Saturday, 03 August 2019 13:40

አገራዊ ወቅታዊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ - በኢሰመጉ ግምገማ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)


              በ2001 በወጣው የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጅ ምክንያት ስሙን “ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ” ወደ “ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ” ለመቀየር ተገድዶ የነበረው አንጋፋው የሰብአዊ መብት ተቋም፤ በቅርቡ የቀድሞ መጠሪያውን መልሶ ያገኘ ሲሆን በአዲሱ የበጎ አድራጎትና ማህበራት
አዋጅ መሠረትም፤ ጠንካራ አደረጃጀት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ተቋሙ በአሁኑ ወቅት እያከናወናቸው ስለሚገኙ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ጉዳዮች ስለ ወቅታዊ የአገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝና የተቋሙን ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም አባተ፤ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡

          የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በአሁኑ ወቅት ያለው ቁመና ምን ይመስላል?
የኢሰመጉን ወቅታዊ ቁመና ለመመዘን በቅድሚያ ተቋሙ ያለፈበትን ሂደት ማየት ያስፈልጋል፡፡ ቀደም ሲል ወጥቶ የነበረው የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጅ፣ እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳረፈባቸው ተቋማት አንዱ ኢሰመጉ ነው፡፡ በተለይ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ላይ እንደ መስራቱ ጉዳቱ የሰፋ ነው፡፡ ለ10 ዓመት የዘለቀው አዋጅ፤ በድርጅቱ ላይ የገንዘብ ብቻ ችግር አይደም ያደረሰው፡፡  እንደ ድርጅትም ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ነው የከተተው፡፡ መጠሪያ ስሙንም እስከ ማጣት አድርሶት ነበር፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ›› የሚለውን ትቶ ‹‹የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ›› እንዲባልም ተገድዶ ነበር፡፡ ለህልውናው ተገዳዳሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ነበር፣ በጠንካራ ትግል ህልውናውን አቆይቶ መዝለቅ የቻለው፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት አንጻራዊ የመስራት ዕድል ቢያገኝም፣ ባለፈው 10 ዓመት ከነበረበት ተፅዕኖ ሙሉ ለሙሉ አልተላቀቀም፡፡ ለምሳሌ ባለፉት በርካታ ወራት ድርጅቱ ያለምንም ባጀት ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው፡። ነገር ግን በሩን ሳይዘጋ ባለው አቅም ሁሉ እየተፍጨረጨረ ነው፣ ራሱን እያንቀሳቀሰ ያለው፡፡ በቅርቡ የፀደቀው አዋጅ፣ ለተቋሙ መልካምና የሚያሰራ በመሆኑ፣ አሁን ወደ ቀደመ እንቅስቃሴው በጥንካሬ ለመመለስ፣ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ነው የሚገኘው፡፡
በአንድ ወቅት በመንግስት የተወረሰባችሁን ገንዘብ ለማስመለስ ጥረት ስታደርጉ ነበር፡፡ ጥረታችሁ ምን ላይ ደረሰ?
አዲሱ የመንግስት አስተዳደር ያመጣውን ተስፋ መሰረት በማድረግ፣ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ደብዳቤ ጽፈናል፡፡ ከህግ አግባብ ውጭ ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ሀብት ታግዶ ነው የሚገኘው:: ይሄን ለማስለቀቅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ጽፈን ነበር፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ያገኘነው ምላሽ፣  መንግስት በዚህ ጉዳይ ጣልቅ መግባት እንደማይችል ነበር፡፡ ነገር ግን ከተለያዩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር መልካም  ውይይቶችን እያደረግን ነው፡፡ የተያዘብን ገንዘብ እንደሚለቀቅ የሚያመላክቱ በጎ ምላሾችን እያገኘን ነው፡፡ ተግባራዊ ምላሹንም እየጠበቅን ነው::
ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ  በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተከስተዋል፡፡  እናንተ እነዚህን ጥሰቶች ለማጣራት ምን ያህል ጥረት አድርጋችኋል?
