Saturday, 10 August 2019 00:00

“ዲያስፖራ” ከሚበጀው የሚፈጀው

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(2 votes)

 የዚህን ጽሁፍ ርእስ “የኮረጅኩት” ከደራሲና ጋዜጠኛ ዓለማየሁ ገላጋይ ነው፡፡ ዓለማየሁ የአንድን ሌላ እውቅ “ጋዜጠኛና ደራሲ” እኩይ ተግባር ለመኮነን ባቀረበው ጽሁፍ ስሙን ጠቀሰና “…ከሚበጀው የሚፈጀው” በሚል ርእስ ነበር መጣጥፉን ያቀረበው:: ይህቺን ርእስ የኮረጅኩበት ዋነኛ ምክንያት፤ ከዓለማየሁ መጣጥፍ ጋር ተመሳሳይ መልዕክእት ያላት ጽሁፍ ለማዘጋጀት በማሰብ ነው፡፡
ጋዜጠኛና ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ የጽሁፉን ጭብጥ አንባብያን ጥሩ አድርገው እንዲጨብጡለት የተጠቀመበት ዘዴ እስከ አሁን ድረስ እንዳልረሳው አድርጎኛል፡፡ ዓለማየሁ የኖህን ልጅ ካምን ታሪክ ነው በጽሁፉ ያቀረበው፡፡ እንዲህ ይላል፤ “አባቱ ኖህ በወይን ጠጅ ሰክሮ ራሱን በማይቆጣጠርበት ጊዜ ራቁትነቱን አይቶ ያልበቃው ካም፤ ወንድሞቹ የአባታቸውን እራቁትነት አይተው እንዲሳለቁ ጠርቶ የአባቱን ሀፍረተ ስጋ እንዲመለከቱ ጋበዛቸው…” ይልና ካምን ለመሆን ህሊና ቢስነትና ድፍረት ብቻ በቂ መሆኑን ነው አለማየሁ የሚነግረን፡፡ ይህንን ተግባር የፈጸመውን “ጋዜጠኛና ደራሲ” ነው ዓለማየሁ “ከሚበጀው የሚፈጀው” ያለው፡፡ እኔ ደግሞ “የዲያስፖራ ነገር ከሚበጀው የሚፈጀው” ሆነብን እያልኩ ነው፡፡ ይህንን እንድል የቀሰቀሰኝን ሃሳብ ከማቅረቤ በፊት ስለ ስደት የመንደርደሪያ ሃሳብ ላቅርብ…
በዓለም ላይ በርካታ ዜጎቿ የተሰደዱባት ሀገር ህንድ ናት፡፡ ህንድ- 15.6 ሚሊዮን ህዝቧ ስደተኛ ነው፡፡ ሜክሲኮ- 12.3 ሚሊዮን፣ ሩሲያ- 10.6 ሚሊዮን እና ቻይና 9.5 ሚሊዮን ህዝብ ተሰዶባቸው፣ ከአንድ እስከ 4ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ አስረኛዋ ሀገር እንግሊዝ ስትሆን 4.9 ሚሊዮን ህዝቧ በስደት ሌላ ሀገር ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያ ስንተኛ ደረጃ ላይ እንደሆነች ባላውቅም 2 ሚሊዮን ገደማ ህዝቧ ስደተኛ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ አሜሪካ ነው ያሉት ይባላል፡፡
ስደተኛን በመቀበል ረገድ አሜሪካ ከዓለማችን አገራት በአንደኝነት ደረጃ ስትገኝ፣ 46.6 ሚሊዮን ህዝብ (የኢትዮጵያን ህዝብ ግማሽ ያህል) ከመላው ዓለም ተቀብላለች፡፡ ሁለተኛዋ አገር ጀርመን ደግሞ 12 ሚሊዮን ስደተኛ፣ ሦስተኛዋ  ሩሲያ- 11.6 ሚሊዮን፣ አራተኛዋ ሳዑዲ ዓረቢያ- 10.2 ሚሊዮን ስደተኛ ተቀብለዋል፡፡ ኢትዮጵያም እንደ አቅሟ ከአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ከሶሪያና ከየመን ጭምር 2 ሚሊዮን ገደማ ስደተኞችን ተቀብላለች፡፡
ሰዎች ሀገራቸውን ለቀው የሚሰደዱበት ምክንያት እንደየ ሀገሩ ሁኔታ ቢለያይም ዋና ዋናዎቹ ገፊ ምክንያቶች ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ጦርነት ናቸው:: ኢትዮጵያውያን ከአፄ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ወደተለያዩ የዓለም ሀገራት ፈልሰዋል:: ኢትዮጵያውያኑን ከሌሎች ስደተኞች ለየት የሚያደርጋቸው ባሉበት ሀገር ሆነው የራሳቸውን ኑሮ ከማደላደል ይልቅ በሀገራቸው ያለን ጨቋኝ መንግስት መታገላቸው ነው፡፡ በዚህ ረገድ አፄ ኃ/ስላሴንና ደርግን ታግለዋል፡፡ ላለፉት 26 ዓመታት ኢትዮጵያን ያስተዳደረውን የህወሓት/ኢህአዴግን መንግስትም ታግለዋል፡፡
