Monday, 29 July 2019 00:00

“የኢትዮጵያን ታሪክ መሰረዝና መከለስ መቆም አለበት”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)


 • አንዱ ጨቋኝ፣ ሌላው ተጨቋኝ ተደርጎ የሚተረከው መሰረት የለሽ ነው
• ዋናው ችግር፤ ታሪክ በፖለቲካ መታሸቱና ለፖለቲካ ኢላማ መዋሉ ነው
• የውሸት ትርክቶችን መጋፈጥ፣ መሟገትና ማረም ያለባቸው ምሁራን ናቸው

         ከ30 አመት በላይ በተለያዩ ጋዜጦች ላይ በታሪክ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ጽሁፎችን አስነብበዋል፡፡ “የለውጥ ምጥ በኢትዮጵያ” የተሰኘ መጽሐፍም አሳትመዋል-- አንጋፋው ጋዜጠኛ ታዲዮስ ታንቱ፡፡ ብዙ ጊዜያቸውን በታሪክ ጉዳዮች ላይ በማንበብና በመመራመር የሚያሳልፉት ታዲዮስ፤ በተዛቡ የታሪክ ትርክቶችና በመፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር አውግተዋል፡፡ እነሆ፡-


      ባለፈ ታሪክ ላይ መግባባት አቅቶን፣ ዛሬ ቂም በቀል የምናወራርድበት ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን፡፡ ምንድን ነው ምክንያቱ? እንዴት በትላንት ታሪክ ላይ መግባባት ተሳነን?
መግባባት ያቃተን ታሪክን የፖለቲካ መሣሪያ አድርገን ለመጠቀም ስለምንፈልግ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም በየፊናው ለሱ ፖለቲካ የሚስማማውን ትርክት እያመጣ፣ ውዥንብር እየነዛ፣ የታሪክ እውነታን እየከለሰና  እየበረዘ ለራሱ የፖለቲካ አላማ ለማዋል ጥረት ያደርጋል፡፡ ለዚህ ነው ባለፈ ታሪካችን መግባባት አቅቶን የምንነታረከው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተጽፈው የቆዩ የታሪክ እውነታዎች፣ የታሪክ ምሁራን ብዙ የደከሙበትን የታሪክ እውነታ ለፖለቲካ አላማ ብለው መቀበል አቅቷቸው፣ በጐን የራሳቸውን የፖለቲካ ማጣፈጫ ነው የፈጠሩት፤ እንዲህ ያለው የክህደት ውዥንብርና የታሪክ ክህደት የመጣው ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ነው፡፡ በወቅቱ የተፈጠረው ታሪክን ለራስ የፖለቲካ አላማ አጣሞ የማቅረብ ነገር  ነው፡፡ ዘረኝነት ባልነበረበት፣ ጐሰኝነት ባልተስፋፋበት ወቅት፣ የተሰራን ታሪክ፣ አሁን ባለው በሱ የዘር መነጽር ውስጥ የመክተት አባዜ ነው፤ የፖለቲካ ልሂቃኑን የተጠናወተው በሽታ፡፡ ታሪክ ተመራማሪና ጋዜጠኛ፤ እውነት አፈላላጊ - እውነት ገላጮች ናቸው፡፡ ሁሌም ሥራቸው እውነትን መመርመር ነው፡፡ ታሪክ ፀሐፊዎች፣ ይሄን ኃላፊነት ምን ያህል ተወጥተዋል የሚለው ግን አጠያያቂ ነው::
እስቲ እንዳንጋባባ አድርገውናል ከሚባሉት አንኳር የታሪክ ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹን ይግለጹልኝ፡፡ እርስዎ ከታሪክ ንባብዎና ፍተሻዎ ምን ተገነዘቡ--?
