Saturday, 10 August 2019 00:00

አዲስ ሐሳብ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ስፖርት ስርነቀል ማሻሻያ!!

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)


                        የጥናት አቅራቢው ደብዳቤ ለዝግጅት ክፍሉ እንደመግቢያ
                                …በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ1ኛው እስከ 12ኛው የአፍሪካ የአግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ድረስ በስፖርቱ ትልቅ ስምና ዝና ነበራት:: ነገር ግን ከዚያ ወርቃማ ዘመን በኋላ እስከ አሁን የእግር ኳስ ስፖርት ደረጃችን መቀነስ ከዓመት ወደ ዓመት ቀጥሏል፡፡ በዚህም ምክንያት አሁንም ከአፍሪካና ከዓለም አቀፍ ደረጃ ጋር በስፖርቱ ልንመጣጠን አልቻልንም፡፡ በእነዚህ የደረጃ መውረድ ዓመታት ይህን አሳሳቢ ሁኔታ ለማስተካከል የመስኩ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች የማያቋርጥ ጥቆማ፣ ግምገማ፣ ተቃውሞና ጥረት ቢደረግም አሁንም በስፖርቱ የሚያረካ ደረጃ መድረስ አልቻልንም፡፡ የችግሩ መሰረታዊ ምንጭና ምክንያት ምን ይሆን?.... በሚል አቶ ሞላልኝ ለአዲስ አድማስ የስፖርት አምድ ደብዳቤያቸውን አድርሰዋል፡፡ “አዲስ ሀሳብ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ስፖርት ሥርነቀል ማሻሻያ” በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ   ከመግቢያው አንስቶ የተለያያዩ ርእሶችን ዳስሰዋል፡፡ ወርቃማው የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ስፖርት ዘመንን መነሻ በማድረግ ይህ ወርቃማ የእግር ኳስ ስፖርት አካሄድ እንዴት ተኮላሸ? የሚለውን ጥያቄ አንስተዋል:: ከዚያም እግር ኳሱን ለማሻሻል የተወሰዱ የማስተካከያና የመፍትሔ እርምጃዎች  ከዳሰሱ በኋላ አዳዲስ የመፍትሔ ሀሳቦችን ሲያነሱ ዋናው መፍትሔ፤ የህዝብ/የግል/ክለቦችን መመስረት እና ማወዳደር የግድ መሆኑን ጠቅሰው የዋናው መፍትሔ መሰረት ቋሚ የታዳጊዎች ውድድር በሀገሪቱ ዙሪያ ማቀጣጠል እንደሆነ በመጠቆም ማጠቃላያቸውን አቅርበዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
         በሞላልኝ ኦርማ (ጥናታዊ ጽሁፍ - ሐምሌ 2011)

         
           መግቢያ
በአገራችን የእግር ኳስ ስፖርት በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤት በማጣታችን ተቃውሞ፣ ትችት፣ ወቀሳ፣ ጥቆማ እንዲሁም ማስተካከያ እርምጃዎች መወሰድ ከጀመሩ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ከመዳከር ውጪ አልፎ አልፎ ብቅ ጥልቅ ብልጭ ድርግም ከሚለው አመርቂ ውጤት በቀር ምንም ተከታታይነት ያለው አንጀት የሚያርስ ነገር