Saturday, 03 August 2019 13:43

ሶቅራጥስ - የዲሞክራሲ ሰማዕት

Written by  አብዱራህማን አ.
Rate this item
(4 votes)

 ብዙ ጊዜ የምጽፋቸው መጣጥፎች ፖለቲካ ቀመስ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ህይወት ግን ፖለቲካ ብቻ አይደለም፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ ደጋግሞ መጻፍ ራሱ ይሰለቻል፡፡ መሰልቸቱ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ጉዳዮቻችን ጭምር ሊጻፍባቸው እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ ከዚህ ሌላ በባህሪዬ በአንድ ጉዳይ ላይ መቸከል አልወድም፡፡ እናም በዛሬው መጣጥፌ ለየት ባለ ጉዳይ ላይ ለማኮር አሰብኩ:: እንዲያው ለየት ያለ ጉዳይ አልኩ እንጂ ከዚያው ከፖለቲካ አልወጣሁም፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት ስለነበረ አንድ ፈላስፋ ታሪክ ልነግራችሁ ወደድሁ - ስለ ግሪካዊው ፈላስፋ ስለ ሶቅራጥስ፡፡ “በጥንታዊ ቅርጻ ቅርፆች ላይ እንደሚታየው ምስል ከሆነ፤ ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ ሶቅራጥስ መልኩ አስቀያሚ ከመሆኑም በላይ ፈላስፋ ነው ለማለት ያዳግታል” ይላል፤ደራሲ ዊል ዱራንት የተባለ ጸሐፊ፤ “የፍልስፍና ታሪክ” በሚል መጽሐፉ:: በመቀጠልም “ሶቅራጥስ ፀጉሩ የተመለጠ፣ ሰፊና ክብ ፊት ያለው፣ አፍንጫው ደፍጣጣ የሆነ፣ ጥልቅና ያፈጠጡ ዓይኖች ያሉት ሰው ነው፡፡ ይህ ገጽታው ከሌሎች ቀደምት ፈላስፋዎች የተለየ በመሆኑ፣ ሸቃይ እንጂ ፈላስፋ ነው ለማለት ያዳግታል” ይላል፤ ዱራንት፡፡
ይሁን እንጂ ሶቅራጥስ በዚያ ወቅት ፕላቶንና አልሲቢያድስን የመሳሰሉ አንቱ የተሰኙ ደቀ-መዛሙርትን ያፈራ ታላቅ የአቴና ፈላስፋ ነበር:: ሶቅራጥስ የፍልስፍናው ተቋዳሽ የሆኑ አያሌ ወጣት ተከታዮችም የነበሩት ሲሆን፤ ለአቴናውያን የዴሞክራሲ ስርዓት መስፈንና ለፍልስፍና የእውቀት ዘርፍ ራሱን አሳልፎ የሰጠ ሰው ነው ይላሉ፤ በሱ ዙሪያ ምርምር ያደረጉ ሊቃውንት፡፡
ስለ ሶቅራጥስ ልደትና ሕይወት ብዙ ዝርዝር ታሪክ አይገኝም። የሶቅራጥስን ያልታወቀ ታሪክ የሚነግሩን ሦስት የታሪክ ምንጮች ናቸው፡፡ እነሱም የፕላቶና የዜኖን ውይይቶችና በዘመኑ የነበረው የአርስቶፋን ቴአትሮች ናቸው፡፡ በነዚህ ምንጮች ላይ እንደተጠቀሰው ከሆነ፤ ሶቅራጥስ የተወለደው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ469 ዓ.ዓ ሲሆን አባቱ ሶፍሮኒከስ፣ በአቴንስ የድንጋይ ንጣፍና የቅርፃ ቅርፅ ባለሙያ ነበር፡፡ እናቱ ፌናሬት ትባላለች፡፡ አዋላጅ ነርስ ነበረች።
