Print this page
Saturday, 17 August 2019 13:38

“ቀጠሮ አክብረሽ አትመጪም ወይ”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

    “ምን መሰላችሁ…‘ምቀኛ’ የግድ ያስፈልጋል፡፡ ዘወር ብሎ የሚያየን ባይኖርም፣ አንድ አስር፣ ሀያ ምቀኞች ያስፈልጉናል፡፡ ችግሮቻችንን ለማሻገር ኢንሹራንሶች ናቸው፡፡--”
             
              እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…እንዲህ አይነት ውርጭ የተላከብን ምን ብናጠፋ ነው! አለ አይደል…ልክ እኮ  ተፈጥሮ ቂም የያዘችብን ነው የሚመስለው፡፡ አንድ ሰሞን ከሰማዩ በታች ብቻ ሳይሆን ከሰማዩም በላይ ምንም የሚያቅተን ነገር የሌለ ይመስለን በነበረ ጊዜ እኮ “ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር እናውላለን!” እያልን የፎከርነውን ያህል፣ ምንም ነገር ላይ አልፎከረንም! “እንያችኋ፣ ያ ሁሉ ፉከራ የት አለ?” የተባልን አይነት፣ በሌለ የአጥሚት እህል ውርጩን ለቆብናል፡፡ (“ሙቅ እጠጣለሁ እንዳትለኝ ብቻ!” ስትል የነበርከው ሰውዬ፤ አማርኛህን አስተካክል፡፡ ሙቅ ማለት ‘ፖለቲካሊ ኮሬክት’ አይደለም…አጥሚት  ነው የሚባለው፡፡ ዱቄቱ በተገኛና ስሙን ከሞንጎሊያም ቢሆን በተዋስን፡፡) እናላችሁ…ኮሚክ እኮ ነው፣ ራሳችንን እንኳን መቆጣጠር አቅቶን እኮ ነው፣ ከተፈጥሮ ጋር “ውረድ እንውረድ…” ካልገጠምን ስንል የኖርነው!
 (ስሙኝማ…ጨዋታም አይደል፣  “ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል፣” የሚሏት ነገር አለች፡፡ ልጄ… ጎመኑ በተገኘና ጉልበት፣ አይደለም በዳገት በቁልቁለትም ይለግም፡፡ ህይወት እኮ ወደ ‘ሰርቫይቫልነት’  እየተሸጋገረ ነው፡፡) 
እናማ… እኮ በየሰልፎቹና በመሳሰሉት ላይ የምናያቸው መፈክሮች…አለ አይደል…አንዳንዶቹ አፍ የሚያሲዙ ናቸው፡፡ “ሁሉም ሰው የየራሱን መፈክር ይዞ ይምጣ…” የተባለ ይመስል “ምን ሲሉ አሰቧቸው!” የሚያሰኙ፣ አይደለም እኛን ትረምፕና ፑቲንን… “ወንዝ ወርደን ይዋጣልን…” የሚያስብሉ ናቸው፡፡
እናማ…ምን ለማለት ነው፤ ዘንድሮ “ሰልፍ ያለ መፈክር አይሆንም…” የሚል የውስጥ ‘ሰርኩላር’ ካለም ቢታሰብባቸው ግድ ነው፡፡ ዘንድሮ እንደሆነ የወንዙን ውሀ ለመበጥበጥ ከኢንዶኔዥያ ዳርቻ የተነሳ አውሎ ነፋስ አያስፈልግም፡፡ ጥቂት ጠብታዎች ይበቃሉ፡፡
