Saturday, 03 August 2019 14:07

ከፋታ ይልቅ ድንፋታ!

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(10 votes)

    አንዳንዶች “ኢትዮጵያ ተሰርታ ያላለቀች ሀገር ናት” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይህንን የሚሉት ሀገሪቱ በህገ መንግስቷ መሰረት ሊያሰራ የሚችል፣ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ለአስተዳደር አመቺ የሆነ፣ ዴሞክራሲያዊ አደረጃጀት ፈጥራ፣ ወደ ልማት አልገባቺም ለማለት ይመስለኛል፡፡ ይህ አባባል አንዳንዶችን ላያስደስት ይችላል፡፡ ግን እየመረረንም ቢሆን ልንቀበለው የሚገባ ሀቅ ነው፡፡ እንደ አንድ ብሔር ኢትዮጵያን ለመፍጠር ቀደምት አባቶቻችንና አያቶቻችን ለፍተዋል፣ ጥረዋል፣ ግረዋል፡፡ አሁን “ኢትዮጵያ” ተብላ ዓለም የሚያውቃትን ሀገር ፈጥረዋል፡፡ ይህቺን “ብሔር”(ሀገር) ለመፍጠር አያት ቅድመ አያቶቻችን እርስ በርስ ተገዳድለዋል፡፡ ተራርደዋል፡፡ ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ አካል ጎድሏል፡፡ ያ መስዋእትነታቸው “ኢትዮጵያ” የተባለች ብሔር ቢያስገኝልንም ይህቺ ሀገራችን በውስጧ ያለነውን ዜጎቿን ፍላጎቶች፣ መብትና ጥቅም በሚያስከብር የህግ አግባብ የተዋቀረች ባለመሆኑ ሀገር የመመስረቱ ሂደት እስከዚህ ዘመን እንደቀጠለ ነው፡፡
አንዳንድ ምሁራን “አለቀለት የሚባል የዴሞክራሲ ግንባታና አለቀለት የሚባል የሀገር ግንባታ ሂደት የለም” ይላሉ፡፡ እንደኔ እንደኔ ግን ሁለት ነገሮች ተለይተው ቢታዩ መልካም ነው፡፡ ሀገር እና መንግስት፡፡ ሀገር ተገንብቶ የሚጠናቀቅ መሆኑ ይታየኛል፡፡ ሀገረ መንግስት ግን እንደ ወቅቱና እንደየዘመኑ እየዘመነ የሚሄድ ነው ብየ አስባለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ሁለቱም ተሰርተው አልተጠናቀቁም:: በተለይም የሀገሪቱ ግንባታ መጠናቀቅ ይገባዋል:: ሁልጊዜ በሱ ስንጨቃጨቅ መኖር የለብንም ባይ ነኝ::
በመሰረቱ የሀገር ግንባታ የትውልድን መስዋእትነት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ያለነው ያልተጠናቀቀ የሀገር ግንባታ ሂደት ጠርዝ ላይ ነው፡፡ ያለን አማራጭ ሁለት ነው፡፡ ወይ ሂደቱን ማጠናከር አሊያም ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ፡፡ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ኃላፊነትን አለመወጣት ብቻ ሳይሆን እልቂትን ማውረስ ነው፡፡ ሁከትና ንትርክን ማሸጋገር ነው፡፡ ሁለቱም አማራጮች በዚህ ዘመን ላለነው ሰዎች ውሳኔ የቀረቡ ናቸው፡፡ ወይ ደፍረን እንወስናቸዋለን አሊያም ፈርተን እናዳፍናቸዋለን፡፡ ደፍረን ከወሰንን መስዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ ፈርተን ካሸጋገርናቸው ባለፈው ሰሞን ከተከልነው ዛፍ ጋር በታሪክ ፊት ማፈሪያ አሻራችንን እናስቀምጣለን፡፡
