Print this page
Saturday, 17 August 2019 13:24

አዲስ ሐሳብ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ስፖርት ስርነቀል ማሻሻያ!!

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(8 votes)


                               የጥናት አቅራቢው ደብዳቤ ለዝግጅት ክፍሉ እንደመግቢያ

         …በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ1ኛው እስከ 12ኛው የአፍሪካ የአግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ድረስ በስፖርቱ ትልቅ ስምና ዝና ነበራት:: ነገር ግን ከዚያ ወርቃማ ዘመን በኋላ እስከ አሁን የእግር ኳስ ስፖርት ደረጃችን መቀነስ ከዓመት ወደ ዓመት ቀጥሏል፡፡ በዚህም ምክንያት አሁንም ከአፍሪካና ከዓለም አቀፍ ደረጃ ጋር በስፖርቱ ልንመጣጠን አልቻልንም፡፡ በእነዚህ የደረጃ መውረድ ዓመታት ይህን አሳሳቢ ሁኔታ ለማስተካከል የመስኩ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች የማያቋርጥ ጥቆማ፣ ግምገማ፣ ተቃውሞና ጥረት ቢደረግም አሁንም በስፖርቱ የሚያረካ ደረጃ መድረስ አልቻልንም፡፡ የችግሩ መሰረታዊ ምንጭና ምክንያት ምን ይሆን?.... በሚል አቶ ሞላልኝ ለአዲስ አድማስ የስፖርት አምድ ደብዳቤያቸውን አድርሰዋል፡፡ “አዲስ ሀሳብ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ስፖርት ሥርነቀል ማሻሻያ” በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ ከመግቢያው አንስቶ የተለያያዩ ርእሶችን ዳስሰዋል፡፡ ወርቃማው የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ስፖርት ዘመንን መነሻ በማድረግ ይህ ወርቃማ የእግር ኳስ ስፖርት አካሄድ እንዴት ተኮላሸ? የሚለውን ጥያቄ አንስተዋል:: ከዚያም እግር ኳሱን ለማሻሻል የተወሰዱ የማስተካከያና የመፍትሔ እርምጃዎች ከዳሰሱ በኋላ አዳዲስ የመፍትሔ ሀሳቦችን ሲያነሱ ዋናው መፍትሔ፤ የህዝብ/የግል/ክለቦችን መመስረት እና ማወዳደር የግድ መሆኑን ጠቅሰው የዋናው መፍትሔ መሰረት ቋሚ የታዳጊዎች ውድድር በሀገሪቱ ዙሪያ ማቀጣጠል እንደሆነ በመጠቆም ማጠቃላያቸውን አቅርበዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
                    በሞላልኝ ኦርማ (ጥናታዊ ጽሁፍ - ሐምሌ 2011)

          የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ሞላልኝ አርማ የእግር ኳስ ስፖርትን የሚወድ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አነድ ልዩ ስሙ ሞላ ማሩ በሚባለው አካባቢ ያደገና የሚኖር ነው፡፡ በሙያው ላይብረሪ አቴንዳንት ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በቦሌ 17 ጤና ጣቢያ ውስጥ በሆስፒታል ሬጅስትራርነት ያገለግላል፡፡ በትምህርቱም በኢቫንጄሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ ባችለር ዲግሪ ፕሮግራም የሥነ መለኮት ተማሪ ነው፡፡
አዳዲስ የመፍትሔ ሀሳቦች
1. ዋናው መፍትሔ
እኔ የምለው መጀመሪያ አሁን ያለንበት ሁኔታ እንዳለ ሆኖ/ በአንድ ምሽትና ንጋት የሚለወጥ ነገር ስለሌለ/ ወደ መጀመሪያው የህዝባዊ ክለቦች አገነባብ መመለስ አለብን፡፡ አሁን ያሉት ቡድኖች ሳይነኩ እንዳሉ ውድድራቸውን እያካሄዱ ቀስ በቀስ ወደ ግል ወደ ህዝብ ክለብነት የሚመለሱበትን ሁኔታ መፍጠር፡፡ ወይም ሌላ አዲስ በህዝባዊ ክለቦች ባለቤትነት ላይ የተመሰረቱ ቡድኖችን መፍጠር:: ይህን በባለሙያዎች አስጠንቶ የሌሎችን ሀገሮች ልምድ በማካተት ፖሊስና ፕሮግራም ቀርፆ ወደ ተግባር መሸጋገር፡፡
በእርግጥ አዲስ ነገር መጀመር ይከብዳል ግን በድፍረት ተጀምሮ ውጤቱ ሲታይ ነው ጥቅሙ የሚረጋገጠው፡፡ ህዝብ ደግሞ አመራር ይፈልጋል እንጂ አዲስ ነገር መጀመርም መፍጠርም አይፈራም:: ሌሎች የምንቀናባቸው ሀገሮች እኮ ልምዳቸው የሚያረጋገጠው እንዲሁ አዳዲስ አሰራሮችንና አካሄዶችን የመከተል ዝንባሌያቸውና ድፍረታቸው ነው እንደዚህ ያገነናቸው፡፡ አሁን የመቶ ዓመት ታሪክ ያላቸው ክለቦች አነሳሳቸው እንዲሁ የአካባቢ ክለብ ከመመስረት እንደሆነታሪካቸው ያስረዳል፡፡ አዳዲስ ሀሳብና አካሄድ ምንግዜም እንደማይነጥፍ የአውሮፓ ኔሽንስ ካፕ ውድድር መጀመርን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንዴት ከአውሮፓ ዋንጫ አካሄድ የተሻለ ውብ አንደሆነ አይተናል፡፡ ለምን ከክለቦች ውድድር ጋር አቀናጅተው ስላደረጉት የቡድኖችንም ሆነ የተጫዋችን ብቃት በዓመቱ ውድድር ሳይደክም ማሳየት በመቻሉ ነው፡፡ ስለዚህም ከዚህ ዓይነት አዳዲስ አሰራርበመማርና በመበረታት መደረግ ያለበት ምንድን ነው? ሁሉም በየአካቢውበፈለገው መንገድና አመሰራረት ለወጣቱ ለእግር ኳስ አፍቃሪውና ተመልካቹ ለግል ባለሀብቱ አዳዲስ ክለቦችን የሚመሰረቱበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ማነሳሳት፡፡ ለእነርሱም የተለየ ውድድር በማዘጋጀት የተጫዋቾቹን ዕድሜ ከ16-19 ብቻ ተወስኖ መጀመር፡፡ ይህን የመንግስት ቢሮ ሳይሆን