የምር እኮ...ዘንድሮ በጓደኞች መካከል መቀላለድ አልተቻለም፡፡ የማታውቁት፣ ምንም የማይመለከተውና ራቅ ብሎ የተቀመጠው ሰው… “እንደሱ ስትል ምን ለማለት ነው!” ብሎ ሊያፈጥ ይችላል፡፡ ድሮ በሳቅ ያንፈራፍሩን የነበሩ በጣም ግላዊና አልፈው ማንንም የማይነኩ ቀልዶች፤ዘንድሮ ሁሉንም የሚመለከቱ አይነት ሆነዋል፡፡ (‘በአጭርነት’ ላይ የምትቀልዱ ወዳጆቼ፤ ፍሬን ያዙማ…የሚመጣው አይታወቅማ! ሰዎች ሊከፉ ይችላሉ! ሰዎች ሲከፉ ደግሞ ‘የአጭሮች ሰልፍ ዲተርሚኔሽን’ ምናምን የሚል ሌላ ጣጣ እንዳይመጣብን፡፡)
እናማ…የቀልድ ነገር ከተነሳ ምን መሰላችሁ…ቀልድ ስታወሩ ጠንቀቅ ነው፡፡ ዘንድሮ ነገሮች የሚተረጎሙበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ህዝቤ በየሀገር ልጅነት ቅርፊት ውስጥ ራሱን ቀብሮ፤ የተቀለደው ሁሉ በእሱና የእኔ ናቸው በሚላቸው ቡድኖች ላይ የተባለ ያስመስለዋል፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… አንድ ሚኒባስ ታክሲ ላይ ምን የምትል ጥቅስ ተለጥፋለች መሰላችሁ… “የእኔ ምቀኛ ገና አልተወለደም…” ትላለች፡፡ አሪፍ አይደል! ቢያንስ ቢያንስ እሱዬው የሆነ ችግር ሲገጥመው “ምቀኞች አላስቀምጥ አሉኝ…” አይልም፡፡
ምን መሰላችሁ…‘ምቀኛ’ የግድ ያስፈልጋል፡፡ ዘወር ብሎ የሚያየን ባይኖርም፣ አንድ አስር፣ ሀያ ምቀኞች ያስፈልጉናል፡፡ ችግሮቻችንን ለማሻገር ኢንሹራንሶች ናቸው፡፡
“ስማ፤ ዘንድሮም እርከን ሳይሰጡኝ አለፉኝ ነው የምትለው?”
“አዎ፤ ጥምድ አድርገው ነው የያዙኝ”
“ይህን ያህል ከአንተ የሚያጋጫቸው ምንድነው?”
“ምቀኞች ናቸዋ፤ ዙሪያዬን በምቀኛ ተከብቤአለሁ”
እሱ እኮ አይደለም በምቀኛ ሊከበብ፣ የመስሪያ ቤቱ ባልደረባ መሆኑን ብዙዎቹ ሠራተኞች አያውቁም፡፡ ከአምስት ቀን ተኩል፣ ሁለት ተኩሉን የት እንደሚሄድ ሳይታወቅ እንዴት ይወቁት! ግን በቃ…ምቀኛ አስፈላጊ ነው፡፡  ለነገሩ እኮ…“ምቀኛ አታሳጣኝ…” የምትል ተረት ቢጤ አለች፡፡ ያው ምቀኛ ሲኖር … በእልህ እንሠራለን የሚል አይነት ነው፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ምን ናፈቀን መሰላችሁ፤ ቀጠሮ የሚያከብር ሰው፣ ቀጠሮ የሚያከብር ተቋም … ማግኘት፡፡ አንድ ሰው ምን አሉ መሰላችሁ… “ጃፓን ውስጥ አንድ ሰው በቀጠሮ ሰዓት ካልደረሰ ወይ ታሟል፣ ወይ ሞቷል ማለት ነው ይባላል”  የቀጠሮ ሰዓት ማሳለፍ ብሎ ነገር የለም ለማለት ነው፡፡ ከሆነ አሪፍ ነው፡፡
እኛ ዘንድ ልክ በቀጠሮ ሰዓት የደረሰ ሰው፤እንኳን ሊጨበጨብለት፣ ችግር እንደደረሰበት ሊታይ ይችላል፡፡
“አንተ ደህና አይደለህም?”
“ደህና አልመስልም እንዴ!”
“በሰዓቱ ደረስክ ብዬ ነው?”
