Friday, 16 August 2019 10:24

የዘመናዊ ሕክምና ፍልስፍናዊ መሰረት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(2 votes)

  ክፍል-፪ የሕክምና ባለ ሙያዎች የሥነ ምግባር ችግርና መፍትሔው
                   
        (ይህ ፅሁፍ ሳንቴ ሜዲካል ኮሌጅ ሐምሌ 20፣ 2011 ዓ.ም ባዘጋጀው 4ኛው አገር አቀፍ የሕክምና አውደ ጥናት ላይ የቀረበ ነው)
                 
               በክፍል-1 ፅሁፌ ላይ ዘመናዊ ሕክምና የዴካርት የአእምሮ - አካል ሁለትዮሽ ፅንሰ ሐሳብ (Cartesian Mind - Body Dualism) ላይ የተመሰረተ እንደሆነና፤ ይሄም አስተሳሰብ አካልን እንደ ሜካኒካዊ ማሽን አድርጎ እንደሚቆጥረው ተመልክተናል:: በተጨማሪም፣ በዚህ የዴካርት የሁለትዮሽ ፅንሰ ሐሳብ ላይ የተመሰረተው ዘመናዊ ሕክምና የሰውን ልጅ ከማሽንነትም አልፎ ወደ ‹‹ታመመ የአካል ክፍልነት›› ማውረዱን አይተናል፡፡
በዛሬው ፅሁፌ ደግሞ፣ ዘመናዊ ሕክምና የሰውን ልጅ ከማሽንነትም አልፎ ወደ ‹‹ታመመ የአካል ክፍልነት›› ማውረዱ እንዴት በሕክምና ባለሙያዎች ላይ የሥነ ምግባር ግድፈቶችን እየፈጠረ እንደሆነ በኮንፈረንሱ ላይ ከራሳቸው ከሕክምና ባለሙያዎች የተሰጡትን ምስክርነቶች እየጠቃቀስን መፍትሔውን እንመለከታለን፡፡
ዘመናዊ ሕክምና በዴካርት የሁለትዮሽ ፅንሰ ሐሳብ ላይ መመስረቱ፣ የሰውን ልጅ ከማሽንነትም አልፎ ወደ ‹‹ታመመ የአካል ክፍልነት›› አውርዶ እንዲመለከተው አድርጎታል፡፡ የዚህ አስተሳሰብ ዋነኛ ችግሩ የሰውን ልጅ በተሟላ ምልዓት መመልከት አለመቻሉ ነው፡፡ አካል የሰውነት አንደኛው ክፍል እንጂ ብቸኛውና ጠቅላይ ሐሳብ አይደለም፡፡ ሰውን በምልዓት ስንገልፀው፡- አካሉን፣ ስሜቱን፣ እምነቱን፣ ሰብዕናውን፣ ቤተሰቡንና ባህሉን አስተሳስረን ነው፡፡ ሰው ጤነኛ የሚሆነው በዚህ ምልዓት ውስጥ ነው፡፡ ከእነዚህ ሰብዓዊ አላባውያን ውስጥ አንዱ፣ ከተጎዳ የሰው ልጅ ይታመማል፡፡ ሕክምናውም በዚያው ልክ እነዚህን የሰውነት አላባውያንን ግንዛቤ ውስጥ ያካተተ መሆን አለበት፡፡
‹‹ሰው አካሉን ነው፤ ያውም የታመመ አካሉን›› የሚለው የዘመናዊ ሕክምና አስተሳሰብ ግን ሰውን ከስሜቱ፣ ከእምነቱ፣ ከሰብዕናው፣ ከቤተሰቡና ከባህሉ ይገነጥለዋል፡፡ ይሄ አስተሳሰብ የሰው ልጅ እንደ ድርና ማግ ሆኖ የተሰራበት የሰውነት አላባውያን (ስሜቱ፣ እምነቱ፣ ሰብዕናው፣ ቤተሰቡና ባህሉ) ለአካላዊ ሕክምናው ምንም አስተዋፅዖ እንደሌላቸው አድርጎ የሚያስብ ነው፡፡ ይሄም ስንኩል ግንዛቤ የዘመናችን የሕክምና ተቋማትና ባለሙያዎች ዋነኛ መገለጫ ባህሪ ሆኗል፡፡
