Saturday, 17 August 2019 13:19

የማያዛልቅ ጥገና፤ ታጥቦ ጭቃ (Fixes that fail)

Written by 
Rate this item
(17 votes)

 (በዶ.ር ኤርሲዶ ሌንደቦ የተዘጋጀውና፣ “ኑሮMap” የተሰኘው የለውጥ መፅሐፍ ውስጥ ከሰፈረ ታሪክ አንዱን ነቅሰን እንድንመለከት ወደድን፡፡ ከዓመታት በፊት የአገራችንን ችግር የተነበየና መፍትሔውንም ያሳየ ግሩም መጽሐፍ ነው፡፡)
የኮንስትራክሽን ኩባንያውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ የመጣ ወጣት መሃንዲስ፤ ኩባንያውን ይበልጥ የሚያሳድጉ ሶስት ፕሮጀክቶችን በኮንትራት ተረክቦ ግንባታ ጀምሯል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ የስኬት መንገድ ላይ የተለያዩ ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ መፍትሔ በማበጀትና የስኬት ጥረትን በመቀጠል ነው ስኬቶችን እውን ማድረግ የሚቻለው፡፡
ወጣቱ መሀንዲስ የስራ ማስኬጃ ገንዘብ ቢያጥረውም፤ ከባንክ ብድር ለማግኘት ጊዜ የሚፈጅ ስለሆነበት፤ በግል ከሚያውቀው ሰው፤ በተወሰነ ጊዜ ከወለድ ጋር የሚመለስ ገንዘብ ተበድሯል፡፡ ችግሩ፤ በተስማሙበት የጊዜ ቀጠሮ እዳውን ለመመለስ አልቻለም፡፡ አበዳሪው እንዳያገኘው መሸሽና ስልኩን መዝጋት፤ እንደ መፍትሔ ሆኖ ታይቶታል፡፡
መፍትሔው ግን ሌሎች መዘዞችን ጐትቶ አምጥቷል፡፡ አንደኛ፤ ሌሎች ደንበኞቹና ተባባሪዎቹም በስልክ ሊያገኙት ስላልቻሉ፤ የተለያዩ ጥቅሞችን እያጣ ነው፤ እየተጐዳ ነው፡፡ ሁለተኛ፤ ከአበዳሪው ስለሸሸ ብቻ ችግሩን ያስወገደ ይመስል፤ እዳውን ለመክፈል የሚያስችል ዘዴ ማፈላለግ አቁሟል፡፡ ሶስተኛ፤ መፍትሔው ከአንድ ሳምንት በላይ አልዘለቀም፡፡ መቼም፤ ከሰው ተደብቆ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችን መምራት አይችልም፡፡
አበዳሪው፤ በሰው በሰው አጠያይቆ፤ የግንባታ ቦታው ድረስ መጥቶ አፋጠጠው፡፡ አሁንስ መፍትሔው ምንድነው? ምናልባት፤ በድርድር ለማግባባት ጥረት ቢያደርግና፤ ወለዱን በማሻሻል የክፍያ ጊዜውን ለማራዘም ቢስማሙስ? ያኔ ወጣቱ መሃንዲስ ፕሮጀክቶቹን አጠናቅቆ፤ በቀላሉ እዳውን መክፈል ይችላል - የተወሰነ ያህል ተጨማሪ ጥረትና ገንዘብ ቢያስፈልገውም፡፡ ወጣቱ መሃንዲስ፤ ይህንን መፍትሔ አልመረጠም፡፡