አልተገኘም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በስፖርቱ ዙሪያ እንዲህ የምንጨነቅበትና የምንቆረቆርበት በቂ ምክንያት አለን፡፡ እንዲያውም ባንቆጭና ባንንገበገብ ይበልጥ አሳፋሪ በሆነብን ነበር፡፡ ይሄን የምንልበት ምክንያት በአፍሪካ ደረጃ ለብዙ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳዎች ግንባር ቀደም እንደሆንን በእግር ኳስ ውድድር ታሪክም የአንበሳ ሚና አለን፡፡ የሀገር ውስጥ ክለቦችን በማቋቋም እንዲሁም በውድድር ከአፍሪካ አልፎ ከአውሮፓ ክለቦች ጋር የተስተካከለ አቅም የነበረን ነን/በንጉሱ ዘመን/፡፡
በአፍሪካ ደረጃም አሁን በስፖርቱ ውጤት ጣሪያ የነኩት የምዕራብና የሰሜን አፍሪካ ሀገሮች ዳዴ ሲሉ እኛ በፋና ወጊነት እንታወቅ ነበር፡፡ ከሁሉ የሚያስቆጨው ደግሞ ከእኛ እኩል ታሪክ ያላት ግብጽ እስከአሁን ደረጃዋን ጠብቃ የመሪነት ክብሯን አስጠብቃ በኩራት በስፖርቱ ስትምነሸነሽ እኛ በፊት የእግር ኳስ ዳዴ ሲሉ ያየናቸው ሀገሮች ጭራን መያዝ እንኳን አቅቶን አሁንም የእነርሱን ውጤትና ደስታ ናፋቂ ሆነን እንገኛለን፡፡
ለመሆኑ ይህ ዕንቆቅልሽ ክስተት በእግር ኳሳችን እንዴት ሊከሰት ቻለ? ምኑ ጋር ነው ችግሩ ? ምን ማድረግ ያዋጣል? በሚለው ባልሳሳት ከሰላሳ ዓመታት ላላነሰ ባለሙያዎቻችን ፣አሰልጣኞቻችን፣ ተጫዋቾቻችን፣ የውጭ ሰዎች ሳይቀሩ የታያቸውን፣ የመሰላቸውን ብለዋል፡፡ እኔም ይህን መስማት የጀመርኩትና የተቆረቆርኩት ከደምሴ ዳምጤ ዕንባ ቀረሽ ቃና ከነበረው ድምፀት አስተያየትና ሙግት ጀምሮ ነው፡፡ ለብዙ ዓመታት የሚለውን ሁሉ ክፍተት አንጠፍጥፎ ብሎ ምንም ፋይዳ ሳይመለከት ቀረ፡፡ እና በተለያዩ ዓመታት በዚህ ርዕሰ ጉዳይ አሁን የተነሱት ጋዜጠኞቻችን ሳይቀር ጥልቅና ሰፋ ያለ ሙያዊ አስተያየት ሲሰጡ ግን ነገሩ አልሳካ ሲል ያማል፡፡ ምን ይሻላል? አረ ምን ይሻላል? እኔ የተለየ ሀሳብ ባነሳ ተሰሚነት አገኝ ይሆን ?ማን ይሰማኛል? በሚል ለብዙ ጊዜ ሳብሰለሰል ቆይቼ አሁን አሁን ትንሽ ከአኔ ሀሳብ ጋር የሚቆራኝ አካሔድ መነሳሳት ስለጀመረ እኔም ሀሳቤን በዝርዝር ለማቅረብ ተነሳሳሁ:: ቀጥታ ወደ መፍትሔው ከመግባቴ በፊት እንዴት ለዚህ አሳሳቢ ሁኔታ እንደተዳረግን ታሪካዊ ምልከታ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
ወርቃማው የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ስፖርት ዘመን
የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ አራዳ እግር ኳስ ክለብ ከተመሰረተ ጀምሮ ይሔን ፈር በመከተል በሀገራችን ብዙ የህዝብ /የግል/ ክለቦች ተመስርተዋል:: ለዚህ በንጉሱ ዘመን የኢ/እ/ፌደሬሽን ለውድድር ሲያወጣቸው የነበሩ ኮሚኒኬዎችን ማመሳከር ይቻላል፡፡
