Saturday, 17 August 2019 13:49

“የታላቋ ትግራይ ብሔራዊ ኮንግረስ” ምን ይዞ መጣ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 • የኛ ብሔርተኝነት ከህወሓት ይሻላል ብለን እናምናለን
       • የትግራይ ህዝብ የሌለበት የኢትዮጵያ ታሪክ የለም

             በቅርቡ የተመሠረተው “ብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ - ባይቶና” (የታላቋ ትግራይ ብሔራዊ ኮንግረስ) ፓርቲ፤ በቀጣዩ ምርጫ አንጋፋውን
ህወሓት ከሚፎካከሩት ፓርቲዎች አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች፤ ህወሓትን በምርጫ ተወዳድሮ ማሸነፍ ከእውነታው የራቀ ነው የሚል አቋም ቢያራምዱም፡፡ ለመሆኑ ባይቶና ለትግራይ ህዝብ ምን አማራጭ ይዞለት መጣ? ከህወሓት ጋር በምን ይመሳሰላል? በምንስ ይለያል? የፓርቲው ርዕዮተ ዓለም ምንድን ነው? በሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የፓርቲውን መስራችና አመራር አባል አቶ ክብሮም በርሄ፤ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡ እንዲህ በማብራራት ይጀምራሉ፡


             “ባይቶና” የተቋቋመው ትግራይ ውስጥ አማራጭ ፖለቲካ ያስፈልጋል በሚል ነው፡፡ በዋናነት የትውልድ ራዕይን መቅረጽ ላይ የሚያተኩር ፓርቲ ነው፡፡ አላማችን በትግራይ የተሻለ ፖለቲካ መፍጠር ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ፤ የራሱ የሆነ ታሪክ አለው ብለን እናስባለን፡፡ በኢትዮጵያ አውድ ውስጥ የራሱ ፀጋና የራሱ ታሪክ አለው፡፡ ያንን ታሪክና ፀጋ ተጠቅሞ፣ ፖለቲካ መስራት ነው ትልቁ ትኩረታችን::
የፓርቲያችሁ ግብና አላማ ምንድን ነው?
እስከ ዛሬ በነበረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ ብዙ ነገር ከውጭ ተገልብጦ ነው ህዝቡ ላይ የሚጫነው:: ቀደም ሲል የማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለም ተብሎ ህዝቡ ላይ ሲጫን ነበር፡፡ ይሄ ዓይነት አካሄድ ደግሞ ለውጥ ማምጣት አልቻለም፡፡ ስለዚህ እኛ አላማ አድርገን የያዝነው፣ በህብረሰባችን ውስጥ ያሉ አስተሳሰቦችንና ፀጋዎችን አንጥረን አውጥተን፣ መልሰን ለህዝቡ መስጠት ነው፡፡ ነባር የፖለቲካ፣ የወታደራዊና የኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳቦች በማህበረሰባችን ውስጥ አሉ። እነዚያን አውጥቶ ጥቅም ላይ ማዋል ነው አላማችን፡፡ በእነዚህ ሃገር በቀል አስተሳሰቦች፣ የህዝባችንን ሁለንተናዊ ሁኔታ ማሻሻል ደግሞ ግባችን ይሆናል ማለት ነው፡፡ ትግራይ በቀል በሆነ አስተሳሰብ፣ የትግራይን ህዝብ ፍላጐት ማሟላትና ህይወቱን መቀየር ነው፤ አላማችን፡፡
ትግራይ በቀል አስተሳሰብ ምን ማለት ነው?
ትግራይ የኢትዮጵያ አንድ አካል ናት፡፡ ለኢትዮጵያ ያላት አስተዋጽኦ ከማንኛውም ክልል የሚያንስም የሚበልጥም አይደለም፡፡ የትግራይ ህዝብ የሌለበት የኢትዮጵያ ታሪክ የለም፡፡ አሁን ባለው ፌደራላዊ አወቃቀር ደግሞ የትግራይ ህዝብ፣ ራሱን በራሱ ያስተዳድራል፡፡ ትግራይ እንዲተዳደር የምንፈልገው፤ በራሱ ታሪክ፣ ባህልና ፀጋ ነው፡፡ ትግራይ ላይ ባለን እንቅስቃሴ፣ ከታሪካችን የተቀዳ ተግባር ነው የምናከናውነው፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከሌሎች ጋር የድርሻችንን መወጣት የምንችለው፣ ትግራይ ላይ ያለንን እሴት ይዘን በመቅረብ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የጋራ ፕሮጀክት ነው፡፡
“ባይቶና” የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ምንድን ነው?