በአገሪቱ ውስጥ ከሚከሰቱ ችግሮች ብዛት አንጻር፣ ኢሰመጉ እያደረገ ያለው ጥረት በቂ ነው ብለን እኛም እናምንም፡፡ ይህም የሆነው ድርጅቱ ባለው ወቅታዊ አቅም የተነሳ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በአገሪቱ የሚታየው ችግር በዚህ አንድ ድርጅት ብቻ ሳይሆን በአስር ድርጅቶችም ይሸፈናል ብለን አናምንም፡፡ በየአቅጣጫው ያሉ የሰብአዊ መብት ጉዳቶችን ለመመርመርና ለመዘገብ በርካታ አቅምና ጥንካሬ ይሻል፡፡ በሌላ በኩል፤ አሁን እንደ ቀድሞ ተንቀሳቅሰን ምርመራችን ለማድረግ፣ አዳዲስ እንቅፋቶች እየገጠሙን ነው፡፡  በቀደሙት አመታት፣ በምርመራ ባለሙያዎቻችን ላይ ጫናና ወከባ ይደረስ የነበረው በመንግስት አካላት ነበር:: ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ባለው ጊዜ ውስጥ ጫናውና ወከባው የሚደርሰው ከመንግስት ውጭ የተለያዩ ቡድኖችና የብሔር አደረጃጀቶች ነው:: እንደዚህም ሆኖ ባገኘናቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ዋና ዋና ክስተቶችን ለመመርመር ሞክረናል ባለፈው ዓመት በደቡብ ክልል በዎላይታና ሲዳማ  መካከል የተከሰቱ ግጭቶች፣ እንዲሁም የጌዲዮ ጉዳይ ተመርምሮ ሪፖርት ለማድረግ ተሞክሯል። በቡራዩ አካባቢ የነበሩ ችግሮች ላይ ምርመራ ተደርጎ ሪፖርቱ ተዘጋጅቷል፡፡ በሰሜን ሸዋ አጣዬ አካባቢ የነበሩ ግጭቶችንም መርምረን አጠናቀን፣ ሪፖርት በማጠናቀር ላይ እንገኛለን። በቅርቡ ሁለቱንም ይፋ እናደርጋለን፡፡
ከቡድኖችና ከብሔር አደረጃጀቶች ጫና አጋጥሞናል ብላችኋል፡፡ ምን አይነት ጫና ነው?
በባለሙያዎቻችን ላይ ማስፈራራቶች፣ ያልተገባ ክትትልና ወከባዎች ይፈፀማሉ፡፡ አሁንም እነዚህን (ሪፖርታቸው የተዘጋጀው) ምርመራዎችን ስናደርግም፣ ከመንግስት በቂ ጥበቃ  አግኝተን አይደለም፡፡ ባለሙያዎቻችን ለጥቃት በጣም ተጋላጭ ሆነው ነው ተግባራቸውን እያከናወኑ ያሉት፡፡ ጫናው ቀነስ ባለ አካባቢ ነው ምርመራችንን ለማከናወን እየጣርን ያለነው፡፡ ጫናው በከፋባቸው አካባቢዎች ነገሮች እስኪረጋጉና አስቻይ ሁኔታዎች እስኪፈጠሩ እየጠበቅን ነው፡፡
አዲሱ አስተዳደር ከመጣ ወዲህ የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምን አይነት ባህሪ ነው ያላቸው? ግምገማችሁ ምን ይመስላል?
ባለፈው አንድ አመት በጎላ ሁኔታ የምናየው፣ ብሔር ተኮር የሆኑ ግጭቶችን ነው፡፡ እነዚህም በአብዛኛው መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ የተደራጁ፣ ብሔራችንን እንወክላለን የሚሉ ቡድኖች እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች በመንግስት አስተዳደር እርከን ውስጥ ያሉ ግለሰቦችንም የሚያሳትፉ ግጭቶች ናቸው ያሉት፡፡ በቀደሙት አመታት፣ በአብዛኛው የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈጸም የነበረው፣ በመንግሥት የፀጥታ ሀይሉ በቀጥታ በሚወሰዱ እርምጃዎች ነበር፡። ባለፈው አንድ ዓመት ግን በአብዛኛው መደበኛ ባልሆነ መንገድ በተደራጁ ሀይሎች በሚፈጠር ግጭት መሀል ነው ሰብአዊ መብቶች እየተጣሱ ያሉት፡፡ በዚህም ሁኔታ ውስጥም መንግስት ሕግ የማስከበር ግዴታውን ሳይወጣ በመቅረቱ በርካታ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ መንግስት ሕግንና ሰላምን ባለመስከበሩ የሚከሰቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ናቸው እየተበራከቱ ያሉት:: በየክልሉ ያሉ ልዩ ሃይሎችም በተወሰነ ደረጃ፣ በሰብአዊ መብት ጥሰቶቹ ላይ ተሳታፊ ሆነው የሚታዩበት አዝማሚያም አለ፡፡
በእናንተ ግምገማ መሰረት፤ በሰብአዊ መብት አያያዝ በመንግስት በኩል የተሻሻሉ ሁኔታዎች አሉ ማለት ይቻላል?
