ በሌሎች ጉዳዮች ማለቴ ነው፡፡ የህግ ስህተት የለበትም ካሉ፣ እዚያው ላይ ነው የሚወስኑት፡፡ የህግ ጥሰት አለበት ብሎ ካመነ ግን የሆነ ነገር ያስተካክላል፡፡ የህግ ስህተት አለበት አሉና ከዚያ ወደ መረጃ ምርመራው ተገባ፡፡ ከስር ፍርድ ቤትና ከይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ጠቅላላ ዶክሜንቱ ተወስዶ፣ ሲታሽ ሲታሽ ቆይቶ ለፍርድ ተጠራን:: ፍርዱ ሲነበብ የሚገርምና አንገት የሚያስደፋ ሆኖ አረፈ፡፡ ይግባኝ ሰሚ ላይ ያለውን እንዳለ ገለበጡና አነበቡት፡፡ ራሱን ማለት ነው፡፡ 17.65 ሚ ብር ዕዳ ክፈሉ፤ ፋብሪካው የእናንተ ነው ፋብሪካው ያረፈበት ቦታ የሻጭ ነው፡፡ እዛ የቆሙ አውቶቡሶች ቢሰሩ ኖሮ ሊያመጡ የሚችሉትን 39 ሚ ብር ክፈሉ ብሎ ፈረደ፡፡ ይሄው ነው፡፡
የዚህ ፋብሪካ ገዢና የላቦራ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር በውቀቱ ታደሰ፣ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ እንደሚገኙም ሰምተናል፡፡ ለምን ታሰሩ?
እሳቸው የታሰሩት የሰበር ሰሚ ችሎቱን ፍርድ ከሰማን በኋላ ነው፡፡ ፍርዱ በዚህ መልኩ ይሆናል ብለን አልጠበቅንም ነበር፡፡ በጣም ነበር ያዘንነው:: እኔም በቦታው ነበርኩኝ፡፡ እኔ በጣም ከመደንገጤ የተነሳ የዶ/ር በውቀቱን ፊት ነበር የማየው ምን ይሆናል? ምንስ ያደርጋል? እያልኩኝ:: ምክንያቱም አንድ ንፁህ ዜጋ፣ በአገሩ ላይ ሀቅ ይዞ፣ ይህ ሁሉ ግፍ ሲሰራበት በብስጭት ምንም ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ በኋላ ከችሎቱ ወጣን፡፡ ደረጀውን ወረድንና ሜዳው ላይ ተሰብስበን “አይዞህ ሁሉም ነገር እንዲህ ሆኖ አይቀርም:: ወደ ህገመንግስት አጣሪ ኮሚሽን ሄደን አቤት እንላለን” አልነው፡፡ ለማንኛውም የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንቷን ወ/ሮ መዓዛን አናግሯት ብለን አብረን ሄድን፡፡ እዛ ቢሮ ስንሄድ መግባት የሚችሉት ዶ/ር በውቀቱና ወ/ሮ መሰረት ገቡ:: ወረፋ ከኋላ የሚጠብቁ ብዙ እንግዶች ነበሩባቸው ወ/ሮ መዓዛ:: ከዚያ ከወ/ሮ መዓዛ ቢሮ ሲወጣ ስልክ እያናገረ ነበርና፣ እዛ መሆናችንን ሲያይ፣ ብዙ ወረፋ ስላለ “እታች ጠብቁን አናግረናት እንመጣለን” አለን፡፡ አምስት ሆነን ነበር የቆምነው፡፡ እኔ ስልክ ለማናገር ራቅ ብዬ ሄጄ ስመለስ ወጥተው ቆሙ፡፡
ከዚያ ዶ/ር በውቀቱን “ምን አለችህ” እያሉ ከብበው ያናግሩታል፡፡ “አሁን ማግኘት አልቻልኩም፤ ከሰዓት በኋላ ቀጥራኛለች፤ ነገር ግን ያ አጭበርባሪ አሁንም እነዚህን ዳኞች አታልሏቸዋል” ሲል ከዳኞቹ መሃል አንዱ፡፡ ምናልክ” ሲለው፤ አንዳንድ ተባባሉ፡፡ አስቢው ያለምንም ምክንያት 39ሚ ብር የባስ ክፈል፤ የገዛኸው ፋብሪካ የቆመበት መሬት ያንተ አይደለም የተባለ ሰው፤ ብዙ ነገር የተበደለ ምን ሊሆን ምን ሊሰማው እንደሚችል አስቢው ከዚያ በኋላ ፖሊስ ጥሩ ተባለ፡፡ ፖሊስ መጣና ያዘው ተባለ፡፡ እኛም እዛው ቆመናል:: ወዲያው ችሎት ተሰየመ፡፡ ተጠሩ:: አምስት ዳኞች፡፡ እነሱ ሲገቡ እኛም ተከታትለን ገብተን ቁጭ እንዳልን ቀደም ብዬ ሳናግረው የነበረው ጠቃሚ ስልክ መልሶ ሲጮህ ላናግር ወጣሁ፡፡ ስም እየጠሩ መዘገቧቸውና ለእስር ወደ አራዳ ምድብ ችሎት ውሰዷቸው ተባለ፡፡ ቀኑ ሰኞ ነው እሮብ ከሰዓት ይቅረቡ ተብሎ ተወሰዱ፡፡
ምክንያቱ ምንድነው ለእስር የዳረጋቸው?