እኛ የትውልድ ራዕይን መቅረጽ ነው የምንፈልገው፡፡ ያንን የትውልድ ራዕይ የምንቀርፀው ደግሞ ከትግራይ ህዝብ እሴቶች ውስጥ ነው:: አጉል የሆነ ብሔርተኝነትን አናራምድም፡፡ መርሃችን፤ የራሳችንን ችግር በራሳችን እንወጣለን የሚል ነው፡፡ ከዚህ ተነስተን፣ በትግርኛ “ዘቤታዊ ዲሞክራሲ” ያልነውን አስተሳሰብ (ርዕዮት አለም) ነው የምንከተለው፡፡ ይሄ ርዮተ አለም፤ በሌሎች ላይ በሚመሠረት ጥላቻ ቤትን የመገንባት ሳይሆን የውስጥ ፀጋን በመጠቀም፣ ድክመትንም ስኬትንም በራስ ብቻ ማከናወን የሚል ነው፡፡ የራስ ድክመትን በሌላው ላይ ማላከክ አንፈልግም፡፡
ያሉንን ቀደምት የስልጣኔ ሚስጥራት ቆፍረን አውጥተን፣ ለዚህ ዘመን በመጠቀም፣ ህዝባችንን የማሻገር አስተሳሰብ ነው የምናራምደው፡፡ የራሳችን የሆነ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳብ አለን፡፡ የራሳችን የሆነ በተለያየ የታሪክ አጋጣሚ የነበረ የፖለቲካ ፍልስፍናም አለን፡፡ በተለያየ ዘመን፣ የተለያየ ወታደራዊ አስተሳሰብ ነበረን፡፡ እነዚህን በቤት ውስጥ የበቀሉ አስተሳሰቦች በመውሰድና በማሳደግ፣ ወደ ቀድሞ ስልጣኔ መመለስ ይቻላል ብለን እናምናለን፡፡
በሰብአዊ መብትና ዲሞክራሲ ረገድስ…?
ማህበረሰባችን የጨዋነትና የሥነ ምግባር፣ ሌላውን ያለመበደል፣ የፍትህና የርዕዮት አስተሳሰቦች አሉት፡፡ የመከባበር አስተሳሰቦችም እንዲሁ፡፡ መከባበር እኮ ዲሞክራሲ ማለት ነው፡፡ ህዝባችን ባህል ውስጥ ይሄ ፀጋ አለ፡፡ ይሄንን ፀጋ አበልጽጐ መጠቀም ይቻላል፡፡ ከውጭ ልንወስድ የምንችለው ነገርም ይኖራል፡፡ ለምሣሌ የሚዲያ ነፃነት ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ዋነኛ መሠረታችን ሀገር በቀል አስተሳሰብ ይሆናል፡፡
ህወሓት የትግራይ ብሔርተኝነት አቀንቃኝ ነው:: በዚህ ረገድ ከህወሓት ጋር ትመሳሰላላችሁ፡፡ እስቲ የምትለዩበትን ይንገሩን?
