Saturday, 20 July 2019 12:11

የማይረካው --

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 ‹‹ሰውየውን አንድ ጊዜ ቀርቦ የማናገር እድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ ችኮ አይደለም፣ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሆኖ ቀርቦ ሲያወራ ግን እንደ ጓደኛ ነው፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስትር እያለ፣ ጋዜጠኞች ቀርበን ‹‹ዶክተር ቃለ ምልልስ ፈልግን ነበር…›› ስንለው.. ‹‹በመጀመሪያ ልስራ፣ በስራዬ ለሀገር የሚጠቅም ውጤት ሳስመዘግብ ቃለ ምልልሱም ይሆናል›› ነበር ያለን፡፡››
ሰውዬው ተቋማቶቹ የቱንም ያህል ስኬታማ ቢሆኑ፣ እርካታ ብሎ ነገር ግን አይታሰብም::… ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከቀረፀው አዲስ እሴት ውስጥ አንዱ ‹‹የማይረካ የመማር ጥማት›› የሚል ነው፡፡ ይህም ቢሆን እንደ ሌሎች ፍልስፍናዎችና እሴቶች ሁሉ ከጥልቁ ማንነቱ፣ እሱነቱ፣ እውነቱና እምነቱ የተቀዳ ነው፡። ሰውዬው የተለያዩ ተቋማትን በማደራጀት ሂደት ውስጥ፣ ተቋሙ በአዋጅ/በደንብ የተወሰነ አላማ ተቀምጦለት እንዲሚቋቋም ይታወቃል፡፡ ነገር ግን እሱ በዛ እንኳን የሚረካ ሰው አይደለም፡፡ ከዚህ በላይ ማድረግ የሚል አቋም አለው፡፡ ስለዚህ ወዲያው የለቱለት ነው ደንብ ማሻሻያ ሀሳብ በማምጣት፣ በብዙ አቅጣጫ የሚሄደው፡፡
ሰውዬውና የእርካታ ጥግ ላለመተዋወቅ የማሉ ይመስላሉ፡፡ ሁሌ የሚማር፣ ሁሌም የሚሮጥ፣ ሁሌም ጀማሪ፣ ሁሌም ጉጉ፣… ሁሌም የተሻለ ለውጥ አሻግሮ የሚያይ፤… ሰራተኛው በአንዱ ስኬቱ ረክቶ ምስጋና ሲፈልግና ሲጨፍር፣ እሱ ሌላ ስትራቴጂ ላይ አቀርቅሯል፡፡… ለምሳሌ ይህ ሰው፣ በሚኒስትርነቱም ሆነ በጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ሹመቱ ዕለት ቢሮው ነበር፡፡ በከፍተኛ ግብግብ የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምስረታ የፀደቀለት ዕለት፣ በወቅቱ ከተለያዩ ሚኒስትሮች በኩል የነበረውን ውጥረት የሚያስታውሰው ሰራተኛ ፈንጠዚያ ላይ ሳለ፣ እሱ ግን በቀጥታ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ወደ ቢሮ ነበር ያቀናው፡፡ ወዲያውም ሌላ እያቋቋመው ወደነበረው የስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት ፕሮዛሉ አቀረቀረ፡፡… ከወራት በኋላ የስፔስ ሳይንስ ተቋምን እንዲያቋቁም በከፍተኛ ፍጭት ተፈቀደለት፡፡ ከምሳ በኋላ ሰውዬው በቢሮው ተገኝቶ ሌላኛው ህልሙ ላይ አድፍጧል፡፡ በሚገርም ሁኔታ፣ በተከታታይ ይሰጥ የነበረውን ስልጠናም በዚሁ ዕለት ከ10 ሰዓት በኋላ በመግባት ተከታትሏል፡፡ እኛም ሰው መሆኑን አብዝተን ተጠራጠርን፡፡
