Saturday, 27 July 2019 13:50

የስርዓት አልበኝነት ትርምስ እና የገናና መንግስት ቁጣ…. ከዚህ ውጭ አንችልም?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

• እስከ ዛሬ መዝለቃችን፣ ገና ድሮ አለመጥፋታችን ‹‹ተዓምር›› ነ

    • ነፃነትን ከሕግ አጣልተን፣ ከሰርዓት አልበኝነት አምታትተን ለክፉዎች ተመቻቸን
                
            የመንግስት ኮስታራ ግንባር ፈታ፣ ቁጣው ረገብ ሲል፣…. (በአገራችን የአላዋቂ ትርጉም፣…. ‹ነጻነት ሲሰፋ›)፣ ከደስታ፣ ከጭብጨባና ከምስጋና ጎን ለጎን፣ ውሎ ሳያድር፣ ከችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ይልቅ፣ የችግር ማርቢያ ሰበቦች ናቸው፤ በየአካባቢው የሚፈለፈሉት።
ለዚያውም፣ በድብቅ የሚሸረቡ ስውር ሴራዎች አይደሉም። በጭራሽ! እንዲያውም፣ የጥፋት መዓት የሚቀፈቀፈው፣ እዩኝ ስሙኝ እየተባለ ነው - እየተፎከረ፡፡ ‹የሕዝብ ጥያቄ› በሚል ትርጉም የለሽ ስያሜ እንደመልካም ሃሳብ እየተሰበከለት፣…. የዘረኝነት መፈክር ዘረኝነትን ማቆንጀት የሚችል ይመስል፤ ‹የብሔር ብሔረሰብ መብት› ወይም ‹የማንነት ጥያቄ› በሚል መጠሪያ እንደ ድንቅ ራዕይ እየተዘመረለት፣…. ‹ዋነኛ የለውጥ ትሩፋትና አቻ የለሽ የነፃነት ፍሬ› እንደሆነ በአደባባይ እየተመሰከረለት ነው፣…. የጥፋት ቅስቀሳና የሰበብ መዓት የሚፈለፈለው - በዲስኩርና በአዋጅ ጭምር እየታጀበ - በየእለቱ በይፋ እየተደጋገመ። ቅንጣት ታህል፣ በድብቅ የተሸረበ አይደለም።
ለነገሩ፣ በስውር ሴራ ምክንያት፣ ለስርዓት አልበኞች ትርምስ አልያም ለአምባገነን ቁጣ የሚንበረከክ አገር የለም። በተቃራኒው፣ አገር በትርምስ የሚጥለቀለቀው፣ ወይም በአምባገነንነት የሚደፈጠጠው፣ ምን እንደታሰበለት በይፋ እየተነገረውና እየሰማ፣ ምን እንደተደገሰለትም ከነመሰናዶው በግላጭ እያየ ነው።
ካሁን በፊት፣ በየክልሉና በየከተማው የተከሰቱ የስርዓት አልበኝነት ትርምሶችን አንድ በአንድ እየቆጠርን መመርመር እንችላለን። በድብቅ ተጠንስሰው ድንገት የተከሰቱ ጥፋቶች አይደሉም። ያ ሁሉ አስነዋሪና አሰቃቂ የስርዓት አልበኝነት ትርምስ የተፈፀመው፣ በአብዛኛው ከበርካታ ወራት የአደባባይ ቅስቀሳ በኋላ ነው።
በወለጋ፣ በሐረርጌ፣ በጌዲኦ፣ በወልቃይት፣ በጎንደር፣ በቤኒንሻንጉል፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ… ስንቱ ይቆጠራል? በአደባባይ የሚካሄድ የወራት ቅስቀሳ፣ ከዚያ በኋላ ዘግናኝ ጥፋት…. እነዚህና ብዙ ተመሳሳይ ትርምሶችን ከነመነሻቸውና ከነአስከፊ መዘዛቸው፣ በተደጋጋሚ ብናይም፣…. ከሳምንት የዘለለ ዘላቂ ግንዛቤና ትምህርት ያገኘንበት አይመስልም።
