Saturday, 27 July 2019 12:34

የ100 ዓመት የቤት ሥራ!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

 ለአምስት ዓመታት (ከ1928-1933) ኢትዮጵያን በወረራ ይዘው የነበሩት ጣሊያኖች፣ ለጊዜውም ቢሆን እቅዳቸው የተሳካው በተከተሉት የከፋፍለህ ግዛ ዘዴያቸው፣ የእስልምና እምነት ተከታዩን በክርስቲያኑ፣ ሌላውን ብሔረሰብ፣ በአማራው ላይ በማነሳሳት ነበር፡፡
የቀይ ኮከብ ዘመቻን ለማስጀመር አሥመራ ላይ ለተዘጋጀ ውይይት በቀረበ አንድ ጽሑፍ፤ የሳለህ ሳቤን ቡድንን ለማዳከም ጀኔራል አባይ አበባ፣ ለአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ቡድን ድጋፍ ያደርጉ እንደነበር፤ ኢሳያስ ደግሞ ኤርትራ ላይ ጦርነቱን አካሂደው የሚፈልጉትን ነፃነት ለማግኘት እንደማይችሉ ስላመኑ፣ ጦርነቱን ወደ መሐል አገር ለመግፋት የሚያገለግሏቸውን ክፍሎች፣ የብሔር ንቅናቄዎችን ይደግፉ እንደነበር ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ለሻዕቢያ ቅርብ አገልጋይ የነበረው ደግሞ ሕወሓት መሆኑ ይታወቃል፡፡
በማዕከላዊ መንግሥት ላይ ቅሬታ የነበራቸው አካባቢዎች፣ የጀብሃንና የሻዕቢያን መንገድ እየተከተሉ፣ የነፃነት ንቅናቄዎች መቋቋማቸውን ቀጠሉ፡፡ የደርግን መንግሥትን በመሣሪያ ትግል ለማስወገድም፣ አንድን አካባቢ ነፃ የማውጣት ወይም የመገንጠል ጥያቄ ያልነበራቸውና ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ለመመስረት ሃሳብ የነበራቸው ኢሕአፓና ኢዲዩ፣ የጦር ሜዳውን ተቀላቀሉ፡፡ አገር በጦርነት እሳት ተለበለበች፡፡
ደርግ ለአገሪቱ የፖለቲካ ችግር፣ ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት አልቻለም፡፡ በመጨረሻ ዘመን ላይ ደግሞ እንደ ጋምቤላ ነፃነት ንቅናቄ፣ እንደ ቤንሻንጉል የነፃነት ንቅናቄ ያሉ ሌሎች መሳሪያ ያነሱ ኃይሎች የጦር ግንባሩን ተቀላቀሉ፡፡
ለደርግ መንግሥት ውድቀት ሁሉም የየአቅማቸወን ያዋጡ ቢሆኑም፣ የበለጠ ጉልበት፣ የድርጅት አቅምና ሠራዊት የነበረው ሕወሓት ኢሕአዴግ፤ መንግሥቱን ተቆጣጥሮ የሽግግር መንግሥት መሠረተ፡፡ የሽግግር መንግሥት ምክር ቤትም ተቋቋመ፡፡
በምክር ቤቱ የፈለገውን ውሳኔ ማሳለፍ የሚያስችለውን ድምጽም ሕወሓት ኢሕአዴግ በራሱ እጅ አፍሶ ወሰደ፡፡
ደርግ መጨረሻ ላይ የነበረውን የአስተዳደር ክልል ማለትም፣ ጠቅላይ ግዛት፣ ክልል ወደሚል መለወጡ፤ የኤርትራን፣ የትግራይን፣ የጋምቤላንና፣ የሶማሌን ራስ ገዝ አስተዳደር ማቋቋሙ፣ ድሮ በአንድ ጠቅላይ ግዛት ሥር የነበሩት፤ ለምሳሌ፡- እንደ ጐንደር ያሉትን ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጐንደር ወዘተ. ብሎ መከለሉ፣ የወረዳ መዋቅርን አስቀርቶ፣ ዝቅተኛው የመንግሥት የአስተዳደር አካል አውራጃ ላይ እንዲቆም፣ ከእሱ በታች የገበሬና የቀበሌ ማኅበራት