ከህወሓት ጋር አንድ አይደለንም፤ እንለያያለን:: ህወኃት በታሪኩ በርካታ ጥሩ ነገሮች የሠራ ድርጅት ነው፡፡ ዛሬ የሚረግሙት ሰዎች ስለበዙ ይሄንን ልንክድ አንችልም፡፡ የሚረግሙት ወገኖች የራሣቸው ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን እኛ እንደምንገነዘበው፤ ህወሓት በጣም የሚያስቀና ታሪክ የነበረው ድርጅት ነው፡፡ በታሪክ አጋጣሚ በተለይ ከተማ ከገባ በኋላ ብዙ ነገሮች አበላሽቶ ይሆናል:: ይህ ሁሉ ሆኖ ግን የኛ ብሔርተኝነት፣ ከህወኃት የተሻለ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ከህወሓት የተሻልን ብሔርተኞች የሚያደርገን ምንድን ነው ከተባለ፣ ህወኃት የትግራይ ብሔርተኝነትን እንደ ታክቲክ ነው የምትጠቀመው፤ እኛ የትግራይ ብሔርተኝነትን እንደ ስትራቴጂ ነው የምንጠቀመው፡፡ ለኛ ብሔርተኝነት፣ ስትራቴጂያችን እንጂ ታክቲካችን አይደለም፡፡ ወደ ስልጣን መወጣጫ እርካብ አድርገን ሳይሆን፣ ወደ ብልጽግናና ስልጣኔ መወጣጫ እርካብ አድርገን ነው የምንጠቀመው፡፡ የትግራይ ብሔርተኝነት፤ የስልጣን ሳይሆን የስልጣኔ መሠረታችን ነው የሚሆነው:: የትግራይ ብሔርተኝነት ፈር እንዳይስትም እንጠነቀቃለን፡፡ ብሔርተኝነታችን ገደብ ያለው፤ በራስ ጥቅምና በራስ ክብር ላይ የተመሠረተ ነው:: በሀገር ደረጃ ደግሞ የእኩልነት መርህን ነው የምናራምደው፡፡
የምርጫ ዋነኛ ተፎካካሪያችሁ ማን ነው?
ብዙዎች “ከህወሓት በምን ትለያላችሁ? የምርስ ትለያያላችሁ ወይ?” የሚል ጥያቄ ይጠይቁናል፡፡ በቀናነት  ለተመለከተን ግን ከህወኃት በጣም ነው የምንለየው፡፡ እኛ የራሳችን ርዕዮት አለም አለን:: በዚህም እንለያለን፡፡ ከአረናም ከሣልሣይ ወያኔም በብዙ እንለያለን፡፡ በትግራይ ብሔርተኝነት ጽንሰ ሃሳብም እንለያያለን፡፡ እኛ ከህወሓት የተሻልን ብሔርተኞች ነን፡፡ ህወሓት ብሔርተኝነትን ለስልጣን አውሎታል፡፡ እኛ ደግሞ ብሔርተኝነትን ለስልጣኔ እናውለዋለን፡፡ ይሄ መሠረታዊ ልዩነታችን ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ፤ ህወሓትን አራት ኪሎ አድርሶታል፡፡ አራት ኪሎ ከደረሰ በኋላ ግን ህወኃት፣ የትግራይ ህዝብን ረስቶቷል ወይም ከድቶቷል ብለን ነው የምናስበው፡፡ በሌላ በኩል፤ ከህወሓትም ሆነ ከሌላው ፓርቲ ጋር ግንኙነታችን፣ የፉክክርም የትብብርም እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡
እንዴት ነው የፉክክርም የትብብርም ሲሉ--?
ለምሣሌ ሁላችንም የትግራይ ፓርቲ ነን፡፡ የትግራይ ፓርቲ ከሆንን፣ በትግራይ ጥቅም ላይ  አንድ ሆነን መስራት እንችላለን፡፡ በኢትዮጵያም ጉዳይ ላይ እንዲሁ፡፡ ማናቸውም ፉክክሮች፣ ህዝቡን መሠረት ያደረገ እንጂ የግል ስልጣንን መሠረት ያደረገ መሆን የለበትም፡፡ በዚህ መልኩ ትብብርም ፉክክርም ሊኖረን ይገባል ብለን እናምናለን፡፡
የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል፤ ‹‹የትግራይ ህዝብ የመገንጠል ስሜት ውስጥ ገብቷል›› ብለው ነበር፡፡ እናንተ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት አላችሁ?
