Print this page
Saturday, 17 August 2019 13:40

ተስፋ ካልቆረጡ ፍትህ ያገኛሉ!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ነዋሪነታችን ኒውዮርክ በአሜሪካ ሲሆን፣ መንግስት ያወጣውን ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ በማሰብ፣ ከልጅነት እስከ እውቀት ያፈራነው ሀብታችንን፤ እውቀታችንን፤ ጉልበታችንንና ጊዜያችንን በአገራችን ላይ ኢንቨስት አድርገን፣ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ለብዙ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረን እንገኛለን፡፡
ከኢንቨስትመንታችን አንዱ፣ በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው ‹‹ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላ/የተ/የግል ማህበር›› ነው፡፡ የድርጅቱን ማኔጅመንት እንስራላችሁ በሚል፣ በደላላ አማካይነት በውቀቱ ታደሰ የሚባል ግለሰብ ቢመጣም፣ በውሉ መሰረት ባለመፈጸሙ ድርጅቱን ለቆ ወጥቶ ነበር፡፡
ሆኖም ምንም ገንዘብ ሳይኖረው፣ የጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያን ኃላ/የተ/የግል ማህበርን ሼር ሙሉ በሙሉ ሽጡልን የሚል ጥያቄ መጣ፡፡ በ22.5 ሚሊዮን ብር ሂሳብ የሽያጭ እና ግዥ የሚል ውል ራሳቸው አዘጋጅተው ምንም ገንዘብ ሳይከፍሉን፣ ወደፊት እከፍላለን፣ ለባንክ የሚከፈለውንም እዳ እንሸፍናለን በማለት በእምነት ተፈራርመን ነበር፡፡
ነገር ግን በውሉ መሰረት ሊፈጽሙልን ባለመቻላቸው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ አቀረብን፡፡ ጉዳዩ በፍ/ቤት እየታየ እያለ፣ እኛ ወደ ውጭ አገር በሄድንበት ጊዜ፣ ከበውቀቱ ታደሰ ጋር በቡድን ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች፣ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን ለሌለው የቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ‹‹ሁከት ይወገድልኝ›› የሚል ሀሰተኛ ክስ በማቅረብ እኔ እንድታሰር ሴራ ጀመሩ፡፡ 8290 ካሬ ሜትር ቦታ በካርታ ቁጥር 83/27፣ በቀን 1996 ዓ.ም የተሰጠ ሆኖ እያለ፣ ከዚህ አጠገብ የሚገኝ፣ በካርታ ቁጥር 83/6፣ በቀን 1983 ዓ.ም በተሰጠ 3015 ካሬ ሜትር ቦታ በመጠቀም ነው የሀሰት ክስ ያቀነባበሩት፡፡ ሀሰተኛውን ክስ በመጠቀም፣ ትዕዛዝ እንዲጻፍላቸው፣ ካደረጉ በኋላ የግል ፋብሪካዬን ይጠብቁ የነበሩትን ሰራተኞች በሀይል በማባረር፤ የሁለቱን ግቢዎች አጥር አፍርሰው በማቀላቀል፣ በግቢ ውስጥ የነበረ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ንብረቶችን በሙሉ በራሳቸው ስልጣን በመቆጣጠር፣ ሌላ አዲስ የጥበቃ ድርጅትም በመቅጠር ንብረቶቼን ለ6 ዓመታት ይዘዋል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም የቢፋ ኢትዮጵያ ኃላ/የተ/የግል ማኅበር የተሰኘ ከኦስትሪያ ኩባንያ ጋር በጋራ የተቋቋመ 3ኛ ፋብሪካችን፣ በመብራት ሃይል እጥረት ችግር፣ ከአጠገቡ ካለው የግል ፋብሪካዬ መብራት ስቦ ሲሰራ ቢቆይም፣ በውቀቱ ታደሰ ያቧደናቸው ግለሰቦች መብራት በማቋረጥ ከ3 ዓመት በላይ የፋብሪካ ስራ እንዲቋረጥ አድርገዋል፡፡