የአወዳዳሪ ማህበር ተመስርቶ ውድድሩን ቢያስፈጽም እንደዚህ ዓይነት ማህበር ለመመስረት ሀገራችን በቂ የሆነ የስፖርቱ ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎችና የዳበረ ልምድ ያላቸው ደጋፊዎች ስላሉ የብዙ ባለሙያና ሰው እጥረት አያጋጥምም፡፡ ስለሆነም ይህ ማህበር በጥናትና በሙያ ላይ የተመረኮዘ ሆኖ ህግን አክብሮና አስከብሮ ከአፍሪካም ሆነ ከዓለም ከሀገራችን ጭምር የእግር ኳስ ስነ-ስርዓትና አካሄድ ባልወጣ መልኩ ተደራጅቶ በራሱ ውድድሮችን የሚያካሄድ መንግስት እንደ መንግስት ማንኛውንም የፀጥታና የፋሲሊቲ ድጋፍና ትብብር የሚያደርግለት መሆን አለበት፡፡ በዚህ አካሄድ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ውድድር ወደ ግል ባለቤትነት አሸጋግሮ የቀድሞውን ስሜትና መንፈስ በመመለስ ወደቀድሞ የእግር ኳስ ውጤታችን የምንደረደርበትን ስልት መቀየስ፡፡ ይህ በሰለጠነው ዓለም የትኛውም የስፖርት ውድድር የተያዘበትና ውጤት የተገኘበት ስለሆነ አሳማኝነቱም አጠያያቂ ስላልሆነ አጠናክሮ መቀጠል፡፡ ፌደሬሽኑ የቁጥጥርና ህግ የማስከበር ስራ ብቻ ቢሰራ ሌላውን ስራ በሙያና በስልጠና በመደገፍ ሌሎች ፍላጎቱና ችሎታው ያላቸው እንዲሰሩ ቢያደርግና እኛም በስፖርቱ ውጤታማነት ከሚምነሸነሹ ሀገሮች እኩል የምንሰለፍበትን አሰራር ቢያሰፍን፡፡ አሁን እኮ ከሰባ እስከ መቶ አመታት  ዕድሜ ያላቸው ዓለምን በስፖርቱ ውድድር እንዱስትሪ የተቆጣጠሩት ክለቦች እኮ አመሰራረታቸውና ታሪካቸው ይኸው ነው፡፡ ከመንደር አካባበቢ እስከ ከተማ አደጉ፡፡ በገንዘብ አቅማቸው በረጅም ጉዞ ታማኝነትና የአስተዳደር ዲስፒሊን ፈረጠሙ፡፡ ዓላማቸውን ለማሳካት ከግል ባለቤትነት መንፈስ ተነስተው ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ በማድረጋቸው ይኸው አሁን የዓለሙን ሁሉ ቀልብ ስበው የዓለም ቱጃሮችዓይን ማረፊያ ሆኑ የኃያላን ሀገራት መንግስታት የህዝባቸውን ቀልብ መሳቢያ አደረጓቸው፡፡
ይኼኔ እኮ በንጉሱ ዘመን የተመሰረቱት ህዝባዊ ክለቦች ባይፈርሱ በዚያው የእኔነት የፍቅርና የባለቤትነት መንፈስ ቢጓዙ አሁን ከአርባ ዓመታት ቦኋላ እንደ አውሮፓና ላቲን ክለቦች የት በደረሱ? በገንዘብ አቅም ቢሆን በክለብ ታሪክና ውጤታማነት፣ ለብሔራዊ ቡድን ብርቅ ተጫዋቾች በማፍለቅ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ስፖርትን ሚዛን ከግብጽ አይደለም ከላቲንና ከአውሮፓ ሀገሮች ተርታ ባሰለፉ:: የግብፆቹ ዛማሊክና አልሀሊ ክለቦች እኮ ከእኛ ሀገር አንጋፋ ክለብ በዕድሜ ቢያንሱ እንጂ አይበለጡም፡፡ ግን በህዝባዊ መሰረታቸውና ባለቤትነታቸው ስለቀጠሉ ግዙፍና ኃያል ሆኑ:: ከአፍሪካ ልቀው በዓለም ታላላቅ የውድድር መድረኮች እንደ ዓለም ክለቦች ሻምፒዮን በመሰለ ውድድር ሳይቀር ለመሳተፍ በቁ፡፡ ይህ ምክንያቱ በዋናነት የህዝብና የግል ክለብነት መሰረታቸው ስላልለቀቁ ነው፡፡