አሻሽሏል ብለን መናገር የምንችለው ምናልባት፣ ከዚህ ቀደም በቀጥታ ጥይቱን ይተኩሱ የነበረው በመንግስት የፀጥታ አካል ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡ አሁን የተደራጁ ቡድኖች፣ አንዳንድ ቦታም የታጠቁ ሃይሎች ናቸው፣ በንፁሃን ላይ ጥቃት እያደረሱ ያሉት፡፡ ይህም ቢሆን መንግስት እነዚህን ቡድኖች የመቆጣጠር ሃላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡ የታጠቁትን ትጥቃቸውን የማስፈታትና የዜጎችን ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራትና የመኖር መብት ማስጠበቅ አለበት፡፡ መንግስት ይሄን ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም፡፡ ስለዚህ መንግሥት በቀጥታ ጥይት ባለመተኮሱ ብቻ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ላይ በተሻለ መልኩ እየሰራ ነው ማለት አይቻልም።  አሁንም ዜጎች ከየትኛውም ቡድንና አካል ተጽእኖ ነፃ ሆኖ የመኖር መብታቸውን መንግስት እያስጠበቀ አይደለም፡፡ ይሄን ባለማድረጉም ከሰብአዊ መብት ጥሰት ተወቃሽነት አያመልጥም፡፡
በቅርቡ ባወጣችሁት መግለጫ፣ “የጅምላ እስር እየተፈፀመ ነው” ብላችኋል፡፡ በእርግጥ የጅምላ እስር እየተፈፀመ ነው?
የጅምላ ከምንለው ይልቅ መጠነ ሰፊ እስራት ብንለው የተሻለ ይሆናል፡፡ በእርግጥ ባህር ዳርና አዲስ አበባ ላይ ከተፈጸሙት ግድያዎች በኋላ፣ መንግስት በባህር ዳርም ሆነ በአዲስ አበባ መጠነ ሰፊ እስራት ፈፅሟል፡፡ ከእነዚህ እስራት መካከል ደግሞ በአንድ የፖለቲካ ቡድን ውስጥ ያሉ ግለሰቦችና አመራሮች እንዲሁም በአዲስ አበባ አስተዳደር ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ሲያቀርቡ የነበሩ ግለሰቦች በብዛት ሰለባ ሆነዋል የሚል እምነት አለ፡፡ የሚታየውም ነገር እንደዚያ ነው፡። ግለሰቦች ከታሰሩ በኋላ በተለይ በምርመራ ወቅት እየቀረበልን ነው የሚሏቸው ጥያቄዎች፣ ከተጠረጠሩበት ወንጀል ይልቅ የፖለቲካ ተሳትፎአቸውን መሰረት ያደረገ ሆኖ ይታያል፡፡ እነዚህ ነገሮች አዝማሚያቸው መልካም አይደለም:: ባለፈው አንድ ወር ገደማ ለምሳሌ ‹አብን› ለኛም ባቀረበው አቤቱታ ላይ በርካታ አመራሮቹና አባሎቹ እንደታሰሩበት ጠቁሟል። ‹የአዲስ አበባ ባለአደራ› የሚባለው አካልም፣ በርካታ አባሎቹ እንደታሰሩበት ገልጿል፡፡ እኒህ ሁኔታዎች አዝማሚያቸው መልካም አይደለም፡፡
በፖለቲካ አመለካከታቸው ነው የታሰሩት የሚያስብል መረጃ አግኝታችኋል?
በፖለቲካ አመለካከታቸው ነው የታሰሩት የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አሁን ያለን መረጃ በቂ አይደለም፡፡ ነገር ግን አዝማሚያቸው መልካም እንዳልሆነ በደንብ መረዳት ይቻላል፡። ለምሳሌ ከሰኔ 15ቱ ክስተት ጋር በተገናኘ የተያዙ ታሳሪዎችን ለመከታተል እንዲሁም እስረኞችን ለመጎብኘት ሙከራ አድርጌያለሁ፡፡ በእስር ቤቱ ላይ የሚያቀርቡትን አቤቱታ ሰምተናል፡፡ በኛ በኩልም የታሰሩበትን ሁኔታ ለመታዘብ ሞክረናል፡። አንድን እስረኛ የሕግ ባለሙያው (ጠበቃው) ብቻውን ሊያገኘው የማይችልበትን ሁኔታ ታዝበናል፤ አብሮት መርማሪው ይኖራል፤ ይሄ በየትኛውም ሁኔታ ተገቢ አይደለም፡፡ መሠረታዊ የሆነ የመብት ጥሰት ነው። አዝማሚያው ወደ ኋላ የመመለስ አይነት ነው። በቶሎ ማስተካከያ ካልተደረገበት ጭልጥ ብሎ ወደ ነበረበት የማይመለስበት ማስተማመኛ የለም፡፡
ከዚህ ቀደም በተለያዩ መንገዶች የማሰቃየት፣ ጨለማ ክፍል የማሰር… ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ አሁንም እነዚህ ነገሮች ይፈፀማሉ?