እኛም ስልጣን የሌለው የወረዳው ፍርድ ቤት የሰጠው ትእዛዝም ቢሆንም፤ የሚመለከተው የጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላ/የተ/የግል ማኅበርን እንጂ የኢንጅነር ጌታቸው እሸቱን በ3015 ካሬ ሜትር ላይ የዋለውን የግል ፋብሪካዬን ስላልሆነ፣ ፖሊሶች ከሕግ አግባብ ውጪ ንብረታችንን አሳልፈው ለሌላ ግለሰቦች ሰጥተውብናል በሚል የተፈጸመውን ስህተት እንዲያርሙና ንብረቴን እንዲመልሱልኝ፣ ለኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አቤቱታ አቅርበን፣ በቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ እንዲጣራ ትእዛዝ ተሰጥቶ ነበር፡፡ ጉዳዩን ለመከታተል ከአዲስ አበባ ወደ ቢሾፍቱ በምሄድበት ጊዜ ስልጣን የሌለው የወረዳው ፍርድ ቤት በሰጠው የእስር ማዘዣ መሰረት፤ የፍርድ ቤት ትእዛዝ ነው በሚል ያሬድ ቤተክርስቲያን አጠገብ ስደርስ የላንቻ ፖሊሶች መኪናዬን አስቁመው ‹‹የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ስለሆነ ወደ ላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ሂድ ይሉኛል እኔም ምን ስላጠፋሁ ነው?›› ብዬ ስከራከራቸው፤ የፌዴራል ፖሊሶችን ጠርተው፣ ከመኪናዬ አስገድደው እንድወርድ ተደርጎ በአደባባይ ሕዝብ እያየ በላንቻ ፖሊስና በፌደራል ፖሊስ ታጅቤ፣ በእግሬ ላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰድኩ በኋላ ‹‹ጉዳዩ ቢሾፍቱ ፖሊስ ጣቢያ ያዘዘው ስለሆነ ወደ ቢሾፍቱ ፖሊስ ጣቢያ ሂድ›› ተብዬ በፖሊስ ታጅቤ፣ ለቢሾፍቱ ፖሊስ ጣቢያ አስረክበውኝ ለአንድ ቀን ከታሰርኩ በኋላ በማግስቱ በፍርድ ቤት ትእዛዝ በብር 5000 ዋስ ተለቀኩ፡፡
ይህም ድርጊት ከሕግ አግባብ ውጭ የተፈጸመ መሆኑን ለሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች አመልክተን፤ አቤቱታችን በኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ ሲታይ ቆይቶ፣ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሚታየው ጉዳይ ጋር የተያያዘ ስለሆነ፣ የፍ/ቤቱ ጉዳይ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ አቤቱታው የሚታይ ነው ተባለ፡፡
በውቀቱ ታደሰም ‹‹በ3015 ካሬ ሜትር ላይ ያለውን የግል ፋብሪካዬን ሸጠናል ብላችሁ ካልፈረማችሁልኝ፣ እየዋሸሁ አሳስራችኋለሁ›› በማለት በእኔና በባለቤቴ ላይ ሲዝትብንና ሲያስፈራራን ነበር፣ እሱና ያቧደናቸው ግለሰቦች፣ የተለያዩ የሀሰት ወንጀሎችን እየፈጠሩ እንድታሰር በማድረግ አሰቃይተውኛል፡፡ ከውጭ አገር ህክምና ወደ አገሬ ስመለስ፣ ኤርፖርት ላይ ተይዤ እንድታሰርም አደርገዋል፡፡ ከአንድ አመት በላይ ከአገር እንዳልወጣ አሳግደውኛል፡፡ ባለቤቴ ጉዳዩን እንዳትከታተል የሀሰት ወንጀል እየከሰሱ ለማሳሰር በፖሊስ ብዙ እያሳደዷት ነበር፡፡
ይህንኑ ጠቅሰን ክስ ስናቀርብ፣ የኛን ክስ ተቀባይነት የለውም በሚል ውድቅ እየተደረገ፤ እኔና ሰራተኞች ስራ እንዳንሰራ፣ እኔና ቤተሰቤ ለ6 ዓመታት ጊዜአችንን ፍርድ ቤት በመመላለስ በከፍተኛ ስቃይና እንግልት ስናሳልፍ፣ በዚሁ የሕግ ጥሰትና ግፍ ምክንያት በብስጭት ታምሜ፣ በውጭ አገር በተከታታይ ህክምና ላይ እገኛለሁ፡፡