በኢህአዴግ ላይ የተደረገውን ትግል ትንሽ ሰፋ አድርገን እንየው፡፡ በውጪ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፤አምባገነኑን የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በመታገል ረገድ የነበራቸው ሚና ከፍ ያለ ነበር፡፡ በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ባለው ጊዜ ለአሜሪካ ኮንግረስ “HR” የተሰኙ የህግ ረቂቆች እንዲወጡ ከፍተኛ ተጽእኖ ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ በአውሮፓ ያሉት ደግሞ ለአውሮፓ ህብረት የተለያዩ የሰብአዊ መብት ገፈፋ ሪፖርቶችን በማቅረብ ጨቋኙን መንግስት አጋልጠዋል፡፡ በግለሰብ ደረጃ እኔ ከማውቃቸው ውስጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ዓለማየሁ ገ/ማሪያም፣ ለ12 ዓመታት ያህል (ቁጥሩ ስህተት ካለው እታረማለሁ) በየሳምንቱ ጽሁፎችን በማቅረብ፣ የማይረሳ ታሪክ ሰርተዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ በአቶ አለማየሁ ጽሁፎች መልእክቶች በአንዳንዶቹ አልስማማም፡፡ እዚህ ላይ ስማቸውን ጠቅሼ ለማንሳት የፈለግኩት ያደረጉትን ጥረት ለማሳየት ነው፡፡ ለአብነት ያህል አቶ አለማየሁን አነሳሁ እንጂ በተመሳሳይ ሁኔታ ብዙ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ድረ-ገፆችን ከፍተው ዘገባዎችን በማተም፣ የህወሓት/ኢህአዴግን መንግስት በማጋለጥ (ከእነ ጉድለታቸውና ድክመታቸው) ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል፡፡
በተለያዩ የዐረብ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በተለይም የሙስሊሞች ጉዳይ ከፍ ብሎ እንዲሰማ የላቀ ጥረት አድርገዋል፡፡ ከኤሌክትሮኒክስ ሜዲያዎች ኢሳት የነበረው ሚና ወደር አልነበረውም፡፡ ኢሳት (ከእነ ጉድለቱና ድክመቱ) የተለያዩ ተጽእኖዎችን ተቋቁሞ፣ የጭቁን ህዝቦች የታፈነ ድምፅ እንዲሰማ ጥረት አድርጓል፡፡ ከኢሳት ጋር መጠቀስ የሚገባቸው እነ OMN እና ሌሎችም ሚዲያዎች፣ ትግሉን በማገዝ የላቀ ሚና ነበራቸው:: ሌሎች ኢትዮጵያውያን የገንዘብም፣ የቁሳቁስም፣ የቅስቀሳም፣ የሰላማዊ ሰልፍም፣… አስተዋጽዖ በማድረግ ተጽእኖ አሳድረው፣ አሁን የምንገኝበት ሁኔታ እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡ በዚህ ተግባራቸው ሁሉም የዲያስፖራ ስደተኞቻችን ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
በአፍሪካ በቅኝ ግዛት ስር ያልነበሩት ሀገሮች ኢትዮጵያና ላይቤሪያ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ላይቤሪያን የመሰረቷት ከአሜሪካ የመጡ በባርነት ውስጥ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ይህቺ ሀገር እስከ አሁን ድረስ የምትመራው አሜሪካ ባሉ የርቀት መቆጣጠሪያ (ሪሞት ኮንትሮል) በጨበጡ ሰዎች ነው፡፡ ኢትዮጵያንም ከአብራኳ የወጡ በአሜሪካና አውሮፓ የሚኖሩ ዜጎቿ በ“ሪሞት ኮንትሮል” ሊመሯት የማይወጡት ተራራና ኮረብታ፣ የማይቧጥጡት ዳገትና ቁልቁለት የለም፡፡