ከአፄ ምኒልክ በፊትም ሆነ በኋላ ባለው ታሪካችን ላይ ነው መግባባት ያልቻልነው፡፡ አንዱ አፄ ምኒልክን ወራሪ ሲያደርጋቸው፣ ሌላው አገር አቅኒ ያደርጋቸዋል፡፡ ወራሪ ነው የሚሉ ወገኖች፤ ምኒልክ ኢትዮጵያን ከቅኝ ገዥዎች ጠብቀው ያቆዩልን መሆናቸውን ህሊናቸው ያውቃል፡፡ አሁን ለወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት ብለው ነው፣ እውነታውን ክደው ወራሪ፣ ጨካኝ፣ ጨፍጫፊ ብለው የሚያቀርቧቸው:: አፄ ምኒልክ፤ ጥቁር ወራሪ ናቸው የሚሉት፣ ህሊናቸው የሚነግራቸውን እውነት፣ በምላሳቸው የሚክዱ፣ የፖለቲካ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ አፄ ምኒልክ፣ ማንንም በተለየ ሁኔታ አልገዙም፡፡ ዘር ለይተው አልገደሉም፤ አላሳደዱም፤ አልጨፈጨፉም፡፡ ዘር መለየትን አያውቁም፡፡ እሣቸው “ግዛቴ የሚሉት” የገበረላቸውን ነው፡፡ ንጉሱ የተወለዱበት የአንኮበር ህዝብ የሚገብርላቸው እንዲሁም የጐጃም፣ ወሎ፣ ባሌ፣ አርሲ፣ ወለጋ ወይም የጅማ ህዝብ ከሚገብርላቸው የተለየ አይደለም፡፡ አንኮበርም ይገብራል፣ ሌላውም ይገብራል፡፡ የአስተዳደር መርሃቸው ይሄ ነው፡፡ የተለየ የአስተዳደር በደል ያደረሱበት ማህበረሰብ የለም፡፡ ሀገር ማቅናታቸው ደግሞ ብዙዎችን  ከነጭ ቅኝ ገዢነት ታድጓቸዋል፡፡
ግብር ሲባል ምን አይነት ግብር ነበር?
የአይነት ግብር ነው ሁሉም የሚገብረው:: የመንዝ፣ የቡልጋ፣ የምንጃር ህዝብም--የአይነት ግብር ነበር የሚገብረው፡፡ የአይነት ግብር ሲባል ገንዘብ አልነበረም፤ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ከብት ሊሆን ይችላል፡፡ የወላይታ፣ የሲዳማ፣ የወለጋ፣ የባሌ ወዘተ -- ህዝብም በተመሳሳይ የአይነት ግብር ነበር የሚገብረው፡፡ እገሌ የኔ ዘር ስለሆንክ፣ ከእገሌ ያነሰ ነው የምተገብረው አላሉም፤ ሁሉንም ነው በእኩል፣ ባለው ሃብት ልክ ያስገበሩት፡፡ ሁሉም የአይነት ግብር፣ በጊዜው በነበሩ የአካባቢ ገዥዎች፣ አካባቢው ያፈራውን ይገብሩ ነበር፡፡ ምኒልክ የተወለዱበት አንጐላ ራሱ፣ ይሄን ግብር ይገብር ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ ከዚህ አንፃር የሚወቀሱባቸው ጉዳዮች በሙሉ ዋጋ ቢስ ናቸው፡፡ ራሳቸውን የቻሉ የጥላቻ ትርክቶችና የፈጠራ ታሪኮች ናቸው፡፡
እነዚህን ታሪኮች ማን ነው የፈጠራቸው? ማንን ነው እርስዎ የሚወቅሱት?
ይሄን ሁሉ ታሪክ የፈጠሩት ወያኔዎች ናቸው:: የቂም ታሪክ ነው የፈጠሩት፡፡ እነዚህን ታሪኮች እንዴት ነው የፈጠሩት ከተባለ፣ የመጀመሪያው፣ የትግራይ ልሂቃን፣ አፄ ምኒልክ ከራስ መንገሻ ስልጣን ቀምተዋል የሚል ቂም አላቸወ፡፡ ዙፋን ወስደውብናል፣የሚል ቂምን ለማወራረድ ነው፣ ይሄ ሁሉ ትርክት የተፈጠረው፡፡ ለዚህ ቂም ማወራረጃ ደግሞ ሌላውንም ህብረተሰብ ባልተገባ መልኩ ቀስቅሰው ተጠቅመውበታል፡፡ አሁንም ከዚህ ስህተት እርምት ለመውሰድ ፍቃደኛ አይመስሉም፡፡
በአብዛኛው የአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስትን፣ ከሌሎች ነገስታት በተለየ የማጥላላትና በስርዓተ መንግስቱ ላይ የማማረር ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ሌሎች በዚህ መጠን ሲወቀሱ አይሰማም፡፡ ለምን  ይመስልዎታል?