የሶቅራጥስ አኗኗር ምን ይመስል እንደነበር በግልፅ አይታወቅም፡፡ ሶቅራጥስ ሲሰራ አይታይም:: እናም አንዳንዶች ስራ አልነበረውም ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ የራሱ ትምህርት ቤት ነበረው፣ ከሚያስተምራቸው ልጆች ገንዘብ ይከፈለው ነበር ይላሉ፡፡ ሌሎች ምንጮች ደግሞ ሶቅራጥስ የአባቱን ሥራ ይሰራ እንደነበር ዘግበዋል፡፡ በአንዳንድ ሰነዶች ላይ እንደተመለከተው፤ሶቅራጥስ ስራ ስላልነበረው ምግብ የሚመገበው ደቀመዛሙርቱ ገበታቸውን እንዲባርክላቸው ሲጋብዙት ነው፡፡ ወጣቶቹ ብዙ ጊዜ አብሯቸው እንዲበላ ይጋብዙታል፡፡ ይህንን የሚያደርጉት የአመጋገብ ስነ ምግባርን ከሱ ለመማር እንደሆነ ይታሰባል፡፡
ሶቅራጥስ ዛንቲፔ የተባለች ሴት አግብቶ ሦስት ወንዶች ልጆች እንደ ወለደ ይነገራል፡፡ ሶቅራጥስ ከሚስቱ ጋር ስምምነት አልነበረውም፡፡ “እንደ ፈላስፋ ቤተሰቡን አይደግፍም” በማለት ቅሬታ ታቀርብ ነበር - ሚስቱ፡፡ “ገንዘብ የሚያስገኝ ስራ አይሰራም፣ ከንቱ ዝናና ውዳሴ ፈላጊ ስለሆነ ወጣቶችን እየሰበሰበ ሲለፈልፍ ይውላል” በማለት ታወግዘው ነበር፡፡ የሶቅራጥስ ሚስት በሶቅራጥስ ፍልስፍና ደስተኛ አለመሆኗን ጽፏል፤ ዜኖን፡፡ ዜኖን የሶቅራጥስን ሚስት “የማትወደድ” ይላታል፡፡ ሶቅራጥስ ከልጆቹ አስተዳደግ ጋር ብዙም ግንኙነት አልነበረውም፡፡ ከራሱ ልጆች ይልቅ ለአቴና ወጣቶች የአእምሮ እድገት የበለጠ ጥረት ማድረጉን ራሱ ሶቅራጥስ ተናግሯል፡፡
ሶቅራጥስ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀውና የሚታወሰው “እኔ የማውቀው አለማወቄን ማወቄን ነው” በሚለው ዘመን ተሻጋሪ አባባሉ ነው፡፡ በርግጥ ከሶቅራጥስ በፊት እንደ ቴሊዝና ሄራክሊተስን (Thales and Heraclitus) የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች፣ ፓርሜንደስንና ዜኖን  (Parmenides and Zeno) የመሳሰሉ ብልሆች፣ ፓይታጎራስንና ኢምፔዶክልስን (Pythagoras and Empedocles) የመሳሰሉ መጪውን ጊዜ የሚተነብዩ አዋቂዎች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ በተፈጥሮ ላይ ያተኮሩ ሊቃውንት ናቸው፡፡ ሶቅራጥስን ከነዚህ የሚለየው ስለ ሰው ልጅ አስተሳሰብ ለማወቅ ጥረት ማድረጉ ነው፡፡
የሶቅራጥስ የፍልስፍና ጥያቄዎች፤ “የሰው ልጅ ክብር፣ ሥነ ምግባር፣ ግብረ-ገብነት፣ የሀገር ፍቅር፣… ስንል ምን ማለታችን ነው?” የሚሉ ናቸው፡፡ በነዚህ ጥያቄዎች ላይ ተመስርቶ ነው አንቱ ያሰኘውን ፍልስፍና ያካሄደው፡፡ ከነዚህ ጥያቄዎች በተጨማሪ ሌሎች ጥያቄዎችንም አንስቷል፤ ሶቅራጥስ፡፡ ከመለሳቸው ይልቅ በእንጥልጥል የተዋቸው በርካታ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ የሚገርመው ነገር ሶቅራጥስ አንድም መጽሐፍ ያልጻፈ ፈላስፋ ነው፡፡ የእርሱ የፍልስፍና ሃሳቦች በደቀ መዝሙሮቹ (በእነ ፕላቶ)ሥራዎች ውስጥ ነው የሚገኙት፡፡