‹‹…አንድ አመት ወደ ኋላ መሻገር እፈልጋለሁ፤ ባለፈው አመት የመንግስት ምስረታ ሲካሄድ፣ መጀመሪያ ከጀርባ በር ወጥቼ ዐብይን አግኝቼው ነበርና፣ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ነበር የጠየኩት፣ ‹‹ገና ምን ሰራሁና ከሰራሁ በኋላ መጥተህ ብታናግረኝ አይሻልም ወይ?›› ብለው ነገሩኝ፤ ፊት ለፊት ሌሎች ሚኒስትሮችን አናገርኩኝ፤ በእርግጠኝነት ከአንድ አመት በኋላ፣ እነዚያን ያናገርኳቸውና አሁን እርስዎን አወዳድሬ ምን ሰሩ ብዬ ብመለከት አይዶን ኖ ምን ላገኝ እንደምችል፤ ዛሬ ግን በጣም ደስ ያለኝ ነገር፤ በእውነትም የተሰራውን ነገር በዓይን በሚታይ መልኩ፣ በአንድ አመት ውስጥ ነው ለውጥ ያየሁትና እጅግ እጅግ እኔ ኢምፕረስድ ሆኛለሁ፤ በዋነኝነት የተሰራው፣ የተሰበረ አመለካከት ነው፡፡…››
በነገርህ ላይ ብዙ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማእከል ወይም ደግሞ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ኦሮሚያ ከተማና ቤቶች ልማት ወይም ደግሞ ኦህዴድ ጽሕፈት ቤት ያሉ ሰዎችን ብትጠይቃቸው፣ ከራስህ ጋር ትፋታለህ፡፡ ከእሳቸው ጋር ስትሰራ ከራስህ ጋር ትፋታለህ፡፡ ከራስህ ጋር ትጣላለህ፡፡ በቃ አንተ አተ ዘ ኢንድ ኦፍ ዘ ዴይ አንተን አትሆንም፤ ሌላ ሰው፣ ሌላ ወንድወሰን ነው የምትሆነው፡፡ ሰርተህ ሰርተህ ራሱ አትጠግብም፤ አትጠረቃም፡፡ ምናልባት አይባል ይሆናል፣ ለምግብ ነው አይደል ይሄ ጅብ ነው በልቶ አይጠግብም የሚባለው? ጅብ ትሆናለህ፡፡ ስራህ ላይ አንድ ስራ ሰጥተውህ፣ ያንን ስራ ብቻ ይዘህ አንተ ትደክማለህ፤ እንደክማለን፡፡ ስራ ሰራሁ ትላለህ፣ አራት ሰአት ላይ ትወጣለህ፣ ቡና ትጠጣለህ፤ ውሃ ትጠጣለህ፤ ደግሞ ታወራለህ ትገባለህ፤ ሁለት ገጽ ታነባለህ ወይ ታያለህ፣ ትሰራለህ፤ ከዛ ደግሞ ምሳ ላይ ትወጣለህ፣ ስምንት ሰአት ራሱ እየተኮፈስክ ነው የምትገባው፡፡ እሳቸው ግን 100 ገጽ ጽፈህ ብትሰጣቸው፣ መቶውን ገጽ አንድ ሰአት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መልሼልሃለሁ ሊሉህ ይችላሉ፡፡ ከዛ ይህንን ሁሉማ አንብበው ሊሆን አይችልም ወይ ተዓምር አለበት ወይ አስማት አላቸው እኚህ ሰው፤ አለበለዚያ 100 ገጽ-- አንተ እኮ በጣም ለፍተህ ምናምን አንብበህ፤… ብዙም አላነበቡትም ብለህ ስትገባ፣ ገጽ በገጽ፣ መስመር በመስመር የሚገርሙ አስተያየቶች አሉ፤ በየገጹ ላይ፡፡ እንዴ አንዳንዴ የመለሱልህን ኢ-ሜይልህን ትከፍትና የመለሱልህን ስራ ማንበቡን ትተህ፣ ስለ እሳቸው ማንበብ ትጀምራለህ፡፡ መጀመሪያ ነው ኮመንቱን አዘጋጅተው የጠበቁኝ እንዳትል፣ ጽሁፉ ያንተ ነው፤አንተ ነህ የላክላቸው፤ለማንም እንዳልሰጠህ አንተ ታውቃለህ:: በዚህ ጊዜ ነው ኮመንት አድርገው የመለሱልኝ እንዳትል በቃ ይጨንቅሃል፡፡ እንደዚህ አይነት ሰው ናቸው፡፡-- ሰአት አይገድባቸውም፡፡ ሰርተው አይደክሙም፤ ልጆቻቸውም በእሳቸው ልክ ሰርተው እንዳይደክሙ የሚያደርግ ሰብእና ያላቸው ሰው ናቸው፡፡››
 (“ሰውዬው” ከተሰኘው የመሐመድ ሐሰን መጽሐፍ ላይ የተቀነጨበ፤ ሚያዝያ 2011 ዓ.ም)

Read 2339 times