Print this page
Saturday, 27 July 2019 14:08

በቀራንዮ አካባቢ የተሠራው ኩዊንስ ሱፐርማርኬት ተመርቆ ሥራ ጀመረ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

በተለምዶ አጠራር ጦር ኃይሎች እየተባለ ከሚጠራው ስፍራ ዝቅ ብሎ፣ በቀራንዮ ክፍለ ከተማ እጅግ ባማረ ግቢ ውስጥ የተሠራው ዘመናዊ ኩዊንስ ሱፐርማርኬት ቀራንዮ ቅርንጫፍ ባለፈው ማክሰኞ ተመርቆ አገልግሎት ጀመረ፡፡
ሱፐርማርኬቱን መርቀው የከፈቱት የዕለቱ የክብር እንግዳ የሼክ መሐመድ አሊ አል-አሙዲ ወንድም፣ ክቡር ሼክ አብደላ ሁሴን አሊ አል አመዲና የሚድሮክ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አረጋ ይርዳው ሲሆኑ ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር፤ ጥራት ያለው ሥራና አገልግሎት በተሰለፍንበት ሁሉ መተግበር እንደሚገባ ከተረዳን፣ ውጤታማ እንደምንሆን እርግጠኛ መሆን እንችላለን ብለዋል፡፡
የአግሮ ኢንዱስትሪ ውጤቶች፣ የእርሻ ምርቶች፣ የባህር ምግቦች፣ የንጽህና መጠበቂያና የታሸጉ ምርቶች፣ መጠጦችና ሌሎች የፋብሪካ ውጤቶችን በችርቻሮና በጅምላ በመሸጥና በማከፋፈል ሥራ የተሰማራው ድርጅት፤ በአሁኑ ጊዜ የካፒታል መጠኑ 23.7 ሚሊዮን ብር፣ የሠራተኞቹ ብዛት 142 የደረሰ ሲሆን፤ ዓመታዊ ሽያጩም ሥራ ሲጀምር 12.1 ሚሊዮን ብር የነበረው በአሁኑ ወቅት ወደ 157 ሚሊዮን ብር ከፍ ብሏል፡፡
ሱፐርማርኬቱ በዓለምአቀፍ ተቀባይነት ባላቸው ደንቦች መሠረት ባደረጉ ዲዛይን የተሠራ፣ አካሄዱም ለደንበኞች ቀላልና ምቹ የግብይት ሁኔታ ለማስፈን ትኩረት የሰጠ፣ ዘመናዊ፣ በመጠን ይዞታውም ትልቅ ሆኖ የተዘጋጀ ነው፡፡ ሱፐር ማርኬቱ ለ50 ተጨማሪ ዜጐች የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን ዓመታዊ ሽያጩም 75 ሚሊዮን ብር እንደሚሆን ተገምቷል ብለዋል - ዶ/ር አረጋ፡፡
የገበያ ማዕከሉን ልዩ የሚያደርጉ ነገሮች በ4,643 ካሬ ሜትር በሆነና ለ100 መኪኖች ማቆሚያ ስፍራ የተዘጋጀለት፣ ለደንበኞችና ለሠራተኞች በቂና ምቹ የሆኑ መፀዳጃ ቤቶች ያሉት መሆኑ፣ በአደጋ ጊዜ የውጭ በሮች የእሳት ማጥፊያ መሳሪያ ያሉት መሆኑ፣ ሱፐር ማርኬቱ በሚገኝበት በቀራንዮ ፕላዛ የነዳጅ ማደያ፣ የተሽከርካሪ እጥበትና መለስተኛ የጥገና አገልግሎት መስጫ፣ የእርሻ ምርቶች መሸጫ፣ ካፌና ሱቅ፣ ባንክ፣ ነዳጅ ማደያ ት/ቤትና ሁለገብ አዳራሽ በአንድ አካባቢ ተደራጅተው መገኘት፤ ደንበኞች በአንድ የንግድ ማዕከል በርካታ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል - ሲሉ ዶ/ር አረጋ ገልፀዋል::
በሌላም በኩል የሚድሮክ ግሩፕ አባል የሆነው ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ፣ ባለፈው ሳምንት ተመራቂ ተማሪዎችንና ቀጣሪዎችን አገናኝቷል፡፡ ‹‹Job Fair›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የግንኙነት መድረክ ዓላማ፣ ቀጣሪ መ/ቤቶችን ከወደፊት ተቀጣሪዎቻቸው ጋር ለማገናኘት፣ ኢንፎርሜሽን እንዲለዋወጡ ለማድረግ እንዲሁም ተመራቂዎችንና ዩኒቨርስቲውን ስለ ወደፊት ቀጣሪዎች እንዲያውቁ ያስችላል ተብሏል፡፡
አብዛኞቹ ቀጣሪ መ/ቤቶች የሚድሮክ ኢትዮጵያ ግሩፕ ሲሆኑ ሌሎችም የግል ድርጅቶች በቀጣሪነት ተገኝተዋል፡፡


Read 2187 times