መገንጠል ሲባል ሰው የሚረዳው ባልሆነ መንገድ ይመስለኛል፡፡ መቼም ትልቅ ሀገር መሆንን የሚጠላ የለም፡፡ ነገር ግን ትልቅ ሀገር ላይ ሆኖ መቻቻል ከሌለ፣ መለያየትም አማራጭ መሆን አለበት እንላለን፡፡ ስለዚህ አሁን ያለውን የህገ መንግስት ድንጋጌ እንደግፋለን፡፡ ነገር ግን በአንቀጽ 39 ላይ የተቀመጠው የመገንጠል ጉዳይ፤ እንዴት መገንጠል ይቻላል የሚል እንጂ ለምን ትገነጠላለህ የሚል ቅድመ ሁኔታ የለውም፡፡ ለምን ትገነጠላለህ የሚል ጥያቄን ባካተተ መልኩ መሻሻል አለበት እንላለን:: አንድ አድርጐ የሚያኖረን መከባበር ነው፡፡ አንድ ፖለቲከኛ ባጠፋ በጅምላ ህዝብ የሚሰደብ ከሆነ፣ መከባበር አይኖርም፡፡ ፖለቲከኛ ባጠፋ ህዝቡ እዳ ከፋይ መሆን የለበትም፡፡ አሁን ያለው አዝማሚያ ግን እንደዚያ ነው፡፡ ይሄ ሁኔታ ካልተስተካከለ ደግሞ ህዝቡ ራሱን ነፃ የማውጣት መብቱ ሊከበርለት ይገባል ብለን እናምናለን፡፡
በህወሓት ላይ ትችቶች ሲሰነዘሩ፣ በህዝቡ ላይ እንደተሰነዘረ አድርጐ የመውሰድ ችግር በአንዳንድ የትግራይ ልሂቃን ይንፀባረቃል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ አስተያየት ላይ እርስዎ  ምን ይላሉ?
በሁለቱም በኩል ነጋዴ አለ፡፡ በአንድ በኩል ህወሓት ሲነካ፣ የትግራይ ህዝብ ተነካ ብሎ የሚነሳ የፖለቲካ ነጋዴ አለ፤ ይሄ ቁማርተኛ ነው፡፡ ህወሓት ራሱ ነው፣ ራሱን ማዳን ያለበት፡፡ ነገር ግን ግልጽ በሆነ መንገድ በህወሓት ሽፋን፣ የትግራይን ህዝብ ለማጥፋት ግልጽ የሆነ ዘመቻ ይካሄዳል፡፡
በማስረጃ አስደግፈው ሊገልፁልን ይችላሉ?
የተጠቃው የትግራይ ህዝብ ብቻ ተለይቶ አይደለም የሚል ክርክር ሊቀርብ ይችላል:: ሌላውም ህዝብ ተመሳሳይ ጥቃት ደርሶበታል ሊባልም ይችላል፡፡ ነገር ግን ወያኔ በሚል ስም ብቻ፣ ስለ ወያኔ መኖር እንኳ የማያቅ የትግራይ ተወላጅ፣ ከአካላዊ ጉዳት ባለፈ፣ ለስነልቦና ችግርም ተዳርጓል:: ቆራሌ እያለ የሚተዳደር ትግራይዋይ፣ በስመ ወያኔ ብዙ ችግር አጋጥሞታል፡፡ ምናልባት ይሄ በሚዲያ አልወጣ ይሆናል እንጂ እኛ በቂ ማስረጃዎች አሉን:: ጉዳቱን እጥፍ የሚያደርገው ደግሞ የሚሞተው ሰው በሚዲያ እንኳን አይጮህለትም፡፡ ይሄ ጉዳት በእነ መለስም ዘመን የነበረ ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ በሚዲያዎችም ጭምር ዘመቻ ተከፍቶ ነበር፡፡
በየትኛው ሚዲያ? መቼ?
ብዙ ሰው እንዲህ ሲባል በስሜት ብቻ የሚነገር ይመስለዋል፤ ግን አይደለም፡፡ እኛ ብዙ ማስረጃዎችን ይዘን ነው የምንናገረው፡፡ ለምሣሌ ‹‹ኢሣት›› ላይ እንዲህ ያለው ድርጊት ተፈጽሟል፡፡   
ምን አይነት ድርጊት?