እኛ ዘንድ እኮ ቀጠሮ አክባሪነት የሚለካው በመምጣትና በመቅረት ሳይሆን “ምን ያህል ደቂቃዎች አሳለፈ” በሚል ነው፡፡ ሠላሳ ደቂቃ ምን አላት! እንደውም
ቀጠሮ አክብረሽ አትመጪም ወይ
ፍቅር የጋራ አይደለም ወይ፣
የምትል ስንኝ ነበረች፡፡ እናማ የተቀጠረችው እስክትመጣ ድረስ የልኡል መኮንን ባቅላባ ቤትን ግድግዳ ተደግፎ፣ ስንት ሰዓት ተገትሮ ሲውል የነበረው፣ የአስራ ዘጠኝ ቁጥር አውቶብስ ፌርማታን ሲቆም የነበረውን ሁሉ --- ቤቱ ይቁጠረው፡፡
 ዘንድሮ…አንድ ሰዓት ሙሉ ጠብቃችሁ ሳይመጣ ሲቀር… “ይህ ሰውዬ ምን ነክቶት ነው?” ብላችሁ ትደውላላችሁ፡፡
የጎረነነ ድምጽ… “ሄሎ!”
“ምነው አሞሀል እንዴ… እየጠበቅኩህ እኮ ነው!”
“ኦ ጂሰስ፣ ረሳሁት…”
ምን! በስንት መከራ የተያዘ ቀጠሮ ረሳሁት!
“ረሳሁት ማለት ምን ማለት ነው?”
“ሶሪ፣ በቃ ነገ አት ዘ ሴም ታይም እንገናኝ---” ስልኩ ጥርቅም ይላል፡፡ እኛ ዘንድ ቀጠሮ ማፍረስ እንዲህ ቀላል ነው፡፡
ቸልተኞች ሆነን ወደኋላ እንዳንቀር
በሁላችንም ዘንድ ቀጠሮ ይከበር
የምትል ግጥም ነበረች፡፡
እኔ የምለው…እግረ መንገድ… እዚህ ሀገር አለባበስ … ፋሺን የምንከተል ነገር መሆኑ እኮ ቀርቷል:: ልክ ነዋ…አሁን፣ አሁን የሚለበሱትን ጂንሶች፣ የብጫቂዎቹን ብዛትና ስፋት ልብ በሉልኝማ፡፡ አሀ…ብጭቅጫቂዎቹን ሁሉ ‘መዘነጫ’ ካደረግናቸው፣ ቤቱስ በምን ይወልወል! (ቂ…ቂ…ቂ…)
ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
በተበጨቀ ጂንስ ተበለጥን ወይ…
የሚል ግጥም እየተጻፈ ሳይሆን አይቀርም፡፡
አንዳንዴ “እየመጣሁ ነው፣ መንገድ ተዘጋግቶብኝ ነው” ይባላል፡፡ መንገዱ እኮ ባዶ ሆኖ እንደውም…አለ አይደል… “የሆነ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምናምን አለ እንዴ!” የሚያስብል ነው፡፡ 
ረዳቱ ጮክ ብሎ “ቀበና፣ አራት ኪሎ፣ ፒያሳ…” እያለ እየጮኸ፣ ሞባይሉ ላይ “ደርሻለሁ-- አራት ኪሎ አደባባይን እያለፍን ነው…” የምንል መአት ነን፡፡ “ታክሲ ውስጥ ያለው ሰው ምን ይላል?”  ብሎ ነገር እንኳ የለም፡፡
በዚህ ላይ ደግሞ ‘ሲኒየር ሲቲዘኑ’ ሁሉ በጨቅ ያለች ጨርቅ ቢጤ ጣል ማድረግ የጀመረበት ጊዜ እኮ ነው፡፡ ሀሳብ አለን…ሁለቱም የተበጫጨቀ ጂንስ ምናምን ከለበሱ፣ ጀርባቸው ላይ ‘አባት’ ‘ልጅ’ የሚል መለያ ይደረግልን፡፡ አሀ…ግራ ገባና! ‘ኋይት ሄይር’ እንደሁ በቀላሉ የተለጠለጠ ኑግ ማስመሰል ቀላል ነው፡፡
ለፖለቲካውም፣ ለተሰጡ ተስፋዎችም፣ ለተገቡ ቃሎችም፣ ለማህበራዊውም ለምኑም… “ቀጠሮ አክብረሽ አትመጪም ወይ፣” ማለት ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!!

Read 3053 times