ከሳምንት በኋላ፣ ሌሎች ተመሳሳይ የጥፋት ዲስኩሮችንና ቅስቀሳዎችን ስንሰማና ስንመለከት፣ ብዙም አያሳስበንም። የተሰበከውና የተዘመረለት ቅስቀሳ፣ ውሎ አድሮ፣ ለወሬም ጭምር ወደሚያሰቅቅ የስርዓት አልበኝነት ጥፋት ተሸጋግሮ፣ የበርካቶችን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ ከመኖሪያና ከኑሮ ሲነቅልስ? እልፍና አእላፍ ለስቃይ ሲዳረጉስ?
በሕይወትና በንብረት ላይ ጥፋት የሰነዘረና የቀሰቀሰ፣ ጥፋት የፈፀመና የተባበረ ወንጀለኛ በሙሉ፣ አንድም ሳይቀር እያንዳንዱ ጥፋተኛ የስራውን ያህል በሕግ ተዳኝቶ የእጁን ማግኘት አለበት ብንል መልካም ነበር፡፡ ለነፃነትና ለሕግ የበላይነት መቆርቆር እንዲህ ነው፡፡ አሁን ይሄ ግልጽ አይደለም? ግልፅ ቢሆን እንኳ፣ ብዙዎች ግን ይምታታባቸዋል፡፡ የኋላ ቀርነት ነገር፣ በትርምስ ማግስት፣ በጅምላና በጭፍን፣ ‹መንግስት ይበላቸው! አፈር ድሜ ያብላቸው፣ ይፍጃቸው›…. የሚል ሌላ የጥፋት ዲስኩር ይደምቃል - አምባገነንነትን የሚጋብዝ ጥሪ ይበራከታል። ቁጡ መንግስት፣…. ከዚያም ገናና እየሆነ፣ ከዚያም አምባገነንነቱ የባሰ እየተተካ ሲሄድ፣…. ቁጣውና ገናናነቱ፣ በአጥፊዎችና በወንጀለኞች ላይ ብቻ እንደማይሆን ጠፍቶን ነው? ይህንንም በተደጋጋሚ አይተነዋል። ያኔ፣…. እንደገና መንግስትን መቃወም እንደበቂ ራዕይ ወደ መቁጠር ልንመለስ ነው?
በቃ፣ የኢትዮጵያ ነገር፣ እንዲህ በሁለት ጥፋቶች መካከል ዡዋዡዌ ሆኖ ይቅር?
ነፃነትን ከስርዓት አልበኝነት የማምታታት ሞኝነት!
‹‹ነፃነት›› ይከበራል ማለት፣ የእያንዳንዱን ሰው ህልውና፣ የኑሮ ትጋቱንና፣ በጥረት ያፈራውን ንብረት አለመንካት፣… ጥቃት እንዳይሰነዘርበትና እንዳይፈፀምበት በሕግ መከልከልና መከላከል፣ ካለፈም በሕግ መቅጣት፣… ይህንን ነፃነትን የመጠበቅና ፍትህን የመተግበር ሥራ በኃላፊነት ተቀብሎ ሕግና ስርዓትን ተከትሎ የሚፈጽም የመንግስት መዋቅር ማደራጀትን ያካትታል፡፡
የመንግስት መዋቅር፣ የፈደራልም ይሁን የወረዳ፣ የክልልም ይሁን የከተማ፣ የዞን ይሁን የቀበሌ፣ ሕግና ስርዓትን በተከተለ አሰራር፣ የእያንዳንዱን ሰው ነፃነትና መብት ከመጠበቅና ከማስከበር ውጭ ሌላ ቀዳሚ ዓላማ፣ ሌላ ቀዳሚ ፋይዳ፣ አገልግሎት ወይም ሌላ ቀዳሚ ስራ የለውም፡፡
በአገራችን አላዋቂዎች አተረጓጎም ግን፣ ‹‹ነፃነት›› ማለት፣ ሰበብ አስባብ በመደርደር፣ በዘር ወይም በመንደር በመቧደን፣ ‹‹የሕዝብ ጥያቄ›› የሚል ጭፍንነትን ወይም፣ ‹‹የማንነት ጥያቄ›› የሚል የዘረኝነት መፈክርን በማስጮህ፣ የሰውን ሕይወት መቅጠፍ፣ ንብረት መዝረፍ፣ ቤት ማቃጠል፣ ከኑሮ ማፈናቀልና ማሳደድ፣ መንገድ መዝጋት፣… በአጠቃላይ ሕግን መጣስ፣ ስርዓትን ማፍረስ፣ የሰው ህልውና ላይ መዝመት… ይሄ ሆኗል የ‹‹ነፃነት›› ትርጉም፡፡
ነፍስ ገዳይ፣ ወሮበላና ጋጠወጥ እንዳሻው የሚፈነጭበት… ሕግ የለሽ አረመኔነት፣ ስርዓት አልበኛ ትርምስ እንደ ማለት አድርገዋል ነፃነት ማለት፡፡ በአጭሩ ነፃነት ማለት፣ ስርዓት አልበኛ ፀረ ሕግ ማለት ሆኖብናል፡፡ ከዚህ የተሳከረ አስተሳሰብ የምናገኘው ውጤት ሁሌም ተመሳሳይ ነው - የአገር ቀውስ (chaos)፡፡