ይህ ሂደት በዚህ ዘመን ባለነው ዜጎች በሰለጠነ አግባብ እንዲቋጭ ካልተደረገ ችግሩ ወደ ቀጣዩ ትውልድ መሸጋገሩ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ይህ ትውልድ ከቀዳሚዎቹ ትውልዶች ደካማና ጠንካራ ተግባራት ተገቢውን ግንዛቤና ትምህርት በመውሰድ አስፈላጊውን መስዋእትነት መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ይህ ትውልድ አስፈላጊውን መስዋእትነት በመክፈል የሀገር ምስረታውን ሂደት ካላሳረገው ሀገሪቱ በቀላሉ ባትፈርስም ህዝቡ ተጨማሪ የከፋ መስዋእትነት መክፈሉና ችግሩም ወደ ቀጣዩ ትውልድ መሸጋገሩ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ስለሆነም፤ የሀገር ግንባታው የተሳካ እንዲሆን ፖለቲከኞች የሚመኙትን ስልጣን ጭምር አሳልፈው በመስጠት መስዋእትነት መክፈል ይጠበቅባቸዋል:: ምሁራን በፖለቲከኞች እየታሰሩ፣ በአክቲቪስቶች እየተብጠለጠሉ ክብራቸውን አጥተውና ተዋርደው እውነቱን በመናገር፣ ሳይንሳዊ ምርምር በማድረግ ለሀገር የሚበጀውን ምክረ ሃሳብ በማቅረብና በመሟገት መስዋእትነት መክፈል ይጠበቅባቸዋል:: ባለ ሀብቶች ሀብት ንብረታቸው እየወደመ፣ ገንዘባቸው እየባከነና ኪሳራ እየደረሰባቸው ሂደቱን የመደገፍ መስዋእትነት መክፈል ይጠበቅባቸዋል:: አርሶ አደሩ ማሳው ላይ ያለ ሰብል እየወደመ፣ አርብቶ አደሩ እንስሳቱ እየተዘረፉ መስዋእትነት መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመንግስት ሰራተኛው፣ ወዛደሩ፣ ጡረተኛው፣ ቸርቻሪውና አገልግሎት ሰጪው… አጋጣሚዎች በሚፈጥሯቸው የሰላም እጦትና አለመረጋጋት ምክንያት ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን ገቢያቸውን እያጡመስዋእትነት መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተማሪዎች የመማር እድላቸውን፣ ሥራአጥ ወጣቶች ለስራ የፈረጠመ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን መስዋእትነት መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ብሔረሰቦች፣ ነገዶች፣ ጎሣዎችና ህዝቦች ለዘመናት ያጧቸውን መብትና ጥቅሞች ለሀገራቸው ህልውና ሲሉ አፍነው ይዘው መስዋእትነት መክፈል ይጠበቅባቸዋል:: በአጠቃላይ ይህ ወቅት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሴት ወንድ፣ ሽማግሌ ወጣት፣ የተማረ ያልተማረ፣ … ሳይለይ መስዋእትነት መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡
እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል አስባለሁ፡፡ ጥያቄው “የሀገር ምስረታው ሂደት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ሊመጣ ያልቻለው ለምንድነው?” የሚል ነው፡፡ መልሱን በአጭሩ “ለፖለቲከኞች ፋታ አለመስጠት” ብሎ ማስቀመት ይቻላል፡፡ ትንሽ ሰፋ አድርገን ብናየው መልካም ነው፡፡ ለመነሻ እንዲሆነን ባለፉት 100 ዓመታት የነበረውን ብቻ እንይ:: ከአፄ ምኒልክ ሞት በኋላ አልጋ ወራሽ የነበሩት ልጅ እያሱ ነበሩ፡፡ ወጣቱ ልጅ እያሱ በዘመናቸው ተራማጅ አስተሳሰብ ይዘው መጥተው እንደነበር የታሪክ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ልጅ እያሱ ከአፋሩም፣ ከኦሮሞውም፣ ከሱማሌውም፣… ጋር “የፖለቲካ ጋብቻ” በመመስረት ኢትዮጵያን በቤተ መንግስቱ ዙሪያ ለማስተሳሰር ያደረጉት ጥረት በወቅቱ በነበሩ “የሸዋ መኳንንት” በበጎነት አልታየም:: እንደ ፖሊስ ያሉ ዘመናዊ ተቋማትን የመመስረት ጅምራቸው አልተወደደም፡፡ ኋላቀር የሆነው ሌባን የማቆራኘት አሰራር እንዲቀር ማድረጋቸውም ግምት ውስጥ አልገባላቸውም፡፡ እናም ፋታ አጥተው ከሀገር ወደ ሀገር እየተሳደዱ በሽኩቻ ተወገዱ፡፡
የንግስት ዘውዲቱ ሞግዚት የነበሩት ተፈሪ መኮንን ተራማጅ ነበሩ፡፡ ሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ህገ መንግስት እንዲኖራት አደረጉ፡፡ ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል እንድትሆን በማድረግ ከዘመነኛ ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ ጥረት ሲያደርጉና ት/ቤቶችን ለማስፋፋት ደፋ ቀና ሲሉ “የካቶሊክ እምነትን ሊያስፋፋ ነው” ተብለው በመኳንንቱ ተወነጀሉ:: ይባስ ብሎ ጣሊያን ሀገሪቱን በመውረሯ ሁሉም ነገር በጅምር ቀረ፡፡ ከጣሊያን ወረራ በኋላ ተፈሪ መኮንን -“አፄ ኃ/ስላሴ” ተሰኝተው ንጉሰ ነገስት ሆነው ስለነበር ከተራማጅነት ወደ ወግ አጥባቂነት ተሸጋገሩ:: ስልጣናቸውን ለማደላደል ቅድሚያ ሰጡ::
በአፄ ኃ/ስላሴ የመጨረሻ የስልጣን ዘመን እነ እንዳልካቸው መኮንንና አክሊሉ ኃ/ወልድ “ፋታ ስጡን” በማለት ለዘመኑ የሚመጥን ህገ መንግስት በማርቀቅ ላይ እያሉ ወታደሩም፣ ተማሪውም፣ ታክሲ ነጂውም፣… “በሰላማዊ ሰልፍ” አጣደፋቸው:: አሁንም ሁሉም ነገር በጅምር ቀረ፡፡
ወጣቱ መኮንን መንግስቱ ኃ/ማሪያም ወደ ስልጣን ሲመጡ ሀገሪቱ ድብልቅልቅ ባለ ጩኸት ውስጥ ነበረች፡፡ ይህንን በተመለከተ ኮ/ል መንግስቱ፤ “የተማሪ ጩኸት ባዶ ነበር፡፡ ቤተ መንግስቱም ባዶ ነበር፡፡ ሰተት ብለን ገባን” ብለው እንደነበር ይነገራል:: ባዶ ቤተ መንግስት ውስጥ ሰተት ብለው የገቡትን ወታደሮች “ህዝባዊ መንግስት አሁኑኑ” እያልን ፋታ ነሳናቸው፡፡ በዚህ ሳንቆም ወታደሮቹ ስልጣን ይዘው 6 ወር ሳይሞላቸው፣ እነ ኢህአፓና ህወሓት በተጣደፈ ሁኔታ ጫካ ገቡ፡፡ ወታደሮቹም በጠመንጃ ምላሽ ሰጡ፡፡
ወጣቱ መለስ ዜናዊ በ1983 ስልጣን ጨበጡ:: ከገጠር የመጡ “ሽፍቶችን” አብረን እየሰራን “ከተሜ” ማድረግ ሲገባን፣ “በ17 መርፌ” እያልን ጠቀጠቅናቸው:: እነሱም በባለ 17 ዓይን የ“ታጋይ” ጫማ ረመረሙን፡፡ … በ2010 “ቲም ለማ” ቀዝቃዛ አብዮት አካሄደ፡፡ ዶ/ር ዓብይ አህመድ አሊ ኢህአዴግን ከውስጡ ፈንቅለው ስልጣን ጨበጡ፡፡ ፍልስፍናዬ “መደመር” ነው አሉ፡፡ እሳቸውንም እነሆ ፋታ ነስተናቸዋል!