የዚያኔው ህብረተሰባችን ምንም እንኳን በትምህርቱና በስልጠናው የገፋ ባይሆንም ከስሜትና ፍቅር በመነሳት በየአካባቢው የራሱን ህዝባዊ ክለቦች በማቋቋም በገንዘብ አቅም በራሱ በመደራጀት፣ተጫዎቾችን መልምሎ በማሰልጠን፣ አሰልጣኞችን ከምንም ተነስቶ በማደራጀት እጅግ በጣም ጣፋጭ እስፖርቱን ለማሻሻል የሚያበቃ በፍቅር ለማሊያውና ለክለቡ ያለውን ሁሉ በመስጠት የሚፎካከር የእግር ኳስ ትውልድ ፈጥረው ነበር፡፡ ውጤቱም ሁሉም እንደሚያውቀው ሶስት የአፍሪካ ዋንጫን አዘጋጅቶ አንዱ በማንሳት ከጌታቸው አበበ እና መንግስቱ ወርቁ አስከ ለማ ክብረትና ንጉሴ ገብሬ/1954-1974/ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ሊረሱ የማይችሉ ብርቅ ተጫዎቾችን አፍርተው ነበር፡፡
ያን ትውልድ በዋናነት ለውጤት ሲያበቃው የነበረው ልክ አሁን በላቲኑና በምዕራቡ ዓለም እንደሚታወቀው ዓይነት አነሳስ ስለነበረው ነው:: አንደኛ የራሱ የቅርብ እሱነቱን የሚወክሉ ክለቦች ተመስርተውለት ነበር፡፡ ለምሳሌ እንደ አካባቢ /ሰፈር/ እና ከተማ ተኰር የሆኑ ማለት በመንግስት መዋቅር ወይም በተቋማትና በድርጅቶች ላይ ያልተመሰረቱ ግን የራሱ የህዝብ ባለቤትነት የነበራቸው ማለት ነው፡፡ ከነዚህም የተነሳ ህዝቡ ከሰፈሩ ከቤተሰቡና ከልጅነቱ ጀምሮ የሚቀረጽበት በእኔነትና በባለቤትነት ስሜቱ ለክለቡ በችሎታውም ሆነ በአለው ነገር የቻለውን ለመስጠትና ውጤታማ ለማድረግ ያለውን አቅም ሁሉ አሟጦ የመጠቀም ፍቅርና ፍላጐት ነበረው፡፡
ይህ ተጫዋቹ በውድድር  ወቅት ላለመሸነፍ ከሚያሳየው ተጋድሎ ፣ እንዲሁም ደጋፊው ክለቡ ከሌላ ተፎካካሪ ክለብ እንዳያንስ በገንዘብ አቅም ደረጃ ያለውን ሁሉ በእልህ በማዋጣት ለማጠናከር መነሳሳትን መፍጠሩ ከሌላው መዋቅር እና ተቋም ተኮር ክለብ አመሰራረት አካሄድ የተሻለ ለመሆኑ መካድ አይቻልም፡፡ ሰው በተፈጥሮው የግሉ ወይም የራሱ የሆነን ነገር ለማበጀት ያለውን አቅም ሁሉ አሟጦ ይጠቀማል፡፡ የጋራ በሆነ ነገር ላይ ያለውን አቅም ሁሉ ለማፍሰሰ ያን ያህል ፍላጐቱ ደካማ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ተመሳሳይ ተነሳሽነት ስለማይኖረውና የዚያኑ ያህል ጉተታ ስለማያጣው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተፈጥሮአዊ ስለሆነ በምንም ሲስተምና ስልጠና ማስተካከል አይቻልም፡፡ ለህዝቡ የራሱ የሆነውን ለራሱ ትቶ በራሱ አካሔድ ላቅ ወዳአለ ደረጃ እንዲደርስ ዕድልና አመራርን ከመስጠትና ወጣ ብሎ ድጋፍ ከማድረግ በቀር፡፡
በእርግጥ በዚያን ወቅት የተቋማት ክለቦች አልነበሩም ማለት ባይቻልም ውስን ነበሩ:: የሰራዊቱ ክለቦችም ነበሩ፡፡ ነገር ግን የህዝባዊ ክለቦች ተጽዕኖ ፈጣሪነት የጐላ ነበር፡፡ እና ያኔ ፉክክሮች ሁሉ በፍፁም የእኔነት ስሜት እንዲካሄዱ ይህ የህዝባዊ ክለቦች ስሜት መሰረት ጥሎ ስለነበር ሳይታሰብ የእግር ኳሱን ዕድገት አፋጥኖታል፡፡ ክለቦች ውጤታማ ለመሆን ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ የመግባታቸው ሚስጥር ተጫዋቾችና ደጋፊዎቻቸው ክለቦቻቸውን እንደራሳቸው የግል ንብረት ስምና እና ዝና ይቆጥሯቸው ስለነበረ ነው፡፡ ለዚህ ነው የያኔውን የእግር ኳስ ደረጃችንን እስከ አሁን የምንናፍቀውና የምንጓጓለት፣ ልንረሳውም የማንችለው ታሪክ የሆነው፡፡
ይህ ወርቃማ አነሳሳችን እንዴት ተኮላሸ?
