Saturday, 27 July 2019 12:08

የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ 11 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 ‹‹ሰኞ የሚተከለው 2 መቶ ሚሊዮን ችግኝ የዓለም ክብረ ወሰን ይሆናል ተብሏል››

              ከነገ ወዲያ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ 2መቶ ሚሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ የተገለፀ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በክረምቱ
ለሚተከሉ 4 ቢሊዮን ችግኞች 11 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሰኞ በመላው ኢትዮጵያ የሚተከለው 200ሚ ችግኝ የዓለም ክብረ ወሰን ይሆናል ብለዋል ጠ/ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ፡፡ ከክረምቱ መግቢያ ግንቦት ወር ጀምሮ እስካሁን በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ አማራ፣
ደቡብና በሌሎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከ2.3 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው የተገለፀ ሲሆን በአጠቃላይ በችግኝ ተከላው 1.9 ሚሊዮን
ሄክታር መሬት እንደሚሸፈን ታውቋል፡፡ በክረምቱ ችግኝ ተከላ ከ4.7 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን አስተባባሪ ኮሚቴው ያስታወቀ ሲሆን ከነገ በስቲያ በሚደረገው መርሃ ግብር 2መቶ ሚሊዮን ችግኝ ከጠዋት እስከ ማታ በመላ ሀገሪቱ ይተከላል ተብሏል፡፡ ቀሪውም እስከ ክረምቱ ማብቂያ ተተክሎ ይጠናቀቃል፡፡
እስካሁን በኦሮሚያ 1.9 ቢሊዮን፣ በአማራ 1.3 ቢሊዮን፣ በደቡብ 1.3 ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ በከተሞች በተመረጡ ስፍራዎች ከ760 ሚሊዮን ችግኞች በላይ እንደሚተከሉ ታውቋል፡፡ በዚህ በአንድ ጀንበር 2 መቶ ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግ ሆነው ሁሉም የመንግስት ሠራተኞች በመርሃ ግብሩ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር በበኩሉ፤
በከተማዋ ባሉ 116 ወረዳዎች 2.8 ሚሊዮን የመትከያ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውንና ለሰኞ መርሃ ግብር ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ በእለቱም 100ሺህ ያህል ወጣቶች በማስተባበር ተግባር እንደሚሰማሩና ሁሉም የመንግስት ሠራተኞች ቢሮዎቻቸውን ዘግተው፣ በመርሃ ግብሩ እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡ በትናንትናው እለትም የአዲስ አበባ አስተዳደር የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ልዩ መድረክን በሚሊኒየም አዳራሽ አከናውኗል፡፡ ሰኞ የሚካሄደውን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አስመልክቶ መልዕክት ያስተላለፉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ “የዛፎች መተከል ጉዳይ ለእኛ የውበት ጉዳይ ብቻ
አይደለም፤ የህልውና ጉዳይ ነው፣ የእምነት ጉዳይ ነው፣ የባህል ጉዳይ ነው፣ የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፣ ዛፍ ማለት እኛ ነን፤ እኛ ማለት ያለ
ዛፍ ምንም ነን” ብለዋል፡፡ ሃገሪቱ የደን ሽፋኗ መመናመኑ ለድርቅና ለተፈጥሮ አደጋዎች አጋልጧታል ያሉት ጠ/ ሚኒስትሩ በዚህ ንቅናቄ ለትውልድ የሚሻገር ተግባር ከውነን የተሻለ ነገን መፍጠር አለብን ብለዋል፡፡ ‹‹የሀገራችንን የደን ሽፋን እንዲያገግም ማድረግ ህልውናችንን ማጽናት፣ እምነታችንን
መጠበቅን ባህላችን ማበልፀግ፣ ኢኮኖሚያችንን ማዳበር ነው›› ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ በመልዕክታቸው ሰኞ በሚደረገው የ2መቶ ሚሊዮን ችግኝ ተከላም፣ በአንድ ቀን 2 መቶ ሚሊዮን በመትከል የአለም ክብረ ወሰንን እንሠብራለን ብለዋል፡፡ መገናኛ ብዙሃንና የሚመለከታቸው ሁሉ ለዚህ ንቅናቄ ለሰጡት ትኩረት ምስጋና ያቀረቡት ጠ/ሚኒስትሩ ዛፍ ብሔር፣ ቋንቋ፣ እምነትና ርዕዮተ ዓለም የለውም፡፡ ሁሉም ዛፍ የሁላችንም ነው የሠራነው ስራም ከእነዚህ ሁሉ በላይ ነው” ብለዋል፡፡ ህብረተሰቡ ሰኞ ሐምሌ 22 በመውጣት በአረንጓዴ ቀን አ ሻራውን እ ንዲያሳርፍም ጠ/ ሚኒስትሩ በመዕልክታቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Read 2461 times