ግብፆች ላይ የሚታየው ጥልቅ የእኔነት የመቆርቆርና የባለቤትነት መንፈስ፣ በውድድሮች ውጤት ሲያጡ የሚያሳዩት የኃዘን ጥልቀትና ቁጭት ሲሳካላቸው በጋራ በአንድነት የሚያሳዩት የደስታ ልቀት፣ ከታላላቅ ክለቦቻቸው ጀምሮ ተገንብቶ ወደ ብሔራዊ ደረጃ ያደገ ነው፡፡ ክብራቸውንና ዝናቸውን ለማስጠበቅ ችሎታቸውን ሁሉ በሙሉ በእኔነትና የባለቤትነት መንፈስ በማውጣት ተገቢውን ተጋድሎ ለማድረግ የሚጠቀሙበት ይህ ማንነታቸው ከስር ጀምሮ በግል ክለቦች እየተገነባ ስለመጣ ነው:: በተለይ ብራዚልን በዋናነት አንስተን ለምንድን ነው የላቲን ሀገሮች በኳስ አጨዋወታቸውም ሆነ በውጤታቸው በዓለም ላይ የበላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑት?  በጣም ብዙ ተጫዋቾችን በዓይነትም በጥራትም ስለሚያፈሩ ነው፡፡ ይህ እንዴት ሆነ? ተጫዋቾቻቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ችሎታቸውን በማዳበር ዕድል ለመስጠት በብዙ ውድድሮች ስለሚያጋጥሟቸው ነው፡፡ ይህ ብዙ ውድድር ከየት መጣ? በጣም ብዙ ክለቦች ስላሏቸው ነው፡፡ ብራዚል ከዓለም በክለቦች ብዛት አንደኛ መሆኗ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ክለቦች እንዴት ተመሰረቱ? በየመንደሩና በግለሰቦች ነዋ! ኋላ ምን ሆኑ? ቢያንስ እንደ ፔሌ ያሉ ምርጥተጫዋቾችን አበረከቱ፡፡ ካልሆነም ከሌላው እየተዋሀዱ ታላላቅ ክለቦችን መሰረቱ፡፡
በፔሌ ግለ ታሪክ መጽሀፍ ላይ አባቱ የራሳቸው ክለብ እንደነበራቸው ተጠቅሶአል፡፡ ይህ ህፃኑ ፔሌ ላይ የዓለም ኮከብ እንዲሆን ጽንስ እስይዞት ይሆን? እና እነዚያ ትንንሽ ክለቦች እንዴት አደጉ በግል ጥረታቸው የተማረከ ህዝብ ወይም የገንዘብ አቅም ያለው ተቀላቀላቸዋ ቦኃላ ከብርቱ ሲፎካከሩ ተመደጉና ታላቅ ሆነው በመስኩ የዓለምን ክብር ተቀዳጁ፡፡ ብዙ ምርጥ ተጫዋቾችንም እነሆ አሉ አበረከቱ፡፡ ለዓለም ታዋቂ ክለቦች የተጫዋቾች አቅርቦት የገበያ ምንጭ ሆኑ፡፡ በተደራጀና ህጋዊ በሆኑ የስፖርቱን ዲስፒሊን በተረዱና በሚያከብሩ አወዳዳሪ ማህበሮች መወዳደራቸውንና መታገዛቸውም ለስኬታቸው ዕገዛ ሆኖላቸዋል፡፡ መንግስት የራሱን ኃላፊነት መወጣቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው:: የላቲን ተጫዋቾችን በኳሱ እንደ አሸን መፍላትና የማይነጥፍ ክህሎታቸውንና ፈጠራዊ ጥበባቸውን ሳስተውል እንዴት እንዲህ ይካኑታል ስል የሚገባኝ ነገር ኳስ ጨዋታን በተደጋጋሚ ባለማቋረጥ በፍቅር ስለሚያዘወትሩት ነው፡፡