ባለን ውስን አቅም የተነሳ ማረሚያ ቤቶችን በሙሉ ማየት አልቻልንም፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ላይ እኔ ራሴ ተገኝቼ ያየኋቸው ነገሮች አሉ። የታሰሩ ሰዎች አሁንም በነፃነት በጠያቂዎች እየተጎበኙ አይደለም፡፡ ለብቻቸው እንደ ልባቸው ከሕግ ባለሙያዎቻቸው ጋር ሊወያዩ አልቻሉም፡፡ ይሄ በግልጽ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ ሌሎች በእስረኞች የሚገለፁ ጨለማ ቤት ወይም ለብቻ ነጥሎ የማሰር… ሁኔታዎችም አሉ። ሙሉውን - ምስል ለመረዳት ግን ጠለቅ ያለ ምርመራ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
ባለፈው አንድ አመት ተኩል በአጠቃላይ የአገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ ምን ይመስላል?
በእርግጥ ከመንግስት በኩል ለማሻሻል የሚታየው ፍላጎት ጠንካራ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ወራት አካባቢ ጠንካራ ፍላጎት እንዳለው በአንዳንድ ተግባራትም ሲያሳይ ነበር፡፡ የተደረጉ መልካም ነገሮች አሉ፡፡ ባለፉት አመታት ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈፅሙ ነበር የተባሉ አካላትን ለህግ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡ ይሄ መልካም እርምጃ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም በፓርላማ ቀርበው “ስናሸብር የነበረው እኛ ነን” ማለታቸውና ሲፈፀም ለነበረው ሰብአዊ ጥሰት እውቅና መስጠታቸው መልካም እርምጃ ነበር፡፡ የሽብር ህጉንም ለማሻሻል  የተሄደበት መንገድም ትልቅ ነገር ነው፡፡ መንግስት በአንዳንድ ጉዳዮች ያሳየውን ቁርጠኝነት ማጣጣል አይቻልም፡፡ ነገር ግን ይሄ ቁርጠኝነት ምን ያል ተጠናከሮ ቀጥሏል፡፡ በተግባርስ ወደ መሬት ወርዷል ወይ የሚለው ጉዳይ ላይ ውስንነቶች አሉ። እርግጥ ነው ሙሉ ስርአቱን መለወጥ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከባድ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት እያየነው ያለ ሁኔታ ግን የታየውን ረጅም ተስፋ ሰጪ ጅምር ወደ ኋላ የሚመልሱ ናቸው።
መንግስት አሁንም የአገሪቱን የሰብአዊ መብት አያያዝ ለማሻሻል ምን ማድረግ አለበት ይላሉ?
መጀመሪያ ተቋማትን ማጠናከር ነው፡፡ በእርግጥ ከረጅም አመታት በኋላ ብዙ ባለሙያ ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተሹሟል። አዲሱ ኮሚሽነር የነበራቸውን የሰብአዊ መብት ስራ ታሪክ ስንመለከት፣ በእጅጉ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ የፍትህ ተቋማትን የማረም እርምጃዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡ እነዚህን ሁሉ አጥርቶ መሄድ ያስፈልጋል። አስፈላጊ ከሆነም እንደገና አፍርሶ መስራትም ይገባል። በተለይ ታሳሪዎች (ከሰኔ 15 ጋር በተያያዘ) የተያዙበት ሁኔታ፣ አንዳንዱ የቀድሞውን ዘመን የሚያስታውስ ነው:: ይሄ የሚያሳየን የፀጥታ መዋቅሩ ላይ ገና ብዙ እንዳልተሰራ ነው፡፡ እነዚህን መለወጥ ያስፈልጋል:: ከዚህ በተጨማሪ እንደ ኢሰመጉ ያሉ ድርጅቶችን ጥረት ማገዝና ጥበቃ ማድረግም አስፈላጊ ነው፡፡
በቀጣይ ኢሰመጉ ምን ለማከናወን አቅዷል?
በዋናነት የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራዎች ነው የሚሰራው፡፡ ባለፉት ወራት የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በሙሉ ለመመርመር ጥረት ያደርጋል፡። በቅርቡ በሲዳማ የተፈፀመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ይመረምራል፡። በተጓዳኝ ደግሞ ከሌሎች የሰብአዊ መብት ጥበቃ ተቋማት፣ ከፍትህ አካላት፣ ከጠቅላይ አቃቢያት ጋር ያለንን ግንኙነት አጠናክረን የሚጠበቅብንን ሁሉ ለመወጣት እንጥራለን፡፡              


Read 577 times