ዘመናዊ ሕክምና ታማሚውን ሰው ከሰብዓዊ አላባውያኑ (human elements) ገንጥሎ ወደ አካላዊ ማሽንነት ማውረዱ፣ ከአካልም አልፎ ወደ ‹‹ታመመ የአካል ክፍልነት›› ማውረዱ የሕክምና ባለሙያዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ግድፈቶችን እንዲፈጥሩ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ ከእነዚህ የሥነ ምግባር ግድፈቶች ውስጥ ኮንፈረንሱ ላይ በተገኙ የሕክምና ባለሙያዎች የተነሱትን አንዳንዶቹን ልጥቀስ፡፡
‹‹ጥቁር በጥቁር የለበስሽው ምን ሆነሽ ነው?››
ፕ/ር መንገሻ አድማሱ (ቀድሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ አሁን ደግሞ የIIfPHC የኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ) ትውስታቸውን እንዲህ ያጋራሉ:: ‹‹አንዲት ታማሚ ጥቁር በጥቁር ለብሳ ወደ ሆስፒታል ስትመጣ፣ የሐኪሞቻችን የተለመደና የመጀመሪያው ጥያቄ ‹‹ምንሽን ነው ያመመሽ?›› የሚል ነው፡፡ ታካሚዋ ግን ከህመሟ ጋር ሐዘን ላይ ነች፡፡ ማዘኗን ደግሞ በባህሏ ገልፃለች፡፡ ምናልባት፣ የህመሟ ምንጭ ወይም ህመሟን ያባባሰባት ሐዘኗ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ፣ ይቺን ታካሚ በመጀመሪያ ‹‹ምንሽን ነው ያመመሽ?›› ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ፣ ‹‹ጥቁር በጥቁር የለበስሽው ምን ሆነሽ ነው?›› ብለን ብንጠይቃት፣ ሕክምናው እዚያ ላይ ያልቃል፡፡››
ፕ/ር መንገሻ ትውስታቸውን በመቀጠል፤ በአንድ ወቅት የሀገራችን ሐኪሞች ላይ የተሰራውን ጥናት እንዲህ ያስታውሳሉ፡- ‹‹በአንድ ወቅት ሐኪሞች በቀኑ ውሏቸው ውስጥ የሚያክሟቸውን ሰዎች ስም ምን ያህል ያስታውሳሉ? ታካሚዎቻቸውንስ በስማቸው ይጠሯቸዋል ወይ? የሚል ጥናት ተደርጎ ነበር፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ነገር፣ ከ85 ፐርሰንት በላይ የሚሆኑት ሐኪሞች፤ የታካሚዎቻቸውን ስም አያስታውሱም፤ በሕክምና ወቅትም በስማቸው አይጠሯቸውም፡፡ ታካሚን በስም መጥራት በሕክምና ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው፡፡››
‹‹ፅንሱ ትንፋሽ የለውም!!››
በኮንፈረንሱ ላይ እውነተኛ ገጠመኛቸውን ያጋሩን ሌላው ሐኪም ደግሞ ዶ/ር ኩኑዝ አብደላ ናቸው፡፡ ዶ/ር ኩኑዝ በጤና ጥበቃ ሚ/ር የካንሰርና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከፍተኛ አማካሪ ናቸው:: ‹‹ባለቤቴ የ6 ወር እርጉዝ እያለች ደሟ ከፍ ብሎ ወደ አንድ የሕክምና ማዕከል ሄድን፡፡ ከዚያም፣ ተለማማጅ ሐኪሟ መጣች፤ በአንድ እጇ አይፓድ ከፍታ ፌስቡክ ታያለች፣ በሌላ እጇ ደግሞ በአልትራ ሳውንዱ የባለቤቴን ሆድ ስካን ታደርጋለች፡፡ እኔም ባለቤቴም በሁኔታው እጅግ ተጨንቀን ባለንበት በዚያ ሰዓት፣ ሐኪሟ እንደ ቀላል ነገር ‹‹ፅንሱ ትንፋሽ የለውም!!›› ብላን ፌስቡኳን እያየች፣ ትታን ወጣች፡፡ የባለቤቴ እንባ ሊቆም አልቻለም፤ ተያይዘን ተላቀስን::››