እንዲህ ደግሞ አንድን ነገር በፍቅር ደጋግሞ መከወን አዳዲስ ነገሮች ለማፍለቅ በር ይከፍታል፡፡ ይህ በጨዋታ ስርዓቱም ከፍተኛ ልምድ ማካበትን ስለሚያጎናጽፍ በቀላሉ በከፍተኛ ውድድሮች ላይ በወሳኝ ቅጽበት በቀላሉ መናበብና መግባባትን ያስችላል፡፡ በተጨማሪም በውድድሮች ሁሉ ጥለቅ ልምድ ስለሚያካብቱ ከሌላው የተመጠነና የተወሰነ ውድድር ሲያደርግ ከቆየው ተጫዋቾች ቡድን ጋር ሲገናኙ ለእነርሱ ያ ሂደት ቀልድ ነው፡፡ ከፍተኛ ባለሙያ እና መለስተኛ ባለሙያ እንደማለት ነው፡፡
ላቲኖች እኮ ኳስን በፉትሳል ደረጃና በበረዶ የገና ኳስ መጫወቻ ሜዳ መጠን ማለት በዚያች ጠባብ የሜዳ ስፋትና ጠባብ የእንግል መጠን ኳስን አዘውትረው ስለሚጫወቱ፣ እንደልብ ለመሆን ጠባብዕድል ባለበት ሁኔታ ራሳቸውን ወስነው ግን የራሳቸውን ጥበብ ቅልጥፍና ፍጥነትና ችሎታ ማፍለቂያ መስክ ስለሚያደርጉት፣እዚያ ጠባብ ሜዳ ውስጥ የሚከሰትላቸው የእግር ኳስ ጥበብ ፈጠራ በሰፊው ሜዳ ለሚያሳዩት ትንግርት መሰረት ሆኖአቸዋል፡፡ ሌላው ዓለምን በሳይንስና በኢኮኖሚ የበላይነት በመምራቱ የሚመፃደቅበትን ያህል አነሱም በዚያው ልክ በስፖርቱ የመመፃደቅ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ምክንያቱም ስራዬ ብለው ዕድሜያቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ጥረታቸውን፣ አቅማቸውን ሁሉ ያለስስት በማፍሰስ ስለሚጥሩ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ይህም አልበቃ ብሎአቸው ኳስን ውሀ ላይ ወደ መጫወት ብቻ ሳይሆን ወደ መወዳደርያም ደረጃ ደርሰዋል፡፡ ሰው ሲለቀቅና ነፃነቱ ሲጠበቅ እኮ የፈጠራ እምቅ ችሎታው አይገደብም:: ስለዚህ ይህ ሁሉ ማጣቀሻና ማመሳከሪያ አኛም ታዳጊዎቻችን በተለያየ ስርዓት ባለው ውድድር አዘውትረን ብናወዳድራቸው ሳያውቁት ላቅ ያለ የችሎታና የማሰብ ማማ ላይ ስለምናወጣቸው ብዙ የግል ክለቦችን መስርቶ ብዙ ውድድሮችን ማድረግ ትውልዱ የአቅሙን ሁሉ አሟጦ በማውጣት ለራሱ ለህብረተሰቡም ሆነ ለሀገሩ የሚያኮራ ውጤትን እንዲያመጣ እንደሚቀርፀው መታመን አለበት፡፡
2. የዋናው መፍትሔ መሰረት
