Saturday, 20 July 2019 12:22

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)


    “ስልጣኔያችን የሚደምቀው፤ በነፃ ግለሰብ ውስጥ ባለ አብሮነት እንጂ በደቦኝነት አይደለም”
            
    ሰካራሞች ሰፈር ገብተህ “ሰክራችኋል”፣ አማኑኤል ገብተህ “አብዳችኋል” ብትላቸው አንተው የሰከርክ፣ አንተው ያበድክ ነው የሚመስላቸው:: ሰዎች የሚሰክሩበት ወይም የሚያብዱበትን ምክንያት የምታውቀው፣ በነሱ ቦታ ሆነህ እንደዚያ እንዲሆኑ ያደረጋቸውን ችግር ስትቀምስ ነው:: የስነ ልቦናም ሆነ ሌላ ድጋፍ ለማድረግ ወይም ልታጠናቸው ከፈለግህ፣ መጀመሪያ እራስህን ለውጥ:: እነሱን ምሰል-- አለበለዚያ አንድ የሰማሁት ተረት አለ፡፡ መንፈሱ እንደዚህ ነው---አንድ ነቢይ ወደ አንድ ከተማ ብቅ ብሎ የአገሩን ንጉሥ…
“ተዘጋጅ፣ ህዝቡንም አዘጋጀው” አለው፡፡
 ንጉሡም …
“ስለ ምንድን ነው የምንዘጋጀው?” በማለት ጠየቀው፡፡
“መጥፎ ጊዜ እየመጣ ነው” አለው ነቢዩ፡፡
“መጥፎ ስትል?”
“አገር ሁሉ የሚያብድበት”
“ምን ቢሆን ነው አገር ሁሉ የሚያብደው?”
“ከወራት በኋላ የሚዘንብ ዝናብ አለ፡፡ እሱን የቀመሰ ሁሉ ያብዳል” በማለት አስረዳው፤ ነቢዩ፡፡
ንጉሡም ያዋቂውን ምክር ተቀብሎ አዋጅ አስነገረ፡፡
“የሚያሳብድ ዝናብ ይጥላል፤ ውሃውን እንዳትጠጡ” በማለት ንጉሱ ህዝቡን አስጠነቀቀ፡፡ ህዝቡ ግን “ንጉሣችን ምን ነካው? ታመመ እንዴ?” እያለ፣ አዋጁን ችላ አለ፡፡ ንግርቱ አልቀረም፡፡ ዝናቡ ጣለ፡፡ አገሬው አበደ፡፡ እየጨፈረም፤ “ንጉሣችን ዝም ያለው፣ ድምፁ የጠፋው ስለታመመ ነው” እያለ ቤተ መንግስቱን ከብቦ መጮህ ጀመረ፡፡
ነገሩ ያሳሰበው ንጉሥም፤ ጥሞና ወስዶ በጥልቀት  አሰበ፡፡ አስቦ አስቦ…ምን ያደረገ ይመስልሃል? እስቲ ገምት…
***
እንደኛ አገር በቀስት ለመዋጋት የተሰለፈ፣ በጐሰኝነት የሰከረ፣ በአጓጉል ዕምነቶችና ልማዶች ለተተበተበ ህዝብ፤ በዕውቀታቸው የቀደሙ፣ የሰለጠኑ፣ የወገኖቻቸውን ጥቅምና ጉዳት ከራሳቸው ጥቅምና ጉዳት በላይ አድርገው የሚያስቡ፤ ከስሜት የራቁ አስተዋይና ብልህ መሪዎች ያስፈልጉታል - ወደ ዕድገት፣ ብልጽግናና ስልጣኔ የሚያሸጋግሩት፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ በየአካባቢው የነበሩ፣ በኋላ ቀር የምርት መገልገያዎችና ግብዓቶችም ቢሆን በተሻለ አምራችነት እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ፣ ጠብ የሚያርቁ፣ ባላጋራ የሚያስታርቁ “ዐዋቂ” ተብለው የሚከበሩና የሚደመጡ፤ ጐልማሳና አዛውንቶች ለየማህበረሰባቸው በሚሰጡት “ምክር” ጠቃሚነት እንደ “ብርቅ” ይታዩ ነበር፡፡ እንደነዚህ ዓይነት “ሞዴሎች” አሁን፣ አሁን በብዛት አይገኙም፡፡ በብዙ የተለያዩ ቦታዎችና ባንዳንድ አጋጣሚዎች እንደምናየው፣ አብዛኛዎቹ በፖለቲከኞች ተጽእኖ ተጠምደዋል ወይም ራሳቸው ፖለቲከኞች ሆነዋል፤ እውነቱን ከመናገርና ማህበረሰባቸውን ያለ አድልዎ ከማገልገል ይልቅ በጥቅም እየተደለሉ ያልተረጋገጠ ወሬና የጠባብ አስተሳሰብ አቀንቃኝ ሆነዋል፡፡ የሚገኙበትን ማህበረሰብ አባላት በአግላይ የጐሰኝነት ስሜት እንዲጠናወቱና እርስ በርስ እንዲጠራጠሩ አድርገውታል፡፡ ሆን ብለው በማወቅ ወይም በመታለልና ባለማወቅ ምክንያት ነባር የምርቃት፣ የግልግልና የሽምግልና ስርዓቶች፣ የድለላና የ “ይስሙላ” እየመሰሉ ነው፡፡