የሽያጭ ውሉን በተመለከተ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦ እየታየ እያለ፣ የበውቀቱ ታደሰ ቡድን በጎን የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትን በመጠቀም፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው እግድ ተሽሮ፣ የታገዱት ንብረቶች ስም እንዲዞርለት አስወስኗል፡፡ ይሄን በተንኮል የተገኘ ውሳኔ በመቃወም በይግባኝ አቤት ብለን፣ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 189908 06/09/2007 በሰጠው ውሳኔ ተሽሯል፡፡
ነገር ግን፣ እነኝህ ግለሰቦች ህግ ሊገዛቸው አልቻለም፡፡ የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ክስ የቀረበባቸው ንብረቶች፣ እንዳይሸጡ እንዳይለወጡ በኮ/መ/ቁ153204 በ03/11/2006 የተሰጠውን የፍርድ ቤት እግድ በመጣስ፣ በራሳቸው ስልጣን በግቢ ውስጥ ያሉ ቤቶችን አፍርሰው፣ ሌሎችንም ንብረቶች በጨረታ ሲሸጡ፣ በወንጀል ከሰናቸው ጉዳዩ በቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ እጅ ይገኛል፡፡
የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት የቀረበለትን ማስረጃ መርምሮ በኮ/መ/ቁ153204 ውሳኔ ሲሰጥ፣ በ3015 ካሬ ሜትር ላይ የሚገኘውን ከሽያጭ ውሉ ውጭ የሆነውን የግል ፋብሪካዬን፣ በኦሮሚያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠውን የተሻረ ውሳኔ በመጥቀስ፣ ለእነርሱ ወስኖ ከውሉ ከብር 22.5 ሚሊዮን ላይ ተቀናሽ ሂሳቦችን ቀንሶ ብር 17.6 ሚሊዮን እንዲከፍሉን ውሳኔ ሰጠ፡፡
ግምቱ ከብር 60 ሚሊዮን በላይ በሆነው በ3015 ካሬ ሜትር ላይ ባለው የግል ፋብሪካዬ ላይ የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም፣ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበን በመዝ/ቁ155684 በቀን 24/01/2011 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ፣ ያልተከፈለን ብር 17.6 ሚሊዮን እንዲከፍሉንና በ3015 ካሬ ሜትር ላይ ያለው የግል ፋብሪካዬን በተመለከተ ከሽያጩ ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑን በማረጋገጥ፣ የኢንጅነር ጌታቸው እሸቱ ንብረት መሆኑን ወስኗል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ
ሆኖም አፈጻጸም ላይ እያለን፣ እነ በውቀቱ ታደሰ በውሳኔው ቅር ተሰኝተናል በሚል ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አመልክተው፣ አፈጻጸሙን አሳግደው ነበር፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ግን፣ በመዝ/ቁ 166294 በሚያዝያ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ፤ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በመዝ/ቁ 155684 በቀን 24/01/2011 ዓ.ም የሰጠውን ውሳኔ አጽድቆልናል፡፡
