Saturday, 17 August 2019 13:05

ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ 3 ኢትዮጵያውያን ሴቶች የአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተባሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

 በመንግስት አመራርነትና በንግድ ሥራ ዘርፍ ከአመቱ 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን እንስቶች ዝርዝር ውስጥ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ሶስት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ተካትተዋል፡፡
በየአመቱ አፍሪካውያን የመንግስት አመራርና የንግድ ባለሙያ ሴቶችን የተጽዕኖ አድማስ እያጠና መቶዎቹን መርጦ ይፋ የሚያደርገው ‹‹አቫንስ ሚዲያ››፤ ከኢትዮጵያ በመንግስት አመራር ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴና የጠ/ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊን ሲመርጥ፣ በንግድ ዘርፍ ደግሞ የሶልሬብልስ ኩባንያ ባለቤት የሆኑትን ወ/ሮ ቤተልሄም ጥላሁንን መርጧል፡፡  
እነዚህ 100 አፍሪካውያን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች፣ ለቀጣዩ የአፍሪካ ትውልድ ትልቅ መነቃቃትንና ተስፋን የሚያጭሩ ናቸው ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ35 አገራት የተመረጡ 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች በዝርዝሩ እንደተካተቱ የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ ፕሪንስ አካፓ አስታውቀዋል፡፡ የተመረጡት ሴቶች አገራቸውን በፕሬዚዳንትነት፣ በጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ በዋና ጸሐፊነት፣ በቀዳማዊ እመቤትነት፣ በሚኒስትርነት፣ በዋና ሥራ አስፈጻሚነትና በኮሚሽነርነት ያገለገሉና  እያገለገሉ የሚገኙ ናቸው ተብሏል፡፡
በመንግስት አመራር ከኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴና ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ በተጨማሪ የላይቤሪያ ም/ፕሬዚዳንት ጅዌል ታይለር፣ የናሚቢያ ጠ/ሚር ሳራ ክዋንባዌላ፣ የተባበሩት መንግስታት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሀመድ እንዲሁም የቀድሞ የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ሄለን ሰርሊፍ ጆንሰን በዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል፡፡
የ100ዎቹ ተፅዕኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን ሴቶች የሕይወት ታሪክና ስኬታማ ስራቸው በመጽሔት ታትሞ እንደሚወጣም ተገልጿል፡፡

Read 7725 times