በነገራችን ላይ ‹‹ኢሳት›› ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሚዲያዎች በሙሉ ከትግራይ በተቃራኒው የተሠለፉ ናቸው ብለን ነው የምናስበው:: ወደ ትግራይ የሚሄደው መንገድ ሲዘጋ፣ ህወሓት እኮ አይደለም የሚጐዳው፤ ህዝቡ ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ሚዲያዎች መቼ ለህዝቡ ቆመው ተከራከሩ? እንኳን መከራከር ስለ ጉዳዩ ዘገባ እንኳ ለመስራት የፈለገ ሚዲያ የለም፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር የሀገሪቱ ሚዲያዎች፣ ከትግራይ በተቃራኒ የቆሙ ናቸው፡፡ ይሄ መሠረታዊ የአስተሳሰብ ችግር ነው፡፡ ለምሣሌ ‹‹ኢሣት›› ህወሓትን መቃወም መብቱ ነው፤ ነገር ግን ‹‹95 ሚሊዮን ህዝብ 5 ሚሊዮን ህዝብ ማጥፋት አለበት›› ብሎ ተናግሯል፡፡ ማንም ሰው ቪዲዮውን ማየት ይችላል፡፡ የቪዲዮ ማስረጃውንም ማቅረብ ይቻላል፡፡
ማን ነው ይሄን የተናገረው?
መሳይ የሚባል ጋዜጠኛ ነው የተናገረው:: ‹‹አሁን የገጠመን ትግል አንድ ገዥ ነኝ የሚል ቡድን ሳይሆን፤ ልግዛችሁ የሚል አናሳ ጐሣ ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ 95 ሚሊዮን ነው፤ ይሄ አናሳ ጐሣ ደግሞ 5 ሚሊዮን ነው›› ሲል ነው የተናገረው፡፡ ማንም ቪዲዮውን አይቶ ይሄን ማረጋገጥ ይችላል፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን እኛ ዝም ያልነው፣ ለኢትዮጵያዊነት ብለን ነው፡፡ ነገር ግን ተገቢ አይደለም፡፡ ሌላም ማሳያ ልጠቅስ እችላለሁ፡፡ በቅርቡ ለውጥ መጣ ተብሎ የተሠራ ዶክመንተሪ ነበር፡፡ በዚያ ዶክመንተሪ ላይ ተጐጂው ኦሮሞና አማራ፣ ጎጂው ወይም ገራፊውና ደብዳቢው ትግርኛ ተናጋሪ ተደርጐ ቀርቧል:: ትግርኛ ተናጋሪ የሚለው አነጋገር፣ የህወኃት መገለጫ አይደለም፡፡ የትግርኛ ተናገሪ ህዝብን ነው የሚያመለክተው፡፡ ለምን ትግርኛ ተናጋሪ ብሎ መግለጽ ተፈለገ? የትግራይን ህዝብ የህልውና ትግል ውስጥ የከተተው፣ ይሄ ሁሉ ተደማምሮ ነው እንጂ ህወሓትን ወዶት አይደለም፡፡
በሌላው የሀገሪቱ አካባቢ የታየው ለውጥ፤ በትግራይ እውን አልሆነም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በናንተ በኩል፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በነፃነት ማካሄድ ትችላላችሁ?
አዎ እንችላለን፡፡ እንደውም በትግራይ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የተሻለ የፖለቲካ ምህዳር አለ ብዬ ነው የማስበው፡፡
እንዴት? በምንድነው የሚሻለው?
ለምሣሌ በፌደራሊዝም ጽንሰ ሃሳብ፣ የራስና የጋራ አስተዳደር የሚባል ነገር አለ፡፡ የጋራ አስተዳደር፣ በጋራ መመካከር የሚመጣ ነው፡፡ የፌደራል መንግስቱ ማለት ነው፡፡ የራስ አስተዳደር ደግሞ በራስ ክልል ውስጥ የሚሆን ነው፡፡ ጭቆናም ካለ እዚያው የሚኖር እንጂ ከላይ የሚመጣ መሆን የለበትም፡፡ ስለዚህ በትግራይ ያለው ፖለቲካ፤ ትግራይ በቀል ነው፡፡ ጭቆናውም ትግራይ በቀል ነው፤ መፍትሔውም ትግራይ በቀል ነው፡፡ ጭቆናው ከሌላ ቦታ አለመምጣቱ ለኛ ትልቅ ፀጋ ነው፡፡
በትግራይ ማንኛውንም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በነፃነት ማካሄድ የሚያስችል ነፃነት አለ?
