Saturday, 20 July 2019 12:23

ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫና በቀውስ ላይ የሚገኘው ካፍ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ በ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫው ላይ 4 ጨዋታዎችን በብቃት መምራቱ መላው ኢትዮጵያውያንን አኩርቷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ትናንት ምሽት በሴኔጋል እና አልጄርያ መካከል የተደረገውን የዋንጫ ጨዋታ እንደሚመራ በሳምንቱ መግቢያ ላይ ሲገለፅ ነበር፡፡ በተለይ በምስራቅና ምዕራብ አፍሪካ አገራት የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ሚዲያዎችና ማህበራዊ ገፆች ይህንኑ መረጃ ምንጮችን ሳይጠቅሱ አናፍሰውታል፡፡ በሳምንቱ መግቢያ ላይ ግን የካፍ ሚዲያ ማዕከል በትዊተር ገፁ ባሰራጨው ዘገባ የዋንጫ ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት የሚመሩት  ደቡብ አፍሪካዊው ቪክቶር ጎሜዝ እንደሆኑ ተገለፀ፡፡ ይሁንና ይህ መረጃ በ24 ሰዓት ውስጥ ከካፍ የሚዲያ ትዊተር ላይ መሰረዙን ለማወቅ ተችሏል:: የ32ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ የዋንጫ ጨዋታው የሚመሩ ዳኞች ሹመት  ማንነት በመጨረሻ መረጃ የተገለፀው ግን ከትናንት በስቲያ ነበር፡፡ በሴኔጋል እና በአልጄርያ መካከል በግብፅ ካይሮ ኢንተርናሽናል ስታድዬምያ ላይ የሚደረገውን የፍፃሜ ጨዋታ ካሜሮናዊው አልዩም አልዩም እንደሚዳኙ፤ ረዳት ዳኞቻቸውም ከካሜሮን መሆናቸውና እና አራተኛው  ዳኛ ከደቡብ አፍሪካ መመደቡን ከካፍ የቅርብ ምንጮች የወጡ መረጃዎች አመልከተዋል፡፡ የካፍ አስተዳደር ያለበት ወቅታዊ ቀውስ የመረጃዎች መዛባት መፍጠሩን የተቹ አንዳንድ መረጃዎች የዋንጫ ጨዋታን የሚዳኙትን ዳኞች በዋዜማ ቀን የሚገለጹ ቢሆኑም አንዳንድ ዘገባዎች ስለ ምደባው የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚያሰራጩት ከካፍ የሚዲያ ማዕከል አፈትልከው የሚወጡ የውዝግብ አጀንዳዎች መሆናቸውን በመጥቀስ ፅፈዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካው ታይም ላይቭ በስፖርት አምዱ እንደፃፈው የኢትዮጵያዊው ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ እና ደቡብ አፍሪካዊው ዋና ዳኛ ቪክቶር ጎሜዝ የዋንጫውን ጨዋታ ለመዳኘት እና በዳኞች ኮሚቴ ለመመረጥ የሚቸገሩበት አጋጣሚዎች በአፍሪካ ዋንጫው ላይ መፈጠራቸውን ነው፡፡ ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ ከግማፅ ፍፃሜ ጨዋታ በኋላ ለዋንጫው ዳኝነት መሾሙ የማይጠበቅ ነበር የሚለው የታይም ላይቭ ዘገባ  ቱኒዚያ እና ሴኔጋል ባደረጉት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ ለቱኒዚያ የፍፁም ቅጣት ምት ወስኖ ከዚያም የሻረበትን ውሳኔ የሚያስተች ነው ብሏል፡፡ በሌላ በኩል በሩብ ፍፃሜው ጋና በቱኒዚያ የተሸነፈችበትን ጨዋታ የመራው ደቡብ አፍሪካዊው ቪክቶር ጎሜዝ ደግሞ ጋና ባለቀ ሰዓት ያስቆጠረችውን ጎል በመሻር የሰጠው ውሳኔ ለፍፃሜ ጨዋታ  ብቁ የማያደርግ ነበር ሲል አውስቷል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የዳኝነት ምርጫውን የሚያከናውነው በካፍ የዳኞች ኮሚቴ፤ ከውድድሩ ጋር በሚሰሩ ኢንስትራክተሮች እና ተንታኞች ጋር ምክር በማድረግ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የ37ዓመቱ ካሜሮናዊ ዳኛ የ32ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ እንዳጫወተ የሚታወስ ሲሆን በፊፋ የዳኞች ፓናል ውስጥ ሲያገለግል 12ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡
ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ በአፍሪካ እግር ኳስ እያገኘ ያለው ተቀባይነት እና ተዓማኒነት እያደገ መሆኑን በ32ኛው አፍሪካ ዋንጫ በነበረው ተሳትፎ እና መነጋገርያነቱ መገንዘብ ይቻላል:: ባምላክ በዳኝነት ሙያው ካገኘው ስኬት ባሻገር በህክምና ምርምር፤ እንዲሁም በክሊኒክ ኮርድኔተርነት እንደሚሰራ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሶስዮሎጂ በዲግሪ መመረቁም ይታወቃል፡፡ አንድ ታዋቂ የግብፅ የስፖርት ተንታኝ ቱኒዚያ ከሴኔጋል ባደረጉት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ላይ ባምላክ ተሰማ ያሳየውን ዳኝነት በማድነቅ ለአፍሪካ እግር ኳስ ተምሳሌት አድረጎ ጠቅሶታል፡፡ ባምላክ ጨዋታውን በተረጋጋ ሁኔታ መምራቱ፤ በተሟላ የአካል ብቃት ጨዋታውን ማካሄዱ እና ከሁለቱም ቡድን ተጨዋቾች ጋር ልዩ መግባባት በመፍጠር ያሳየው ዳኝነት በተመለከተ መስክሯል፡፡ የ38 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ 27 ኤሊት ዋና ዳኞች አንዱ ሲሆን በእግር ኳስ ዳኝነት የ15 ዓመታት ልምድ ያካበተና  በፊፋ  ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛነት ከ9 ዓመት በፊት የተመዘገበ ነው፡፡ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ በ8 የተለያዩ የእግር ኳስ ውድድሮች ከ56 በላይ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ሰርቷል፡፡ በ3 የአፍሪካ ዋንጫዎች 7 ግጥሚያዎችን ሲያጫውት፤ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር 3 የዋንጫ ጨዋታዎችን መርቷል፡፡
በ3 የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ በዋና ዳኝነት ሲሰራ 7 የአፍሪካ ዋንጫ ግጥሚያቸውን አጫውቷል:: በ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ግብፅ ላይ ኢትዮጵያን በብቃት በመወከል ለመላው ኢትዮጵያውያን ኩራት ለመሆን የበቃው፤  ሁለት የምድብ ጨዋታዎች፤ 1 የሩብ ፍፃሜ እና 1 የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት በመምራት ነው፡፡  ሁለቱ የምድብ ጨዋታዎች ቱኒዚያ ከአንጎላ 1 እኩል እንዲሁም ካሜሮን ከጋና 0ለ0 የተለያዩባቸው ጨዋታዎች ሲሆኑ፤ በሩብ ፍፃሜ ደግሞ አይቬሪኮስት ከአልጄርያ ተገናኝተው በመለያ ምት አልጄርያ 5ለ4 ያሸነፈችበትን እንዲሁም በግማሽ ፍጻሜ ሴኔጋል ቱኒዚያን በተጨማሪ ክፍለጊዜ 1ለ0 ያሸነፈችበትን ጨዋታዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪ  በ2015 እኤአ በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አንድ ጨዋታ እንዲሁም በ2017 እኤአ በ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ጨዋታዎችንም መርቷል፡፡ ከአፍሪካ ዋንጫ ባሻገር በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ 14፤ በካፍ የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ  21፤ በአፍሪካ ዞን የዓለም ዋንጫ ማጣርያ 8፤ በፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ 2፤ በካፍ ሱፕር ካፕ 1፤  በፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ 1 እንዲሁም በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ 2 ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት አጫውቷል፡፡ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር 3 የዋንጫ ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት ለመምራት የበቃ ሲሆን እነሱም በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ  በ2016 17 አልአሃሊ ከዋይዳድኤሲ፤ በ2017 ቨ18 ኤስፔራንስ ከአልአሃሊ እንዲሁም በአፍሪካ ክለቦች ሱፕር ካፕ በ2018 19 ኤስፔራንስ ከራጃ ካዛብላንካ የተገናኙባቸው ናቸው:: በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ማህበር (ፊፋ) በሁለቱም ፆታዎች በዋና ዳኝነት እና በረዳት ዳኝነት የተመዘገቡት ኢትዮጵያውያን 22  ናቸው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኞች በወንዶች 7፤ በሴቶች 4 ሲሆኑ  በኢንተርናሽናል ረዳት ዳኝነት የተመዘገቡት ደግሞ 7 ወንዶች 4 ሴቶች ናቸው፡፡
የካፍ አስተዳደር ከ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ ፈተና ውስጥ ይገባል
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ በፊት በካይሮ ባካሄደው ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈ ታውቋል፡፡ በ2021 እኤአ ላይ የሚካሄደውን 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ካሜሮን በሙሉ ፈቃደኝነትና ዝግጁነት ማመልከቷን የተነጋገረው ካፍ ከ5 ወራት በኋላ በሴኔጋል በሚያደርገው ጉባኤ ውሳኔውን እንደሚያሳልፍ ገልጿል፡፡ ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ እና የምድብ ድልድልም እጣ በማውጣት ይፋ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያ ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሚደረገው ማጣርያ በምድብ 11 ከማዳጋስካር፤ አይቬሪኮስትና ኒጀር ጋር መደልደሏን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ግብፅ 32ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በ5 ወራት ዝግጅት በ ተሳካ ሁኔታ ማስተናገዷን የካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ እንዲሁም የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ አድንቀዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ዋና ፀሃፊዋን ሴኔጋላዊት ፋቲማ ሳሞራ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የአስተዳደር ስራዎች ለሚቀጥሉት ስምንት ወራት በበላይ ጠባቂነት እንድታገለግል መሾሙ የሚታወቅ ሲሆን፤ የካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ተግባራዊ የሆነ ድጋፍ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬን ፕሬዝዳንት እና ሌሎች አመራሮች በሙስና የተከሰሱት ከወራት በፊት ሲሆን የፊፋ የስነምግባር ኮሚቴ አስፈላጊ ምርመራ እያደረገ ነው፡፡ የግብፅ መንግስት የአፍሪካ ዋንጫውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ከ542ሺ ዶላር በላይ ወጭ ማድረጉን ያስታወቀ ሲሆን ይህን በጀት ከ32 የተለያዩ ስፖንሰሮች ማግኘቱንና የግብፅ መንግስት ቀሪውን ድጋፍ መስጠቱን ገልጿል:: በአፍሪካ ዋንጫው ከተለያዩ የአረብ አገራት እና የአፍሪካ አገራት ከ700ሺ በላይ ቱሪስቶች ገብተው በሚደረገው የተሳካ መስተንግዶ የግብፅ ኢኮኖሚ በተለይ በቱሪዝም መስክ 20 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገቢ እንደሚገኝ ተስፋ ተደርጓል፡፡