እንዲያገለግሉ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ሕወሓት ኢሕአዴግ፤ የጋምቤላ፣ የሶማሌ፣ የአፋርና የትግራይ ራስ ገዝ አስተዳደሮችን ሰርዞ፣ በዋናነት በብሔር አሰፋፈር ላይ የተመሰረቱ አስራ አራት ክልል መስተዳድሮችን አቋቋመ፡፡ ክልል ሁለት - አፋር፣ ክልል አራት - ኦሮሞ፣ ክልል አምስት - ሶማሌ፣ ክልል አስር - ሐረሪ አንዳንድ ሲይዙ፣ ከትግራይ ጀምሮ ሌሎች፣ ከአንድ በላይ ብሔረሰቦች በውስጣቸው የሚገኙ ሆኑ፡፡
ከክልል አምስት እስከ ክልል አስር አንድ የነበሩት አምስት ክልሎች፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ መንግሥት በሚፀድቅበት ጊዜ ተጨፍልቀው፣ አንድ ክልል ተደርገው፣ የፌደራል መንግሥቱን ከመሠረቱት ዘጠኝ ክልሎች አንዱ ተደረጉ፡፡ ከመጨፍለቃቸው በፊት አሁን አሁን ምሁራን ተወያይተውበታል እየተባለ ነው፡፡ ይህ ለኔ ፈፅሞ አዲስ ነው፡፡  የማውቀው ክልሉ ሲጨፈለቅ በክልሉ ውስጥ ይነቀሳቀሱ የነበሩ የኢሕአዴግ ደጋፊ ፓርቲዎች ግንባር መደረጋቸውን ነው፡፡ የክልሎች መጨፍለቅ ዋና ምክንያት ደግሞ በ1984 ዓ.ም ላይ በሽግግሩ መንግሥት ምክር ቤት አባል የነበሩና ከዚያ ውጪ የሚገኙ 17 በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ “ደቡብ ኅብረት” በሚል ስም መሰባሰባቸውና እነሱን ለማዳከምም ሕወሓት ኢሕአዴግ ቆርጦ መነሳቱ ነው፡፡ ለምን የኅብረቱ አባል ሆናችሁ? ተብለው ከሽግግር መንግሥቱ ምክር ቤት የተባረሩ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደነበሩም የሚዘነጋ አይደለም፡፡
ሰሞኑን የክልልነት ጥያቄያችን ተገቢውን መልስ በወቅቱ አላገኘም በማለት በተፈጠረው ተቃውሞ፤ በዘር ላይ ያተኮረ ጥቃት፣ ግፍና በደል ተፈጽሟል:: አባትና ልጅ በዘራቸው ምክንያት በድንጋይ ተወግረው ተገድለዋል፡፡ አንዳንድ መረጃዎችም፤ የሟቾቹን ቁጥር እስከ ሃምሳ እያደረሱት ነው፡፡ ሸሽተው ሕይወታቸውን ማትረፍ የቻሉ እድለኞች ናቸው፡፡ ብዙዎች እድሜ ልካቸውን ለፍተው ያከማቹት ንብረት፣ የእሳት እራት ሆኗል፡፡ ከእሳት የተረፈውም ለዘራፊ ሲሳይ ሆኗል፡፡
በዞኑ ነገሮች በፍጥነት እየተለዋወጡ እንደነበር መገንዘብ ይገባል፡፡ የክልሉ መንግሥት ችግሩ ሳይባባስ ለመቆጣጠር ያደረገውን ጥረት በተመለከተ መረጃ ባፈላልግም አልተሳካልኝም፡፡ ከሐምሌ 16 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ኮማንድ ፖስት እንዲቋቋምና በፌደራሉ መንግሥት እንዲመራ የወሰነው የክልሉ መንግሥት፤ ለምን ቀድሞ “እኔ ነገሩ አላማረኝም” ብሎ ይህን እርምጃ አልወሰደም? ‹‹አስቸኳይ የጊዜ አዋጅ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የግድ ሰው መሞትና ንብረት መውደም፣ መሠረተ ልማት መፍረስ ነበረበት?›› የሚል ጥያቄም አጥብቆ መጠየቅ ይገባል::