አፄ ቴዎድሮስ፤ የኢትዮጵያ አንድነትን ለማምጣት ወጥነው ሲንቀሳቀሱ፣ ህልማቸውን ዳር ሳያደርሱ አለፉ፡፡ አፄ ዮሐንስም ያን ያህል ጠንካራ አልነበሩም:: ውስን አካባቢዎችን ይገዙ ነበር፡፡ እሳቸውም ለአገር ዋጋ የከፈሉ ናቸው፡፡ አፄ ምኒልክ ግን ኢትዮጵያን አንድ አድርገው፣ አዋህደው ያስተዳድሩ ስለነበር፣ የአካባቢ የጎጥ አንበሎች፣ እኛ የምንከበርበትን የገዥነት ስልጣን ምኒልክ አሳጥተውናል የሚል ቅሬታ ነበራቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ፍፁም ተቀብለዋቸው ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ ማድረጋቸው፣ በየአካባቢው ይፈፀሙ የነበሩ በርካታ ያልተገቡ ድርጊቶችን፣ የባሪያ ፍንገላን ጨምሮ አስቀርቷል፡፡ ይሄም ጥቅም አስገኝቷል፡፡ ለምሳሌ እኔ የተወለድኩበት የወላይታ ማህበረሰብ፣ አንድ የአካባቢ ገዥ ሞቶ ሲቀበር፣ አብረውት አራት አገልጋዮቹ፣ በአራቱም የጉድጓድ ማዕዘን ከእነ ሕይወታቸው ይቀበሩ ነበር፡፡ ያ የቀረው በምኒልክ ዘመን ነው፡፡ ሌሎች በርካታ አሁን ግን አሰቃቂ የሆኑ ባህላዊ ድርጊቶች እንዲቀሩ የተደረገው በአፄ ምኒልክ ነው፡፡ አሁን የወላይታም ሆነ የሌላው “በምኒልክ ተበድያለሁ” የሚሉ ሰዎች የሚያነሱት፣” ምኒልክ ወሮኛል” በሚል ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህን የመሳሰሉ አሁን ሲታሰብም ሆነ ሲሰማ፣ ምቾት የማይሰጡ ባህሎችን እንዲቀሩ ማድረጋቸውን አያነሱም፡፡ እኛ የራሳችን አገር የነበረን ነበርን የሚል ቅሬታም ይቀርባል፡፡ ይሄ ነገሩን አጥልቆ ካለማየት የሚመነጭ ነው፡፡ አፄ ምኒልክ የግዛት ማስፋፋት ያደረጉት ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን ለመቀራመት ባሰፈሰፉበት ወቅት ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬ ከምኒልክ በፊት አገር ነበረን የሚሉ አካላት፤ የቅኝ ገዥዎች ሰለባ ሆነው ማንነታቸውን ያጡ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ምኒልክ በኢትዮጵያ አንድነት እንዲፀኑ በማድረጋቸው፣ የተለወጠ የተቀየረ ማንነት የላቸውም፡። ሲዳማ ድሮም ሲዳማ ነው፤ ዛሬም ሲዳማ ነው፡፡ ወላይታ ድሮም ወላይታ ነው፤ ዛሬም ወላይታ ነው፡፡ ሶማሌ ትናንትም ዛሬም ሶማሌ ነው:: የሃረር ኢምርም፣ ከአፄ ምኒልክ በፊት ለግብፆች ይገብር ነበር፡፡ በኋላ አፄ ምኒልክ፤ ለባዕድ ከምትገብር ለኔ ገብር ብለው ነው ያስገበሩት፡፡
የአካባቢ መኳንንትነትና የጎጥ ባላባትነትን አስቀርተው በአንድ ጠንካራ ንጉሠ ነገስት እንዲያድሩ ነው ያደረጉት፡፡ ሌላው አፄ ምኒልክ፤ “እኛን የክርስቲያን አገር አካል አደረጉን ወይም የአቢሲኒያ አካል አደረጉን” የሚል ቂምም አለ፡፡ እውነት ለመናገር አፄ ምኒልክ በሃይልና በጉልበት እምነቱን ያስቀየሩት ማህበረሰብ የለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ዛሬ አፄ ምኒልክን የሚወቅሱ አካላት እንዲማሩ፣ የስልክና የፖስታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ በየአካባቢው ት/ቤት እንዲከፈት ያደረጉ ሰው ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይኑን እንዲገልጥ ያደረጉ መሪ እንጂ ታሪክን ለፖለቲካ ዓላማ አጣምመው የሚያቀርቡ ወገኖች እንደሚሉት፣ ጨቋኝ አልነበሩም፡። ምኒልክ አዲስ አበባ ውስጥ ቁጭ ብለው፣ ለየአካባቢው ገዥዎች በየጊዜው፣ “ሕዝቤን አትበድሉ” እያሉ  ደብዳቤ ይጽፉ ነበር፡፡ ምኒልክ ከተቀመጡባት ዙፋን፣ ለራሳቸው ምንም ሀብት ያልነበራቸው ንጉሠ ነገስት ነበሩ፡፡ አፄ ምኒልክ፤ ይሄን ሁሉ የአገር አንድነት የማስጠበቅና የማሰልጠን እሳቤ የወሰዱት ከአፄ ቴዎድሮስ ነው። ምኒልክ ውሃ አጠጥተው ኮተኮቱት፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ ፍሬውን ለቀሙት፤ ነው የሚባለው፡፡
አንዳንድ የኦሮሞ ልሂቃን አፄ ምኒልክን ክፉኛ የሚኮንኗቸው ለምንድን ነው?
