Saturday, 03 August 2019 13:35

ኢንስትራክተር አብርሃምና ዋልያዎቹ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)


                     • ከዓለም 211 አገራት 150ኛ፤ ከአፍሪካ 54 አገራት ደግሞ 44ኛ
                    • በ6ኛው ቻን፤ በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫና በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች
                       


           የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባለፉት 5 የውድድር ዘመናት በደረጃው በሚያሳስብ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በፊፋ የዓለም እግር ኳስ ደረጃ በ1049 ነጥብ ከዓለም 211 አገራት 150ኛ፤ ከአፍሪካ 54 አገራት ደግሞ 44ኛ ደረጃ ላይ ተመዝግባለች፡፡ ዋልያዎቹ በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ ባለፉት 3 እና 4 የውድድር ዘመናት የነበራቸው ተሳትፎ ደካማ ነበር፡፡ በማጣርያ ጨዋታዎች ላይ ከሜዳቸው ውጭ ተደጋጋሚ ሽንፈት እየገጠማቸው ሲሆን በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎችም አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ አቅቷቸዋል::  ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አቋም መውረድ ባለፉት 6 ዓመታት 4 ዋና አሰልጣኞችን መቀያየሩ፤ ለተለያዩ ውድድሮች በሚያደርጋቸው ዝግጅቶች በቂ የአቋም መፈተሻ ግጥሚያዎችን አለማግኘቱና ልዩ  ትኩረት አለመስጠቱ፤ በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በተለያዩ ስታድዬሞች ማከናወኑና ሌሎች አስተዳደራዊ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ:: ዋልያዎቹ በቀጣዩ የውድድር ዘመንም ከላይ በተጠቀሱት ችሮች ይፈተናሉ፡፡ በተለያዩ ውድድሮች  በሚኖራቸው ተሳትፎ ትልቁን ጥረት ከብሄራዊ ቡድኑ አባላት መጠበቅ ግድ ይሆናል፡፡ ቢያንስ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በሶስት የተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች  ከ9 የተለያዩ የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ጋር በሚያደርጓቸው የማጣርያ ጨዋታዎች ያሉትን እድሎች በመጠቀም ደረጃቸውን ያሻሽሉ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2020 እኤአ ለሚካሄደው እና ከኢትዮጵያ መስተንግዶ በተወሰደው 6ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን ፤ በ2021 እኤአ ላይ አይቬሪኮስት ታስተናግደዋለች ተብሎ ከዚያም አዘጋጅነቱ ለካሜሮን ይሰጣል በተባለው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እንዲሁም በ2022 እኤአ በመካከለኛው ምስራቅ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ኳታር በምታስተናግደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የቅድመ መጣርያ እና የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ይኖሩታል፡፡
ባለፈው ሰሞን ከጅቡቲ ጋር ለ2020 ቻን ለማለፍ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታቸውን አድርገው ረጅሙን ጉዞ የጀመሩት ዋልያዎቹ ለመልሱ ጨዋታ እየተዘጋጁ፤ በ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከአይቮሪኮስት ማዳጋስካርና ኒጀር ጋር መደልደላቸውን አውቀዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያውም የምድቡን የመጀመርያ ጨዋታ ከማዳጋስካር ጋር ከሜዳው ውጭ በጥቅምት ወር ያደርጋሉ፡፡  ከዚያ በፊት ደግሞ ለ2022 ኳታር የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያውን ቅድመ ማጣሪያ ግጥሚያቸውን ከሌሴቶ ብሔራዊ ቡድን ጋር ከሜዳው ውጪ ጳጉሜ  ላይ ይጫወታሉ፡፡ ይህ የስፖርት አድማስ አጭር ሀተታ ስለ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ፤ በቻን፤ በአፍሪካ ዋንጫ እና በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች ያሉትን መርሃ ግብሮችና ተጋጣሚዎቹን  ብሄራዊ ቡድኖች በአጭሩ የሚያስተዋውቅ ነው፡፡
ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ
ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት መስራት ከጀመረ 1 ዓመት በላይ ወይም  380 ቀናት ተቆጥረዋል:: የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን  ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ሲሾመው የሁለት አመት ኮንትራት በማስፈረም ሲሆን  ወርሀዊ ደሞዙ ከጥቅማ ጥቅም ውጪ 125 ሺህ ብር መሆኑ ተወስቷል:: ዋና አሰልጣኙ  በሰውነት ቢሻው ሰብሳቢነት ከሚመራው ብሄራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው ጋር የሚሰራ ሲሆን፤ የቀድሞ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች የነበሩት ፋሲል ተካልኝ እና ሙሉጌታ ምህረት  በምክትል አሰልጣኝነት አብረው እያገለገሉ ናቸው፡፡
የ49 ዓመቱ ኢንስትራክተር  አብርሃም በአገር ውስጥ ከሚገኙ አሰልጣኞች ባላቸው ዓለም አቀፍ ልምድ እና የሙያ ብቃት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ከወረደበት አቋም መልሶ እንዲያገግም ግንባር ቀደም ምርጫ ይሆናል፡፡ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ በነበራቸው ተመክሮ የቡና፣ የኒያላ፣ የወንጂ ስኳር እና የእህል ንግድ ክለቦችን አሰልጥኗል፡፡  ከዚያም በየመን እግር ኳስ  የሚጠቀስ ታሪክ የነበረው ሲሆን በቴክኒክ ዲያሬክተርነት እንዲሁም በዋና አሰልጣኝነት የየመን ብሄራዊ ቡድን ለሶስት አመታት እንዳገለገለ ይታወቃል፡፡ በተለይ በጦርነት ታምሳ ከዓለም የስፖርት እንቅስቃሴ ውጭ የነበረችውን የመንን ለእስያ ዋንጫ እንድታልፍ ያደረገው አስተዋፅኦ የሚደነቅ ሲሆን ብሄራዊ ቡድኑ ባጋጠመው የገንዘብ እጥረት በሻምፒዮናው ሳይሳተፍ ከቀረ በኋላ ከሃላፊነቱ ራሱን ማግለሉ ይታወሳል፡፡ ከዋናው የየመን ብሄራዊ ቡድን በፊትም  በእስያ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ የመንን ቡድን አሰልጥኖም ነበር፡፡
ኢንስትራክተር አብርሃም በአፍሪካ እግር ኳስ በአሰልጣኝነት፤ በአሰልጣኞች አሰልጣኝነት ከፍተኛ ደረጃ እንደደረሰና በአገር ውስጥ እና በአህጉራዊ መድረኮች በመስራት ልዩ ልምድ ማካበቱም ይታወቃል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከወር በፊት ግብፅ ባስተናገደችው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በካፍ የቴክኒክ ጥናት ቡድን ሲያካትተው፤  የአሠልጣኞች አሠልጣኝ ተብለው ከሚጠቀሱ አፍሪካዊ ኢንስትራክተሮች አንዱ ስለሆነ ነበር:: ኢንስትራክተር አብርሃም በአፍሪካ ዋንጫው የቡድኖቹን ቴክኒካዊ ብቃት ከመገምገም ባሻገር የየጨዋታውን ኮከብ ተጨዋቾች ምርጫ በማከናወን ልዩ ሚናውንም ተወጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የቻን ማጣርያ ጅቡቲን ከሜዳ ውጭ 1ለ0 ባሸነፈው ቡድን የሰራበትን ሃላፊነት ጨምሮ በአሰልጣኝነት የስራ ዘመኑ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ያደረጋቸው ጨዋታዎች ብዛት 11 የደረሰ ሲሆን አራቱን አሸንፎ በአራቱ አቻ በመውጣት በ3 ሽንፈት ገጥሞታል፡፡
ኢንስትራክተር አብርሃም ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ለመስራት ባላቸው ኮንትራት ከ1 ዓመት ያነሰ ጊዜ ይቀራቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋልያዎቹና ዋና አሰልጣኙ በሚቀጥሉት ዓመታት የሚኖራቸውን ጉዞ ከግምት ውስጥ በማስገባት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡ ይህም የኮንትራት ማራዘሚያ ማድረግን፤ የወዳጅነት ጨዋታዎች በብዛት የሚገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸትን፤ በሜዳ የሚደረጉ ጨዋታዎችን በተለያያዩ ስታድዬሞች የሚያስተናግድበትን ሁኔታ በመቀየር ቋሚ ስታድዬም መምረጥን… ሌሎችንም ድጋፎች ማጠናከር ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢንስትራክተር አብርሃምን የ380 ቀናት የስራ ቆይታ አስቀድሞ ከነበሩት አሰልጣኞች