ረቡዕ ቀረቡ፡፡ እኛም ተገኘን፡፡  ክሱ ተነበበ፡፡ “ችሎት በመድፈር፣ ያልተገባ ነገር ፈጽመዋል” ይላል::
ከችሎት ወጥታችሁ ሜዳ ላይ እያላችሁ ነበር ዶ/ር በውቀቱና ዳኛው የተነጋገሩት፡፡ እንዴት ክሱ ከችሎት መድፈር ጋር ተያያዘ?
እኔም የሚያናድደኝ ይሄ ጉዳይ ነው ሌላው የተነጋገሩት ዶ/ር በውቀቱና አንዱ ዳኛ ናቸው:: ሌሎቹ አራቱ ዳኞች ባላዩት በሌሉበት “ችሎት ደፍረዋል” ብለው አብረው ፈረዱ::
የባሰ ያዘንኩትና እጅግ እጅግ ተስፋ መቁረጥ በውስጤ የተንሰራፋው በዚህ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ውጭ አገር ሄጃለሁ፤ ውጭ የመኖርም ዕድል ገጥሞኛል:: አሁን እዚህ በመምጣቴ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ በጣም አዝኛለሁ፡፡
እስራቱ በዶ/ር በውቀቱ ብቻ ላይ አልተፈፀመም:: ሌሎቹ ለምን አብረው ታሰሩ?
ዶ/ር በውቀቱ ሲሳደብ ቆመው አይተዋል ተብለው፤ ነው እግዚአብሄር ያሳይሽ፡፡ ከዚያ ፍርዱ ሲነበብ፤ ዶ/ር በውቀቱና ባለቤታቸው ወ/ሮ መሰረት 6 ወር፣ የወይዘሮ መሰረት ሁለት ወንድሞችና አንድ እህት፣ አንዷ የዶ/ር በውቀቱ ታላቅ እህት ደግሞ አንድ ወር፡፡ ተፈረደባቸው፡፡ የሚገርምሽ ነገር ከታሰሩት ሁለቱ ለረጅም አመት በውጭ አገር ቆይተው ከመጡ ገና ሦስተኛ ቀናቸው ነበር፡፡ ቁጭ ከምንል አብረን ችሎቱን እንከታተል ብለው ነበር የሄዱት:: አንዱ ውጭ አገር ከሄደ ከ37 አመት በኋላ ወደ አገሩ ነው የመጣው፡፡ እህቱ በ27 ዓመቷ ነው የመጣችው፡፡ ምንም በማያውቁት፣ በሌሉበት ነገር 1 ወር ሙሉ ታስረው ነው የተፈቱት፡፡ የተፈቱ ቀን በሌሊቱ በረራ ነው ከአገር ወጥተው የሄዱት በዚህ በጣም አዝናለሁ፡፡ “እንዴት አምኜ ልደር ነው” ያለው፡፡ ከዛ በኋላ የዛሬ ሳምንት (ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን) ወ/ሮ መሰረት ተለቀዋል፡፡ ከፍተኛ የህክምና ክትትል ይደረግላቸው ስለነበር፣ እነዛ የህክምና ማስረጃዎች ቀርበው፣ ከሁለት ወር በላይ ታስረው ተፈትተዋል:: ከባለቤታቸው ጋር 6 ወር ነበር የተፈረደባቸው፡፡ ዶ/ር በውቀቱ ገና 4 ወር ያህል ይቀረዋል:: በነገራችን ላይ የወ/ሮ መሰረትን ጉዳይ ለፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ አቅርበን ነው የተፈቱት፡፡ በዚህ አጋጣሚ ፕሬዚዳንቷን እናመሰግናለን፡፡
የሰበር ሰሚ ችሎት ከፈረደባችሁ በኋላ ሻጮች ፋብሪካውን በአፈፃፀም ለመረከብ ሲሞክሩ፤ አፈፃፀሙን የሚሰሩት ሰዎች ጉዳዩ ግራ እንደገባቸውና ለሻጮች ለማስረከብ ተቸግረው ሁለት ጊዜ መመለሳቸውን እንዲሁም እናንተ የፋብሪካው ርክክብ ለሻጮች እንዳይፈፀም እግድ ማውጣታችሁን ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ይስጡኝ?