ለዚህ ውድቀት በእኔ ዕይታ የመጀመሪያው ምክንያት ሊሆን የሚችለው ሀገራችን በሶሻሊስት ስርዓት ርዕዮት በተመራችበት ወቅት ነበር፡፡ ይህ ስርዓት የግል ንብረትንና ኢኮኖሚን ስለማያበረታታ በመሆኑም የህዝቡ የግል ንብረት የነበሩትን የኢትዮጵያ ህዝባዊ ክለቦች እንዲፈርሱ ወሰነ፡፡ ለምሳሌ በራሪ ኮከብ፣አንድነትንና የአዲስ ከተማ እግር ኳስ ክለቦችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ስለሆነም እንደዚያ ሲንቦገቦግ የነበረው የሀገራችን እግር ኳስ ውጤት ደረጃና ጥንካሬ ላይ ውሀ ተቸለሰበት፡፡ ቢያንስ ከ1940-1970 ዓ.ም ኢትዮጽያ ስትከተለው የነበረው ተደራጅታበትና ተንሰራፍታበት የነበረው የእግር ኳስ ውጤቷንና ታሪኪን ገንብታበት የነበረው የግል ህዝባዊ ክለቦች ሁሉ ፈርሰው አፈር ድሜ እንዲበሉ ተደረገ/1970 ዓ.ም/
ከዚያ በኋላ ለጥቂት ጊዜ የቀድሞው አሻራ አልለቅ ብሎ የትግል ፍሬን የመሰለ አስፈሪ ቡድን ተከስቶ ነበር፡፡ የህዝቡ ሳይሆን የድርጅት ክለብ በመሆኑም እሱም ዕድሜው በአጭር ተቀጨ፡፡ በመሆኑም ከዚያን ወቅት ጀምሮ የሀገራችን እግር ኳስ በውጤታማነት ሊዘልቅ አልቻለም፡፡ መሰረቱ ስለተናደ ቀስ በቀስ መዳከሙ ተንሰራፍቶ ብርቅ ብርቅ እግር ኳስ ተጫዋቾችን የሚፀንሱ ምንጮች ሁሉ ደርቀው/ህዝባዊ ክለቦች/ የሀገሬ እግር ኳስ በውጤት አልባነትና በብርቅዬ ተጫዋቾች በብዛት መትረፈረፍ ዕጦት ድርቅ ተመታ፡፡ ከዚያ በኋላ የነበረውን ጩኸት ከደምሴ ዳምጤ ቦኋላ የመጡ እውነተኛና ብቃት ያላቸው የስፖርቱ ጋዜጠኞች ስለሚያውቁት ለእነርሱ እተወዋለሁ፡፡
በእርግጥ የሶሻሊስቱ ስርዓት በራሱአካሄድ እግር ኳሱን በቀበሌ እና በከፍተኛ መዋቅር ደረጃ ሊያስቀጥለው ሞክሮ ነበር፡፡ ይህም መጀመሪያ ጥሩ ይመስል ነበር፣ያለፈው የህዝባዊ ክለቦች ውስጥየነበሩ ቅሪት ሆነው ስለነበር በተጫዋችነትም በአሰልጣኝነትም የቀበሌንና የከፍተኛን ውድድር መጀመሪያ ዓመታት ላይ አደማምቀውት ነበር፡፡ በኃላ ግን እነዚህ በግል ባለቤትነት ሳይሆን በወል ባለቤትነት የተመሰረቱ ቡድኖች ባለቤት አልባ እየሆኑ መጡ፡፡ እንደራሱ የሚቆጥራቸው ባለቤት ስለሌላቸው በውድድር ፕሮግራም ውጤት ወቅት የሚገነቡ በኋላ ውድድሩ ሲያልቅ ክረምት ላይ የሚፈርሱ ሆኑ፡፡ ተጫዋቾችን ባለቤት አልባና ዓላማ ቢስ አድርገው ለዲስፕሊን እንዳይገዙ ፈትተው ለቀቋቸው፡፡
