Sunday, 18 August 2019 00:00

እናትና ልጅ በአዲሱ የኢቦላ መድሃኒት መፈወሳቸው ተነገረ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 የኢቦላ ቫይረስ ተጠቂዎችን 90 በመቶ እንደሚያድን የተነገረለትና ባለፈው ማክሰኞ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ይፋ የተደረገው አዲሱ የኢቦላ መድሃኒት፣ በቫይረሱ ተጠቅተው በማዕከል ውስጥ የነበሩ እናትና ልጅን ሙሉ ለሙሉ መፈወሱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ረቡዕ ዕለት ይፋ ያደረገውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በኢቦላ ቫይረስ ተጠቅተው ጎማ በተባለው አካባቢ በህክምና ማዕከል የነበሩና በአዲሱ መድሃኒት ህክምና የተደረገላቸው ሁለት የአገሪቱ ዜጎች ሙሉ ለሙሉ ተፈውሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል፡፡
ኤምኤቢ114 የተባለውና በአሜሪካ ሳይንቲስቶች የተሰራው አዲሱ የኢቦላ መድሃኒት ውጤታማ መሆኑ መረጋገጡን ተከትሎ፣ በቫይረሱ የተጠቁ ሌሎች ሰዎችን በአፋጣኝ ለማከም ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ዘገባው አመልክቷል፡፡ በአዲሱ መድሃኒት ከህመማቸው የተፈወሱት እናትና ልጅ፣ መድሃኒቱ በተሰጣቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ድነው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ተስፋ ቆርጠው የነበሩ ቤተሰቦቻቸውና የአካባቢው ነዋሪዎች በደስታ ደማቅ አቀባበል እንዳደረጉላቸውም ገልጧል፡፡
የአዲሱ መድሃኒት መገኘት በኢቦላ ሳቢያ ወደ ከፋ የጤና ቀውስ ልትገባ ከጫፍ ደርሳ ለነበረችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች አገራትም ትልቅ የምስራች መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ኢቦላ ባለፉት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ በኮንጎ ከ1 ሺህ 900 በላይ ሰዎችን ለሞት መዳረጉንም አስታውሷል፡፡

Read 3679 times