የታሪክ ምሁራን እንደሚነግሩን ግለሰቦች ታሪክን የመቀየር አቅም አላቸው፡፡ ሬዲዮ፣ መኪና፣ ኤሌክትሪክ፣ ኮምፒዩተር፣… የተፈለሰፉት በግለሰቦች ነው፡፡ እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ዓለምን ለውጠዋል፡፡ በፖለቲካም ተመሳሳይ ህዝብ ጠቀም ለውጦችን ያመጡ ግለሰቦች አሉ፡፡ ቱርክን የለወጣት ሙስጠፋ ሀሰን አታቱርክ ነው፡፡ ቢስማክ ጀርመንን፣ ጋርባልዲ ጣሊያንን፣ ጆርጅ ዋሽንግተን አሜሪካንን፣ ማንዴላ ደቡብ አፍሪካን፣… ለውጠዋል ወይም እነዚህ አገሮች እንዲለወጡ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል::
ቅድመ አያቶቻችን ለእያሱ፣ አያቶቻችን ለአፄ ኃ/ስላሴ፣ ለእንዳልካቸውና ለአክሊሉ፣… የነፈጉትን ፋታ የመስጠት እድል እኛ ለዶ/ር ዓብይ ልንሰጣቸው ይገባል፡፡ እስቲ ትንሽ የሚሄዱበትን እንይ፡፡ ሁሉም ነገር በእጃችን ነው፡፡ ቄሮው ከህዝብ ጋር ነው፣ ፋኖው ከህዝብ ጋር ነው፣ ዘርማው ከህዝብ ጋር ነው፣ ኮበሌው ከህዝብ ጋር ነው…፡፡  ዶ/ር ዓብይ ከሐዲዱ እወጣለሁ ካሉ ያደርሰናል! ከፋታ ይልቅ ወደ ድንፋታ ያደላው የፖለቲካ ባህላችን መቀየር አለበት!
ፋታ የመስጠትንና የሀገር ግንባታን ጉዳይ እዚህ ላይ ቆም ላድርግና አንድ “ፋታ ያልሰጠነው” ወቅታዊ ጉዳይ ላንሳ፡፡ የደቡብ ክልልን አደረጃጀት በተመለከተ ሀገሪቷ አሏት ከተባሉ ምሁራን ውስጥ የተወሰኑት ኃላፊነቱን ወስደው አጠኑ፡፡ ውጤቱንም አግባብ ባለው አደረጃጀት ሰንደው ለሚመለከተው አካል አቀረቡ፡፡ ሌሎች ምሁራንም ሃሳብ እንዲሰጡበት ተደረገ፡፡ ጥናት ሳይንስ ነው፡፡ ሳይንስ ደግሞ “ብሔር” የለውም፣ አድሎ አያደርግም፡፡ መረጃው የተሰበሰበው ከህዝብ ነው፡፡ ከህዝብ የተገኘው መረጃ በሳይንሳዊ መንገድ ሲተነተን ለእከሌ ለእንቶኔ ሳይል የምርምሩን ውጤት ይነግረናል፡፡ አለቀ! - የሆነው ይሄ ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ አሁን ያሉት ዞኖች አስተዳደሮች ክልል ለመሆን ጥያቄ እያቀረቡም፤ እየወሰኑም ያሉት የዞን ምክር ቤት አባላት ናቸው፡፡ የዞን ምክር ቤት አባላት ደግሞ “ነፃ ባልሆነ ምርጫ፣ ብቻቸውን ተወዳድረው ያሸነፉ ካድሬዎች” ናቸው:: እነዚህ ካድሬዎች ትክክለኛ የህዝብ ወኪሎች አለመሆናቸውን ጭምር ነው ጥናቱ ያረጋገጠው:: ምክንያቱም የዞን ምክር ቤት አባላት ተሰብስበው “ክልል እንሁን” የሚል ውሳኔ አሳለፉ፡፡ ጥናቱን ያደረጉት ምሁራን በቀጥታ ህዝቡ ጋ ሄደው “ክልል መሆን ትፈልጋለህ ወይ?” ብለው ሲጠይቁት፤ እንዲህ ዓይነት ፍላጎት እንደሌለው ነገራቸው፡፡ ጥናቱን ያደረጉት ምሁራን ይህንን ከሰሙ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎችን ሰበሰቡና “ፍትህ ከሰፋ፣ ሙስና ከቀነሰ፣ የፖለቲካ ስልጣን አንድ ስፍራ ካልተማከለ፣ የልማት ተጠቃሚነት ከተረጋገጠ፣…” ህዝቡ አንድ ላይ መሆንን እንደሚመርጥ አመላከቱ፡፡