የግል ህዝባዊ ክለቦች ተጫዋቾች ስላልሆኑ ቁጥጥሩ በላላ የቡድን አገነባብ አካሄድ ውስጥ ገቡ:: ውድድሩ ሲያልቅ ጠያቂ የሌላቸው እንደፈለጉ መሆኑ የሚችሉ አደረጋቸው፡፡ በአማተሪዝም ስም ፕሮፌሽናሊዝም ስለተዳከመ የሁሉም ትጥቅ ተፈታ:: በፊት ግን ቢያንስ በክለባቸው ተፎካካሪ ለመሆንና ለክለባቸው ፍቅር ሲሉ እንደልብ ከመሆን ይቆጠቡ ነበር፡፡
በውድድሮች ወቅትም ለስፖርቱ  ልምዱም ዕውቀቱም የሌላቸው ባለስልጣኖች እና ኃላፊዎች ያለሙያቸው ጣልቃ ይገቡ ስለነበረ ስፖርቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመውደቅ ስበት ውስጥ ገባ፡፡ ይህ የሳሳ አያያዝ በኋላ አልቀረለትም ጠንካራ መሰረት ላይ ስላልተገነባ የቀበሌ ቡድኖች  መፈራረስ ጀመሩ:: ጥሩ ልምድና ዕውቀት ያላቸው አሰልጣኞችም ሆነ ተጫዋቾች በዕድሜም ይሁን በሌላ ከተሳትፎ ሲገለሉ እነሱን በብቃት የሚተካ የቡድን አገነባብ ስላልነበረ በየአካባቢው ያለውን ትውልድ በጥሩየእግር ኳስ ስሜትና ችሎታ የሚገነባ ተተኪ እየጠፋ መጣ፡፡
ለህዝቡ በየሰፈሩና በየመንደሩ ባለቤት ሆኖ ይህን ስፖርት የሚያስቀጥልለት ወገን በመጥፋቱ እንደሚታወቀው ወጣቱ ባብዛኛው የራሱን ማንነት መልክና ቅርጽ በስፖርቱ ይዞ እንደመቅረጽ በሌሎች ተጽዕኖዎች መውደቅ ጀመረ፡፡ የቀበሌ ቡድኖች ውድድርም ከነአካቴው ቀርቶ ህዝብ ከትላልቅ የስቴዲየም ውድድሮች ውጪ በቅርቡ በእሱነቱ ደረጃ የሚወክለውና በስፖርቱ ተፎካክሮ የሚያረካው ቡድንም ሆነ ስፖርተኛ አጥቶ የበይ ተመልካች ሆኖ ቀረ/ምንም ማጋነን የሌለበት/፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያ በእግር ኳስ ተመልካች እና አፍቃሪ በስሜትም በቁጥርምበፍቅርም ስፖርቱ ከፍተኛ ደረጃ እንደደረሰባቸው ሀገሮች ነው:: ግን የሚያመረቃ የኳስ ጨዋታ ጥበብና ችሎታ እንዲሁም ውጤት ለማግኘትና ለማየት ያልታደለ ግን በዚህ ሁሉ ጥማት አሁንም ለስፖርቱ ፍቅሩንና ትኩረቱን  ያልነፈገ፣ ግን እርካታውን ከራሱ ልጆች ሳይሆን ከሌሎች የሚቋደስ ሆነ፡፡ ይህ ተመልካች በትክክለኛ አሳማኝ ብቃትና ችሎታ የሀገሩ ቡድንም ሆነ ክለብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤት አምጥቶለት የሚደሰተውን ደስታና የሚገልፀውን ስሜት ለማየት እንበቃ ይሆን? በኋላ መፍትሔ ብለን የተከተልውን አካሄድ ታዳጊዎችን በፕሮጀክት አሰባስቦ ማስልጠን ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ዓለሙ ሁሉ የሚከተለው አካሄድ ነው፡፡ እኛ ጋ ግን ውጤቱ አሁንም ያቀድነው ደረጃ ላይ አላደረስንም፡፡