‹‹ሐኪሟ እንዳለችው ፅንሱ ትንፋሽ ባይኖረው እንኳን (አይደለም እንጂ) ታካሚዎቻችንን እንደዚህ ነው ወይ ማናገር ያለብን? የእኛ አንዲት ቃል ታካሚዎቻችንን ብቻ ሳይሆን መላው ቤተሰባቸውን የመስበርም ሆነ የመጠገን ኃይል እንዳለው ማወቅ አለብን፡፡››
‹‹የአስታማሚዋን ፊት ማየቴ በጀኝ››
ሌላኛው ትዝብት የመጣው ደግሞ ከኮሌጁ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ከዶ/ር ልሳን ሰይፉ ነው፡፡ ‹‹በአንድ ወቅት በዕድሜ ገፋ ያሉ አንድ ታካሚ ነበሩኝ፤ 24 ሰዓት የምታስታምማቸው ደግሞ ሴት ልጃቸው ነች፡፡ አንድ ጊዜ ከታካሚዬ ጋር እያወራሁ በመሃል የልጃቸውን ፊት ሳየው ደነገጥኩ፡፡ ታካሚዬን አንድ ጊዜ ውጭ ቆዩኝ ብዬ ልጅቷን ‹‹አንቺ ግን ደህና ነሽ?›› ብዬ ስጠይቃት፣ ልጅቷ ምንም ቃል ሳትተነፍስ ለቅሶ በለቅሶ ሆነች:: እናትና ልጅ አንዳቸው ሌላቸውን እያዩ ተያይዘው እየታመሙ እንደሆነ ገባኝ፡፡ ከዚህ በኋላ ያደረኩት ነገር፣ ለታካሚዬ ከማጠፋው ጊዜ በላይ ከልጅቷ ጋር አወራሁ፤ ልጅቷም ቀለል አላት፡፡ ይሄንን ያዩት እናቷም በፍጥነት መዳን ጀመሩ፡፡ የልጅቷን ፊት ማየቴ በጀኝ!!››
ከእነዚህ ትዝብቶች ጀርባ የምንረዳው ነገር፣ ዘመናዊ ሕክምና ያረፈበት ፍልስፍናዊ መሰረት፣ ሐኪሞች ከታካሚዎቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሰብዓዊነቱን ገንጥሎ ሜካኒካዊ እንዳደረገው ነው፡፡ ይሄ በሐኪሞችና በታካሚዎች አካል መካከል ያለው ግንኙነት፣ ከሰውነት ይልቅ ሜካኒካዊ እሳቤ ላይ መመስረቱ ከላይ እንዳየነው ሐኪሞችን ከፍተኛ ለሆነ የሥነ ምግባር ችግር ተጋላጭ እንዲሆኑ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ ችግሩም ዓለማቀፋዊ ስፋት ያለው ነው፡፡
የሥነ ሰብዕ ትምህርቶች (Humanities)
እንደ መፍትሔ
ይሄንን ችግር ለመቅረፍ ምዕራባውያን ያመጡት መፍትሔ የሥነ ሰብዕ ትምህርቶች (ታሪክ፣ ኪነ ጥበብ፣ ሥነ ፅሁፍ፣ ፍልስፍና … የመሳሰሉት) ከሕክምና ትምህርቶች ጋር እንዲሰጡ ማድረግ ሲሆን፣ ግቡም ምልዑ (well-rounded) የሆኑ ሐኪሞችን መፍጠር ነው፡፡ ምልዑ ሐኪም በሕክምናው ብቻ ሳይሆን ከታካሚዎች ጋር ያለው ግንኙነትም የሰውነት አላባውያንን ያካተተ ስለሆነ የተዋጣለት ነው፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ የሥነ ሰብዕ ትምህርቶች አስፈላጊነት፣ የሐኪሙን ሰብአዊ ስሜት በመኮትኮት ‹‹ሰው ማለት አካል ነው›› ከሚለው ሜካኒካዊ እሳቤ እንዲወጣ ማድረግ ነው፡፡ ይሄም በተራው፣ ሐኪሙ ከታማሚው ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ቤተሰባዊነት ከፍ ያደርገዋል፡፡
