Saturday, 03 August 2019 13:46

የቀይ ሽንኩርት ‘ህልም’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)


           “ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… በምኑም በምናምኑም የምናነሳት አሜሪካ እኮ በአንድ ጣራ ስር በሚኖሩ የቤተሰብ አባላት መካከል የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞች ይንጸባረቃሉ፡፡ ባል ሪፐብሊካን ቢሆን፣ ሚስት ዲሞክራት ትሆናለች፡፡ አንዱ ጽንስ ማቋረጥን ሲደግፍ፣ ሌላው ሊቃወም ይችላል፡፡ አንዱ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ወዳጅ መሆን አለብን ሲል፣ ሌላው “አልስማማም፣” ሊል ይችላል፡፡--”
                 
             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“እርስ በእርሳቸው ተፋጁ፣ ተላለቁ፣” ምናምን ከሚሉት ያለፉት ወራት አስከፊ ዜናዎች ለጊዜውም ቢሆን እንኳን… “ከጫፍ ጫፍ ተባብረው በጋራ ችግኝ ሲተክሉ ዋሉ፣” መባል ለአፍ የሚቀል ይመስላል እንጂ ከ‘ሰበር ዜናነቱ’ አልፎ… አለ አይደል… “ምነው በሁሉም ነገር እንዲህ በተባበርን!” አስብሎ የሚያስመኝ ነው፡፡ የምንመኘው ነገር መብዛቱ!
ነገርዬውማ… አንዳንዴ አቅም ሲያንሰን ወይም ያነሰን ሲመስለን የምኞት መጨረሻዋ፣ ቀበሮ ጉድጓዳችን ነው! (እሱንም አያሳጣን!…) ችግሮች ሲበዙና እንደ ቀድሞው “ሆዴ፣ አንጀቴ…” እያላችሁ የምታማክሩት ሰው ሲያንስ፣ ጭራስ ሲጠፋም፣ የሆድ የሆድን ለመመካከር አስቸጋሪ ሊሆን እኮ ነው፡፡
“ስማ አከሊትን ለማገባት ወስኛለሁ፡፡”
“እሷ ደግሞ ማናት?”
“ያቺ የሰፈራችን ልጅ፣  ባለ ‘ትሪፕል’ ዳሌዋ እንኳን…”
“አንተ ሰውዬ፣ ያምሀል እንዴ! ምንነቷን አውቀህ ነው የምታገባት?”
“አንተ የማታወቃት ይመስል ምንነቷን ምናምን ማለት ምን ማለት ነው! ከአስር ዓመት በላይ አንድ ሰፈር፣ ያውም ጎረቤት ሆነን ኖረን ምንድነው ከማርስ ከምናምን የመጣች የምታስመስላት!“
“ስማ ወዳጄ… አስር ዓመት በለው፣ ሰላሳ ዓመት በለው፣ እነሱ አይነት ቁጥሮች ሁሉ ‘ዲሊት’ ተደርገዋል፡፡ አሁን የሚጠየቀው ስንት ዓመት አብረህ ኖርክ ተብሎ ሳይሆን ‘ለመሆኑ የትውልድ ስፍራዋ የት ነው፣’ ተብሎ ነው፡፡”
“እኔ የት ትወለድ የት ምን አገባኝ! ለምን ለእኔ ስትል ከፈለገች በሞንጎሊያ፣ ቀበሌ ዘጠና ዘጠኝ አትወለድም! እንዴት ነው ማሰብ የጀመርከው!”