 አሁን ባለው በአዲሱ የለውጥ ሥርዓት፣ ፍትህ አግኝተን የተወሰነውንም ገንዘብ መክፈል ስለማይችሉ ራሱ ውል የተደረገበት ማኅበር ተሸጦ እንዲከፍለን ተወስኖ፣ በአፈጻጸም ላይ እያለን እውነታው አልዋጥ ያላቸው እነ በውቀቱ ታደሰ፣ አሁንም ለኢፌዲሪ የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ የጠ/ፍ/ቤት ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር ይቃረናል በሚል ባቀረበው አቤቱታ መሰረት፣ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ አፈጻጸሙ ለጊዜው እንዲታገድ ተደርጓል፡፡
በበኩላችን መንግስት አምኖባቸው ሕግን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ በአገሪቱ የመጨረሻውን ፍትህ እንዲሰጡ የተቀመጡትን የተማሩ ዳኞች፣ በየደረጃው ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር ይቃረናል ተብሎ የቀረበብን አቤቱታ በአጭር ጊዜ ተመርምሮ እግዱ እንዲነሳልን አመልክተን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡
ነገር ግን የእነ በውቀቱ ታደሰ ቡድን፣ በተለይ አሰፋ አዳነ የሚባለው ግለሰብ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ትክክለኛና ፍትሀዊ የሆነ ውሳኔ በራሱ መንገድ የተሳሳተ ትርጉም እየሰጠ፣ በእኛና በፍርድ ቤቱ ላይ የሀሰት ወሬ በተለያዩ ጋዜጦች እያሰራጨ ይገኛል፡፡
ከሀሰተኛ ወሬዎቹም መካከል በአዲስ አድማስ 15/11/2011 ዓ.ም ‹‹ፋብሪካው ያንተ ነው፤ ያረፈበት ቦታ ግን ያንተ አይደለም›› በሚል ያወጣው እውነታውን ሸፍኖ ሀሰተኛ ተራ ወሬ ሲሆን፣ 3015 ካሬ ሜትር ላይ ያለው ፋብሪካንም በተመለከተ ከውሉ ጋር ግንኙነት የሌለው፣ የራሱ ካርታና ፕላን ያለው፣ ግብር የሚከፈልበት እራሱን የቻለ የኢንጅነር ጌታቸው እሸቱ ኬሚካል ኢንዱስትሪ ንብረት ነው፡፡ ይህም ማስረጃዎቹ ለፍርድ ቤት ቀርበው፣ ተመርምሮና ተጣርቶ የኢንጅነር ጌታቸው እሸቱ መሆኑ ውሳኔ የተሰጠበት ነው፡፡
ቀጣሪውን ለማስደሰት ሲል በተለያዩ ጋዜጦች በተከፈተው የወሬ ዘመቻ፣ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ለማንቋሸሽ፣ ከእውነት የራቀ ሀሰተኛ ትርጉም እየሰጠ የሚነዛው ወሬ፣ ከተማረ ሰው የማይጠበቅ አሳፋሪ ሀሰተኛ ወሬ ነው፡፡
በኛ በኩል ለ6 ዓመታት ከፍተኛ ኪሳራና እንግልት እየደረሰብን፣ ተስፋ ሳንቆርጥ ፍትህን ፍለጋ በትግስት ቆይተን፣ አሁን በተፈጠረው የተሻለ አስተዳደር ምክንያት፣ ፍርድ ቤቶች ያለ ተጽዕኖ እንዲሰሩ በተፈጠረው እድል፣ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጡት ውሳኔ፣ ሕገ መንግስቱን ያገናዘበ በአገሪቱ ላይ ፍትህ መኖሩን የሚያሳይ ትክክለኛ ፍትሀዊ ውሳኔ ሲሆን ለፍርድ ቤቶቹም ያለንን አክብሮት እየገለጽን፣ ህብረተሰቡ በሚያደርጋቸው ውሎች ላይ በቅድሚያ ትኩረት እንዲያደርግና ውል ከመፈጸሙ በፊት የተለያዩ የህግ አማካሪዎችን እንዲያማክር እናስገነዝባለን፡፡     


Read 1658 times
Administrator

Latest from Administrator