ወዳጄ፡- በፖለቲካ ተፅዕኖ ሰበብ ባህላዊ የአብሮነት ቅርሶች (Social Values) መቀጨጫቸው ወይም እየተዳከሙ መምጣታቸው፤ ምናልባት የሽግግር ጊዜ ምልክት ሆኖ ሊቆጠር ይችላል:: በእንደዚህ ዓይነት ወቅት “ህዝብ” ወይም ደቦኛ የሚመስለው ስብስብ፤ ጥሩ መሪዎች ካገኘ በመጪዎቹ ጊዜያት ትልቅ ማህበራዊና ግላዊ ጥቅም በሚያስገኝ ለውጥ እየታገዘ ወደ ተሻለ፣ ሁሉን አቀፍ፣ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚን መሰረት ወደ ሚያደርግ ስርዓት ይገሠግሳል፤ ወደ ብሩህ ነገ፣ ወደ ስልጣኔ፡፡ መሪዎቹ ብቁ ካልሆኑ ግን ጉዞው አደገኛ ነው፡፡ አንድ እርምጃ ወደፊት የቀደመ እየመሰለ፣ አስር እርምጃ የኋሊዮሽ ያሽቆለቁላል፡፡ ወደ ጭለማው ዋሻ!!
ወዳጄ፡- ደቦኛነት ብዙውን ጊዜ ባጋጣሚ በሚፈጠር ስሜታዊነትና ስነልቦናዊ አንድነት ስለሚቆራኝ፣ ለልማትም ለጥፋትም ሊውል የሚችል ጭፍን ዐቅም አለው፡፡ ደቦኛነት በትክክል ካልተመራ ዘለቄታዊ ጥቅሙን በርካሽና አላፊ ጥቅም ይቀይረዋል፡፡ “ያብረቀረቀ ሁሉ ወርቅ እየመሰለው” ይታለላል፡፡ ደቦኛነት የሚያተርፈው ከወዳጅነት፣ ከስልጣኔና ከዓለም አቀፋዊነት ሳይሆን ከቁጭት፣ ከሃሜት፣ ከስስትና ከራስ ወዳድነት ነው፡፡ ደቦኛ ራዕይ የለውም፡፡ በየአንዳንዷ ቅጽበት ስለሚገፈታተር ቆሞ ለማሰብ ይቸግረዋል፡፡ የብዙ የተለያዩ ሃሳቦች ቋት ስለሆነም የቱን ለቆ፣ የቱን እንደሚጨብጥ ግራ ስለሚጋባ ራሱን ችሎ አይቆምም!
ወዳጄ፡- የነቃ ማህበረሰብ በሚኖርበት ዓለም፤ መሪዎች ሲሳሳቱ ወይም ቀሽም እየሆኑ ሲያስቸግሩ ህዝብና ሚዲያው ቀጥ ያደርጋቸዋል፡፡ የማይሆነውን “አይሆንም”፣ ለተገቢው ደግሞ “ብራቮ” በማለት ያበረታታል፤ ያርማቸዋል፡፡ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን በተቆጣጠረበት ጊዜ ሕዝብን በየአካባቢው እየሰበሰበ፣ የተለያዩ ሰዎችን መድረክ ላይ እያቆመ “ፍረዱበት” ይል ነበር፡፡ አንዳንድ ስሜታውያን “ይሙት” ካሉ ወዲያው ይገድላል፡፡ “ይፈታ” ከተባለም እንደዚያው፡፡ አድሮ ውሎ ሊያስከትል የሚችለውን ፀፀት፣ ቆም ብሎ ማሰብ አልተቻለም:: ፍትህ ገጭ፣ እርገጭ ሆና ነበር፡፡ መቶ ብር ሰረቀ የተባለ ሌባ ተገድሏል፡፡ የዛሬ ሌባ ማን እንደሆነ፣ ምን ያህል እንደሚሰርቅም  አስቡት፡፡
ወዳጄ፡- ዓለም በተመሳሳይ ስርዓት የምትተዳደርበት ዘመን ሩቅ አይደለም፡፡ በዚያን ጊዜ የሁሉንም ህዝቦች ጥቅምና ጉዳት ያላገናዘበ ውሳኔ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ኢ-ፍትሃዊ  ነውና:: እያንዳንዱ ሰው በፈለገበት ቦታ ተፈጥሯዊም ሆነ ሲቪል መብቶቹ ተከብረው የመኖር፣ የመስራት፣ ቤተሰብ የመመስረት፣ በመረጠው አስተዳደር የመገልገል ነፃነት እንጂ በተመሳሳይ ቋንቋና ስነ ልቦናዊ አጥር ውስጥ ተገድቦ፣ በስልጣኔ በረከቶች እየተጠቀመ፣ በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ ኋላቀርነትን የሚጭንበት ዕድል መናኛ ነው፡፡