አዎ አለ፡፡ ነፃነቱ አንፃራዊ ቢሆንም አለ፡፡ ቢያንስ ሠላም አለ፤ ገብቶ መውጣት ይቻላል፡፡
ሠላሙ የሰፈነው በህግ የበላይነት ነው ወይስ በመሣሪያ አፈሙዝ?
በመሣሪያ የበላይነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ማወቅ ያለብን፣ በሌላው አካባቢ፣ በመሣሪያም ሠላም ማስፈን አልተቻለም፡፡  ለህግ መግዛት፣ በህግ መግዛት፣ ያለ ህግ ማስተዳደር የሚባሉ ሃሳቦች አሉ:: አሁን ትግራይ ላይ ያለው (rule by law) በህግ ማስተዳደር ነው፡፡ ለህግ እየተገዛን ነው እንጂ በህግ እየተገዛን አይደለም፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ ያለው፣ ያለ ህግ መገዛት ነው፡፡ ትግራይ ላይ ግን ቢያንስ ለህግ መገዛት አለ፡፡ በአሁኑ ወቅት ትግራይ ከሌላው ኢትዮጵያ ምንም የጐደለባት የለም ማለት ይቻላል፡፡ ቢያንስ ያለ ህግ መገዛት የሚባል ነገር የለም፡፡
ህወኃት ‹‹ጠላት መጣብህ›› እያለ ህዝቡን እያስፈራራ ለመግዛት እየሞከረ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እናንተስ?
ህወኃት እውነቱን ነው፡፡ በዚህ በኩል እንደግፈዋለን፡፡ ሊያጠፉን የመጡ ሃይሎች እጃቸውን እስኪሰበስቡ ድረስ በዚህ መንገድ እንታገላቸዋለን፡፡
እነዚያ ሃይሎች እነማን ናቸው?
እገሌ ነው፣ እገሌ ናት ማለት አያስፈልግም፤ ራሳቸው በግብራቸው እየተገለጡ ነው፡፡ ጉዳዩ አስተሳሰብ ነው፤ በግለሰቦች የሚወከል አይደለም፡፡ ፋሽስት የሆነ አስተሳሰብ እስካለ ድረስ ህዝቡ ለዚህ እንዲዘጋጅ ማድረግ አለብን፡፡
ምን ዓይነት ኢትዮጵያን ነው የምትፈልጉት?
ኢትዮጵያ ውስጥ ትክክለኛ የፌደራል ስርአት እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ ድብብቆሽ ላይ የተመሠረተ፣ በተረኝነት የተመሠረተ፣ ‹‹እኔ አብላጫ ህዝብ ስለሆንኩ ልመራህ ይገባል›› በሚል አስተሳሰብ ውስጥ መኖር አንፈልግም፡፡ ሁላችንም እንደ አንድ ዜጋ፣ መብታችን ተከብሮ ነው መኖር ያለብን:: ክልሎች የክልልነታቸው መብት ሳይሸራረፍ የሚከበርበትን ኢትዮጵያ ነው የምንፈልገው፡፡ አባቱ በሠራው ሃጢያት ልጅ የማይወቀስባትን ኢትዮጵያ ነው የምንሻው፡፡
ሚኒሊክ ባጠፋ የሚኒሊክ ልጅ፣ መንግስቱ ባጠፋ የመንግስቱ ልጅ፣ መለስ ባጠፋ የመለስ ልጅ፣ ዐቢይ ባጠፋ የዐቢይ ልጅ… የማይወቀስባትን ኢትዮጵያ ነው የምንፈልገው፡፡ ሰው ራሱ ባጠፋው ራሱ ነው መጠየቅ ያለበት እንጂ ልጁ ወይም ዘመዶቹ መሆን የለበትም፡፡ በዚህ ረገድ መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ መምጣት አለበት፡፡  

Read 3703 times