በአፍሪካ ዋንጫው የግብፅ መስተንግዶ የተደነቀ ቢሆንም በአስተዳዳሩ ላይ የሚታዩ አንዳንድ ቀውሶች ከውድድሩ በኋላ መነጋገርያ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡
የአፍሪካ ዋንጫው በመላው ዓለም በሚካሄዱ ውድድሮችም ትኩረት ያጣ ሲሆን ዋናዋናዎቹ የዊምብልደን የሜዳ ቴኒስ ፍፃሜ፤ የዓለም የክሪኬት ዋንጫ እና የፎርሙላ ዋን ግራንፕሪ ውድድሮች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
በተጠቀሱት ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮችና ሌሎች ምክንያቶች የአፍሪካ ዋንጫው በስታድዬም ድርቅ የተመታ ሲሆን በአማካይ ከ5ሺ እስከ 7ሺ ደጋፊዎች ስታድዬም ይገቡ የነበረው የአዘጋጇን ግብፅ ብሄራዊ ቡድን ለመደገፍ ብቻ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ግጥሚያዎች በስታድዬም ያገኙት ተመልዕካች  ቢበዛ ከ3ሺ አይበልጥም፡፡ ለተፈጠረው የተመልካች ድርቅ የግብፅ ብሄራዊ ቡድን ከግማሽ ፍፃሜው በፊት መሰናበት፤ የስፖርት መሰረተልማቶች ብቁና የተሟሉ አለመሆን፤ በአስተናጋጅ ከተሞች ከስታድዬም ወደ ስታድዬም በሚደረጉ ጉዞዎች ምኙ የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖሩ እንዲሁም ውድድሩን በቲቪ ስርጭት የመታደም ሁነሬታ እና በዲጂታል አውታሮች ሰፊ ሽፋን ማግኘቱ ምክንያቶች ሆነው ቀርበዋል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮፌደሬሽን የገባበት የአስተዳር ውጥረት እና የሙስና ቀውስ ከውድድሩ ጋር ተያይዞ መነጋገርያ ሆነ የሰነበተ ሲሆን፤ ፊፋ በኮንፌደሬሽኑ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ እና ስራዎች ጣልቃ መግባቱን ፈጥሮታል፡፡ የአፍሪካን እግር በኳስ በካፍ ዙርያ የተሰበሰቡ እና በአመራር ላይ የሚገኙ 22 ግለሰቦች ተቆጣጥረውታል በሚል ከየአቅጣጫው ውንጅላው በዝቷል፡፡
የካፍ አስተዳደር በአፈጣኝ ለውጥ ካላመጣ ያሉትን ውስን የስፖንሰርሺፕ ድጋፎች ሊያጣ እንደሚችልም ተሰግቷል፡፡ ለካፍ በማርኬቲንግ ስራዎች አጋር ሆኖ የሚሰራው የፈረንሳዩ ኩባንያ ላጋርዴር በአህጉራዊ ተቋም የተፈጠሩት አስተዳደራዊ የስነ ምግባር ጥሰቶች እና በከፍተኛ አመራሮቹ ላይ የሚቀርቡ ክሶች ከስፖንሰሮቹ አንዱ የሆነውን ቪዛ ኩባንያ ከውድድሩ ሊያርቀው እንደሚችል ያሰጋል በሚል ኢንሳይድ ዎርልድ ፉትቦል ዘግቧል፡፡ ላጋርዴር ከካፍ ጋር  በ2017 ላይ በፈፀመው ስምምነት በማርኬቲንግ እና በተለያዩ የንግድ ስራዎች እስከ 2028 እኤአ ድረስ እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማድረግ ነው፡፡
የፈረንሳዩ የነዳጅ ኩባንያ በ2016 እኤአ ላይ ከካፍ ጋር በፈፀመው ስምምነት መሰረት ለስምንት አመታት በአህጉሪቱ ከፍተኛ የእግር ኳስ ውድድሮች ብቸኛው አብይ ስፖንሰር የሚቀጥል ሲሆን ከ2017 እኤአ 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ 10 የአህጉሪቱን ውድድሮች እንደሚደግፍ ነው፡፡
ካፍ በአፍሪካ ዋንጫ አብይ ስፖንሰር ቶታል ጋር በገባው ውል ለስምንት ዓመታት 250 ሚሊዮን ዶላር ገቢ  ማግኘቱ  የአፍሪካ ዋንጫውን ለማካሄድ የሚያስችለው ቢሆንም ከቶታል ጋር የውል ስምመነቱን ለመቀጠል ወይንም ሌሎች ስፖንሰሮችን ለመማረክ ችግር እንደሚሆንበት እየተገለፀ ነው፡፡ በሌላ በኩል ካፍ ከታዋቂ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ጋር የሚሰራበት ውል የሌለው መሆኑ የአስተዳደሩን ክፍተት የሚያጋልጥ ሲሆን በ2016 እኤአ ላይ ከአዲዳስ ጋር የነበረው ውል ከተፈፀመ በኋላ ተተኪውን ኩባንያ ማግኘት እያዳገተው መጥቷል፡፡

Read 12781 times