ይህን አካሄድ መከተል ከጀመረን ብዙ ዓመታት ቢቆጥሩም አሁንም ከውጤት አልባነት የተነሳ ትችቱ፣ ቅሬታው፣ ተቃውሞው አልለቀቀንም:: ማለት በአፍሪካና በዓለም ደረጃ እንድ እርምጃ እንኳን እንድንራመድ አላገዘንም፡፡ በነገራችን ላይ የታዳጊዎች በየስፖርት ዘርፉ በፕሮጀክት ታቅፎና አካዳሚ ገብቶ መሰልጠን የሰለጠነው ዓለም ያመነበትና ውጤታማ የሆነበት አካሄድ ስለሆነ እኔ ምንም ቅሬታና ተቃውሞ የለኝም፡፡
ነገር ግን እኛ ጋ ለምንድን ነው በአሰብነው ልክ ያላሳኩልን? ለምን ዓይነ ግቡ የሆኑ ክለቦችና ብሔራዊ ቡድን የመመስረት ደረጃ ላይ አላደረሱንም? ልጆቻችን ተፈጥሮአዊ ችሎታና ጥበባዊ ብቃትን አልተካኑም? አሰለጣጠናችንን በአኛ ዓውድ አላደረግነውም ወይስ ይህ አካሄድ ስኬታማ እንዳደረጋቸው የላቲንና የአውሮፓ ሀገሮች በግልና በህዝባዊ ክለብ ላይ ስላልተመሰረቱ ና በእኔነት ስሜት እንዳይጫወቱ ከፍተኛውን የሞራልና ያለመሸነፍ ስነ ልቦና አላቀዳጃቸውም?
የተወሰዱ የማስተካከያና የመፍትሔ እርምጃዎች
በዚህ ግራ አጋቢ ወቅት ብዙ የስፖርት ባለሙያዎች የታዳጊዎች ፕሮጀክትና ስልጠና ላይ ለማተኰር ተገደዱ፡፡ በእርግጥ ይህ አሁንም ዓለሙ ሁሉ የሚያምንበትና የሚከተለው አካሄድ ነው::
በእርግጥ የኢኮኖሚ አቅም የስልጠና ዕውቀትና ልምድ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ፍላጐት በእኛና በእነርሱ መካከል ውጤት እንዳናመጣበት ለልዩነት ምክንያት ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ግን እነሱ የመጀመሪያውን ግዴታ ተወጥተውታል:: እነዚህ ታዳጊዎች በእኔነት የክለቡ ፍቅር ስሜት እንዲቀረፁ አድርገዋል፡፡ ሥነልቦናቸው ላይ መስራት ብቻ ሳይሆን እነርሱም እንደዚያው ሆነው ተገኝተዋል:: የግል ህዝባዊ ክለቦች ናቸው:: የማሸነፍ የመግነን ፍላጎትና ስሜቱ ቀደም ብሎ ተገንብቶ ይህን ለማሳካት ስልጠናውንና ክትትሉ ይከተላል:: የመጀመሪያው ግን ክለቡን የእኔ የግሌ ነው የሚያስብል ስነ ልቦና መገንባቱ ነው ወሳኙ:: እሱ ነው ውጤታማ ታዋቂ እንዲሁም ጥበበኛ ተጫዋች ለመሆን የፍላጐቱ መሰረቱ፡፡ ያም ሆኖ በአኛ ሀገር የታዳጊዎች ፕሮጀክትም ሆነ ስልጠና ዘለቄታዊነቱ አጠያያቂ ነው:: የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ከፋሲሊቲና ከገንዘብ ዕጥረት ባሻገር ሰልጣኞች ስልጠናውን ለዘለቄታው የሚጠቀሙበት ሁኔታ ያለመመቻቸት ማለት ተግባራዊነቱን የሚያስቀጥልለት ሁኔታ አለመቀናጀቱ ነው፡፡