‹‹አካልና አእምሮ የተለያዩ ናቸው›› የሚለው የዴካርት ፍልስፍና፤ ሐኪሙ የታማሚው አካል ላይ ብቻ እንዲያተኩር ያደርገዋል፡፡ የሥነ ሰብዕ ትምህርቶች ለሕክምና ተማሪዎች አስፈላጊ ሆነው የሚመጡትም፣ ሐኪሙ ከዚህ የዴካርት እሳቤ እንዲሻገርና ጤና የአካልና የአእምሮ ደህንነት ጥምር ውጤት መሆኑን እንዲገነዘብ ለማስቻል ነው፡፡ ከላይ ‹‹የሰውነት አላባውያን›› ያልናቸው ነገሮች በሙሉ በታካሚው አእምሮ በኩል የምናገኛቸው ናቸው፡፡
ጤና፤ የአካልና የአእምሮ ደህንነት ጥምር ውጤት ከሆነ ደግሞ የታመመ ሰው መታከም ያለበት አካሉንም አእምሮውንም ነው፡፡ አእምሮው ውስጥ ደግሞ ስሜቱ፣ እምነቱ፣ ህልሙ፣ ቤተሰቡና ባህሉ አለ፡፡ የታመመው አካል የሚታከመው በመድሃኒት ሲሆን፣ የታመመው አእምሮ የሚታከመው ደግሞ በሐኪሙ አያያዝና እንክብካቤ ነው፡፡ አካል መድሃኒት ሲፈልግ፣ አእምሮ ደግሞ ራሱ ሐኪሙን ይፈልጋል፡፡
በሕክምና ሙያ ውስጥ የሥነ ሰብዕ ትምህርቶች አስፈላጊ ሆነው ከመጡ ወዲህ የ‹‹ሐኪምነት›› ትርጉሙ እንደገና እንዲከለስ እየተደረገ ነው፡፡ በዴካርት ፍልስፍናዊ እሳቤ ላይ በተመሰረተው ትርጉም ከሄድን፣ ሐኪም ማለት የታመመን አካል የሚያክም ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ ይህ ትርጉም በታካሚው በኩል ያለውን ማዕዘን አያካትትም፤ የአንድ ወገን ትርጉም ነው፡፡
ሥነ ሰብዕ ላይ ያረፈው አዲሱ ትርጉም ግን በሐኪሙና በታካሚው መካከል ያለውን ግንኙነት ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በዚህም አዲስ አቀራረብ፣ ሐኪም ማለት ‹‹ታማሚውን አካል›› ሳይሆን ‹‹ታማሚውን ሰው›› (የታመመውን አካልና አእምሮ) የሚያክም ባለሙያ ነው፡፡ (A good physician treats the disease; whereas, the great physician treats the patient who has the disease.)
የሥነ ሰብዕ ትምህርቶች፣ ምልዑ ሐኪሞችን ለመፍጠር ያላቸውን ሚና እየተገነዘቡ የመጡት ምዕራባውያን፤ የሕክምና ት/ቤቶቻቸው በሥርዓተ ትምህርታቸው ውስጥ የሥነ ሰብዕ ትምህርቶች እንዲካተቱ እያደረጉ ነው፡፡ የሥነ ሰብዕ ትምህርቶች፤ ሐኪሞች የምልከታ፣ የመመርመርና የግንኙነት ክህሎቶች (observation skills, diagnostic/clinical skills and communication skills) እንዲያዳብሩ እንደሚያደርግ በጥናት ተረጋግጧል:: ለምሳሌ፣ እ.ኤ.አ በ2008 የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ፤ የሕክምና ተማሪዎች የሥነ ጥበብ ትምህርት (ስዕል) ከተማሩ በኋላ የምልከታ ክህሎታቸው በ38 ፐርሰንት አድጓል፡፡ ይሄንን ውጤት የተመለከተው የአሜሪካ የሜዲካል ኮሌጆች ማህበር፤ በስሩ ያሉት የሜዲካል ኮሌጆች የሥነ ሰብዕ ትምህርቶችን እንዲያካትቱ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2836 times