Tuesday, 30 July 2019 00:00

ስለ አዲሱ የእንግሊዝ ጠ/ሚ ቦሪስ ጆንሰን አንዳንድ ነገሮች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የእንግሊዝ የወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ቦሪስ ጆንሰን በአብላጫ ድምጽ ማሸነፋቸውን ተከትሎ፣ ባለፈው ረቡዕ የቀድሞዋን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ በመተካት አዲሱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በይፋ ስልጣን ተረክበዋል፡፡
የመዲናዋ ለንደን ከንቲባ በመሆን ያገለገሉትንና እ.ኤ.አ በ2016 እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነቷ ትውጣ የሚል ሃሳብ በማቀንቀን በይፋ ዘመቻ ማድረግ የጀመሩትን ቦሪስ ጆንሰንን በተመለከተ፣ የተለያዩ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ካወጧቸው ዘገባዎች ጥቂቱን እነሆ ብለናል፡፡
የግል ህይወት
ከዲፕሎማት አባት እና ከአርቲስ እናት እ.ኤ.አ 1964 ሰኔ 19 ቀን ኒውዮርክ ሲቲ ውስጥ የተወለዱት ቦሪስ ጆንሰን፣ ብራስልስ ዋን በተባለ ትምህርት ቤት በኤተን ኮሌጅና በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እንደተከታተሉ የህይወት ታሪካቸው ያሳያል፡፡
ሁለት ጊዜ ትዳር መስርተው ያፈረሱት ጆንሰን በአሁኑ ጊዜም ኬሪ ሲሞንድስ ከተባለች ወዳጃቸው ጋር እንደሚኖሩ ተነግሯል፡፡
በእንግሊዝ ፓርላማ የወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ የሆኑት ቦሪስ ጆንሰን፣ እ.ኤ.አ ከ2008 እስከ 2016 ድረስ የእንግሊዝ ርዕሰ መዲና ለንደን ከንቲባ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፣ ከ2016 እስከ 18 ደግሞ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል፡፡
ደራሲና ጋዜጠኛው ጆንሰን
አዲሱ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፤ “ሰቨንቲ ቱ ቨርጂንስ” የተሰኘውን ተወዳጅ ረጅም ልቦለድ ጨምሮ አራት  መጽሐፍትን ለንባብ ያበቁ ምርጥ ደራሲ ስለመሆናቸው ዘ ጋርዲያን ይመሰክርላቸዋል፡፡
ቦሪስ ጆንሰን ታዋቂዎቹን ታይምና ዴይሊ ቴሌግራፍ መጽሔት ጨምሮ በተለያዩ ታዋቂ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ለረጅም አመታት በሪፖርተርነትና በአምደኝነት እንደሰሩ የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ በተለይም የአውሮፓ ህብረት አገራትን የሚተቹ ጽሁፎችን ለንባብ በማብቃት እንደሚታወቁ አስነብቧል፡፡ ጥሩ ጸሃፊ እንጂ የፕሬስ ህግና መመሪያዎችን የማያከብሩ ጋዜጠኛ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ጆንሰን፣ የተዛባ ጽሁፍ አውጥተዋል በሚል ከታይም መጽሔት መባረራቸውን ዘ ጋርዲያን ያስታውሳል፡፡
ጨዋታ አዋቂውና ፈጣን ተናጋሪው
ለማዳመጥ የሚከብድ ፍጥነት ያለውና በጩህት የታጀበ ንግግር መለያቸው እንደሆነ የሚነገርላቸው ቦሪስ ጆንሰን፣ በአንደበተ ርዕቱነታቸውና የተመረጡ ቃላትን በመጠቀም እንደሚታወቁ የዘገበው ቢቢሲ፣ ጮክ ብለው መናገራቸውን በልጅነታቸው ከነበረባቸው የመስማት ችግር ጋር የተያያዘ ነው ይላል፡፡
ቦሪስ ጆንሰን ከፈጣን ተናጋሪነታቸው ባልተናነሰ በጨዋታ አዋቂነታቸውና ቀልዶችን በመፍጠር እንደሚታወቁም ቢቢሲ ይገልጻል፡፡
ከ970 ሺህ ዶላር ወደ 187 ሺህ ዶላር?
ፎርብስ መጽሄት የቦሪስ ጀንሰንን ገቢ አስመልክቶ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ እንዳለው፣ ሰውዬው በፓርላማ አባልነታቸው በከንቲባነታቸውና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ዘመናቸው ያገኙት የነበረው ገቢ እንዲሁም በንግግር፣ በደራሲነትና በጸሐፊነት የሚከፈላቸው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡
ሰውዬው ከመስከረም ወር 2018 እስከ ሰኔ ወር 2019 በነበሩት ጊዚያት በድምሩ 970 ሺህ ዶላር ገቢ ያገኙ ሲሆን፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው ያገኙት የነበረው 176 ሺህ ዶላር እንደነበርም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በህዳር ወር 2018 እስከ ሰኔ ወር 2019 በተለያዩ መድረኮች ላይ ንግግር በማድረግ ብቻ 560 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንደተከፈላቸው የሚነገርላቸው ጆንሰን፣ በ2018 ብቻ ከዴይሊ ቴሌግራፍ ጋዜጣ በደመወዝ መልክ 342 ሺህ ዶላር ያህል እንደተከፈለላቸውና  ለህትመት ካበቋቸው አራት መጽሐፍት ከ2017 እስከ 2019፣ 61.7 ሺህ ዶላር ያህል ገቢ እንዳገኙ ተዘግቦላቸዋል፡፡
ይህንን ሁሉ ገቢ ያገኙ የነበሩት ቦሪስ ጆንሰን በእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው የሚያገኙት አመታዊ ደመወዝ 186 ሺህ  ዶላር እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ አዲሱ ስልጣን ከገንዘብና ከገቢ አንጻር እንደማያዋጣቸው አውስቷል፡፡


Read 5952 times