ከሁሉ ይበልጥ “ስነ ምግባር ምንድነው?” እንዲሁም “ጥሩ የመንግስት አስተዳደር የትኛው ነው?” በማለት ያነሳቸው የፍልስፍና ጥያቄዎች፣ በወቅቱ ለነበሩ ወጣት አቴናውያን ፈታኝ ነበሩ:: በሌላ በኩል፤ “የሰው ልጅ ለህግ ተገዥ እስከ ሆነ ድረስ ያሻውን እንዳይሰራ የሚያግደው የለም” ይል ነበር፤ ሶቅራጥስ፡፡ በወቅቱ የነበሩ ሱፊስቶች (አንደበተኞች) ይህንን የሶቅራጥስን ሃሳብ ይቃወሙ ነበር፡፡
ሶቅራጥስን ሞት ያስፈረደበት ክስ ምክንያቶች በርካታ ናቸው፡፡ ሶቅራጥስ በህይወት የነበረበት ዘመን አቴናውያን በስፓርታና በአጋሮቿ ጦርነት ተሸንፈው ከነበሩበት ከፍታ ወርደው በማሽቆልቆል ላይ እስከነበሩበት ጊዜ ድረስ ነው፡፡ አቴንስ ከደረሰባት ሽንፈት ለመረጋጋትና ለማገገም በፈለገችበት ወቅት፣ የአቴና ህዝብ ዲሞክራሲን እንደ ውጤታማ የመንግስት አስተዳደር ያለማየት ጥርጣሬ ውስጥ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ሶቅራጥስ ዴሞክራሲን በመንቀፍ ይተች ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የፖለቲካ ሰበብ ተፈልጎ ተከሰሰ፤ የሚሉ አሉ፡፡ ሌላው ምክንያት ሶቅራጥስ ለአቴና ከተማ ታማኝ አለመሆኑን በመግለጽ፣ በወቅቱ ከነበረው የአቴናውያን ፖለቲካና ከህብረተሰቡ አካሄድ ጋር መጋጨቱ ለክስ እንዳበቃው ይነገራል፡፡ በፍልስፍና ውይይት፣ በሚያደርጋቸው ክርክሮች ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስፓርታን ያደንቃል፣ ለአቴንስ ያለውን ጥላቻ ይናገራል፡፡ እናም የሶቅራጥስ አንዱ ጥፋት ተደርጎ የተወሰደው በከተማዋ ላይ የሚሰነዝረው ማህበራዊና ሥነ ምግባራዊ ነቀፋ ነበር ይባላል፡፡
ፕላቶ ሶቅራጥስን “የሀገሪቱ አናዳጅና አስቸጋሪ ሰው” ይለው ነበር፡፡ ፍትህንና መልካምነትን ተግባራዊ በማድረግ አንዳንድ ሰዎችን ያበሳጫቸው ነበር፡፡ በዚህ መልኩ የአቴናውያንን የፍትህ ስሜት ለማሻሻል ያደረገው ሙከራ በወቅቱ ፖለቲከኞች በጥሩ መንፈስ ባለመታየቱ፣ ምናልባት ለመገደሉ ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሎ ይታሰባል። ከተለያዩ ሰነዶች ላይ ካገኘኋቸው መረጃዎች እንደተገነዘብኩት፤ በጥቅሉ በሶቅራጥስ ላይ የቀረቡት ክሶች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛ፤ “በዴሞክራሲ ስም የአቴንስ ወጣቶችን አእምሮ በማበላሸት ምግባረ ብልሹ አድርገሃል” ሁለተኛ፤ “ከሃይማኖት አፈንግጠህ ኃጢያተኛ ሆነሃል ማለትም በግሪክ አማልክት አላምንም ብለሃል” የሚሉ ናቸው፡፡ ክሱ ይህ ከሆነ የፍርድ ሂደቱንና የሞት ቅጣቱን አፈጻጸም የሶቅራጥስ ደቀመዝሙር የነበረው ፕሌቶ ጽፎታል፡፡ ፕሌቶ እንዲህ ይተርከዋል…
ያኔ በአቴንስ ሰዎች ተከሰው የሚቀርቡት ህዝብ ፊት ነበር፡፡ የአቴንስ ህዝብ ተሰበሰበ፡፡ ሶቅራጥስም ህዝቡ ፊት ቀረበ፡፡ የህዝቡ ውሳኔ አጭርና ግልጽ ነበር፡፡ ከህዝቡ መሀል አኒተስና ሜሉተስ የተባሉ ሰዎች ተነሱና “ቅጣቱ ሞት ይሁን” የሚል ሃሳብ አቀረቡ፡፡ ይህ ሃሳብ በብዙዎቹ ተሰብሳቢዎች ተደገፈ፡፡ የመንጋ ፍርድ ተሰጠ!
