Saturday, 27 July 2019 13:55

የፍኖተ ሰላም ዩፎዎች!!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ባህር ዳር እንደገባሁ ባጃጅ ተሳፈርኩ ባጃጅ ማለት ከብዙ ጨርቅና ትንሽ ብረት የተሰራች ለአቅመ ተሽከርካሪነት ያልደረሰች…”ደራሲ በዕውቀቱ ስዩም ከአፍሪካ መዲና (አንዳንዶች የአፍሪካ ዋና መሽኛ ይሏታል) አዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር ሲሄድ ከተማዋን እንደበርሃ አንበጣ በባጃጅ ተወርራ ሲመለከት የተናገረው ነበር፡፡
ወዳጄ በዕውቀቱ ስዩም በባህር ዳር የባጃጅ ቁጥር መብዛት ቢገረምም ለኔ ይበልጥ አስገራሚ የሆነብኝ ግን በፍኖተ ሠላም ጐዳናዎች ላይ እንደ ሮኬት ሲወነጨፉ የሚውሉት ባጃጆች ቁጥር ነው፡፡ ፍኖተ ሠላም በግምት ከ50ሺህ የማይበልጥ ነዋሪና አንድ ባለ አንድ መስመር የአስፋልት መንገድ ብቻ ያላት ቢሆንም የባጃጆች ቁጥር ግን ይገርማል፡፡
የባጃጅና የሶስት ቁጥር ዝምድና ይገርመኛል፡፡ ባጃጅ በሶስት ጐማዎች የምትሽከረከር እጅግ አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ስትሆን የተሰራችውም ከብረት፣ ከጨርቅና ከጐማ መሆኑ፣ እንዲሁም በውስጧ ሶስት ተሳፋሪዎችን ብቻ ማቀፍ መቻሏ የባጃጅንና የሶስት ቁጥርን ዝምድና ያጠናክርብኛል፡፡ በአንዳንድ የሀገራችን ከተሞች (አዲስ አበባን ጨምሮ) ከሶስት ተሳፋሪዎች በላይ በመጫን የባጃጅንና የሶስት ቁጥርን ዝምድና ለማፍረስ የተነሱ ቢመስልም በፍኖተ ሠላም ግን ይህ አይሰራም ከሶስት ሰው በላይ በባጃጅ ማሳፈር ነውር ነው፡፡
ከተማዋ አንድ አስፋልት የዋና ጐዳና መስመርና ጥቂት ከኮብልስቶን (የህወሓት ትምህርት ፖሊሲ ያፈራቸው ወጣቶች ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው “ገንዘብ የሚያፍሱበት የስራ መስክ” ይሉታል ኮብልስቶንን) የተሰሩ መንገዶች ቢኖራትም ባጃጆች ግን በዚህች ብቸኛ ጐዳና እና ገባር መንገዶች ላይ ከጋማ ከብቶች፣ መንገዳቸውን ከማይጠብቁ እግረኞች እና ሌሎች ተሽከርካሪዎች ጋር እየተጋፉም ቢሆን ያለመታከት ሲበሩ ይውላሉ፡፡ እዚህ ላይ አንድ የታዘብኩትን ሁነት ላክል፡፡
በአዲስ አበባ ብዛት ያላቸው ሰዎች መንገድ ዳር ቁመው ከታየ ታክሲ ወይም ሌላ የትራንስፖርት አገልግሎት እየጠበቁ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ በፍኖተ ሠላም ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሕዝብ ያለምንም ምክንያት የከተማዋን ብቸኛ የአስፋልት መንገድ በሆል ቆሞበት የነበሩ ቋሚዎች ወደ መሀል በመግባት ያለከልካይ መሀል አስፋልት ላይ ቆመው ወሬያቸውን በኩራት ሲደልቁ ለተመለከተ፤ መንገዱ የተሰራው ለመኪና ነው ወይስ ለእግረኞች የወሬ መኮመሪያ ብሎ እንዲጠይቅ ያስገድደዋል፡፡ ያም ሆኖ በመኪና አደጋ ህይወቱ የሚያልፍ ሰው አለመኖሩን ስሰማ ገርሞኛል፡፡ ይበልጥ የሚገርመኝ ደግሞ የፍኖተ ሰላም ጎረቤት የሆነችው የአዊ ብሔረሰብ ዞን መናገሻዋ ኮሶ በርና ሌሎች የአዊ ብሔረሰብ ዞን ትንንሽ ከተሞች ሳይቀሩ የመንገድ ላይ ህግ በማክበር ከኢትዮጵያ ቀዳሚ መሆናቸው ነው፡፡ ፍኖተ ሰላም ከጐረቤቷ መማር አልቻለችም ማለት ነው ወይም በዘመኑ ህወሓት ወለድ የፖለቲካ ቋንቋ “ፍኖተ ሰላም ከጐረቤት አገር የልምድ ልውውጥ መውሰድ ይቀራታል” ማለት እንችላለን!!
ፍኖተ ሰላም ከመሄድ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በባህር ዳር የባጃጅ ትራንስፖርት የመጠቀም ዕድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ የተሳፈርኩባት ባጃጅ ሌሎች ሁለት ሰዎች እንዲሳፈሩላት በሯን ከፍታ ተሳፋሪ ብትፈልግም ድርሽ የሚል ጠፍቶ ለረጅም ደቂቃዎች መጠበቅ ግድ ብሏት ነበር፡፡
ጥበቃው ሲሰለቸኝ በኔ ጉትጎታና ተጨማሪ ክፍያ ለመክፈል ፍላጐት በመግለጼ እኔኑ ይዛ በረረች እንጂ ሌሎች ሁለት ሰዎች በመጠበቅ ውላ ባለማደሯ ማረጋገጫ መስጠት አይቻልም፡፡ አንዳንድ የባህር ዳር ቧልት አዋቂዎች “አንድ ባጃጅ አንድ ተሳፋሪ ካገኘ ሌሎች ሁለት ባጃጆች ከፊትና ከኋላ ሆነው ያን እድለኛ ባልንጀራቸውን እንደ አምባሳደር አጅበው ይሄዳሉ” ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡
በፍኖተ ሰላም ግን እንደዚህ አይነት የተሳፋሪ ድርቅ የለም፡፡ በአጭር አገላለጽ የፍኖተ ሰላም ባጃጆች ለደቂቃም ጾም የለባቸውም፡፡ ተሳፋሪ ለመሳፈር ባጃጆችም ደንበኞቻቸውን በፍጥነት ለማገልገል ቃለ መሃላ የፈጸሙ ይመስላሉ፡፡
(ደራሲና ጋዜጠኛ ይርጋ አበበ በላቸው “ኢካቦድ”
በሚል ርዕስ ካወጣው መጽሐፍ የተቀነጨበ፤)

Read 2460 times