ሌላው መፍትሔ ምናልባት “ሌላው ሀገር ያልተሞከረ” ሊሆን ይችላል፣ ለሚመሰረቱ አዳዲስ ክለቦች መሰረት ሊሆኑ የሚችሉና አዲሱን ትውልድ ሁሉ በጠንካራ የፉክክር ስሜት ውስጥ ከተው በሀገሪቱ ከዳር እስከዳር የእግር ኳስ ጨዋታን እንደገና እንደ አዲስ ለማቀጣጠል የሚረዱ የታዳጊዎች ውድድርን መቅረጽ ነው፡፡ ይህን በእርግጥ የመስኩ ተመራማሪዎች በደንብ አጥንተውና ተንትነው ሊያፀድቁት ይችላሉ፡፡ ነገሩ ምንድን ነው? ታዳጊዎችን ለሁለት ከፍሎ ከ7-11 ዕድሜ እና ከ12-15 ዕድሜ ያላቸው እንደ አቅማቸው ቡድን መስርተው የቡድናቸው ቁጥር ብዛት፣ የሜዳው ስፋትና ርዝመት፣ የአንግሉ ቁመትና ርዝመት ለሁለቱም ወገን እዲመጥን ለማድረግ በባለሙያዎች በጥልቀት አስጠንቶ ቋሚ ውድድር እንዲያደርጉ ማድረግ:: የሚጫወቱበት የጊዜ መጠንና ዕረፍታቸውንም ጭምር በሳይንሳዊ መንገድ በማጥናት ትንሹ ካታጎሪ ያለ እግር ኳስ ህጎች ከግልጽ ጥፋቶች ባሻገር ማለት ነው፡፡ ታላቁ ካታጎሪ ግን ከግልጽ ጥፋቶች ባሻገር መጠነኛ የእግር ኳስ ህጐችን እንዲተገብሩ በማድረግ በእነርሱ ልክ እግር ኳሱንና ህጉን ከማለዳው እንዲያጣጥሙ ማለማመድ እና ከ16-20 ዕድሜ ያሉትን ግን ለአዳዲስ ክለቦች መመስረቻ ዕድሜ ብቻ ቢደረግ፡፡
ለታዳጊዎች ወይ የመንግስት መዋቅር ወይ የሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ወይ ፌደሬሽኑ አስተባባሪና አወዳዳሪ መዋቅር ዘርግተው ወይ አዲስ በሚመሰረቱት አወዳዳሪ ማህበራት ጠሪነት በፈቃዳቸው ከየሰፈራቸው ቡድን መስርተው እንዲመጡ በማድረግ በዓመት ሁለቴ በሴሚስተር የተከፈለ ውድድር እንዲያደርጉ ማመቻቸት፡፡ የጊዜው ወሰን ከሶስት እስከ አራት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እና የአንድ ወር ተኩል ዕረፍት መስጠት:: ከሁለተኛው ሴምስተር ውድድር ቦኃላክረምቱን እንዳለ ማሳረፍ፡፡ ከዚያ የመጀመሪያውን ተርም አሸናፊና የሁለተኛውን ተርም አሸናፊ በዓመቱ መጨረሻ ላይ በማወዳዳር አሸናፊውን የዓመቱ ሻምፒዮን ማድረግ፡፡
በዚህ አይነት የውድድር አካሄድ በታዳጊዎች ውስጥ የማያቋርጥና ተከታታይነት ያለው የውድድር ስሜት ማስረጽና እነርሱም ለዚህ ባለ ዓላማ የሆኑና ራሳቸውንና ችሎታቸውን ሳያቋርጡ ጠብቀው እንዲሄዱ ፈር ማስያዝ፡፡እዚህ ላይ መንግስት ሁሉን ኃላፊነት መወጣት ስለማይችል ውድድሮችን ለአወዳዳሪ ህጋዊ ማኀበራት በመተው ለማኀበራቱ  የፋሲሊቲና የደህንነት ከለላ በመስጠት እንዲሁም በየውድድሩ ፍትሀዊ ገቢ ኖሮአቸው ራሳቸውን በበቂ ሁኔታ እንዲያተስዳድሩ በማድረግ ውድድሮችን ያለ የመንግስት የስራ ጫና ማከናወን፡፡
እዚህ ላይ የሚነሱ የበጀት ፋሲሊቲዎችና የዳኞችን አቅርቦት ጥያቄ ውድድሮቹን መንግስት እመራለሁ ካለ በራሱ አካሔድ ያየዋል፡፡ ማህበራት የሚመሩት ከሆነ ግን እነርሱም በራሳቸው አካሄድ ሊመልሱት ይችላሉ፡፡ ግን ዋናው መጀመር ነው፡፡ ከተጀመረ በኋላ ህዝቡ በባለቤትነት ከያዘው ከመንግስት ኃላፊነት ውጪ ያሉትን ጉዳዮች ህዝቡ በመነሳሳት ይሸፍነዋል፡፡ ዳኞቹን በተመለከተ ዝንባሌው