አመፀኞች መንገድ መስበራቸውን፣ ግንድ ጥለው መኪና እንዳያልፍ ማድረጋቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ በምስል አስደግፎ ዘግቧል፡፡ ይህ ከዚህ ቀደም በየአካባቢው ከተደረጉ የአመፀኛ እንቅስቃሴዎች የተለየ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ ቀጣዩ ምን ሊሆን እንደሚችል እጅግ ያሳስባል፡፡ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር መንግሥት ያለ አቅሙን ሁሉ ተጠቅሞ ሁኔታውን መከላከል ይኖርበታል፡፡ አየር ወለድ ማዝመት ባይቻል እንኳን በሄሊኮፕተር ኃይል አስገብቶ፣ ለሕዝብ መድረስና ህይወትና ንብረት መታደግ ተገቢ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡
በክልሉ የሚገኙ ሌሎች አስር ብሔረሰቦች ተመሳሳይ ጥያቄዎች አንሰተዋል፡፡ እነሱም ሕገ መንግሥቱ የሰጠንን ክልል የመሆን መብት ማግኘት አለብን እያሉ ነው፡፡ የእነሱም እንዲህ ደም በሚፈስበት፣ ንብረት በሚወድምበት፤ ሰው በሚፈናቀልበት መንገድ ነው ጥያቄያቸው የሚመለሰው? መንግሥትስ የሁኔታውን መባባስ አይቶ፣ ምን የጥንቃቄ እርምጃ ለመውሰድ አስቧል?
ከአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ከእነ ዶ/ር  አምባቸው መኮንንና ከእነ ጀነራል ሰዓረ መኮንን ግድያ በስተቀር፣ በሕዝብ ላይ የተፈፀሙ ሌሎች ጥቃቶች የተካሄዱት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ከአገር መውጣት እየጠበቁ ነው፡፡ ይህ ‹‹ግጥምጥሞሽ ነው›› ብሎ ብቻ ማለፍ የሚቻል አይመስለኝም:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዙሪያቸውን ቢቃኙ መልካም ነው፡፡ ለእርሳቸው አጀንዳ እያዘጋጀ፣ የራሱን አላማ የሚያስፈጽም ስውር ሴረኛ  ቢኖርስ? ነገሩ በጣም  አሳሳቢ ነው፡፡
ወደ ኋላ እንመለስ፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያን በዘር ከፋፍሎ ለመግዛት ከሰማንያ ሶስት ዓመት በፊት ሙከራውን አደረገ፡፡ እስከ መጨረሻው ባያዘልቀውም ለተወሰነ ጊዜ ተጠቀመበት፡፡ ሕወሓት ኢህአዴግ፤ ይህን ሃሳብ እንደገና አንስቶ ላለፉት 28 ዓመታት በአደባባይ ሲሰብክበት ኖረ፡፡ ዛሬ የዚህን መጥፎ ዘር ሰብል እየሰበሰቡ ነው፡፡ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ወጣት፤ በዘረኝነት ስሜት ከራሱና ከዘሩ ውጭ ሌላውን አጥብቆ እንዲጠላ ሆኖ ተሰብኳል፡፡ የእሱ ዘር ካልሆነ ሌላው ቢሞት፣ ቢፈናቀል፣ ቢሰደድ፣ ንብረቱ ቢወድም ለእርሱ ምኑም አይደለም፡፡ ከእሱ ዘር ውጪ ያለው ሁሉ ለእርሱ መጥፋት ያለበት ዘር ነው፡፡
የዛሬን አያርገውና፤ ‹‹ለኢትዮጵያ የመቶ አመት የቤት ሥራ ሰጥቻታለሁ›› ብሎ እንደነበር ሻዕቢያ ብዙዎቻችን እናስታውሳለን፡፡ ያ የመቶ አመት የቤት ሥራ ደግሞ ሌላ አይደለም፤ አገር እያፈረሰ ያለው ዘረኝነት እንጂ!!

Read 2311 times