Saturday, 17 August 2019 13:42

‹‹ቀጣዩ ምርጫ በስጋት የታጀበ ተስፋ ያዘለ ነው››

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  - ከምርጫ በኋላም ሀገር እንደምትኖር ማሰብ ያስፈልጋል
             - ፖለቲከኞች በአገር አንድነት ላይ መግባባት ላይ መድረስ አለባቸው


             ቀጣዩንስ አገራዊ ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ ለማካሄድ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫው ይካሄድ ይተላለፍ በሚለው ጉዳይ ላይ ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋርተወያይቶ የሚወሰን እንደሚሆን
ጠቁሟል፡፡ ከወቅቱ “የመድረክ” እና “የኦፌኮ” ሊቀ መንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና ጋር በቀጣዩ ምርጫ ሁኔታ ላይ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ አለማየሁ አንበሴ ቆይታ አድርጓል፡፡


           ኢህአዴግ ቀጣዩ ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚካሄድ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ የፓርቲያችሁ   አቋም ምንድን ነው?
ምርጫው በሕገ መንግስቱ በተቀመጠው አግባብ መሰረት ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ እኛም ስንጠይቅና ስናስብ ነበር፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ባሉበትም እኔ ጉዳዩን ጠንከር ባለ መንገድ አንስቼላቸው ነበር:: ለውጡ ወደ ሕዝቡ እንዲደርስ ሌላ አስማታዊ ቀመር የለውም። ያለው ቀመር ሕዝብ በነፃነት በመረጠው ሰው እንዲተዳደር ማድረግ ብቻ ነው:: ምርጫውን አስመልክቶ ኢሕአዴግ ያሳለፈውን ውሳኔ እንደግፋለን፡፡ ተገቢ ውሳኔ ነው፡፡ ዋናው ነገር ግን ምርጫው ነፃ፣ ተአማኒና ሁሉን አካታች እንዲሆን፣ የምርጫ ቦርድ፣ እስከ ታች መዋቅር ድረስ ነፃና ገለልተኛ ሆነው ዳኝነት ሊሰጡ በሚችሉ ሰዎች ይገባዋል፡፡ መንግስት በዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይኖርበታል፡፡ ብሄራዊ መግባባት መፍጠር የሚቻልበት ሁኔታም ሊመቻች ይገባል፡፡
ከምርጫው በፊት ብሄራዊ መግባባት መቅደም አለበት እያሉ ነው?
ምርጫ ማካሄድ ከሁለት መጥፎ ነገሮች የተሻለውን የመምረጥ ጉዳይ ነው የሚሆነው። ምንም ይሁን ምን፣ ምርጫ ማካሄድ የተሻለ ነው። ነገር ግን የአገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች ቀድመው ወደ ብሄራዊ መግባባት ከገቡ፣ በእጅጉ የተሻለው የመጀመሪያ አማራጭ ይሆናል፡፡ ላለፉት 50 አመታት አይናችን ከስልጣን ውጪ ማየት ስላልቻለ፣ በየጊዜው ምኒልክ ቤተ መንግስት የሚገባውም በስልጣኑ ለመቆየት፣ ከውጪ ያለውም ለመግባት በሚደረግ ፍትጊያ እየታመስን ኖረናል፡፡ አሁን የተሳካና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲደረግ ከተፈለገ፣ በሙሉ ልብ ብሄራዊ መግባባት ላይ መስራት ያስፈልገናል፡፡ ገዥው ፓርቲ፣ በተለይ፣ አገሪቷንና ሕዝቦቿን ወደ ብሄራዊ መግባባት ቢመራ፣ የተሻለ አማራጭ ነው ብዬ አምናለሁ። ካልሆነ ግን “የተሻለውን መጥፎ መምረጥ”  እንደሚባለው፣ ምርጫው መካሄድ አለበት፡፡
የምርጫ ቦርድን ጨምሮ የፍትህ ተቋማት በቂ ለውጥና ማሻሻያ ሳይደርግባቸው ትክክለኛ ምርጫ ማካሄድ ስለማይቻል ምርጫው ቢራዘም” የሚል ሃሳብ የሚያቀርቡ ወገኖች አሉ፡፡ እናንተ ምን ትላላችሁ?
