Saturday, 10 August 2019 00:00

“አብን” የታሠሩ አባላቱን ለማስፈታት የተለያዩ የትግል ስልቶችን መንደፉን አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)


                                   ከፓርቲዎች የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ ስምምነት ራሱን ሊያገል እንደሚችል ገለፀ

            የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአመራሮቹና በአባላቱ ላይ እየተፈፀመ ያለው እስር ወከባ የፓርቲዎች የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ መርህን የጣሰ መሆኑን በመጥቀስ፣ ራሱን በቀጣይ ራሱን ከስምምነቱ ሊያገል እንደሚችል ያስታወቀ ሲሆን፤ የታሠሩትን አባላቱን ለማስፈታት የተለያዩ የትግል ስልቶች መንደፉን ገልጿል፡፡
ንቅናቄው፤ በአባላቱ፣ በአማራ የመብት ጥያቄ አራማጆችና አንቂዎች ላይ መጠነ ሰፊ እስራት መፈፀሙን ጠቁሞ የታሰሩትን ለማስፈታት በቅድሚያ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የተደራጀ አቤቱታ ለማቅረብ መዘጋጀቱን ሊቀመንበሩ ዶ/ር ደሣለኝ ጫኔ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጥያቄ እናቀርባለን ያሉት ዶ/ር ደሣለኝ፤ ይህ አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቶ የታሠሩ የማይፈቱ ከሆነ ንቅናቄው ሠላማዊ ሠልፎችን ጨምሮ፣ የሰላማዊ ትግል አይነቶችን በሙሉ ተጠቅሞ በመንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
የአመራርና አባላቱን እስር አስመልክቶ ሊወስድ ባሰባቸው ፖለቲካዊ እርምጃዎች ዙሪያ ምክክር መደረጉንና በቅድሚያ እንዲፈቱ ለመንግስት ይፋዊ ጥያቄ ማቅረብን እንደሚያስቀድም የጠቆመው ንቅናቄው፤ ጥያቄው ምላሽ የማያገኝ ከሆነ ግን ወደ መጠነ ሠፊ ሠላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንደሚገባ አስረድቷል፡፡
የአባላቱን እስራት በተደጋጋሚ ለጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤትና ለፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት እንዲሁም ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቤቱታ ቢያቀርብም፣ እስካሁን ቀና ምላሽ አለማግኘቱን በመጠቆም፤ ፓርቲዎች የሚተዳደሩበት የቃል ኪዳን ስምምነት በኢህአዴግ የማይከበር ከሆነ ንቅናቄያቸው ከስምምነቱ ራሱን እንደሚያገልም አስታውቋል፡፡
“አሁን እየተፈፀመ ያለው እስራት የጋራ የቃል ኪዳን ሠነድ ስምምነቱን ባልተከተለ መንገድ ነው” ያሉት ዶ/ር ደሣለኝ፤ “ድርጊቱም የዜጐችን  የፖለቲካ ጥያቄ በሃይል የማፈንና የመድፈቅ ተግባር ነው” ብለዋል፡፡
የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ለታሰሩት የንቅናቄው አባላት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባው ያስገነዘቡት ሊቀመንበሩ፤ በአማራ ተወላጅ የመንግስት ተቋማት ሠራተኞች፣ በአዲስ አበባ የአዴፓ አባላትና አመራሮች፣ በህግ ባለሙያዎች፣ በጋዜጠኞችና ጦማሪያን ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው አስታውቀዋል፡፡    

Read 5025 times