ህዝብ እንደዚያ ዓይነት ፍርድ ቢሰጥም፤ ጥፋተኛው ሰው ህዝብን ይቅርታ ከጠየቀ ፍርዱ ይነሳለታል፡፡ ሶቅራጥስም ይቅርታ የመጠየቅ መብት ነበረው፡፡ ቢጠይቅ ኖሮ የሞት ቅጣቱ ይነሳለት ነበር፡፡ ሶቅራጥስ ግን ይህንን ማድረግ አልፈለገም:: ይልቁንም ከተሰበሰበው ህዝብ የተሰጠውን የደቦ ውሳኔ በፀጋ ተቀበለ፡፡ ይቅርታ አለመጠየቁ ደግሞ የተሰበሰበውን ህዝብ ይባስ አናደደው፡፡ ንቀት መሰለው፡፡ በደቦ ዴሞክራሲ፣ በህዝብ የተሰጠን ውሳኔ መቀበል ለሌሎች አርአያ መሆን ነው ብሎ ያሰበው ሶቅራጥስ፤ ከይቅርታው ሌላ ይግባኝ መጠየቅ ይችል ነበር፡፡ ይግባኝ መጠየቅም አልፈለገም…
በህዝብ የተሰጠው የሞት ፍርድ ፀና፡፡ ወዲያውኑ ወደ እስር ቤት ተላከ፡፡ በዚህ ጊዜ ጓደኞቹና ተማሪዎቹ ከታሰረበት ስፍራ ድረስ በመሄድ፣ ለእስር ቤቱ ኃላፊዎች ጉቦ በመስጠት እንዲያመልጥ መንገዱን አመቻቹለት፡፡ በወቅቱ የ70  ዓመት የእድሜ ባለፀጋ የነበረው ሶቅራጥስ፣ ይህንንም አላደርገውም አለ፡፡
ለማምለጥ ያልፈለገበትን ምክንያት በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡ አንደኛ፤ “እንደዚህ ዓይነት ሽሽት ከአንድ እውነተኛ ፈላስፋ የማይጠበቅ፣ ሞትን የመፍራት እርምጃ ነው” ብሎ ያምን ስለነበር አላደረገውም፡፡ ሁለተኛ፤ “ከእስር ወጥቶ በከተማው ህጎች ስር ሆኖ ለመኖር ከተስማማ፣ በዜጎች በወንጀል መከሰሱ የማይቀር መሆኑን መገንዘቡና ያን ካደረገ ደግሞ ከሀገር ጋር ያደረገውን “ማህበራዊ ውል” የሚያፈርስ መሆኑና ይሄ ደግሞ ሕገ-መንግስታዊ ያልሆነ ተግባር በመሆኑ ነው” የሚሉ ወገኖች አሉ:: ሦስተኛ፤ “በጓደኞቹ ተነሳሽነት ካመለጠ ጓደኞቹ በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ ብሎ በማሰቡ ነው” የሚሉም አሉ፡፡
በፕሌቶ መነጽር፣ በእስር ቤቱ የነበረውን ድባብ በዓይነ ኅሊናችን እንይ፡፡ የፕሌቶ ትረካ ይቀጥላል…
“ደስ ይበላችሁ!” ሲል ጮኸ ሶቅራጥስ፤ በኀዘን ለተሸማቀቁ ወዳጆቹ፡፡ “ደስ ይበላችሁ! የምትቀብሩት ሥጋውን ብቻ ነው በሉ” አላቸው፡፡
የእስር ቤቱ ዋርድያ ሶቅራጥስ ዘንድ ቀረበና “ሶቅራጥስ ሆይ! ጨዋና የተከበርክ ለሆንከው ለአንተ እንደ ሌሎች የሞት ፍርደኞች የተበጠበጠ መርዝ መስጠት ቀርቶ ቁጣና ስድብ ወይም ክፉ ፊት ለማሳየት ድፍረት የለኝም፡፡ ይሁን እንጂ፣ የእኔ የሥራ ድርሻ ምን እንደሆነ ታውቀዋለህና ሁሉንም ነገር ከዚህ አኳያ ተመልከተው” አለውና በእንባ የተሞሉትን ዓይኖቹን እየጠራረገ ፊቱን አዞረ፡፡