የኦሮሞ ልሂቃን አስተዋይ ቢሆኑ ኖሮ፣ ለአፄ ምኒልክ አሰላ ላይ ሃውልት ሊሰሩላቸው ይገባ ነበር:: ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለኦሮሞ ባለውለታ ናቸው፡፡ ኦሮሞ በቀድሞ ጊዜ እርስ በእርሱ አይተዋወቅም:: ጅማን አባጅፋር፣ ወለጋን እነ ኩምሣ ዋረዳ፣ ሃረርን የሃረር ኢምሬት--ሌሎችም እንደዚያው ነው ሲያስተዳድሩ የነበረው፡። ህብረት፤ አንድነት አልበረውም፡፡ ዛሬ ኦሮሞ ለፈጠረው አንድነትና ህብረት፣ አፄ ምኒልክ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አፄ ምኒልክ ኦሮሞን በተለየ ሁኔታም፣ ኦሮሞ በመሆኑ ብቻ አልበደሉም፡፡ እንደውም እምነት ያሳደሩበትና የጦር አበጋዞቻቸው ያደረጓቸው ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ ጥላቻው የስሜት ውጤት እንጂ በአመክንዮ የሚሄድ አይደለም፡፡ አፄ ምኒልክ ኦሮሞን አንድ አድርገው፣ የኢትዮጵያ አካል በማድረግ ከማስተማራቸው በስተቀር የፈፀሙት የተለየ በደል የለም፡፡ እምነት እንኳ ለማስለወጥ የወሰዱት የሃይል እርምጃ የለም፡፡ ይሄን በታሪክ ጠቅሶ ሊከራከር የሚችል ሰው የለም:: እነ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ፣ እነ ፊታውራሪ ባልቻ፣ እነ ራስ ጎበና፣ እነ ራስ ዳርጌ፣ ከአፄ ምኒልክ ጋር አገር ያስተዳድሩ ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ የወረራና የወራሪነት ጉዳይ ከተነሳ ግን ብዙ ማስረጃ አቅርቦ ወራሪው ማን ነው? ተወራሪው ማን ነው? የሚለውን መከራከር ይቻላል፡፡ ከታሪክ ውስጥ ፖለቲካ ወጥቶ፣ ንፁህ ታሪክ ላይ የምንነጋገር ከሆነ፣ ለመግባባት ብዙም አያስቸግረንም፡። ዋናው ችግር ታሪክ በፖለቲካ መታሸቱና ለፖለቲካ ኢላማ መዋሉ ነው፡፡
እነዚህን የተዛቡ የታሪክ አቀራረቦች፣ እንዴት ነው ከፖለቲካ ኢላማ ነጥሎ፣ ንጹህ ታሪክ ማድረግ የሚቻለው?
ኢትየጵያን እኛ በምንፈልገው መንገድ እናቋቁማለን በማለት፣ የውሸት ትርክትና የጥላቻ ንግርት እያመጣን፣ ለትውልዱ መንገሩ ዋጋ ያስከፍላል፤ አስከፍሎናል፡፡ አንዱ ጨቋኝ ሌላው ተጨቋኝ እንደነበር ተደርጎ የሚተረከውም ምንም መሰረት የሌለው ነው፡፡ በብሄሩ ምክንያት በተለየ ሁኔታ የተጨቆነ የለም፡፡ አፄ ምኒልክ  የተወለዱበትን አንጎላላንም ሆነ ጂማን እኩል ያስገብሩ ነበር፡፡ እኔ ከነጠረ ቦታ ነው የወጣሁት፤ ብለው አያውቁም፡፡ ሁሉንም “ሕዝቤ” ነው የሚሉት፡፡ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ አማራ---በመሆኑ የበደሉት በደል የለም፡፡ ይሄን እውነት ምሁራን በሚገባ መግለጥ አለባቸው፡፡ ጋዜጠኞች፤ ከፖለቲከኞች የቀረበላቸውን፣ ለፖለቲካ አላማ ተጣሞ የተሰነደ ታሪክ ማነብነብ የለባቸውም፡፡ እውነቱን መመርመር አለባቸው፡፡ ጡት ቆረጠ፣ እጅ ቆረጠ ሲባል፤ የት? መቼ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል:: ተቆረጠ ከተባለም እጅና ጡት ሲቆረጥ፣ ምኒልክ ያውቁ ነበር? ለምሳሌ የአድዋ ጦርነት ሲካሄድ የባንዳዎች እጅና እግር የተቆረጠው በአፄ ምኒልክ  እውቅና ነው፡፡ እንዲህ አይነት እውነቶች አሉ፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን ጡት ቆረጡ፤ እጅ ቆረጡ--የሚባለው ምንም ማስረጃ የሌለው የውሸት ትርክት ነው፡፡
ይሄን እርስዎ  እውነት ያሉትን ጉዳይ የመግለጥ ኃላፊነት የማን ነው? ማን ነው ሃቁን መናገር ወይም መስበክ  ያለበት?
