Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 09 June 2012 09:52

ጎል የታለ ጎል....?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በ2014 ብራዚል ለምታዘጋጀው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የምድብ ማጣርያ ነገ በአዲስ አበባ ስታድዬም ኢትዮጵያና ሴንትራል አፍሪካን ሪፖብሊክ በሁለተኛ ዙር ግጥሚያ ይገናኛሉ፡፡ ዛሬ ደግሞ በሌላ የምድቡ ጨዋታ ቦትስዋና ጎረቤቷን ደቡብ አፍሪካን ታስተናግዳለች፡፡ ምድቡን በ3 ነጥብና በ2 የግብ ክፍያ የሚመራው ባለፈው ሳምንት ቦትስዋናን በሜዳው 2ለ0 ያሸነፈው ሴንትራል አፍሪካን ሪፖብሊክ ነው፡፡ ከሳምንት በፊት 1ለ1 አቻ የተለያዩት ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን አከታትለው ሲይዙ ቦትስዋና ያለምንም ነጥብ በሁለት የግብ እዳ  መጨረሻ ነች፡፡  በሁለተኛ ዙር የማጣርያው ጨዋታዎች ለሁሉም የምድብ 1 ቡድኖች ማሸነፍ ወሳኝ ሲሆን በተለይ  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በነገው ጨዋታ ሴንተራል አፍሪካን ሪፖብሊክን ማሸነፉ ምድቡን የሚመራበትን  እድል ይፈጥራል፡፡

ለ20ኛው የዓለም ዋንጫ  በሚደረገው የምድብ ማጣሪያ ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከደቡብ አፍሪካ ፣ ሴንትራል አፍሪካ ሪፖብሊክና እና ከቦትስዋና ጋር መደልደሏ ይታወቃል፡፡ 15 ወራትን የሚወስደው የዚሁ ምድብ ማጣርያ በ3ኛ ዙር የሚቀጥለው ከሰባት ወራት በኋላ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቀሪ ጨዋታዎቿ ከሰባት ወራት በኋላ በሜዳዋ  ከቦትስዋና ጋር፤ ከ10 ወራት በኋላ ከሜዳዋ ውጭ ከቦትስዋና እንዲሁም በሳምንቱ በሜዳዋ ደቡብ አፍሪካን አስተናግዳ ከ13 ወራት በኋላ ደግሞ ሴንትራል አፍሪካ ሪፖብሊክን ከሜዳዋ ውጭ በመግጠም ትጨርሳለች፡፡

በምድብ 1 ያሉት የኢትዮጵያ ተፋላሚዎች  የተለያዩ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ቦትስዋና በገንዘብ ችግር ምክንያት በቂ ዝግጅት አልነበራትም፡፡ የሴንትራል አፍሪካ ሪፖብሊክ  ብሄራዊ ቡድን ደግሞ  የማጣርያ ጨዋታውን በድል ቢጀምርም ለአገሪቱ እግር ኳስ ከፍተኛ መሻሻል ምክንያት የነበሩትን ፈረንሳዊ አሰልጣኝ የ9 ወር ደሞዝ መክፈል ባለመቻሏ አጥታለች ፡፡ ደቡብ አፍሪካ  በኢንተርናሽናል ጨዋታ 8 ወር ሳታሸንፍ ቆይታ  ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ ጋር በሜዳቸው አቻ ከተለያየች በኋላ አሰልጣኟን በማባረር ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባለፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ ባደረገው ጨዋታ በዚያ የሚኖሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የሰጡት  ድጋፍ ለቡድኑ ጥንካሬ የነበረው ሚና በተለያዩ ዘገባዎች በአድናቆት ተወስቷል፡፡ በሮያል ባፎኪንግ ስታዲየም በተከናወነው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሳላዲን ሰኢድ በ30ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መሪነቱን ይዞ ነበር፡፡ ቡድኑ በ71ኛው ደቂቃ በተቆጠረበት ግብ ግን አቻ ለመውጣት ተገዷል፡፡  የሁለቱ ቡድኖች በአቻ ውጤት መለየያት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ መነቃቃት ቢፈጥርም ለደቡብ አፍሪካ ቀውስን ፈጥሯል፡፡ የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን በጨዋታው ማግስት የብሄራዊ ቡድኑን አሰልጣኝ ፒትሶ  ሞሲማኔ  ለቡድኑ አይጠቅሙም በሚል ምክንያት ያባረረ ሲሆን አሰልጣኙ ቀሪ የ2 አመት የስራ ኮንትራት እየቀራቸው ውሉን በማፍረሱ  እስከ 600ሺ ዶላር ካሳ ሊከፍል ይገደዳል፡፡ የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙሃናት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ያልተጠበቀ ጥንካሬ መደነቃቸውን በዘገባዎቻቸው ሲያወሱ በተለይ ለሳላዲን ሰኢድ ከፍተኛ አድናቆት እንደሰጡም ለመረዳት ተችሏል፡፡ዋልያዎቹ ከሳምንት በፊት ከሜዳ ውጪ ባደረጉት ጨዋታ ነጥብ ለመጋራት መቻላቸው በቀጣይ ለሚጠብቋቸው ጨዋታዎች ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ የነገውን ጨዋታ ከሴንተራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር በሜዳውና በደጋፊው ፊት ሲያደርግ ግን በብዙ ጎሎች የሚያሸንፍበትን ጨዋታ እንዲያሳይ  ከፍተኛ ፍላጎት አለ፡፡

