Saturday, 20 July 2019 12:29

የሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች ስልጣን ለመጋራት ተስማሙ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የሱዳን ወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤትና የአገሪቱ ተቃዋሚ ሃይሎች ስልጣን ለመጋራት የሚያስችላቸውንና ለወራት የዘለቀውን ህዝባዊ ተቃውሞና ግጭት ያስቆማል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን  ስምምነት ባለፈው ማክሰኞ መፈራረማቸው ተዘግቧል፡፡
ሁለቱ ሃይሎች አንድ ሌሊት ሙሉ ሲወያዩና ሲከራከሩ ቆይተው በስተመጨረሻ የተፈራረሙት ስምምነት፣ የአገሪቱ ከፍተኛው የስልጣን እርከን የሆነውን ሉዐላዊ የጋራ ምክር ቤት አቋቁሞ፣ ለሶስት አመታት ያህል እየተፈራረቁ ለማስተዳደርና  በቀጣይም አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል እንደሆነ የዘገበው ቢቢሲ፤ የወታደራዊ ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀ መንበር ሞሃመድ ሃምዳን ዶጋሊ ስምምነቱን “ታሪካዊ ክስተት” ሲሉ በአድናቆት መግለጻቸውን አመልክቷል፡፡
ተቀናቃኝ ሃይሎቹ ከህገ መንግስት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚያደርጉት ቀጣይ ስምምነት አርብ ዕለት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው ገልጧል፡፡
ሱዳንን ለ30 አመታት ያህል ያስተዳደሩት ኦማር አልበሽር ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ በህዝባዊ ተቃውሞ ከመንበራቸው መባረራቸውን ተከትሎ፣ ስልጣኑን የያዘው ወታደራዊ ምክር ቤት፣ ስልጣኑን በሲቪል ለሚመራ መንግስት ያስረክብ በሚል ሱዳናውያን ለወራት ተቃውሞ ሲያደርጉ እንደቆዩ ይታወሳል፡፡

Read 7068 times