Saturday, 17 August 2019 13:03

የአለማችን ቢሊየነሮች ባለፈው ሰኞ 117 ቢ. ዶላር ከስረዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የአሜሪካ የአክሲዮን ገበያ ባለፈው ሰኞ የአመቱን ከፍተኛ የዋጋ ማሽቆልቆል ማስተናገዱን ተከትሎ፣የአለማችን 500 ቢሊየነሮች በአንድ ቀን ብቻ፣ ሃብታቸው በ117 ቢሊዮን ዶላር መቀነሱን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
በዕለቱ ከሃብታቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ቅናሽ ያስተናገዱት የአማዞን ኩባንያ መስራች አሜሪካዊው ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ ሲሆኑ ሃብታቸው በ3.4 ቢሊዮን ዶላር ቢቀንስም፣ የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋነቱን ግን የነጠቃቸው የለም ተብሏል፡፡ ሃብታቸው በከፍተኛ መጠን ከቀነሰባቸው ሌሎች የአለማችን ቢሊየነሮች መካከል 2.7 ቢሊዮን ዶላር ያጣው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙከርበርግ እንደሚገኝበት የጠቆመው ዘገባው፤18 የአለማችን ቢሊየነሮች በዕለቱ ሃብታቸው በ1 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከዚያ በላይ መቀነሱን አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የአይፎን አምራች የሆነው የአሜሪካው አፕል ኩባንያ፤በአለማቀፉ የሞባይል ገበያ የ2019 ሁለተኛው ሩብ አመት የሽያጭ ድርሻ ወደ 4ኛ ደረጃ ዝቅ ማለቱን ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡ የደቡብ ኮርያው ሳምሰንግ በሩብ አመቱ 75.1 ሚሊዮን ሞባይሎችን በመሸጥ አለማቀፍ የሞባይል ሽያጭ የአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን የጠቆመው ዘገባው፤ ሁዋዌ በ58.7 ሚሊዮን ሁለተኛ፣ በአለማቀፍ ደረጃ እምብዛም የማይታወቀው ሌላኛው የቻይና ኩባንያ ኦፖ በ36.2 ሚሊዮን ሶስተኛ ደረጃን መያዛቸውን አመልክቷል፡፡
አፕል ኩባንያ እስከ ሰኔ በነበሩት ሶስት ወራት የሸጣቸው ሞባይሎች 35.3 ሚሊዮን እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ በዚህም በሽያጭ ወደ አራተኛ ደረጃ ዝቅ ሊል መገደዱን ገልጧል፡፡ በአለማቀፉ የሞባይል ገበያ ድርሻ ሳምሰንግ 23 በመቶ፣ ሁዋዌ 18 በመቶ፣ ኦፖ 13 በመቶ፣ አፕል 11 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ባለፉት ሦስት ወራት ለሽያጭ የበቁ ሞባይሎች ቁጥር 331.2 ሚሊዮን እንደሆነም አመልክቷል፡፡

Read 1115 times