በዋልያዎቹ አጨራረስ ላይ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአጨራረስ ችግር ለበርካታ ዓመታት በእግር ኳሱ ላይ ሰፍኖ የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በተለያዩ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች በሜዳው ብዙም ባይሸነፍም ብዙውን ግዜ 1ለ0 ብቻ እየረታ ካልሆነለት ደግሞ 0ለ0 አቻ እየተለያየ ከሜዳ ውጭ ደግሞ በተጋጣሚዎቹ 3 ጎሎችና ከዚያም በላይ እየገባበት በመሸነፍ ከበርካታ የማጣርያ ውድድሮች ውጭ መሆኑ ተለምዶ ቆይቷል፡፡ ለዚሁ የብሄራዊ ቡድኑ ግብ የማስቆጠር ችግር የተለያዩ ምክንያቶች ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የእግር ኳስ ተጨዋቾች በየሰፈሩ በሚጫወቱት ኳስ የግብ አግዳሚ ባልተሰራለት እና ጠባቦቹ የፒቲ ጎሎችን በሚጠቀሙ ሜዳዎች እየተጫወቱ ማደጋቸው የግብ አዳኝነታቸውን እንዳሳሳው የሚገልፁ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ብሄራዊ ቡድኑ ለረጅም ግዜ ውጤት  ከማጣቱ ጋር በተያያዘ በተለይ ከትልልቆቹ የሰሜን አፍሪካና የምዕራብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ሲገናኝ በስነልቦና በኩል የሚፈጠርበት ድክመት ላለበት የግብ ችግር ሰበብ የሚያደርጉም አሉ፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በተቃራኒዎቹ ላይ በሜዳው ሲጫወት  አንድ ጎል አግብቶ ውጤት ለማስጠበቅ በሚል ፍራቻ አጨዋወቱ ሲበላሽበት  በተደጋጋሚ መታየቱን በመጥቀስ ለአጨራረስ ችግሩ ምክንያት መሆኑን የሚያስረዱም ይኖራሉ፡፡ አሁን ያሉት ዋና አሰልጣኝ እንኳን በዚህ አሳሳቢ ችግር ትኩረት በማድረግ ለአጥቂዎች የተለየ ልምምድ በመስጠት እንዳይሰሩም ችግር አለባቸው፡፡ ምክንያቱም አሰልጣኙ ተመሳሳይ ልምምድን ለማከናወን ሌሎቹን የቡድኑ ተሰላፊዎች ወይንም ወይም አጥቂዎቹን ለይቶ የሚያሰራ ብቁ እና ረዳት አሰልጣኝ ስለሚያስፈልጋቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአጨራረስ ችግርን በአሃዛዊ መረጃዎችም ማሳየት ይቻላል፡፡ ዋልያዎቹ በዓለም ዋንጫ የማጣርያ ውድድሮች ባላቸው ታሪክ 34 ጨዋታዎች አድርገው በ7 ድል፤ በ10 አቻ ውጤት ሲቀናቸው በ17 ጨዋታዎች ተሸንፈዋል፡፡ በእነዚህ ጨዋታዎች በተጋጣሚዎቻቸው ላይ 40 ጎሎች ሲያስቆጥሩ 55 የገባባቸው ሲሆን በአንድ ጨዋታ በአማካይ ግብ የማስቆጠር እድላቸው በ1.18 የሚተመን ነው፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ውድደሮችም