Print this page
Saturday, 10 August 2019 00:00

የአዲስ አበባ ሆቴሎች፣ በውድነት ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆነዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

የዋጋ ዝርዝር የሚያጠናው የእንግሊዝ ኩባንያ፣ የሆቴሎቹን ጥራት ለመፈተሽ ባለሙያዎችን እልካለሁ ብሏል

           የአዲስ አበባ ሆቴሎች የመኝታ ክፍል ዋጋ በአማካይ 164 ዶላር (4900 ብር) እንደሆንና  ከሌሎች የአፍሪካ አገራት እንደሚበልጥ የሆቴሎችን ዋጋ የሚያጠናው ከተር ኩባንያ ሀሙስ ባወጣው ሪፖርት ገለፀ፡፡
ኩባንያው እስከ ሀምሌ 2011 ዓ.ም ለ12 ወራት  ባደረገው ጥናት፣ አለማቀፍ ደረጃ ያላቸው የአፍሪካ ሆቴሎችን በዋጋ  አነፃጽሯል፡፡ በቀን ለአንድ መኝታ ክፍል በአማካይ 164 ዶላር ከሚከፈልባቸው የአዲስ አበባ ሆቴሎች በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጡት በጋና የአክራ ሆቴሎች ናቸው በ160 ዶላር፡፡ ሶስተኛ ደረጃ የያዙት በናይጄሪያ የሌጎስ ሆቴሎች 133 ዶላር ይጠይቃሉ፡፡
አዲስ አበባ ከሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ጋር ስትነፃፀር፣ አለማቀፋዊነቷ እየጨመረ እንደሆነ ሪፖርቱ ሲያስረዳ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት አንድ ምክንያት እንደሆነም ይጠቅሳል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአለማቀፍ ደረጃ ተቀባይነቱ እየጨመረ መምጣቱም ለአዲስ አበባ ጠቅሟል፡፡ በዚያ ላይ፣ የአፍሪካ ህብረትና የዩኤን ተቋማትን ያቀፈች ከተማ በመሆኗ፣ አለማቀፍ የዲፕሎማሲ መናኸሪያነቷ እየደራ ነው ብሏል - አጥኚው ኩባንያ፡፡
በአዲስ አበባ 22 ሆቴሎች በአዲስ እቅድና ግንባታ ወደ ስራ ለመግባት ተፍተፍ እያሉ በመሆናቸው፣ 4,800 የመኝታ ክፍሎች ለአገልግሎት ሲበቁ፣ የከተማዋ ተፈላጊነት ይጨምራል ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ የሆቴሎች ተፈላጊነትና ዋጋ በየአመቱ እንደሚጨምር በጥናት ቢረጋገጥም፣ የአገልግሎት ጥራታቸውስ እንዴት ነው የሚለው ጥያቄ ገና መጠናት እንዳለበት ኩባንያው ጠቅሷል፡፡ የሆቴሎቹን የመኝታ ክፍሎች ጥራትና የስብሰባ አዳራሾችን ምቹነት ለመፈተሽ ወደ አዲስ አበባ የጥናት ቡድን እንደሚልክ ኩባንያው ገልጿል፡፡  
የአዲስ አበባ ሆቴሎች በዋጋቸው ውድ ቢሆኑም፣ በተጠቃሚ ብዛትም ግን ከአፍሪካ በ4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ የሆቴሎቹ መኝታ ክፍሎች ባዶ ከሚያድሩበት ጊዜ ይልቅ በስራ ላይ የሚውሉበት ጊዜ ይበዛል - ከመቶ ቀናት ውስጥ 58 ቀናት ተገልጋይ ያገኛሉ፡፡
በደራ ገበያ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆኑት በግብጽ የካይሮ ሆቴሎች ናቸው፤ 74.5 በመቶ የመኝታ ክፍላቸውን ስራ ላይ ያውላሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ የኬፕታውን ሆቴሎች 65 በመቶ፣ በጋና የአክራ ሆቴሎች 60 በመቶ የመንታ ክፍሎቻቸውን በጥቅም ላይ አውለዋል፤ ገቢም አግኝተውበታል ብሏል ሪፖርቱ፡፡

Read 4389 times