ወደድንም ጠላንም፣ ፈለግንም አልፈለግንም፣ ስልጣኔያችን የሚደምቀው በአብሮነታችን ውስጥ ባለ ነፃ ግለኝነት ወይም በነፃ ግለሰብ ውስጥ ባለ አብሮነት እንጂ በደቦኝነት አይደለም፡፡ የኛም ሆነ የሌሎች ሀገራት ታሪክ፣ አርኪዮሎጂካዊ ግኝቶች፣ ስነ ጽሑፍና ቅርፃ ቅርጽ፣ ስዕልና ስነ ቃሎች ባጠቃላይ የዓለም ታሪክ እንደሚያስረዳው፤ በአካባቢው ከሚኖሩ ሌሎች ማህበረሰቦች ጋር ሳይወራረስ ራሱን ችሎ የቆመ ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግና ልማድ የለም፡፡ ቢኖርም በቁጥር አናሳ ነው፡፡ የአኗኗሩ ኋላቀርነት፣ ድህነቱና የፖለቲካ ተጽእኖ ስለ ሸበበው እንጂ ሥነ ልቦናዊ ዘይቤውም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ በመላው አገራችን በሚኖሩ ማህበረሰቦች የሚነገሩ ቋንቋዎች ውስጥ የምናገኛቸው አባባሎች፣ ተረትና ምሳሌዎች ሌሎች አፍሪካውያንን ጨምሮ ቀደም ብሎ በተፃፉ በአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩስያ፣ ፐርሺያ፣ አረብና ለሎች ሀገራት ስነጽሑፍ ውስጥ ለመኖራቸው የማያጠራጥር ማስረጃ አለ፡፡ ሥዕልና ሙዚቃን ጨምሮ የእምነት፣ የሃይማኖት፣ የአምልኮትና የጥንቆላ መመሳሰልም የዚያኑ ያህል ነው፡፡
የኦማን ባህላዊ ሙዚቃና ሽብሸባ ውስጥ የያሬድ ዜማ፣ መቋሚያ፣ ጽናጽልና ከበሮ እነ ዜማው ሲወርድ በቴሌቪዥን ተመልክቻለሁ፡፡ ማን “ምንና ምንን” ከማን ወሰደ? የሚለውን ጥያቄ ለሊቃውንቱና በጉዳዩ ላይ ጥናት ለሚያደርጉት እተወዋለሁ:: ዋናው ጉዳይ ግን የስልጣኔ፣ የሳይንስና የጥበብ ዕድገት እዚህ ዘመን ላይ የደረሰው ተያያዥነት ባላቸው የተለያዩ የእምነትና የባህል ውርርስና የተጣማጅነት ጉዞ እንደሆነ መረዳት ነው፡፡
ወዳጄ፡- አገርም የዚሁ ለቁጥር የሚታክት የዘመን ጉዞ፣ የታሪክ፣ የእምነት፣ የባህልና ወግ ፍሬ ናት፡፡ አገር እንስራ ተብላ የተሰራች አይደለችም፡፡ እውነት እውነት እልሃለሁ ፖለቲካው ቅጥ ባጣበት በዚህ ወቅት ህዝቡ ደግፎኛል፣ ሽማግሌ መርቆኛል እያልክ፣ ባንዲራ ከመስቀልህ፣ መዝሙር ከመዘመርህ በፊት ደጋግመህ አስብ፡፡ ሙሶሎኒና ሂትለርም ተመርቀው፣ ተባርከው፣ ተጨበጭቦላቸው ነበር፡፡ የማታ ማታ ትርፋቸው ውርደት ሆነ እንጂ፡፡ እናም ወዳጄ፤ “አንዴ ለመቁረጥ አስር ጊዜ ለካ” መባሉን አትዘንጋ፡፡
***
ወደ ተረታችን ስንመለስ፡- ምክር አልሰማ ብሎ ያበደው ህዝብ፣ እየጨፈረ ወደ ቤተ መንግስት ሲመጣ፤ ብልሁ ንጉስ እንደነሱ ያበደ መስሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል፣ አገሬው “እሰይ ንጉሣችን ዳነ” በማለት ወደመጣበት ተመለሰ ይባላል፡፡
የመሪነት ነገር ከተነሳ አይቀር ታላቁ Te ching (Lao Tzu)
“…I take no action and the people of themselves are transformed. Act without action. Do with out ado. Therefore; the sage never strives for the great” በማለት ጽፎልናል፡፡
ሠላም!!   

Read 1306 times