ትክክል ነሽ፡፡ ሻጮች የመጀመሪያውን አፈፃፀም ሰኔ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ይዘው መጡ፡፡ ካርታ ቁጥር 83/6 ማለትም ፋብሪካው ያረፈበት 3015ካ.ሜ ቦታ የሻምበል ጌታቸው (የሻጩ) ስለሆነ እንድታስረክቡ ከተሸጠው ጌትሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ፋብሪካና ይዞታ ውጭ ያለውን ይላል፡፡ ፈፃሚዎቹ መጡና አዩ፡፡ ፋብሪካና ቦታው አንድ ሆነ፡፡ ይሄ አስቸጋሪ ነው ብለው ተመለሱ፡፡ በተመለሱ በ10ኛው ቀን ይሄንኑ ማዘዣ ይዘው መጡ፡፡ አሁን መለካት ጀመሩ፡፡ ሲለኩም 3015 ካ.ሜ ቦታ ላይ አርፏል፡፡ ትዕዛዙ ደግሞ “ይዞታውንና በይዞታው ላይ ያረፈውን ንብረት፤ ነገር ግን ከተሸጠው ጌትሸት ዲተርጀንትና ማሸጊየ ፋብሪካ ውጭ” ይላል፡፡ በሁለተኛውም ማስረከብ አልቻሉም፡፡
ስለዚህ እኛ ግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ለህገ መንግስት አጣሪ ኮሚሽን አቀረብን፡፡ “ያለ አግባብ የገዛነው ንብረት እየተወሰደ ስለሆነ፣ ከፍተኛ የህግ ጥሰት እየተፈፀመብን ነው ሀብት የማፍራት መብታችንን ተነፍገናል” ብለን ሰበር ሰሚ ችሎት የፈረደው የእኛን ሀቅና ማስረጃ ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው፡፡ እናንተ ጉዳዩን እስከምታዩት ድረስ ሀብትና ንብረታችን ለሰው እንዳይሰጥብን እግድ አውጡልን ብለን አመለከትን ከግንቦት 15 ቀን 2011 እስከ ቅርብ ሀምሌ 3 ድረስ “ሰው አልተሟላም፤ ስብሰባ ላይ ነን፣ ሲሉ ቆይተው ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዕግድ ወጣልን፡፡ ጉዳዩ ታይቶ ብይን እስኪሰጥ ርክክቡ እንዲታገድ ዕግድ ወጥቷል፡፡ እግዱ በወ/ሮ መዓዛ ፊርማ የወጣ ነው፡፡ እኛም የህገ መንግስት አጣሪ ኮሚሽን እንደ ይግባኝ ሰሚና ሰበር ሰሚ ችሎት ሳይሆን ማስረጃውንም መርምረው፣ ቦታው ድረስ ሄደው አይተው፣ ትክክለኛ ፍርድ ይፈርዳሉ የሚል እምነት አለን፡፡
ግንቦት 15 ቀን 2011 ለህገመንግስት አጣሪ ኮሚሽን ጉዳያችሁን አቀረባችሁ፡፡ የህገ መንግስት አጣሪ ኮሚሽኑ ለእናንተ ባይፈርድ ቀጥሎ የምትሄዱት ወዴት ነው?
ከዚያ በኋላ ወደ እግዚአብሔር ነው የምንሄደው:: ነገር ግን በህገ መንግስት አጣሪ ኮሚሽኑ  እውነት ይወጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የባንኩ መረጃ፣ ውላችን፣ የቢሾፍቱ ከተማ መሬት አስተዳደር የፃፈው ማስረጃ፣ እነዚህን ሁሉ እውነቶች አይተው ቦታውን ሄደው ተመልክተው ከህሊናቸው ጋር ሆነው፣ ጉዳዩን ካዩት፣ ሃቃችን አፈር ይለብሳል ብለን አናምንም፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት እውነት አፈር አራግፋ ካልተነሳች ግን ከእኛ ታሪክ፣ ከእኛ ውጣ ውረድና በእኛ ላይ ከተፈፀመው ክህደት ሌላው እንዲማር ስለምንፈልግ፣ ወደ እናንተ ጋዜጣ መጥተናል፡፡ ከዚያ በተረፈ ለተፈፀመብን  ግፍና እንግልት ሁሉ ህዝብ ይፍረደን ነው የምንለው፡፡


Read 9402 times