እነዚህን ተቋማት ማን ነው  የሚያስተካክለው? ዋናው የማስተካከያ መንገድ እኮ ሕዝቡ በሚያምናቸው ሰዎች እንዲዋቀሩ ማድረግ ነው:: ይሄን በፍጥነት ለማድረግ የሚያስቸግር ነገር የለውም። የሚያስቸግረውን ነገር ጠቅሶ የሚከራከር ካለ ማቅረብ ይችላል፡፡ ለኔ ግን ምንም የሚያስቸግር ነገር የለውም። ኢህአዴግ ቁጥር 2፤ ሽግግሩን በራሴ ብቻ እመራለሁ በማለቱ ነው ራሱንም ሆነ አገሪቱን ውጥረት ውስጥ የከተተው፡፡ ሆኖም በሙሉ ልብና በቅንነት ከተሰራ፣ እነዚህን ተቋማት በአጭር ወራት ውስጥ ማስተካከል ይቻላል፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ ገዥው ፓርቲ፣ የሕዝብ ተቀባይነት ካላቸው የፖለቲካ ሀይሎች ጋር ተቀናጅቶ መስራት ይችላል። እነዚህ ሀይሎች ከአምስትና ስድስት አያልፉም፤ ጥቂት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጋር ተቀምጦ መነጋገር እንዴት አልተቻለውም፡፡ ለአገራችን ምንድን ነው የሚያዋጣው… ብሎ መነጋገሩ ምንድን ነው የሚቸግረው? የፖለቲካ ድክመት ነው እንጂ ይሄን ማድረግ አስቸጋሪ አይደለም። አሁን ችግር እየፈጠረ ያለው፣ ሁሉም የየራሱን ህልም ለማሳካት እየተሯሯጠ መሆኑ ነው፡፡ ዛሬም የየራሳቸውን ህልም ለማሳካት ተሯሩጠው ከወደቁት ቀደምቶች መማር አልቻልንም፡፡ ደርግም የራሱን ህልም ይዞ ሄዷል፡፡ ኢሕአፓና መኢሶንም የየራሳቸውን ህልም ይዘው ሄደዋል፡፡ ኢህአዴግ ቁጥር አንድም ህልሙን ይዞ ሄዷል፡፡ ኢህአዴግ ቁጥር ሁለትም ካልተጠነቀቀ ይሄን ስህተት ነው የሚደግመው፡፡ አገሪቷ በቂ የሰው ሀይል አላት፡፡ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ ካለ በአንድ ወር ውስጥ ሁሉንም አስተካክሎ ማጠናቀቅ አይከብድም፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር የጊዜ ሳይሆን የቁርጠኝነት ነው። ችግሩን አንዳች ሚስጥር አድርገን ማየት የለብንም። የፖለቲካ ፍላጐቱ ካለ፣ በአንድ አመት አይደለም፣ በአንድ ወር ብዙ ነገር መስራት ይቻላል፡፡
የምርጫውን መራዘምና አለመራዘም በተመለከተ መወሰን ያለበት ማነው? ህዝቡ ነው ፓርቲዎች?
ላለፉት 27 አመታት ህዝቡ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫን  ሲጠይቅ ነው የኖረው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከሕዝብ የወጣን ነን ብለው… ይሄን ሲያስተጋቡ ኖረዋል። ፓርቲዎች የሕዝብን ጥያቄ መመለስ እንጂ በሕዝብ ጉዳይ የመወሰን ስልጣኑ የላቸውም፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ለመወሰን የሚችለው “ምን ትፈልጋለህ?” ተብሎ ሲጠየቅ ነው:: በኛ በኩል ሕዝቡ እየገለፁልን ያለው፣ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ሕዝቡ የመናገር፣ በጉዳዩ ላይ ሀሳቡን የማቅረብ መብት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት ይሄን እድል አላገኘም፡፡ ስለዚህ በዚህኛው ምርጫ፣ በሕገ መንግስቱ የተጻፈውን መተግበሩ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። የሕዝብን መብት ከልክሎ፣ ሕዝብ ነው መወሰን ያለበት እያሉ መቀለድ የትም አያደርስም፡፡
እርስዎ በተደጋጋሚ “ድርድርና ውይይት መደረግ አለበት” ሲሉ ይደመጣል፡፡ ለውጡ ከተጀመረ አንስቶ ደግሞ በየጊዜው የተለያዩ ፖለቲካዊ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው፡፡ በእነዚህ ውይይቶች ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
በአብዛኛው ‹‹የደንቆሮዎች›› አይነት ውይይት ነው የሚካሄደው፡፡ መጥፎ  ላይሆኑ ይችላሉ፤ ግን አንዱ የሌላውን አያዳምጥም፤ የራሱን ብቻ ነው የሚያወራው። “የደንቆሮዎች” ውይይት ያልኩት ከዚህ አንጻር ነው፡፡ ላለፉት አራትና አምስት አመታት የተለፋበት ይህ ለውጥ፤ እንዴት እንደመጣ፣ ማን እንዳመጣው? ማን ዋጋ እንደከፈለበት… የመሳሰሉ ጉዳዮች በውይይቶቹ ውስጥ አልተካተቱም፡፡ ስለዚህ ለኔ ውይይቱ “የደንቆሮ” ውይይት ነው፡፡ ያን ያህል ጠቃሚም አይመስሉኝም፡፡
እርስዎ በትክክል ምን አይነት ውይይት ነው የሚያስፈልገው ይላሉ?