ጋር ማነፃፀር ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የቅርብ ጊዜ ታሪክ  በዋና አሰልጣኝነት ለረጅም ግዜ በመቆየት ግንባር ቀደም የሆኑት ለሁለት ጊዜያት በሃላፊነቱ የነበሩት ሰውነት ቢሻው ሲሆኑ፤ በመጀመርያ 609 ቀናት ከዚያም በሁለተኛ ጊዜ ቅጥራቸው 830 ቀናት በድምሩ 1439 ቀናትን በማስመዝገብ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ጀርመናዊው ፒተር ሽናይተገር በ1095 ቀናት አገልግሎታቸው ሲሆን፤ ዮሐንስ ሳህሌ ለ398፤ ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ ለ364 ቀናት፤ አሸናፊ በቀለ ለ309 ቀናት፤ ስኮትላንዳዊው ኢፌም ኦኑራ ለ293 ቀናት፤ፈረንሳዊው ዲያጎ ጋርዜቶ ለ190 ቀናት፤ ቤልጅማዊው ቶም ሴንት ፌንት ለ161 ቀናት እንዲሁም ገብረመድህን ሃይሌ ለ159 ቀናት በሃላፊነቱ መቆየት ችለዋል፡፡
በ6ኛው የቻን ማጣርያ
ለ2020 የቻን ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአንደኛ ዙር ማጣርያ የመጀመርያ ግጥሚያውን  ከጅቡቲ ጋር በማድረግ ጀምሯል:: ዋልያዎቹ ከሜዳቸው ውጭ ከጅቡቲ በሃሰን ጉሌድ ኦፕቲዶን ስታድዬም በተገናኙበት ግጥሚያ፤ በአምበሉ አስቻለው ታመነ ብቸኛ ጎል አሸንፈዋል:: የመልስ ጨዋታውን በድሬዳዋ ስታድዬም የሚያደርጉ ይሆናል፡፡ በደርሶ መልስ ጨዋታው ጥሎ የሚያልፈው ብሄራዊ ቡድን በሁለተኛው ዙር ማጣርያ ለደርሶ መልስ ግጥሚያዎች የሚገናኘው ከሩዋንዳ ነው፡፡
የጅቡቲ ብሄራዊ ቡድን በፊፋ የዓለም የእግር ኳስ ደረጃው 195ኛ ደረጃ ላይ ሲሆን፤  ዋና አሰልጣኙ ከፈረንሳይ ቦርዶክስ የተገኙትና ለመጀመርያ ጊዜ ብሄራዊ ቡድንን ለማሰልጠን በጁቢቲ የጀመሩት  ጁሌያን ሜቴ ናቸው፡፡ ከሀገር ውስጥ ሊግ በሚመረጡ ተጫዋች ብቻ በሚዋቀሩ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የሚደረገው የቻን ማጣሪያ በሞቃታዋ ጅቡቲ የመጀመሪያ ጨዋታውን  ባደረገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የነበሩ 20 ተጨዋቾች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ግብ ጠባቂዎች
ተክለማርያም ሻንቆ (ሀዋሳ ከተማ)፣ ምንተስኖት አሎ (ባህር ዳር ከተማ)
ተከላካዮች
 አስቻለው ታመነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ደስታ ደሙ (ወልዋሎ)፣ ያሬድ ባዬ (ፋሲል ከተማ)፣ ወንድሜነህ ደረጀ (ባህር ዳር ከተማ)፣ አህመድ ረሺድ (ኢትዮጵያ ቡና) ጌቱ ኃይለማርያም (ሰበታ ከተማ)፣ አምሳሉ ጥላሁን (ፋሲል ከተማ)፣ ረመዳን የሱፍ (ስሑል ሽረ)
አማካዮች
 አማኑኤል ዮሐንስ (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ሙሉዓለም መስፍን (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ሐይደር ሸረፋ (መቐለ)፣ አፈወርቅ ኃይሉ (ወልዋሎ)፣ ሱራፌል ዳኛቸው (ፋሲል ከነማ)፣ ታፈሰ ሰለሞን (ሀዋሳ ከተማ)
አጥቂዎች
 አቤል ያለው (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል (መቐለ)፣ ፍቃዱ ዓለሙ (መከላከያ)፣ አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)
በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ
በ2021 እኤአ ላይ ካሜሮን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 11 ከአይቬሪኮስት፤ ከኒጀርና ከማዳጋስካር ጋር መደልደሉ ይታወቃል፡፡ ወደ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ  የሚካሄደው የምድብ ማጣርያ የሚጀመረው ከ3 ወራት በኋላ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጀመርያ ጨዋታው ከሜዳ ውጭ ከማዳጋስካር ጋር ይገናኛል፡፡ በሁለተኛው ጨዋታ በሜዳው ከአይቬሪኮስት ጋር፤ በ3ኛው ጨዋታ ከሜዳው ውጭ ከኒጀር ጋር፤ በ4ኛው ጨዋታ በሜዳው ከኒጀር ጋር፤ በ5ኛው ጨዋታ በሜዳው ከማዳጋስካር እንዲሁም በስድስተኛው ጨዋታ ከሜዳ ውጭ ከአይቬሪኮስት ጋር የሚገናኝ ይሆናል፡፡