እኔ እንደተገነዘብኩት የምሁራኑ የጥናት ውጤት የነገረን ነገር በሕዝብና በፖለቲከኞቹ መካከል ሰፊ ልዩነት ያለ መሆኑንም ነው፡፡ ፖለቲከኞቹ “አንዴ የክልልነት ጥያቄ ስላቀረብን ክልል ካልሆንን ሞተን እንገኛለን” ከሚሉ የምሁራኑን ምክረ ሃሳብ ቢቀበሉ ይሻላቸዋል፡፡ (ቀደም ሲል “ፖለቲከኞች የሚመኙትን ስልጣን ጭምር አሳልፈው በመስጠት መስዋእትነት መክፈል ይጠበቅባቸዋል” ያልኩት ይህንን ነው) ዛሬ የዞን ፖለቲከኞች ፍላጎታቸውን በህዝቡ ላይ መጫን ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ፣ የክልል ፕሬዝዳንት ተብለው፣ ለራሳቸው ቪ-8 መኪና ገዝተው ዝም ሲሉት ህዝቡ“ወደ ነበርንበት እንመለስ” ብሎ እነሱንም ውሳኔያቸውንም እንደሚገለብጠው ሊገነዘቡት ይገባል፡፡
በሰለጠነው ዓለም አንድ ሰው ፖለቲከኛ የሚሆነው ህዝብን ለማገልገል ነው፡፡ በአፍሪካ ስልጣን የሚያዘው በህዝብ ለመገልገል ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በኛም ሀገር እየተስተዋለ ነው፡፡ አፍሪካ መራመድ ያልቻለቺው ብዙሃን ድምፅ አልባዎች አፋቸውን እንዲዘጉ ተደርገው፣ ጥቂት ጯሂዎች መድረኩን በመያዛቸው ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ዛሬ በእኛም ሀገር እየታዬ ነው፡፡
ፖለቲከኞቻችን ከታሪክ የተማሩ አይመስሉም:: ዛሬም ህዝብን ለመጨረስና ለማጫረስ ተግተው እየሰሩ መሆኑን በሀዘን ስሜት ተውጠን እያስተዋልን ነው፡፡ አንድ የታሪክ ምሁር እንዳሉት “የጣሊያን ወራሪ ኃይል ከፈጀው ይልቅ ጣሊያን ከሄደ በኋላ የመጡ ፖለቲከኞች የፈጁትና ያስፈጁት ህዝብ ቁጥር ስፍር የለውም”፡፡ፖለቲከኞቻችን እስካሁን በፈሰሰው ደም የረኩ አይመስሉም፡፡ አሁንም በህዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ የህዝብ ደም ለማፍሰስ ተራራ እየቧጠጡ ነው፡፡
የአስተሳሰብ አብዮት ባልተደረገበት ሁኔታ የልማት፣ የዴሞክራሲና የፖለቲካ አብዮታችን የተሳካ ሊሆን አይችልም፡፡ (ምን ዓይነት አብዮት ያስፈልገናል በሚለው ላይ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ) ዘመናዊ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ያንን መሸከም የሚችል ህዝብ ሊኖር ይገባል፡፡ ይህንን በመገንባቱ ሂደት ምሁራን የላቀ ሚና እንዳላቸው ይታመናል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ምሁራንና ህዝቡ ሊናበቡና ሊደማመጡ ይገባል፡፡
በኢትዮጵያ በትግልና በመስዋእትነት የተገኙ አጋጣሚዎችን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ደጋግሞ ታይቷል፡፡ አሁንም የታሪክ መታጠፊያ ላይ ደርሰናል፡፡ ሌላ እድል እጃችን ላይ አለ፡፡ መደማመጥ ከቻልን፣ በሰከነ መንፈስ ማሰብ ከቻልን፣ “ለሀገር አሳቢ” ፖለቲከኞቻችን እድል ከሰጠናቸው የሀገር ምስረታችንን ሂደት በሰለጠነ አግባብ ወደተሻለ ደረጃማሸጋገር እንችላለን፡፡ ፈጣሪ ሁልጊዜ እድል ሊሰጠን እንደማይችልም መገንዘብ መልካም ነው፡፡


Read 10181 times