እንዲህ ያሉ የውሸት ትርክቶችን ፊት ለፊት ወጥተው መጋፈጥ፣ መሟገትና ማረም ያለባቸው ምሁራን ናቸው፡። ፖለቲከኝነት እውነቱን እንደጋቱት ማድረግ አለባቸው፡፡ ምሁራን ወገንተኝነት ሳያሳዩ፣ ለታሪክ ብቻ በመቆም ነገሩን ማስተካከል ይችላሉ:: ከየማህበረሰቡ የወጡ ምሁራን፤ ፖለቲካን ከታሪክ እውነት መነጠል አለባቸው፡፡ በዚያው ልክ ማንኛውንም የታሪክ እውነት ግልጥልጥ አድርጎ ማቅረብም ያስፈልጋል፡፡ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ጋዜጠኞችም፤ ይህን እውነት ፊት ለፊት ተጋፍጠው፣ ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ጋዜጠኛ በሰይፍ ስለት ላይ ሆኖ ነው እውነትን መግለጥ ያለበት፡፡
ኢትዮጵያዊነትና የብሔር ብሔረሰቦችን ጉዳይስ እንዴት ያዩታል?
አንዲት ታላቅ ኢትዮጵያ ለትውልድ እንድትተላለፍ ነው ፍላጐቴ፡፡ የብሔር ብሔረሰብ መብት የሚባል ነገር፣ በማህበራዊ ሳይንስ፣ በአስተዳደር እኩልነት ነው የሚገለፀው፡፡ ለአንዱ የተለየ ነገር ለማሟላት መታሰብ የለበትም:: የፖለቲካ ስልጣንም በዚህ መያዝ አይገባም፡፡ በቋንቋው መማር፣ መተዳደር ይችላል፡፡ ዋናው ማወቅ የሚገባው፣ ኢትዮጵያን ወረስናት እንጂ እኛ አልፈጠርናትም፡፡ ይህቺን የወረስናትን ሀገር እንዳለች ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ማንኛውንም መስዋዕትነት መክፈል አለብን፡፡
ብሔራዊ ስሜት ማበብ አለበት፡፡ ከብሔር ብሔረሰብ ትምክህት ይልቅ ኢትዮጵያዊ ትምክህት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትና ስነ ልቦና ማደግ አለበት፡፡ ስለ ጐጥ፣ ስለ አካባቢ፣ ስለ ብሔረሰብ ብሔርተኝነት ስንደሰኩር ብንውል፣ ማነስ እንጂ አያተልቅም፡፡ ሰፊ አያደርግም፡፡
አሁን ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን በቀላሉ መፍጠር የሚቻል ይመስልዎታል?
ይቻላል፡፡ ግን ቆርጦ የተነሳ አካል የለም:: ፍቃደኝነትና ተነሳሽነት በምሁራን ዘንድ የለም:: እንደውም ገና ናቸው፡፡ ምሁራን ኃላፊነታቸውን ቢወጡ፣ የክልል ስሜት ያለው ሁሉ፣ ኢትዮጵያን አግዝፎ እንዲመለከት ማድረግ ይቻላል፡፡ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ መንግስት ሲፈጠር፣ ጠንካራ ሀገራዊ አንድነት ይኖረናል፡፡ ያን ጊዜ ይሄን የተዛባ ትርክትና ብሔረሰባዊ ብሔርተኝነት መለወጥ ይቻላል፡፡ ወደ ትልቁ ኢትዮጵያዊነት ከፍታ ማውጣት ይቻላል:: የኢትዮጵያን ታሪክ መሰረዝና መከለስ መቆም አለበት፡፡ ቀደም ብለው የተፃፉት እንዳሉ ይቀመጡ በጥርጣሬ ላይ ያሉ በምሁራን ተፈልፍለው ይውጡ:: ከዚህ በተረፈ ግን ታሪክን በፖለቲካ ማሸት መቆም አለበት፡፡


Read 8053 times