Saturday, 17 August 2019 14:08

የጣፋጭ ግጥሞች ቅኝት

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

 ግጥም፤ ዜማ የተነከረ ቃል፣ የተመረጠ ሀሳብና ከፍታ ስለሆነ፣ በዝርው ከሚጻፉት ይልቅ ለልብ ይቀርባል። እኛ አገር ሁሉም እጁን እየሰደደበት ዝቅ አለ እንጂ በእጅጉ ዘውድ የደፋ ጥበብ ነው:: እረኛ አጥቶ ባከነ እንጂ የጥበብ ዕንቁ ነው፡፡ ያለ ልክ አደባባይ ላይ እየወጣ ግን ስንዴውን እንክርዳዱ ውጦት፣ ቀልሎ ታየ፡፡
ቀደም ካሉት አመታት፣ የግጥም መጻሕፍት ህትመት ያነሰው በ2010 ዓ.ም ነበር፡፡ በሚገርም ሁኔታ የታተሙት ከአስራ አምስት በታች መሆናቸው፣ ምክንያቱን ለማወቅ የሚያጓጓ ነው፡፡ ጉጉቱን ለአጥኚዎች ትቼ፣ ከነዚያ ጥቂት ህትመቶች ውስጥ የተሻለ ውበትና እውነት ያየሁበትን የገጣሚ መዘክር ግርማን ‹‹ወደ መንገድ ሰዎች›› የተሰኘ መድበል ለመዳሰስ እሞክራለሁ። ዳሰሳዬ ከሌሎች አላባዎች ፍተሻ ይልቅ ሀሳብ ላይ የተቃኘ ይሆናል፡፡ ‹‹ጅብ ድሮና ዘንድሮ›› በሚለው ልጀምር፡-
የድሮ ጅብ ትህትናው
ከማያውቁት ሄዶ ‹‹ቁርበት አንጥፉልኝ››
ነበረ ልመናው።
የዛሬ ጅብ ድፍረቱ
ባለቤቱ እያየው፣ ባይኑ በብረቱ
ይሰለቅጥና፣ ላሚቱን ዘርግፎ
እብረቱ ያድራል፣ ቁርበቷን አንጥፎ፡፡  
የዚህን ግጥም ፍካሬያዊ ፍቺ ይዞ መነሳት፣ ለግጥሙ ሀሳብ ጥሩ መንደርደሪያ ይሆናል የሚል ምርጫ አለኝ፡፡ ‹‹ጅብ›› የሚለውን ባለ አራት እግር ሳይሆን ባለ ሁለት እግር ጅብ መውሰድ ያዋጣል፡፡ ከርሳም፣ ሆዳም፣ ዘራፊ፣ ቀማኛ ብንለው ለዘመናችን አውድ ትክክለኛውን መልክ ይሰጠናል፡፡ የኛ ዘመኑ፤ ጅብ ዐይን ያወጣ በአደባባይ የሚዘርፍ፣ ዘርፎ እዚያው አጠገባችን ፎቅ የሚሰራ ነበር፡፡ የድሮ ጅብ የዘረፈውን ዘርፎ፣ ፊት ለፊታችን ፎቅ አይገትርም፤ ውድ ሸቀጦች አንጠልጥሎ፣ በውድ መኪና ጡሩንባ እየነፋ አያደነቁርም። ባይሆን ወደ ሌላ ቦታ ዞር ብሎ፣   ሰርቶ ያገኘው እንዲመስል፣ ብዙ መላ ይፈጥራል፡፡ አሁን ግን ነገሩ ሁሉ የግሪንቢጥ ሆኖ፣ ከኛው በልቶ እኛው ላይ ያገሳል፡፡
መጽሐፉ ውስጥ በርካታ የፍቅር ግጥሞች አሉ:: በአጠቃላይ ፍቅር ፍቅር የሚሸተቱ ስንኞች ብዙ ናቸው፡፡ አጫጭርም ረዣዥምም አሉ፡፡ ጥቂቱን ማየት ያዝናናል፡፡ ‹‹የአፍቃሪ ስንብት›› የሚለውን እነሆ፡-
እሄዳለሁ ብለሽ ሻንጣሽን ካነሳሽ
ትናንትናችንን በዛሬ ከረሳሽ
አላስገድድሽም መሄድ ካሻሽ ሂጂ
ባይሆን ተከትዬሽ እመጣለሁ እንጂ፡፡