ሃቀኛ ውይይትና ድርድር ነው መካሄድ ያለበት:: ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች፣ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ፣ መሰረታዊ የአገሪቱን አጀንዳዎች አንጥረው አውጥተው፣ ጠንካራ ውይይት ማድረግ አለባቸው፡፡
በምን አጀንዳ ላይ ነው የሚወያዩት?
ለምሳሌ የአገር አንድነት ጉዳይ፣ የዴሞክራሲ ጥያቄ፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የማድረግ ጉዳይ፣  እውነተኛ የፌዴራሊዝም አስተዳደር ጥያቄ… እነዚህ ናቸው መሰረታዊ የአገሪቱ ጥያቄዎች፡፡ እነዚህ ላይ ነው መነጋገር የሚያስፈልገው፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ግን ሁሉም የየራሱን ህልም መናገር እንጂ የአገሪቱ መሰረታዊ ጉዳዮች በተጠና መልኩ ቀርበው፣ ውይይት እየተካሄደ አይደለም፡፡      
በተለይ ከምርጫ በፊት ውይይትና ድርድር ሊደረግባቸው ይገባል የሚሏቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
በቀዳሚነት በአገር አንድነት ላይ መግባባት ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ የዚህን አገር አንድነት እንዴት እንጠብቅ? ብለን መክረን፣ ቃል ኪዳን አስረን ነው፣ ወደ ምርጫ መግባት ያለብን። ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ ደግሞ ይሄ አንድነቱ የተጠበቀ አገር፣ እንዴት በተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ይተዳደር የሚለው ነው። የመቻቻል ፖለቲካን እንዴት እንፍጠር የሚለው ሌላው ትልቁ ጉዳይ ነው የሚል እምነት አለኝ። ሌሎቹ ከምርጫ በኋላ የሚመጡ ናቸው።
የመገንጠል፣ የራስን ክልል ያለማስደፈር ከሚሉ ገመድ ጉተታዎች መውጣት አለብን፡፡ ይልቁንም፣ እንዴት በአገር አንድነት ላይ መግባባት እንችላለን? እንዴት አንድ የጋራ አገር እንፈጥራለን? የመቻቻል ፖለቲካ እንዴት ባህል ይሁን? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ተደራድረን፣ የቃል ኪዳን ውል ማሰር አለብን፡፡ ይሄን ስናደርግ ግን የየራሳችንን የተለጠጡ ህልሞች ወደ ጐን ትተን፣ መሃል መንገድ ላይ እንዴት እንገናኛለን የሚለውን ማሰብ አለብን፡፡
“ብሄር አቀንቃኝ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች በተበራከቱበት ሁኔታ፣ በሀሳብ ላይ የተመሰረተ ፉክክር አድርጎ ምርጫ ማሸነፍ አይቻልም” የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን እርስዎ ይላሉ?
ዋናው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር፣ የድርጅት ቅርጽ አይደለም፡፡ እኔ የነበርኩበት መኢሶንና ኢህአፓ በርዕዮተ አለማቸው፣ በድርጅታዊ ቅርጻቸው ህብረ ብሄር ነበሩ፡፡ በእርግጥ ከዚያ በኋላ የተመሰረቱ፣ ህብረ ብሄር ነን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ ህብረ ብሄራዊ ናቸው ለማለት ይቸግረኛል። ትንሽ ፋቅ ሲደረጉ ወይ የአማራን ወይ የኦሮሞን፤ ሲጠብም የአንድ አካባቢ ተወላጆች ስብስብ ሆነው ልናገኛቸው እንችላለን፡፡ ይሄ ደግሞ ዘንድ በሁሉም ዘንድ የቅርፅና የአደረጃጀት ችግር መኖሩን ያሳያል። ስለዚህ በተለይ ሕዝቡ፤ የተሻለ የፖለቲካ አቋምና ሃሳብ ማን ነው የሚያራምደው? ማን የተሻለ ፖሊሲ አለው? ማን በአንድነት ይመሩኛል የሚለው ላይ ማተኮር ይበጀዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ያለውን ለኢትዮጵያ ህዝብ መተው ይሻላል፡፡