ዲያስፖራው ገንቢ ብቻ ሳይሆን አፍራሽነቱም እየተስተዋለ ነው፡፡ ብሔር ተኮር ቅስቀሳና ሴራ በመቀመም፣ ሃይማኖት ተኮር ቅስቀሳና ደባ በማቀነባበርና በድረ ገፆች በማሰራጨት አውዳሚ ሚናም ተጫውተዋል፡፡ “ሁሉን ነገር ማድረግ እችላለሁ” በሚል መንፈስ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው ይታያል፡፡ አሁን አሁን ከዲያስፖራ በየሶሻል ሚዲያው የሚለቀቀውን ነዛሪ መልእክት ስመለከት፤እውነት እነዚህ ኃላፊነት የማይሰማቸው ሰዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው? ሀገራቸውን ይወዳሉ? ወገናቸውን ያፈቅራሉ? የሚሉ ተከታታይ ጥያቄዎች በአእምሮ ይመላለሳሉ፡፡ በርግጥ ይህንን ሁሉ የተንኮል ተግባር የሚፈጽሙት በብዙሃኑ ስደተኞች ውስጥ የተደበቁ፣ የበግ ለምድ የደረቡ ጥቂት ተኩላዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እናም ብዙኃኑ ዲያስፖራ ሊዋጋቸውና ሊያጋልጣቸው ይገባል፡፡
አሜሪካ ቬትናምን በወረረቺበት ወቅት ብዙዎቹ አሜሪካውያን በሀገራቸው ድርጊት ደስተኛ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም “oppose the war support the army” የሚል ሃሳብ ያራምዱ ነበር:: የእኛዎቹ የዲያስፖራ ወንድም እህቶቻችን ግን ለዓባይ ግድብ ድጋፍ እንዳይዋጣ ገንዘብ መድበው ይቀሰቅሱ ነበር፡፡ ከዚያ ስህተታቸው ያልተማሩት ወገኖች፣ ዛሬም ወገናቸው እርስ በርሱ እንዲጫረስ ክብሪት እየጫሩ  ነው፡፡
ዲያስፖራዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መንግስት፣ በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመስርተው መውቀስም መክሰስም መብታቸው ነው፡፡ የዶ/ር ዓብይን መንግስት ለመናጥና ለማስጨነቅ፣ ያለ የሌለ አጀንዳ ቀርጸው ፋታ ከማሳጣት አልፈው፣ ህዝብ ከህዝብ እንዲጫረስ በጀት መድበው “መንገድ ዝጋ፣ ይህን አቃጥል፣ ያንን አፍርስ…” የሚል መመሪያ በማስተላለፍ፣ በእሳት መጫወታቸው ግን አሳፋሪ ነው፡፡ በሰለጠነ ሀገር፣ ከሰለጠነ ማህበረሰብ ጋር እየኖሩ፣ የጋርዮሽ ዘመን ቀረርቶ ማሰማት ነውር ነው:: እነዚህ ወገኖች በዴሞክራሲ ውቅያኖስ ውስጥ እየኖሩ ያልረጠቡ ዓሣዎች ሆነዋል፡፡ የእኛዎቹ ስደተኛ ወንድም እህቶቻችንን ተግባር መዘርዘር ውስጥ መግባት አልፈልግም፣ አስፈላጊም አይደለም::
በበኩሌ ዲያስፖራዎች ምን እንደሚፈልጉ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ መንግስታችን ለእነሱ ምን ያላደረገው ነገር አለ? ለወቀሳ እንዲያመቸን አንዳንዶቹን በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች እናንሳ፡፡ ለ27 ዓመታት ተዘግቶ የነበረው ኬላ ተነሳ፡፡ ዜጎች እንደ ልባቸው እንዲወጡ እንዲገቡ ተደረገ፡፡ በወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸው ምህረትና ይቅርታ ተደረገላቸው፡፡ በሌሎች ሀገሮች የታሰሩ ስደተኞች እንዲፈቱ የዲፕሎማሲ ጥረት ተደረገ፡፡ የዲያስፖራ ጉዳይን የሚከታተል መስሪያ ቤት ተከፈተ፡፡ ሀገራቸውን በልማት እንዲያግዙ የዲያስፖራ ፈንድ ተቋቋመ፡፡ ዲያስፖራዎች በሀገሪቱ ኢንቨስትመንት ያለ ገደብ እንዲሳተፉ የህግ ማሻሻያዎች ተደረጉ… ዲያስፖራው ምን ያልተደረገለት ነገር አለ?... ተግባራቸው ግን “ከሚበጀው የሚፈጀው” ሆኖብናል፡፡ የእስካሁኑ አንዴ አልፏል፡፡ የአሜሪካንን የዴሞክራሲ አየር እየተነፈሱ፣ ኢትዮጵያን የሚያምሱ ዲያስፖራዎች ልብ ሊገዙ ይገባል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1572 times