“እንደ ዘመኑ፣ እንደ ዘመኑ ነው ማሰብ የጀመርኩት፡፡ ስማኝ ወዳጄ፤ በአሁኑ ጊዜ ‘የሀገር ልጅ ዘው፣ ዘው፣’ ሹሩባዋ ጠይሟ ምናምን ብሎ ነገር ለዘፈን ብቻ ነው፡፡ እንደውም ሞንጎሊያ ያልካት ነገር ተመችታኛለች፡፡ ጎግል ግባና ‘የሞንጎሊያ ሚስት ያለህ፣” በልና ፈልግ እንጂ ይሄ ‘ትሪፕል’ ዳሌ፣ ‘ደብል ብሬስት’ ምናምን የምትለውን ነገር እርሳው፡፡”
ይሄም በዛ፡፡ ፋዘሯ እኮ እንትን ሪል እስቴት አስር ጂ ፕላስ ዋን አላቸው” የሚሉ ‘ፍሪ ማርኬትን’ በትዳር የሚሞክሩ ‘አንተረፕረነር’ ወጣቶችን ማሳነፍ ነው፤ (ቂ…ቂ…ቂ…) እናማ…ይህኛውም ተጋነነ፡፡ (ለነገሩ እዚህ ሀገር ምን የማይጋነን ነገር አለ!) ግን እመኑኛ፣ ነገሮችን ከአሁኑ ፍጥነታቸውን ካልቀነስንላቸው… ሲያዛጋንም፣ ሲያስነጥሰንም፣ ሲያደናቅፈንም  “የትውልድ ስፍራው እኮ እንደዚህ ነው፣” “አፍ መፍቻው እንደዛ ነው፣” በሚል ማሰብ አይነት ካልቆመ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን የባሰው ነው የሚመጣው፡፡ ደግሞላችሁ ትዳርን የመሳሰሉ ነገሮችን በተመለከተ ‘ሶስተኛው ወገን፣’ ማለትም ወላጆች ፈቃድ ሲጠየቁ፣ እንደ በፊቱ ከቤትና ከመኪና የላቀ የሚጎላው…አለ አይደል… “ለመሆኑ የየት አካባቢ ሰው ነው?” ማለት እየተለመደ መጥቷል ይባላል…በጥናት የተደገፈ መቶኛ ምናምን ነገር ያቀረበልን ባይኖርም፡፡
እናማ… በዚህ አይነት ከቀጠለ ወደፊት ወላጆችን “ልጃሁን ለልጃችን…” ብሎ ፈቃድ ከማግኘት ይልቅ በአምስት ሺህ ብር መነሻ ካፒታል፣ የባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ግንባታ ፈቃድ ማግኘት ሊቀል ይችላል፡፡ (አሀ…ነገሮች ማጋነኑ በራሱ ‘ፉክክር’ እየመሰለ ስለመጣ… በተለይ በፖለቲካው… እኛም የማጋነን ‘መብታችንን’ መጠቀማችን እንደሆነ ልብ ይባልልንማ!) ለነገሩ ወላጆችም ቢሆኑ ባለው ሁኔታ የልጆቻቸው ደህንነት ቢያሳስባቸው አይገርምም፡፡ 
“ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደደው…” የሚለው በአሥራ ሰባተኛው ክፍል ዘመን የነበረና “የዛሬው ቀን በታሪክ ውስጥ” አይነት ፕሮግራም ላይ ብቻ የሚቀርብ ይመስላል፡፡ “እንዴት ነው ጎረቤቴን የምወዳት! እኛ እናቷ ጥቁር ድመታቸውን በቀን አስር ጊዜ በአጥር ሲሰዱብኝ ነበር እኮ! ይሄን የምረሳ መሰለሽ!!”
“ታዲያ ድመት ሲልኩብሽ የነበሩት እናቷ፣ እሷ ምን አደረገችሽ!” (የምር ግን ብዙ ቦታ እንደ ልብ መንቀሳቀስ መብት የተጠበቀላቸው የሚመስሉት ድመቶች ናቸው፡፡ መግቢያና መውጫ መንገድ አያጡማ! በየት ፈልፍለው እንደገቡ ሳናይ ሲቧጭሩን ነው የምንነቃው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
“ተይ እባክሽ የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም፡፡”
እንዲህ ነው… ሀገርን ያጠፋው “የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም” ነገር ነው፡፡ ኮሚኩ ነገር እኮ ‘የወጋ’ የተባለው ወገን አብዛኛው እንኳን እዛ ሊደርስ ‘ስፒል’ እንኳን ላይኖረው ይችላል:: ‘የተወጋ’ የተባለውም…“ለመሆኑ ምንህን ነው፣” ቢሉት የሚያሳየው ጭረት ላይኖር ይችላል፡፡ ግን ደግሞ እዛ ማዶ…“ጭረት ባይኖርብህም በቃ ተጎጂ ነህ ተብለሀል ተጎጂ ነህ፣” አይነት የሚል አለ:: የሀገራችን ፖለቲካ እዚህ አይነት ‘ከፍታ’ ላይ ነው:: ለነገሩ “እስቲ ማስረጃ አቅርብ፣”  “መረጃውን ያገኘኸው ኬትኛው ምንጭ ነው?” ብሎ ነገር ስሌለ አያሳስብም፡፡ “በዚህማ አንደራደርም!” “እንትን መለወጥ ብሎ ነገርማ አይታሰብም» የሚል በበዛበት መስቀለኛ ጥያቄ፣ ምናምነኛ ሙግት ብሎ ነገር የለም፡፡  እናላችሁ…በሆነ፣ ባልሆነው “የማን ቤት ፈርሶ የማን ሊበጅ…” እየሆነ ጠንካራ ማህበራዊ ግንኙነት መሰረቶች አየተነቃነቁ ነው፡፡ ከአስራ አንደኛው ሰዓት በፊት እነሱን መልሶ ቀጥ ማድረግ ደግሞ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡
በዚያ ሰሞን የሆነ ሰው መስሪያ ቤቱ ከአዲስ አበባ ወደ ሌላ ከተማ ቅርንጫፍ እንደሚለወጥ ይነግረዋል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖም የተባለው ከተማ የሰውየው የትውልድ ስፍራና አብዛኞቹ ዘመዶቼ የሚላቸው አሁንም የሚኖሩበት ስለነበር ዝውውሩን የተቀበለው በደስታ ነው፡፡ ለአንድ ጓደኛውም የዝውውሩን ዜና በጨዋታ መልክ ይነግረዋል፡፡ ጓደኛ ሆዬም…
“ካልጠፋ ስፍራ እንዴት እዚያ ይልኩሀል!” ብሎ አካባቢው ላይ ብዙ ደስ የማይሉ ቃላት ይወረውራል፡፡ የተናገራቸው አብዛኞቹ ነገሮች ደግሞ የዘንድሮን የጥላቻ ፖለቲካ የሚሸቱ ነበሩ:: እናላችሁ… እንደ ብዙዎቻችን ከሆነ ይህ ሰው የተወለደባት ከተማ እንደዛ መአት ሲወርድባት ሲሰማ የሸሚዙን እጅጌ ወደ መጠቅለል መግባት ነበረበት፡፡ ሆኖም ጓደኛውን እንደዛ ያናገረው የአቋም ጉዳይ ሳይሆን የዘንድሮ የ“እኛና እነሱ” ፖለቲካ መሆኑ ስለገባው ነገሩን በፈገግታ ያልፈዋል:: በማግስቱ ግን የተወለደው እዛ አካባቢ መሆኑንና ብዙ ዘመዶችም እዛ እንዳሉት ሲነግረው ያኛው ይደነግጣል፡፡ ሰውየው ግን ነገሩን በጣም አቅልሎ በጓደኛነት መንፈስ የመጣለትን ዝም ብሎ መናገሩ ከሰዎች ጋር ሊያጋጨው እንደሚችልና ጊዜው አስቸጋሪ እንደሆነ ይመክረዋል፡፡
የምር ግን… አለ አይደል…በአሁኑ ጊዜ ስንቶቻችን ነገሮችን እንደዚህ ሰው በሰከነ መንፈስ እንደምናይ መገመት እንኳን አስቸጋሪ ነው፡፡ መላ ቅጡ የጠፋና፣ ከእውቀትና ከምክንያታዊነት ይልቅ ግብዝነትና ከ“እኛ በላይ ለአሳር፣” የበዛበት ፖለቲካችን እየፈጠረ ያለው ማህበራዊ ቀውስ ቀላል አይደለም፡፡ አስተሳሰብ ሁሉ እየጠበበ፣ እየጠበበ ከልዩነት ጋር አብሮ መኖር የሚባለው ነገር መኖሩን እየረሳነው ይመስላል፡፡ አያሳዝንም! 
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… በምኑም በምናምኑም የምናነሳት አሜሪካ እኮ በአንድ ጣራ ስር በሚኖሩ የቤተሰብ አባላት መካከል የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞች ይንጸባረቃሉ፡፡ ባል ሪፐብሊካን ቢሆን፣ ሚስት ዲሞክራት ትሆናለች፡፡ አንዱ ጽንስ ማቋረጥን ሲደግፍ፣ ሌላው ሊቃወም ይችላል፡፡ አንዱ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ወዳጅ መሆን አለበት ሲል፣ ሌላው “አልስማማም፣” ሊል ይችላል::
 ግን ምንም አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት አንድ ገበታ ከመቅረብ አያግዳቸውም:: አንዴ እየጎረሱ ሦስቴ “አንቺ እንዴት ብለሽ ነው ዴሞክራቶችን የምትደግፊው!” ቅብጥርስዮ አይባባሉም፡፡ ፖለቲካውን በፖለቲካነቱ ይይዙታል:: እንደ እኛ የተነጠሰውንም፣ የተበጠሰውንም ነገር ፖለቲካ እየቀቡ አይናቆሩም፡፡
“ህልም ሳይ አደርኩልህ፡፡”
“ምን አየህ?”
“ሽንኩርት ስልጥ አየሁ፣”
“ሽንኩርት! ሰዉ ስንት ነገር ያያል አንተ ሽንኩርት ስትልጥ ታያለህ!”
“መርጬ የማየው ፊልም አደረግኸው እንዴ!”
“ለምን መሰለህ… እሱን ህልም ያየኸው ሰዉን እንደ ሽንኩርት እየላጥክ አስለቀስከው ለማለት ይሆናል፡፡” (ወይ ደግሞ ሌላኛዋ… “ታድለሽ፣ አንቺስ ቢያንስ፣ ቢያንስ በህልምሽ አየሽው፡፡ እኔ ነኝ እንጂ ምነው መብላቴ ቀርቶ አንድ ኪሎውን ልጬ ዓይኔ ላይ በሞጀርኩና ሳምንት ባለቅስኩ እያልኩ ያለሁት!” ትል ይሆናል!)
(ክፋቱ ምን መሰላችሁ… ሽንኩርትን ከፖለቲካ እንዳናወጣው ተወደደ፣ በጣም ተወደደ! ሀሳብ አለን… እለታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢያችን በዶላር ምናምን መሰላቱ ቀርቶ በቀይ ሽንኩርት ይሰላልንማ!)
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2953 times