ብሄራዊ ቡድኑ ባንድ ጨዋታ ግብ የማስቆጠር እድሉ በ1.05 የተወሰነ ሆኖ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ቡድኑ ካለፈው አመት ወዲህ ባደረጋቸው ግጥሚያዎች ውጤቶች ምን ያህል የግብ ድርቅ የተመታ መሆኑንም ማመልከት ይቻላል፡፡ አምና ዋልያዎቹ በሴካፋ ውድድር ላይ በነበራቸው ተሳትፎ ከሱዳንና ከማላዊ ጋር 1 እኩል በሆነ ተመሳሳይ አቻ ውጤት ሲለያዩ በማላዊ ደግሞ 2ለ0 መሸነፋቸው ይታወሳል፡፡ የዛሬ ሳምንት  ብሄራዊ ቡድኑ  ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዝ  አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው  ስለጨዋታው ሲናገሩ በደቡብ አፍሪካ ጫና ከበዛብን እንደ ቼልሲ እንከላከላለን  ቢሉም  የሳላዲን ቡድኑን መቀላቀል ያለብንን ግብ የማስቆጠር ክፍተት ይሞላዋል ሲሉ በተጨማሪ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ነገ ከሴንተራል አፍሪካ ጋር በሚደረገው ግጥሚያ በመከላከል ላይ ያተኮረ አጨዋወት ለዋልያዎቹ አያወጣም፡፡ የሳላዲን ብቻ ሳይሆን የብሄራዊ ቡድኑ ሙሉ ተሰላፊዎችና አጥቂዎች በግብ አዳኝነት በከፍተኛ ደረጃ  ጥረት ማድረጋቸው የሚጠበቅ ሆኗል፡፡ ዋልያዎቹ ነገ በ2014 የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ሁለተኛ ዙር ከሴንተራል አፍሪካን ሪፖብሊክ ተጫውተው  በሳምንቱ ደግሞ በ2013 በደቡብ አፍሪካ ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከሜዳው ውጭ በመልስ ጨዋታ ከቤኒን  ጋር ይገናኛሉ፡፡ ከ5 ሳምንታት በፊት እዚህ አዲስ አበባ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለ2013 የፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከቤኒን አቻው ባደረገው ጨዋታ ያስመዘገበው ውጤት 0ለ0  ነበር፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይም የዋልያዎቹ አጨራራስ ችግር አነጋግሮ ነበር፡፡የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጎል የማስቆጠር ነባር ችግሩን ነገ በሚያደርገው የዓለም ዋንጫ የሁለተኛ ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታና ከሳምንት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ከቤኒን ጋር ከሜዳው ውጭ በሚያደርገው የመልስ ጨዋታ መለወጥ ይኖርበታል፡፡