ሕይወት ሲረግፍ፣ አገር ሲቃጠልና ሲተራመስ፣ ‹‹የሕግ የበላይነት ይከበር›› ብለን የምር ብንጮህ መልካም ነበር፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? ‹‹የሕግ የበላይነት›› የሚለው ሀሳብ፣ ሁሌም አብሮን ሊኖር የሚገባው፣ የነፃነት ማስጠበቂያ መሳሪያና አለኝታ መሆኑ ይዘነጋል፡፡ በተቃራኒው፣ ‹‹ሕግ ይከበር››፣ ‹‹የሕግ የበላይነት ይከበር›› ለሚሉ አባባሎች፤ ‹‹መንግስት እንዳሻው እርምጃ ይውሰድ›› የሚል ትርጉም እንሰጣቸዋለን፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ‹‹አምባገነንነትን የመመኘት ጥሪ›‹› ሆኖብናል - የህግ የበላይነት፡፡
ነገር ከስሩ ሲጣመም፣ እንደዚህ ነው:: የነፃነትና የሕግ የበላይነት ትርጉሞችን እያጣመምን፣ ሁሉንም ነገር እያበላሸን፣ መውጫ በሚያሳጡ አጣብቂኞች መካከል፣ በአምባገነንነትና በትርምስ፣ በፈረቃ የመሰቃየትና የመጥፋት ዥዋዥዌ እናደርገዋለን፡፡ ነፃነት ማለት ሕግና ስርዓትን ማፍረስ፣ አገርን ማቃጠልና ሕወይትን ማጥፋት ሲሆንብን፤…. የሕግ የበላይነት ደግሞ፣ ሕግ የማይገዛው የመንግስት የዘፈቀደ ጉልበት መስሎ ሲታየን፣… አትጠራጠሩ፣ ነገር ከስሩ ተበላሽቶብናል፡፡ ተሳክሮብናል፡፡ እንዲያውም ነገርን ከስሩ አበላሽተናል፡፡ ተሳክረናል ቢባል ይሻላል፡፡
በእስከ ዛሬው አያያዛችን እስከ
ዛሬ አለመጥፋታችን ‹‹ተዓምር›› ነው!
አንዳንዴ ከምር ካሰባችሁትኮ፣ እስከ ዛሬ መዝለቃችንና መቆየታችን ያስገርማል:: ገና ድሮ አለመጥፋታችን ያስደንቃል፡፡ በእርግጥ፣ የጠፋ የለም ማለት አይደለም፡፡ የብዙ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ጠፍቷል፡፡ የሚሊዮኖች ኑሮ እንዳልነበረ ሆኗል፡፡ ለዚህ ሁሉ ጥፋት የምንጋለጠው ግን፣ ለክፉዎች ቅስቀሳና ለጨካኞች የወንጀል ዘመቻ የምንመቻችላቸው ግን፣ በተሳከረ አስተሳሰብ ምክንያት ነው፡፡
ተሳክረን እየተደናገርን፣ ወዲህ ወዲያ እየተደናበርን፣ ጋጠወጦችን በእንጭጩ መግታት ስለተሳነን፣ ወሮ በሎችና ነፍስ ገዳዮች የሚፈነጩበት አጋጣሚ እንዳይፈጠር መከላከል ስላቃተን ነው፣ የክፋት ምርኮኛ የወንጀለኞች ሰለባ የምንሆነው፡፡
እንዲያም ሆኖ፣… እንዲያ ብዙ ነገር አበላሽተንም፣ ተሳክሮብንም፣ ዛሬም ድረስ፣ አገራችን ገና አልፈረሰችም፡፡ ሕግና ሥርዓት ገና ጨርሶ በትርምስ አልተዋጠም፡፡
ነገር ግን፣ እስከ ዛሬ በመጣንበት የጥፋት ቁልቁለት ብዙ መቀጠል አይቻልም፡፡ በጊዜ ወደ ህሊና ተመልሰን የክፉዎችን የጥፋት ቅስቀሳ መመከት፣ የጥፋት ዘመቻቸውንም ማስቀረት ካልቻልን፣ ለይቶልን መከስከሳችን፣ በትርምስ መፈራረሳችን፣ አልያም ለምነን ተለማምጠን አምባገነንነትን መጋበዛችንና የገሃነም ስቃይ መፍጠራችን አይቀሬ ይሆናል፡፡   


Read 1472 times