Saturday, 27 July 2019 12:13

መልክቶቻችሁ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 “ክልል ካልሆንን ሞተን እንገኛለን!”

         ሰሞኑን በኤልቲቪ፣ የወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄን አስመልክቶ ቃለ ምልልስ የተደረገላቸውን አንድ የዩኒቨርሲቲ መምህርና የህግ ባለሙያ የሰጡትን ማብራሪያ በጥሞና አደመጥኩኝ፡፡ በነገራችን ላይ ከአንድ ዓመት ወዲህ በደቡብ ክልል፣ በዘመቻና በፉክክር በሚመስል መልኩ የክልልነት ጥያቄ ማቅረብ የጀመሩ ዞኖች ተወካይ ነን ባዮች (ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች) ለምን ጥድፊያ ውስጥ እንደገቡ ግራ ግብት ይላል፡፡ በቴሌቪዥን መስኮት ሲቀርቡ ለምን እንደሚቆጡና ማስጠንቀቂያ እንደሚያበዙም አላውቅም፡፡ አንድ ጥያቄ አለኝ::
 ለመሆኑ እኒህ ወገኖች “የክልልነት ጥያቄ” የሚያቀርቡት ለሕዝቡ ምን ሊፈይዱለት ይሆን? የኑሮ ደረጃውን ያሻሽሉለታል? የሥራ ዕድል ይፈጥሩለታል? ለሰራተኛው የደሞዝ ጭማሪ ያደርጉለታል? የተሻለ የጤና አገልግሎት ያቀርቡለታል? ወዘተ… ጥያቄው ብዙ ነው፡፡
እነዚህን መሰረታዊ ጥያቄዎች የማይመልሱ ከሆነ፤ ከዚህ ሁሉ ጥድፍያና ወከባ በስተጀርባ ሌላ አጀንዳ እንዳለ መጠርጠር ተገቢ ነው::  በተለይ ሀገር በነውጥ ማዕበል እየተናጠች፣ ግጭትና መፈናቀል በየቦታው እየፈነዳ ባለበት በዚህ ሰዓት “ዛሬውኑ ክልል ካልሆንን ሞተን እንገኛለን” ማለት የጤና አይደለም፡፡
ፖለቲከኞችና “የክልልነት ጥያቄ” አቀንቃኝ ልሂቃን (አክቲቪስቶች)፤ ከዚህ “አንገብጋቢ” የክልል አጀንዳ፤ የሚያገኙትን በቅጡ ብናውቅ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ምናልባት የበለጠ ሥልጣን?... ጥቅም?... ሀብት?...እንደው ምን ይሆን እንዲህ ዓይናቸውን አስጨፍኖ “አሁኑኑ ክልል!” የሚያስብላቸው?!
እንደ ማንኛውም የአገራችን ፖለቲከኛና ልሂቃን ‹‹የምንታገልለት ሕዝብ?” ማለት ቢያበዙብንም ቅሉ፤ የፈረደበት ምስኪን ሕዝብ ግን ክልል በሆነ ማግስት፣ ሌማቱ ሞልቶ እንደማያድር ጠንቅቀን እናውቃለን:: ሕዝቡ ክልል ከመሆን አንዳችም ጠብ የሚልለት ነገር እንደሌለ ይታወቃል፡፡ እነሱ ግን ሎተሪ የሚደርሰው እያስመስሉት ነው:: ባይሆን ሎተሪው የሚደርሰው ለእነሱ ነው - ለፖለቲከኞቹና አክቲቪስቶቹ፤ ለነገዎቹ የክልሉ ባለሥልጣናት!!
ሳላስበው ወደ ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ገባሁ እንጂ የእኔ ጥያቄ፣ (ስጋቴም ነው) ዞኖቹ ወደ ክልልነት ባደጉ ማግስት፣ የየአካባቢው ተወላጅ ባልሆኑ ዜጐች  ላይ የሚደርሰውን አስከፊ የመፈናቀልና የሞት አደጋ ማነው የሚታደጋቸው የሚለው ነው፡፡
ወደ ኤልቲቪ ልመልሳችሁ፡፡ የወላይታን የክልልነት ጥያቄ የሚያስረዱት “ተወካይ ነን” ባዮች፤ ክልል በመሆን ሂደት፤ “የአካባቢው ተወላጅ ባልሆኑ ዜጎች ላይ ጥቃትና መፈናቀል እንደማይደርስ ምን ማስተማመኛ አለ?›› በሚል ከጋዜጠኛ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ ‹‹ማስተማመኛው ህገ መንግስቱ ነው›› ብለዋል:: ግን የምራቸውን ነው?! ህገ መንግስቱ መቼ በሲዳማ ለተፈናቀሉትና ጥቃት ለደረሰባቸው… ማስተማመኛ ሆነ? ከዚህ ቀደምስ… በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በግፍ ሲባረሩና ሲፈናቀሉ ሕገ መንግስቱ መቼ አዳናቸው? ህገ መንግስቱ ዜጎችን ከመፈናቀል ታድጎ ያውቃል እንዴ? እነዚህ የክልል ጥያቄ አቀንቃኞች “ህገመንግስቱ ይታደጋቸዋል” ሲሉ ከአንጀታቸው ነው ወይስ ከአንገታቸው? ለነገሩ እነሱ የፈለጉትን ያግኙ እንጂ አገርና ህዝብ በአንድ እግራቸው ቢቆሙ ደንታቸው አይመስለኝም:: ለዚህ ነው እየሆነ ያለው ሁሉ የሚሆነው፡፡ ለማንኛውም ግን አሁንም መንግስት ለዜጐቹ ጥላ ከለላ ሊሆናቸው ይገባል፡፡ ያለበለዚያ የምንፈራው ይደርሳል፡፡
ዳዊት - ከአዲስ አበባ

Read 1464 times