ሶቅራጥስ የእስር ቤቱን ዘብ አተኩሮ አየውና “ብዙ አትቸገር፡፡ አትጨነቅ፡፡ ያልከኝን ለመፈጸም ዝግጁ ነኝ” አለው፡፡ በወቅቱ ከአጠገቡ ወዳልተለዩት ጓደኞቹ ዘወር አለና፤ “ምን ዓይነት ደግ ሰው መሰላችሁ፡፡ እዚህ እስር ቤት ከገባሁ ጊዜ ጀምሮ ሳይጠይቀኝ ውሎና አድሮ አያውቅም፡፡ አያችሁ አይደል ለእኔ ያለውን ኀዘን በጭንቀት ሲገልጽ?... እውነቱን ነው! እሱ ያለውን መፈጸም አለብኝ! መርዙ ተዘጋጅቶ ከሆነ ኩባያው ይምጣልኝ፡፡ ካልሆነም የሚመለከተው ሰው እንዲያዘጋጅ ይሁን” አለ ሶቅራጥስ፡፡
“በቂ ጊዜ አለ” አለ ክሪቶ፤ ቀጥሎም “ፀሐይዋ ገና ጋራውን አልዞረቺም፡፡ ጊዜ የማይሰጠውን መርዝ ጠጥተህ ለመሰናበት አትጣደፍ፡፡ ለዚህ ማን ቀድሟቸው ያዘጋጁልሃል…” አለው፡፡
“ልክ ነህ ክሪቶ፡፡ የተናገርከው እውነት ነው፡፡ አዎ! በማዘግየታቸው የሚጠቀሙ መስሏቸው ነው… እናም ቶሎ አምጡልኝ ማለቴ ተገቢ ነው - መርዙን ዘግይቼ በመጠጣቴ የማገኘው ጥቅም አይኖርምና! ሳልጠጣ በመዘግየቴ የማጠፋውም የምጠቀምበትም ጊዜ፣ ቀድሞ የሞተ ህይወቴን ጊዜ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በራስ ላይ እንደ መሳቅ ነው የምቆጥረው፡፡ እናም እንዳልኩህ ቶሎ ቢመጣልኝ ይሻላል - አትከልክሉኝ”
ክሪቶ ይህንን ሲሰማ ተላላኪውን ጠቀሰው፡፡ ተላላኪውም ወደ ውስጥ ገባ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ከእስር ቤቱ ዘበኛ ጋር አንድ ኩባያ መርዝ (ሄልሞክ) ይዞ መጣ፡፡ በዚህ ጊዜ ሶቅራጥስ እንዲህ አለ፤ “አንተ በዚህ ጉዳይ ልምድ ያለህ ወንድሜ፤ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ብትነግረኝ” መርዝ ያመጣውን ሰውየ ጠየቀው፡፡
“ከጠጣህ በኋላ እግሮችህ መራመድ አቅቷቸው እስኪዝሉ ድረስ ተንቀሳቀስ፡፡ ያኔ መርዙ በሰውነትህ ይሰራጫል” አለና ኩባያውን ሰጠው፡፡
ሶቅራጥስ ያለ ምንም መደናገጥና መርበትበት ተቀበለውና፤ “ከመጠጣቴ በፊት ለየትኛውም አምላክ የሚቀርብ ስርዓተ ቅዳሴ ይኖራል?...” አለ፡፡
መርዙን የሰጠው ሰውየም፤ “በቂ ነው ብለን ያመንበትን ያህል ብቻ ነው የምናዘጋጀው ሶቅራጥስ” አለው፡፡
“ገብቶኛል” አለ ሶቅራጥስ፤ “ተረድቼዋለሁ፡፡ ከዚህኛው ዓለም ወደዚያኛው ዓለም ለሚያጓጉዘኝ አምላክ መጸለይ እችላለሁ ወይም መጸለይ አለብኝ ወይ? ይህስ ጸሎት ይፈቀድልኛል? ማለቴ ነው” አለና ኩባያውን ወደ ከንፈሩ አስጠግቶ ጨለጠው፡፡
