Saturday, 17 August 2019 12:58

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በየመን ለስቃይና ብዝበዛ መጋለጣቸውን ሂውማን ራይትስ ዎቸ ገለፁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)


                     5 ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን በየመን ታግተዋል ተባለ

           ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በየመን ለከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ብዝበዛ መጋለጣቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች ከትናንት በስቲያ ሀሙስ ባወጣው ሪፖርቱ የጠቆመ ሲሆን 5 ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን ታስረው በስቃይ ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡
የኢኮኖሚ ችግር፣ ድርቅ፣ ስራ አጥነትና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ኢትዮጵያውያን ታዳጊ ወጣቶች አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ምክንያት ናቸው ያለው ሂውማን ራይትስ ዎች የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን ከሕገወጥ ደላላዎችና ከስደት ስቃይ እንዲታደግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጅቡቲን መነሻ አድርገው፣ በባህር የጀልባ ጉዞ 24 ሰዓት በመጓዝ ሳውዲ አረቢያ ድንበር ከደረሱ በኋላ ወደ ሳኡዲ ከተሞች ለመግባት ቢያንስ 5 መቶ ኪ.ሜ ያህል በእግራቸው ይጓዛሉ ያለው ሪፖርቱ፤ በእነዚህ ጉዞዎች በርካቶቹ በቃላት ለመግለጽ አስቸጋሪ የሆኑ ስቃዮችን ይጋፈጣሉ ብሏል፡፡
በዚህ መልኩ ሳውዲ አረቢያ ገብተው የነበሩና በቅርቡ ከሳውዲ በሀይል የተባረሩ 12 ያህል ኢትዮጵያውያንን እንዳነጋገረ የገለጸው ተቋሙ፤ አብዛኞቹ ለአካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት መጋለጣቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ስደተኞቹ በጉዟቸው ወቅት የመን ከደረሱ በኋላ ሕገ ወጥ ደላሎች ወዳዘጋጇቸው እስር ቤቶች እንዲገቡ ይደረጋል፤ ሴቶች ይደፈራሉ፣ ወንዶች ይደበደባሉ ያለው ሪፖርቱ፤ ቤተሰቦቻቸውም ተጨማሪ ገንዘብ ልከው ልጆቻቸውን እንዲያስለቅቁ አስፈሪ መልዕክት ይደርሳቸዋል፡፡ በዚህ ስደተኞቹም ቤተሰቦቻቸውም ለከፍተኛ ብዝበዛ እየተጋለጡ መሆኑን አረጋግጫለሁ ብሏል -ሂውማን ራይትስ ዎች፡፡
በአሁኑ ወቅት በዚህ መልኩ በደቡባዊ የመን ሶስት ቦታዎች ላይ ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ታግተው፣ ለከፍተኛ ሰብአዊ መብት ጥሰትና ብዝበዛ መዳረጋቸውን ሪፖርቱ አትቷል፡፡
ስደተኞቹ በብዛት ከደቡብ፣ ከኦሮሚያ፣ ከአማራና ትግራይ ክልሎች የሚጋዙ መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ መንግስት በእነዚህ ክልሎች ያለውን ሁኔታ እንዲፈተሸ መክሯል፡፡
በተመሳሳይ በሳውዲ አረቢያ መንግስት በሕገወጥ መንገድ ድንበር አሳብረው በመግባት ተወንጅለው ከሚታሰሩ የተለያዩ አገራት ዜጎች መካከል ኢትዮጵያውያን ከግማሽ በላይ (51.5 በመቶ) ድርሻ እንዳላቸው የተገለፀ ሲሆን በአሁን ወቅት በአማካይ በወር 10 ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከሳውዲ አረቢያ በሃይል ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በሳውዲ አረቢያ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙም ተመልክቷል፡፡  

Read 610 times