Saturday, 27 July 2019 12:07

የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የመታሰቢያ ስያሜዎች እንዲመለሱ ለጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄ ቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 መንግስት በአዲስ አበባ ሐውልት እንዲያቆምላቸው ተጠይቋል

         ለቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የመታሰቢያ ሃውልት በአዲስ አበባ እንዲቆም፣ በስማቸው ተሰይመው የነበሩ የተለያዩ ተቋማት ስያሜም ወደነበሩበት እንዲመለሱ በስማቸው የተቋቋመው የመታሰቢያ ማህበር ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ላቀረበው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን አስታውቋል፡፡  
ማህበሩ በዛሬው እለት (ሐምሌ 20 ቀን 2011) በዋቢ ሸበሌ ሆቴል የግርማዊነታቸውን 127ኛ የልደት በዓል የሚያከብር ሲሆን በሥነስርዓቱ ላይም በእለቱም የንጉሠ ነገሥቱ መታሰቢያዎች ተመልሰው በሚፀኑበት ሁኔታ ላይም ምክክር ይደረጋል ተብሏል፡፡
በአፄ ኃይለሥላሴ ስም ይጠሩ ከነበሩ ተቋማት መካከል በራሣቸው መኖሪያ ቤት የከፈቱት የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጠቃሽ ሲሆን ቀድሞ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ” ተብሎ ይጠራ እንደነበር ይታወቃል::
አሁን እንጦጣ አጠቃላይ ተብሎ የሚጠራው ት/ቤትም ቀድሞ ተፈሪ መኮንን የሚል ስያሜ የነበረው ሲሆን ት/ቤቱ ወደ ቀደመው ስያሜው እንዲመለስ ብርቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ንጉሴ አምቦ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያም በስማቸው ይጠራ እንደነበር ነው ማህበሩ ያስታወሰው፡፡
የንጉሱ መታሰቢያ ስያሜዎችን ለማስመለስ ከሚደረገው ጥረት ጐን ለጐን የአፍሪካ ህብረት፤ ለአፍሪካ አንድነትና ህብረት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ያቆመላቸው ሐውልት እንዳለ ሆኖ ንጉሠ ነገስቱ ለሀገራቸው ላደረጉት አስተዋጽኦ በአዲስ አበባ ቀድሞ የሌኒን ሃውልት በነበረበት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጽ/ቤት ፊት ለፊት ሃውልታቸው እንዲቆም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የመታሰቢያ ማህበሩ “የቀድሞ ንብረቶቼ ናቸው” ያላቸው ህንፃዎችም እንዲመለሱለት ለጠ/ሚኒስትሩ በላከው ደብዳቤ መጠየቁን ጠቁሞ፤ ከእነዚህም መካከል ግዮን ሆቴል መግቢያ አካባቢ የሚገኘው “ሃዲያ ሱፐር ማርኬት” የሚገኝበት ህንፃ ተጠቃሽ መሆኑን አቶ ንጉሴ አስረድተዋል፡፡
በዛሬው እለት 127ኛ የልደት በአላቸውን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ልኡላን ቤተሰቦች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የሚዘክረው መታሰቢያ ማህበሩ በአሁኑ ወቅት በስማቸው ለ4መቶ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ድጋፍ እያደረገ በማስተማር ላይ እንደሚገኝና ከእነዚህም 3 መቶ ያህሉ መመረቃቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዛሬው እለት ከቀኑ 8 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ልደታቸው የሚከበረው አፄ ኃይለሥላሴ፤ ከ127 አመታት በፊት ሀረር ኤጀርሳ ጐሮ ነበር የተወለዱት፡፡ ኢትዮጵያንም ከ5 አስርት አመታት በላይ መርተዋል፡፡

Read 1305 times