አበዳሪውን በፈገግታ ተቀብሎ፤ ከከተማ ውጭ ስልክ የማይሰራበት ቦታ ሄዶ እንደነበር በውሸት ለማሳመን ከሞከረ በኋላ፤ ቼክ ፈርሞ ሰጠው፡፡ በቃ በዚሁ ተገላገለ፡፡
ግን እስከ መቼ? ባንክ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ ለስራ አውጥቶ እንደጨረሰው ያውቃል:: ቢሆንም ለጊዜው፤ ከአበዳሪው ተገላግሏል፤ ችግሩን ፈታ፡፡ ምን ዋጋ አለው? መፍትሔው አልሰራም፡፡ አበዳሪው ቼኩን ለመመንዘር ወደ ባንክ ከሄደ በኋላ ባዶ እጁን ወደ ወጣቱ መሃንዲስ ተመለሰ፤ እዳውን ለማስከፈል፡፡ ብቻውን አይደለም፡፡ ፖሊስም ጭምር እንጂ፡፡
ወጣቱ መሐንዲስ፤በደረቅ ቼክ አጭበርብረሃል ተብሎ ተከሰሰ፡፡ ከተፈረደበት ብዙ ነገር ያጣል፤ እዳውን ከካሳ ጭምር ይከፍላል፤ ለጠበቃና ለቅጣት ተጨማሪ ገንዘብ ያወጣል፤ የገንዘብ እጥረቱን ይበልጥ የሚያባብስ፡፡ በዚያ ላይ ፍ/ቤት በመመላለስና በእስር፤ የስራ ጊዜውን ያባክናል፤ ፕሮጀክቶቹ ይዳከማሉ - የገንዘብ ምንጮቹን ይጐዳል፡፡ “የማያዛልቅ ጥገና” እንዲህ ነው፡፡
ዋናው መሰረታዊው ችግር፤ የገንዘብ እጥረት ቢሆንም፤ ወጣቱ ግን ሁነኛ መፍትሔ እንደመፈለግ፤ በቁንጽል የችግሩ ውጫዊ ምልክት ላይ አተኮረ - የአበዳሪ ጭቅጭቅ ላይ፡፡ ለአሁኗ ቅጽበት፤ ወይም ለዛሬ ብቻ፤ ከአበዳሪ ጭቅጭቅ ለመገላገል ጊዜያዊ መፍትሔዎችን (የማያዛልቁ ጥገናዎችን) መርጧል፡፡ ውሳኔውንና ድርጊቱን ከነገ ህይወቱ ጋር አያይዞ ለማየት አልሞከረም፡፡ የገንዘብ እጥረት ችግሩን ከማባባስ አልፎ፤ የገንዘብ ምንጩን የሚጐዳ ተጨማሪ ችግር እንደሚመጡበት ለማሰብ አልፈለገም፡፡
የማያዛልቅ ጥገና፤ የተለመደ የሰዎች ባህርይ ነው፡፡ ብዙዎቻችን፤ የዋና ዋና ነገሮችን መስተጋብር በማገናዘብ፤ መሰረታዊውን ችግር ከመጋፈጥ ይልቅ፤ የችግሩ ውጫዊ ምልክት ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡
ውጫዊው የችግር ምልክት፤ ለብቻው በቁንጽል ጐልቶ ስለሚያስጨንቀን፤ በአሁኗ ቅጽበት ለብቻው ገንኖ ስለሚያዋክበን፤ ፈጣን የህመም ማስታገሻና የችግር ማብረጃ ለማግኘት እንጣደፋለን - ሌሎች ዋና ዋና ነገሮችንና ነገን ሳናስብ፡፡
በጊዜያዊ ማብረጃ፤ የችግሩ ምልክት እንዲጠፋ ያደርግልናል፡፡ ግን፤ ዋናው ችግር ስላልተወገደ፤ ምልክቱም ከጊዜ በኋላ መልኩን ቀይሮ ወይም ከቀድሞው ገዝፎና በርክቶ እንደገና መከሰቱ አይቀርም፡፡ በጊዜያዊ ማስታገሻ ራሳችንን በማታለል፤ ለመሰረታዊው ችግር ሁነኛ መፍትሔ ስላላበጀንለት፤ የችግሩ ምልክት ተባብሶ ሲመጣብንስ?