ያላቸውን ወጣቶች በማሰልጠን ማዘጋጀት ይቻላል:: እንደ ውድድሮቹ ብዛት መጠን በሀገሪቱ በርካታ ወጣትዳኞች በራሳቸው ተነሳሽነት ውድድሮችን መዳኘት ከተለማመዱ በልጅነት የተጀመረ የዳኝነት ሙያ ከዕድሜ ጋር መንጥቆ በትምህርትና በስልጠና ሲደገፍ ምን ዓይነት ጥራት ያላቸው ዳኞች ለሀገሩ ሊበረከቱ እንደሚቻልም መገመት አይከብድም:: በዓለም አቀፍ ደረጃ በርክተው ተወዳዳሪ ያረጉን ይሆን? የበጀት ጉዳይ የወጣቶችን አና የልጆችን ጉዳይ የሚከታተሉ የሚኒስቴርመስሪያ ቤቶች የእግር ኳስ ፌደሬሽንና መንግስት ይህን ሀሳብ ካመኑበት በጀቱን ቢያንስ ከአጋዥ ወገኖች ጋር በመተባበር ማዘጋጀት አለባቸው፡፡
በእርግጥ በአንድ ጊዜ በሀገሪቱ ዙሪያ ይህን ቶሎ መተግበር አይታሰብም ግን በተመረጡ ከተሞች ጀምሮ በኋላ ውጤቱን እያዩ ማስፋፋት:: ይህ ዕቅድ ግሩም የእግር ኳስ ጥበብና ችሎታ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊ የሀገሪቱን ለጆች ከነተሰጥኦቸው የማይመክኑበት ግን የመታየት ዕድል ገጥሞአቸው በችሎታቸው ራሳቸውንና ሀገራቸውን የሚጠቅሙበትን ዕድል እንደ የምዕራብ አፍሪካና የላቲን ታደጊዎች ዕድሉን ያመቻችላቸው ይሆን?
የፋሲሊቲ ጥያቄ ሊሆን የሚችለው የሜዳ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ሌላውን በራስ መተማመን እንዲያዳብሩ ለቡድኖቹ ይተዋል፡፡ ቡድን ገንብቶ ማስተዳደሩም ሆነ አሰልጣኝ ማዘጋጀት ይህ ዝንባሌው ላላቸው ታዳጊዎች ከባድ አይሆንም፡፡ በራሳቸው ፍላጎት ስለሚነሳሱ በጉጉት ያሟሉታል እንጂ አይከብዳቸውም፡፡ ሜዳው ግን በከተማዋ ሆነ በሌሎች ሰፋፊ ይዞታ ባላቸው ተቋማት ውስጥ ማለት ታዳጊዎቹ ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ብዙ ባልራቀ ሁኔታ ሊዘጋጅ ይገባዋል፡፡
ቻይና የራሷን የእግር ኳስ ደረጃ ከሌላው ዓለም ለማስተካከልና በመላው ሀገሪቱ የእግር ኳስ ደረጃዋን በስር ነቀል ደረጃ ለመለወጥ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ይዛ ወደ ዘጠና ሺህ የሚጠጉ ህጻናትን ከስር ከመሰረት ኮትኩታ በእግር ኳስ ጥበብና ችሎታ ቀርፃ በዓለም ደረጃ ተፍካካሪ ለመሆን ዕቅድ ነድፋ እየሰራች ነው፡፡ በእርግጥ ይህ የራሷ አካሄድ ነው፡፡ ቀጥታ መኮረጅ ቢቻልም ባይቻልም ቅሉ በዚህ ቁጥር አይደለም ግማሹን ወይ ዕሩቡን እኛ እናድርገው ብንል ፋሲሊቲውን ሆነ በጀቱን መሞከር ይከብዳል:: ግን በአኛ ዓውድና አቅም የምንችለውን ከሰራን ውጤታችን ከቻይና ላያንስ ወይንም ሊበልጥ ከቻለስ ማን ያውቃል፡፡ ቻይና ኢኮኖሚዋን ገንብታ ከዓለም ኃያላን ተርታ ለማሰለፍ ከሰላሳ ዓመታት በፊት አቅዳ አሁን በአሳማኝ ሁኔታ እንዳሳካቺው የእግር ኳስ ዕቅዷንም እንደምታሳካ መጠራጠር ስንፍና ነው:: እንደ ኢኮኖሚዋ ሁሉ በእግር ኳስ ስፖርታም ከጥቂት ዓመታት በኋላ ታሪክ የምትሰራ ከሆነ እኛ የአቅማችንን ያህል የህዝባችንን የታዳጊዎቻችንን በጐ የፉክክር መንፈስ እንደ ገፀ በረከት ቆጥረን በእኛው ልክ አሁኑን መስራት ካልጀመርን እሷም ስታልፈን መቆጨቱ በቀጣይ ትውልድ ተወቃሽ እንዳያደርገን አሰጋለሁ፡፡
ሰው በተፈጥሮው ተፎካካሪ ነው፡፡ ታዳጊዎች ላይ ደግሞ ይህን ጥሩ ተፈጥሮአዊ ፀጋ በአግባቡ ከተጠቀምንበት አዲስ  የአግር ኳስ ትውልድ ፈጥረን ስፖርቱን የግሉ የራሱ ያደረገ ጠንካራና የማይነቃነቅ መሰረት ላይ የቆመ ትውልድ ፈጥረን በስፖርቱ በሀገርም ይሁን በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታሪካችንን አድሰን ክቡር ታሪካችንን ማስመለስ እንችላለን፡፡ አዚህ ላይ ግን አሁን እያደረግን ካለነው የቡድን አመሰራረትና አደረጃጀት በአንዴ እንውጣ ማለት አይደለም፡፡ በሂደትና ቀስ በቀስ ደግሞም አሁን ያለንበትን ደረጃም በማያዛባ መልኩ መሆን አለበት፡፡ የአሁኑ አካሄዳችን  ብቻ ትክክል ነው ብሎ የሚያምን ካለም ይህን አስተሳሰብ በማክበርና በማስከበር ማለት ነው፡፡
የአካዳሚዎችም አካሄድ በተመሳሳይ መልኩ መጠበቅ አለበት፡፡ ይህ ግድ ነው፡፡ ያለንን የደረስንበትን በአግባቡ መያዝ አለብን፡፡ ከዓመታት በኋላ ትልቅ ውጤት የምንጠብቅባቸው በታዋቂና አሳማኝ አሰልጣኞች የፕሮጀክትና የአካዳሚ አካሄዶች አሉን፡፡ እነሱንም አክብረን ውጤቱንም በትዕግስት እየጠበቅን ሌላም አዳዲስ አካሄዳችን ማሰብና መሞከር ተገቢ ነው፡፡ ዋናው የሚፈለገው ዕንቆቅልሽ ሆኖ ግራ ካጋባን አመርቂ የእግር ኳስ ውጤት ማጣት ጥማት መላቀቅ ነው፡፡    
ማጠቃለያ
ከመጨረሻ ይህን በማለቴ ሐሳቤን በማቅረቤ ሁለት ነገሮችን እጠብቃለሁ፡፡ አንደኛው እነዚህ ሐሳቦች ለሀገሬ እግር ኳስ ውጤታማነት ማንሰራሪያና የትንሳኤ ማብሰሪያ መላና ምክንያት ከሆኑ የብዙ ዓመት ቁጭቴ በእርካታና በተሰፋ ይታደሳል፡፡ ሁለተኛው በየአጋጣሚው የሀገሬ እግር ኳስ ደረጃና ውጤት መጥፎ ክስተት በታወሰ ቁጥር ከሚቆጠቁጠኝ ስሜት ፋታ ለማግኘት ይረዳኛል:: ምክንያቱም ሁሉም የሚመለከተው አካል ሁሉ ለስፖርቱ ትንሳኤ የሚችለውን ሲጥር ሳለ እኔም የማምንበትንና ለመፍትሔው ስልት ይቀይሳል የምለውን በመተንፈሴ የህሊና ዕረፍት ይሰጠኛልና ነው፡፡ ሁሉም ነገር ግን ጥልቀት ያለው ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ጥናትና ትንተና ግምገማና ሂስ መሰረት ታይቶ የሚያሳምን ከሆነ ብቻ መተግበር እንዳለበትም አምናለሁ፡፡

Read 20499 times