በትራንስፈር ማርኬት 23 ተጨዋቾች የሚገኙበት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  ስብስብ በአማካይ እድሜው 24.5 ዓመት ሆኖ ሲመዘገብ በዝውውር ገበያው የተተተመነው በ1.13 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡ በብሄራዊ ቡድኑ ከአገር ውጭ ይጫወታሉ ተብለው የተጠቀሱት 4 ተጨዋቾች ሲሆኑ የቡድኑ የዋጋ ተመንም በእነዚህ ተጨዋቾች የወጣ ነው፡፡ በግብፁ ክለብ የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ  በአሁኑ ወቅት የብሄራዊ ቡድኑ ውድ ተጨዋች የሆነው በ400ሺ ዩሮ የዝውውር ገበያ ዋጋው ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀስው ኡመድ ኡክሪ በ300ሺ ዩሮ ሲሆን፤ በስፔን የሚጫወተው ቢኒያም በ225ሺ ዩሮ እንዲሁም ጋቶች ፓኖም በ200 ሺሮ የዝውውር ገበያ ዋጋቸው ተከታታይ ደረጃ ይወስዳሉ፡፡
የአይቬሪኮስት ብሄራዊ ቡድን  በፊፋ የዓለም የእግር ኳስ ደረጃ ከዓለም 57ኛ ከአፍሪካ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ በአይቬሪኮስት ቡድን ያሉ 23 ተጨዋቾች  በዝውውር ገበያው ዋጋቸው ሲተመን በ284.7 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡ ከ23 ተጨዋቾች መካከል በአውሮፓ ደረጃ የሚጫወቱት 21 ፕሮፌሽናሎች ሲሆኑ በአማካይ እድሜያቸው 27.1  ዓመት ነው፡፡ ከአይቬሪኮስት ተጨዋቾች በዝውውር ገበያው ውድ ዋጋ ያለው 45 ሚሊዮን ዩሮ የተተመነው ዊልፍሬድ ዘሃ ነው፡፡ የኒጀር ብሄራዊ ቡድን በፊፋ የዓለም የእግር ኳስ ደረጃው በዝውውር ገበያው የዋጋ ተመኑ 14.03 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን፤ ግብፅ አስተናግዳ በነበረችው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳተፍ የበቃው የማዳጋስካር ብሄራዊ ቡድን ደግሞ በዝውውር ገበያው የተተተመነው በ 2.63 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡
በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የ2021 አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በምድብ 11 ከአይቮሪኮስት፣ ኒጀር፤ ማዳጋስካርና ኢትዮጵያ የሚገናኙባቸው ጨዋታዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ከጥቅምት 29- ህዳር 1 ቀን 2012
አይቮሪኮስት ከ ኒጀር
ማዳጋስካር ከ ኢትዮጵያ
ኅዳር 8-10 ቀን 2012
ኢትዮጵያ ከ አይቮሪኮስት
ኒጀር ከ ማዳጋስካር
ነሐሴ 25-26 ቀን 2012
አይቮሪኮስት ከ ማዳጋስካር
ኒጀር ከ ኢትዮጵያ
ጳጉሜ 2-4 ቀን 2012
ማዳጋስካር ከ አይቮሪኮስት
ኢትዮጵያ ከ ኒጀር
መስከረም 24-26 ቀን 2013
ኒጀር ከ አይቮሪኮስት
ኢትዮጵያ ከ ማዳጋስካር
ጥቅምት 30 ቀን 2013
አይቮሪኮስት ከ ኢትዮጵያ
ማዳጋስካር ከ ኒጀር
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ
በ2022 እኤአ ላይ ኳታር በምታስተናግደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ በአፍሪካ ዞን በሚደረገው ማጣርያ በመጀመርያው ዙር የሚሳተፉት 28 ብሄራዊ ቡድኖች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጀመርያ ዙር የደርሶ መልስ ማጣርያ የተመደበው ከደቡብ አፍሪካዋ ሌሶቶ ጋር ነው፡፡ ከሁለቱ ቡድኖች  ጥሎ ማለፍ የሚችለው በከፍተኛ ደረጃ ላይ ወደ የሚገኙትና በምድብ ማጣርያ ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከሚሰለፉት 26 አፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ተርታ ይሰለፋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ለ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በአንድ ምድብ እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን ባህር ዳር ላይ በተደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ በጋቶች ፓኖም እና ሳላዲን ሰዒድ ጎሎች 2-1 ስታሸንፍ በተመሳሳይ ሌሶቶ ላይም በጌታነህ ከበደ ሁለት ጎሎች ኢትዮጵያ 2-1 ማሸነፏ የሚታወስ ነው። አዞዎቹ በሚል ቅፅ ስማቸው የሚታወቀው የሌሶቶ ብሄራዊ ቡድን በፊፋ የዓለም የእግር ኳስ 144ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ 23 ተጨዋቾች የሚገኙበት ስብስቡ በአማካይ እድሜው 26.4 ዓመት ሆኖ ሲመዘገብ በዝውውር ገበያው የተተመነበት ዋጋ በ 675 ሺ ዩሮ ነው፡፡

Read 9986 times