ድሮ የለመድነውን ጊዜያዊ ማስታገሻ (ችግር መሸፈኛ) መጠኑን ከፍ አድርገን፤ ሌላም ማስታገሻ ጨምረን እንሞክራለን፡፡ ይህም ተመልሶ ችግሩን እያባባሰ፤ አዙሪቱ እየከረረ ይሄዳል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሱስ እስኪመስልባቸው ድረስ ይቀጥላሉ፡፡
ካነበብነው የአሳዎች ታሪክ እንዳየነው፤ ለምግብ የሚሆን የባህር ዕፅዋት የተከሉት አሳዎች፤ የምግብ እጥረትን ለዘለቄታው ለማስወገድ ሳይሆን ለቅጽበት ረሃባቸውን ለማስታገስ ነበር የጓጉት፡፡ ዕፅዋቱ ደግሞ፤ ለማደግ ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡
አሳዎቹ፤ “ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ ለማረስም፤ ለመዝራትም፤ ለማጨድም ጊዜ አለው” የሚለው የተፈጥሮ ህግ (እውነት) አልገባቸውም፤ የአሁኗ ቅጽበት ላይ ብቻ ነው ያተኮሩት፡፡ በዚያ ላይ፤ ለማደግም ሆነ ለመፍጠን፤ አስፈላጊ የሆኑ ዋና ዋና ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ውሃ፤ አፈርና ማዳበሪያ ሊያገኝ የሚችል ጠንካራ ስራስር፤ እንዲሁም የፀሐይ ብርሃንን መቀበል የሚችል ጤናማ ቅጠል፡፡ አሳዎቹ ግን፤ በቁንጽል የተክሎቹ ግንድ መርዘምን ብቻ ነው የፈለጉት፡፡
አሳዎቹ፤ እንዲህ ራሳቸውን የቅፅበታዊነትና የቁንፅልነት እስረኛ በማድረግ፤ ተክሎቹን ወደ ላይ በመጎተት እድገታቸውን ለማፍጠን ሞክረዋል፡፡ ዘዴያቸው፤ ለጊዜው የሰራ ቢመስልም፤ የተክሎቹ እድገት አልፈጠነም፡፡ የተክሎቹ ስራስር ተጎድቶ እድገታቸው ተገታ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ጭራሽ ተክሎቹ ጠውልገው መሞት ጀመሩ - በማያዛልቅ ጥገና ወደ ባሰ ውድቀት፡፡
አንዳንዶቹ አሳዎች፤ የፀሐይ ሃሩር ሲያስቸግራቸው፤ ሃሩሩን ተቋቁመው ወይም የፀሐይ መከላከያ ባርኔጣ በመጠቀም፤ ተክሎቹ ፀሐይ ሊያገኙ በሚችሉበት ማሳ ላይ ለመትከል አልመረጡም፡፡ ተክሎቹ አፈር ላይ መተከላቸውን ብቻ በቁንጽል በማየት፤ ዛሬ ከሃሩር ማምለጣቸውን ብቻ በመመልከት፤ ዋሻ ውስጥ ለመትከል ሄደዋል፡፡ ግን የሚያዛልቅ አልነበረም፡፡ ተክሎቹ ጠወለጉ፤ ረሃቡም ከፋ፤ በየእለቱ ምግብ ፍለጋ በፀሐይ ሲንቃቁና በሃሩር ሲጠበሱ ይውላሉ፡፡
ረሃባቸውን በቅፅበት ለማሸነፍ ጓጉተው፤ የወዳደቁ ነገሮችን ለቃቅመው የበሉ አሳዎች፤ ለጊዜው ረሃባቸው የታገሰ ቢመስልም፤ ወዲያው ታመሙ፡፡ ረሃብን የሚያስታግስ ምግብ ለመፈለግ እንኳ መንቀሳቀስ አቃታቸው፡፡ የማያዛልቅ ከሻፊ ጥገና (የደመነፍስ መፍትሄ) በውድቀት ነው የሚቋጨው፡፡ ለዚህም ነው፤ የዛሬ ‹‹ችግሮች››፤ ትናንት ‹‹መፍትሄ›› የነበሩ ናቸው የሚባለው፡፡ የማያዛልቁ መፍትሄዎች፤ ችግርን ያስከትላሉ፡፡   

Read 9248 times