ህብረ ብሔርም ይሁኑ የብሔር ድርጅቶች፣ “አንድ ሀገር ነው ያለን” በሚለው ጉዳይ ላይ መግባባት ላይ መድረስ አለባቸው፡፡ ዋናው የምርጫ መለኪያ መሆን ያለበት፤ ማን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ይመራል ወይም እየመራ ነው የሚለው ነው:: ህብረ ብሔሮችም ያሸንፉ፣ በብሔር የተዋቀሩ ፓርቲዎች፤ ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበት፤ አንድ የጋራ ሀገር የመኖር ጉዳይ ነው፡፡ የ “አብን” ሀገር፣ የ “ኦነግ” ሀገር፣ የ “ህወኃት” አገር፣ የ “ኦፌኮ” ሀገር… የሚባል ነገር የለም፡፡ “አንድ ሀገር ነው ያለን” በሚለው ላይ ትክክለኛ ድርድር ያስፈልጋል ያልኩት ከዚህ አንፃር ነው፡፡ ይሄን ካላደረግን ግን አሁንም ባለፉት 50 ዓመታት በሄድንበት መንገድ ነው የምንሄደው:: የብሔር ፖለቲካም ሆነ የዜግነት ፖለቲካ የሚያራምዱ ሃይሎች፤ ከሰማይ የወረዱ አይደሉም:: ከዚሁ ማህበረሰብ የወጡ ናቸው፡፡ ነገሩ በዚህ ልክ ነው መታየት ያለበት፡፡
የብሔር እንቅስቃሴ አራማጆችን ለማፈን ጥረት ማድረግ በራሱ ሀገሪቷን ውድ ዋጋ ሊያስከፍላት ይችላል፡፡ የብሔር ንቅናቄዎችን፣ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ እንኳ ጡረታ ማስወጣት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ በሀገር አንድነትና በመቻቻል ፖለቲካ ተደራድሮ፣ በቃል ኪዳን መተሳሰር ይሻላል:: መሀል መንገድ ላይ መገናኘት የግድ ነው፡፡
በሁለቱ የፖለቲካ ሃይሎች መካከል ጥርጣሬ የነገሰ ይመስላል
እርግጥ ነው ፖለቲካ ሁሌም ከስጋት የተነጠለ አይደለም፡፡ ነገር ግን ብሔርተኞች ያሠጋሉ የሚሉ ሃይሎች፤ ከብሔርተኛ ሃይሎች የተሻለ ስራ ሰርተውና ህዝቡን አሳምነው መገኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ብሔርተኛ ድርጅቶችም ራሣቸውን ከኢትዮጵያ ነጥለው የትም እንደማይደርሱ ማወቅ አለባቸው:: “አብን” አማራን ገንጥሎ የትም አይደርስም፡፡ “ህወሓት” ትግራይን ገንጥሎ የትም አይደርስም:: “ኦነግ”ም ኦሮሞን ገንጥሎ የትም አይደርስም:: ስለዚህ የተሻለ የፖለቲካ ስርአትና የነገይቷን ኢትዮጵያ እንዴት አብሮ መፍጠር ይቻላል በሚሉ ጉዳዮች ላይ የበለጠ ጊዜን ማጥፋት የተሻለ ነው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ግን “አብን” ወይም “ኦነግ”ን ብንከስ፣ የኢትዮጵያን ችግር አንፈታም፡፡ እርስ በርስ መካሰሱ የትም አያደርሰንም፡፡ እነዚህን የብሔር ድርጅቶች “እኛ የተሻልን ኢትዮጵያውያን ነን” ማለቱ እምብዛም አይጠቅመንም፡፡ ይልቁንስ በኢትዮጵያ ህዝብ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገሩ ነው የሚሻለው፡፡ ምርጫው ይራዘም ማለትም የትም አያደርስም፡፡ ከዲሞክራሲ መሸሽ ዞሮ ዞሮ፣ አደጋ ነው፡፡
ኦፌኮ ለምርጫው ዝግጅት ጀምሯል ማለት ይቻላል?
የምንችለውን ያህል እየተዘጋጀን ነው፡፡ ግን ገንዘብ የለንም፡፡ የአቅማችንን ያህል እየሞከርን ነው:: የምርጫ ቦርድ መዋቅር እስከ ታች ድረስ በነፃና ገለልተኛ አካላት እንዲዋቀር፣ መንግስት በፍጥነትና በሙሉ ልቡ መስራት አለበት፡፡
ከቀጣዩ ምርጫ ምን ይጠብቃሉ?
ኢህአዴግ፤ ከስልጣን በኋላም ሀገር ትኖራለች ብሎ፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ  በሙሉ ልብ ከሠራ፣ የተሻለች ሀገር መፍጠር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ምርጫው ለስልጣን ገመድ ጉተታ የሚውል ከሆነ፣ ውጤቱ መልካም አይሆንም፡፡ ኪሳራ ነው፡፡ ለኔ ቀጣዩ ምርጫ፣ በስጋት የታጀበ ተስፋ ያዘለ ነው፡፡


Read 1845 times