Saturday, 03 August 2019 14:00

‹‹የማይንከባከቡት ችግኝ፤ ልጅ ወልዶ እንደመጣል ይቆጠራል››

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

 ንግድ ባንክ ‹‹በአረንጓዴ አሻራ ቀን›› ከ23 ሺህ ችግኞች በላይ ተከለ
                         

               የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው ሰኞ፤ በ‹‹አረንጓዴ አሻራ ቀን››፤ በተለያዩ 12 ቦታዎች፣ ከ23 ሺህ በላይ ችግኞች መትከሉን አስታወቀ፡፡ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በአገር አቀፍ ደረጃ ለመተግበር ባንኩ፣ በአዲስ አበባ ከተማ በየካ ክ/ከተማ በተለምዶ ‹‹ጣሊያን ምሽግ›› እየተባለ በሚጠራው አካባቢና በቢሾፍቱ ከተማ  ከ20 ሺህ በላይ ችግኞች የተከለ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ከአንድ ሺህ በላይ የባንኩ የማኔጅመንት አካላት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ሠራተኞችና የባንኩ ስፖርተኞች ተሳትፈዋል፡፡
በቢሾፍቱ የችግኝ ተከላ ወቅት የባንኩ ዋና የፋይናንስ መኮንን ወ/ሮ መሊካ በድሪ ባደረጉት ንግግር፣ ከበርካታ ዓመታት በፊት 40 ከመቶ የነበረው የደን ሽፋን ተመናምኖ ወደ 3 በመቶ ወርዶ ነበር፡፡ ለዚህ የአካባቢ ጉዳይ እንደ ባንክ ምላሽ ፣ለመስጠት አካባቢያችንን ከብክለት  እንዲሁም የደን ሀብታችንን ከውድመት መከላከል፣ ዘላቂ በሆነ መንገድ መተካትና መንከባከብ የሚጠበቅብን ነው ብለዋል፡፡
ባንኩ ባለፉት ዓመታት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመሥራት ውጤት የታየባቸውን ሥራዎች ሲሰራ የቆየው የሚጠበቅበትን ማኅበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ነው ያሉት ወ/ሮ መሊካ፤ “ባንኩ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ለረጅም ዘመናት እየተመናመነ የመጣውን የአገራችንን የደን ሀብት መልሶ ለመተካት፣ የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን መሸፈን ትኩረት የሚያሻው ተግባር በመሆኑ ነው፤ ባለፉት ዓመታት ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለው ብለዋል፡፡
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የቢሾፍቱ ከተማ ም/ከንቲባ ባደረጉት ንግግር፤ የተተከሉት ችግኞች እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው ሲገልጹ፤ ‹‹ችግኝን ተክሎ መሄድ ማለት ልጅን ወልዶ መጣል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ቦታ አንድ ቀን መጥታችሁ የምትዝናኑበት ቦታ እንዲሆን እየመጣችሁ ተንከባከቡት›› በማለት አሳስበዋል፡፡
ባንኩም በተለያዩ ቦታዎች የሚተክላቸውን ችግኞች እንደሚንከባከብ ሁሉ፣ በቢሾፍቱ ከተማ ከቢሾፍቱ ሐይቅ በስተደቡብ ባለው ኮረብታማ ስፍራ የተከላቸውን ችግኞች የሚንከባከቡ ሰራተኞችን እንደሚቀጥር ገልጿል፡፡
እንደ ንግድ ባንክ ሁሉ አያሌ የመንግስትና የግል ተቋማት እንዲሁም መላ ኢትዮጵያውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ በተሳተፉበት በዚህ የአረንጓዴ አሻራ ቀን፤ ኢትዮጵያ በዕለቱ ለመትከል በዕቅድ ከያዘችው 200 ሚሊዮን በላይ ከሦስት መቶ ሃምሳ ሦስት ሚሊዮን በላይ ችግኞች በመትከል በህንድ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን ለማሻሻል በቅታለች፡፡
ይህንኑም አገራዊ ስኬት ከዋሺንግተን ፖስት እስከ አሶሼትድ ፕሬስና ሲኤንኤን አልጀዚራ የመሳሰሉ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች እየተቀባበሉ አስተጋብተውታል፡፡

Read 2033 times