የኡባንጊ ጭራቆች

ነገ ዋልያዎቹ የሚገጥመው የሴንትራል አፍሪካ ሪፖብሊክ ብሔራዊ ቡድን የታችኛው ኡባንጊ ጭራቆች በሚል ቅፅል ስሙ ይታወቃል፡፡  የሴንትራል አፍሪካ ሪፖብሊክ ብሔራዊ ቡድን ባለፉት 2 ወራት በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ አመርቂ መሻሻል ካሳዩ ቡድኖች ዋና ተጠቃሽ ሊሆን የበቃው ከነበረበት ደረጃ ስምንት እርከኖችን በመውጣቱ ሲሆን በዚያ አገር እግር ኳሱ ባለፉት 21 ወራት 79 እርከኖችን በመውጣት ከፍተኛ ለውጥ ማሳየቱን ፊፋ በኦፊሴላዊ ድረገፁ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ ገልጿል፡፡ ከ2 ዓመት በፊት የሴንትራል አፍሪካ ሪፖብሊክ በእግር ኳስ ደረጃው 202ኛ ነበር፡፡ 5 ሚሊዮን ህዝብ በሚኖርበት ሴንትራል አፍሪካ ሪፖብሊክ የቅርጫት ኳስ በአመዛኙ ተወዳጅ ስፖርቱ መሆኑን ያወሳው የፊፋ ዘገባ ባለፈው ዓመት ብሔራዊ ቡድኑ ወደ 2014 የዓለም ዋንጫ የምድብ ድልድል የገባው ያለ ቅድመ ማጣሪያ መሆኑን ጠቅሶ በእግር ኳስ ፈጣን ዕድገት እየታየ መምጣቱን አመልክቷል፡፡

ከሴንትራል አፍሪካን ሪፖብሊክ ተጨዋቾች የ23 ዓመቱ ማፑው ያንጋ ተጠቃሽ ይሆናል፡፡ የቡድኑን ተከላካይ መስመር ባጠናከረ ብቃቱ ለነገው ጨዋታ ወሳኝ ይሆናል በሚል የተጠቀሰው ያንጋ ከስምንት አመቱ ጀምሮ በፈረንሳይ የኖረ ሲሆን ዘንድሮ በሊግ 1 ሻምፒዮን ሊሆን የበቃውን ሞንትፕሊዬርን በአምበልነት በመምራት ከፍተኛ አድናቆት ያገኘ ነው ፡፡ በሴንትራል አፍሪካ ሪፖብሊክ ቡድን ለፈረንሳይ ሊጐች የሚጫወቱ ሌሎች ምርጥ ተከላካዮችም  በነገው ጨዋታ ይኖራሉ፡፡

በጎል ዶት ኮም ትንበያ

ጎል ዶት ኮም በኢትዮጵያና በሴንተራል አፍሪካን ሪፖብሊክ ጨዋታ ላይ ከአንባቢዎቹ አሰባስቦ በድረገፁ ይፋ ባደረገው ትንበያ 3ቱ ዋና ግምቶች አሸናፊነቱን በሙሉ ለዋልያዎቹ ያደረጉ ናቸው፡፡ በጎል ዶት ኮም አንባቢዎች ትንበያ መሰረት 21.21 በመቶ  3ለ1፤ 18.18 በመቶ 2ለ0 እንዲሁም 15.15 በመቶ 2ለ1 በሆነ ውጤት ኢትዮጵያ ሴንተራል አፍሪካን ሪፖብሊክን እንደምታሸንፍ ተገምቷል፡፡

ሳላ ብልሁ ወዳጅ

የግብፁ ክለብ ዋዲ ዳግላ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ባለፈው ሳምንት 1 እኩል ከተለያዩበት ጨዋታ በኋላ ግብ ያስቆጠረውን ሳላዲን ሰኢድ በኦፊሴላዊ ድረገፁ ፎቶውን በማስቀመጥ ብልሁ ወዳጅ በሚል አሞካሽቶታል። ሳላዲን ሰኢድ ወደ ግብፁ ዋዲ ዳግላ ክለብ የተዛወረው ባለፈው ዓመት ሲሆን በዝውውሩ የግብፁ ክለብ ለቀድሞ ክለቡ ቅዱስጊዮርጊስ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ከፍሏል፡፡ በዝውውሩ ወቅት የወጡ መረጃዎች ሲያመለክቱ በዋዲ ዳግላ ክለብ በወር ከ200ሺ ብር በላይ ተከፋይ እንደሚሆን ተገልፆ ነበር፡፡ በዝውውሩ መሳካትም ሳላዲን ሰኢድ በግብጽ የሚጫወት የመጀመርያ ኢትዮጵያዊ ተጨዋችም ሆኗል።

 

 

 

Read 3361 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 10:03