ፕላቶ ከዚህ በኋላ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ በማለት በዝርዝር ያቀርበዋል፡፡ “እስከጠጣበት ሰዓት ድረስ ብዙዎቻችን ኀዘናችንን ውጠን እናየው ነበር፡፡ በአንድ ትንፋሽ መጨለጡን ካየን በኋላ ግን ራሳችንን መቆጣጠር አልቻልንም፡፡ … እንባዬ ይጎርፍ ጀመር፡፡ ፊቴን ሸፈንኩና ለራሴ አለቀስኩ፡፡ እውነቱን ለመናገር ለእርሱ አልነበረም የማለቅሰው፡፡ ለራሴ ነበር የማለቅሰው - እርሱን መሳይ ወዳጄን እንዳጣ አንዳች መከራ ወርዶብኛልና! እኔ ብቻ አልነበርኩም - ክሪቶም እንዲሁ እንባውን መግታት አልቻለም:: ክሪቶ እያለቀሰ መሄድ ሲጀምር ተከተልኩት:: እስከዚያች ሰዓት ድረስ ማልቀሱን ያላቋረጠው አፖሎዶሩስ (Apollodorus) ድምጹን ዘለግ አድርጎ ያለቅስ ጀመር፡፡ የእርሱ ጩኸት ሁላችንንም ፍርሃት ለቀቀብን”
“ይህ ሁሉ ያልተለመደ ጩኸት ምንድነው?!” አለ ሶቅራጥስ ከእንቅስቃሴው ቆም ብሎ፡፡ ቀጥሎም፤ “…ወንድ ልጅ በጸጥታ መሞት አለበት ሲባል ሰምቻለሁ:: ዝም በሉ! ታገሱ!” አለ፡፡
ቀጠለ ፕላቶ፤ “ይህንን ስንሰማ ሀፍረት ተሰማን:: ለቅሷችንን አቆምን፡፡ እርሱ ግን እንቅስቃሴውን ቀጠለ፡፡ በመጨረሻም በጀርባው ተጋደመ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ እግሮቹን አንፈራገጠ፡፡”
“ምን ተሰማህ?” አለው መርዙን የሰጠው ሰውዬ::
“ምንም” አለ፡፡
እግሮቹ ተዘረጉ፡፡ መቀዝቀዝም ጀመሩ፡፡ … “መርዙ ልቡ ጋ ሲደርስ ፍጻሜው ይሆናል” አለ ሰውየው፡፡ የሰውነቱ ቅዝቃዜ እየጨመረና በድን እየሆነ ሄደ… ፊቱን ሸፍኖት ስለነበር ሰውየው ገለጠና አየው፡፡ በጣም ተዳክሟል፡፡ መልሶ ሸፈነው፡፡
ሶቅራጥስ በመጨረሻዋ ሰዓት ምን ተናገረ? የሶቅራጥስ የመጨረሻዎቹ ቃላት ምፀታዊ ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ወይም ቅንነትን የሚያሳዩ ናቸው። ሶቅራጥስ የመጨረሻ ቃሉን ለክሪቶ ነው የተናገረው:: እንዲህ ነበር ያለው “ክሪቶ አንድ ዶሮ ከአስሌፒስ ወስጄ ነበር፡፡ አስታውሰህ እዳዬን እንድትከፍልልኝ አደራ” የሶቅራጥስ የመጨረሻ ቃላት ነበሩ…
“እዳው ይከፈላል” አለ ክሪቶ፤ “ሌላስ ምን የምትለው ነገር አለ?”
መልስ አልነበረም፡፡ ከአንድ ከሁለት ደቂቃ በኋላ እንቅስቃሴ ተሰማ፡፡ ሰውየው ፊቱን ገልጦ አየው፡፡ የሶቅራጥስ ዓይኖች ተጨፍነዋል፡፡ ክሪቶም ዓይኑን ጨፈነ፡፡ አፉን ከደነ፡፡ የጓደኛችን መጨረሻ ይኸው ነበር - አለ ፕላቶ፡፡
የታላቁ ፈላስፋ የሶቅራጥስ አሟሟት ይህንን ይመስላል፡፡ ተፈላሰፈ፡፡ ብዙ ተከታዮችን አፈራ፡፡ የዴሞክራሲ ሰማእት ሆኖ በሞቱም አስተማረ!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው:- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 1960 times