እንደአቅማቸው በየግላቸው የሚሳተፉበት ሰፊ የውድድር መስክና የክለብ አደረጃጀት የለም፡፡ የአካዳሚዎች አካሄድ ጥሩ ሆኖ ሳለ አሁንም የማነሳው ጥያቄ የሌላው ዓለም የአካዳሚ አመሰራረትና የእኛ ልዩነት ምንድን ነውእነርሱጋ የመንግስት አካዳሚ በብቸኝነት የለም ሁሉም የግል ናቸው፡፡ በአርግጥ የመንግስት አካዳሚ መኖሩ ጥሩም ተገቢም ነው:: ቢያንስ ቢያንስ ለሁሉም መሰረትና ለሀገርም ተወካይ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእርሱ በፊት ግን የግል ክለቦች አካዳሚ ይቀድማል፡፡ ለምን በራስ ማንነትና ባለቤትነት ላይ ስለሚመሰረቱ፣ የአካዳሚውም ሰልጣኝ ታዳጊዎች በግልም ሆነ በህብረት በዚህ ስሜት ስለሚገነቡ፣ከታች ጀምሮ ጠንካራ የሥነ ልቦና አንድነትና የችሎታ ጥምረት ይዘው ስለሚመጡ፣ውድድር ላይ ለማሸነፍ ዋናው መሰረቱ በችሎታ የታገዘ ጽኑ ፍላጎትና ተነሳሽነት በመሆኑ ከነዚህ ግብዓቶች የተነሳ ውጤት ለማምጣት የሚመክታቸው አይኖርም፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሁሉ በፊት የ” እኔ” ማለት የራስ ባለቤትነት መንፈስና ስሜት ወሳኝ ነው ማለት ነው፡፡ የእኛ ሀገር እግር ኳስ ውጤት ማጣት ዋነኛ ምክንያት ይህ ነው፡፡
ተጫዋቾች በአብዛኛው ቡድናቸው ላይ በግልና በራስ ባለቤትነት ስሜት ላይ ተመስርተው አይመጡም፡፡ ስለዚህ ይህ ውጤታማ ለመሆን ያላቸውን ነገር ሁሉ የመጠቀም ተነሽነታቸው ላይ ተጽዕኖ ያመጣል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የእግር ኳስ አካዳሚ ባልተስፋፋባቸው ዘመን ተነስተው ዓለምን ያስገረሙ ተጫዋቾች እንደ ጋራንቻ፣ፔሌ፣አዞፒዮ ፑስካሽ የቶታል ፉትቦል ፈላስፋውጆሀን ክሩፍ--- ሁሉም መሰረታቸው በግል ክለቦች ማንነት ላይ መኮትኮታቸው ነው፡፡ ያ የግል ባለቤትነት መንፈስ ያላቸውን ተስጥኦ ሁሉ አውጥተው እንዲጠቀሙ ረድቷቸዋል፡፡ ጥብቅ ክትትሉም ዲስፒሊንድ እዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ስለዚህ የሚቀድመው ተፈጥሮአዊ ችሎታና ስሜት ከዚያ ጠንካራ የግል እና የእኔነት ስሜት እንዲኖር በግል ክለቦች ውስጥ መታቀፍ ነው፡፡ ይህ የዳበረ ማንነት በብሔራዊና በሀገር ደረጃሲጎለብት ማንም የማይበግረውን ማንነት ይዞ ብቅ ይላል፡፡ ምክንያቱም በውድድሮች ሁሉ የግል ክለባቸውን ክብር ለማስጠበቅበሚያደርጉት ጥረት በብዙ የላቀ ችሎታ በሚጠይቁ ውድድሮች ሰለሚታሹበችሎታቸውና በልምዳቸው የላቀ ደረጃ ላይ ስለሚደርሱ ነው፡፡
(ይቀጥላል)


Read 4359 times