‹‹ካልሄድኩ›› ብላ እግሯን ያነሳች ተፈቃሪ አለች:: ይህች ሴት ዛሬ የበቀለች አይደለችም፤ ትዝታ ቋጥራለች፣ ፍቅርን ጎርሳለች፡፡ ግን ያ ምስል፣ ያ ጥፍጥና የጠፋት ይመስላል፡፡ ሌላ ቦታ አምሯታል:: ግጥሙ ውስጥ የሚናገረው ገፀ ሰብ ደግሞ ‹‹ቅሪ!›› ብሎ ሊያስገድዳት አልወደደም፡፡ ‹‹ትሂድ!›› ብሎ ሊያሰናብታትም አልሆነለትም፡፡ ስለዚህ ‹‹ ትሂድ›› ብሎ እርሱም ተከትሏት ሊሄድ አስቧል፡፡ ከራሱ ጋር እየተጓተተ፣ ከነፍሱ ጋር እየተሟገተ የተሸነፈ ይመስላል። ግማሽ ትዝታ፣ ግማሽ ተስፋ! ይህ ደግሞ ያጋጥማል፡፡ ‹‹Poetry comes to us bringing life›› የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ሕይወት ይዞ ይመጣል፡፡ ሕይወት ውስጥ የሳቅ ብርሃን፣ የእንባ ነጠብጣቦች አሉ፡፡ ግና ገጣሚ አይሰብክም፣ ገጣሚ አያስተምርም!... የነፍሱን ዘንግ በሚያወዛውዘው ወጀብ ውስጥ ሆኖ ቀለሙን ይረጫል።
ገጣሚው ስለ ፍቅር በተለይ ስለ ማራኪነት የፃፉት አንድ ግጥም፤ ሙዚቃው ሳይቀር ነፍስ ያስደንሳል፡፡ አድናቆቱ እንደ ፊልም አንዲቷን - ቀዘብ - ውልብ  ያደርጋል፡፡
‹‹ደማምዬ ልጅ ናት››
ከዘፈን ገላዋ፣ ከለምለም እወዳ
ቀምሞ የሰራት፣ እሪኩም ዘመዳ
ደማምዬ ልጅ ናት… በደማምነቷ
የተከለከለ፣ በተስኪያን መግባቷ፡፡
መድረኩን ቢነሷት፣
ማህሌት ቢገፏት፣ ባይሰጧት ዲቁና
ከንፈሯ ለሃሌ፣ አይኗ ለትወና…
የጻፈችም እንደሁ፣ ጥርሷን አስመስላ
ያወራችም እንደሁ፣ ልብ ጨርቅ አስጥላ
የሳቀችም እንደሁ፣ እርግፍ እንደ ሾላ!
እርግፍ እንደ ሾላ፣ ቁጣዋን ሰምቼ
እሆዷ እንድገባ፣ በጇ ተነስቼ፡፡
ግጥምን ከሙዚቃ ነጥለን ሀሳብ ብቻ ነው ብለን ለምንሞኝ ሰዎች፤ ዜማ ምን ያህል ምትሀት እንዳለው የምታሳይ ግጥም ናት። ቤት አመታቷ፣ ከአናባቢ መረጣ ጀምሮ የተሳካላት ናት፡፡ የስነ ግጥም ተመራማሪው ኢ. ኤኒ ግሪዲንግ ላምቦርን የሚለውንም ማስታወስ ይሄኔ ነው፡፡  ‹‹The first and most fatal mistake we can make in regard to poetry is to forget the poetry was born of music››
ይህ ሀሳብ ሁሌ ሊታሰብ የሚገባ ነው፡፡ ከሙዚቃ ጋር የተወለደው የማህጸን ልጅ፣ ደረቅ ቃልና ሀሳብ ለሚመስለን ሰዎች፣ መዘንጋት የሌለበት መድኃኒት ይመስለኛል፡፡
ገጣሚው፣ የተቃራኒ ፆታ ፍቅርን ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ፍቅርንም በግጥሞቹ ቃኝቷል፡፡ ብዙ የአገራችንን ገጣሚያንን ያማለለ፣ ብዕር ያስመዘዘው መስከረም እርሱንም በውበት ጥቅሻ፣ በውበት ጉርሻ፣ ቀልቡን ስቦታል፡፡ ጥቂት ስንኞቹን እወስዳለሁ፡፡ ‹‹የምስራቺቱ›› የሚል ርዕስ ሰጥቶታል፡፡
መሽቶ ለጠፋ’ቃ፣ ሲነጋ እንፈልገው
             ብሎ ለተባለ
የሆነ ፈገግታ ንጋት የመሰለ
ቃል ጠቋሚ ጥቅሻ፣ ሽፋኗ ላይ አለ፡፡
አረንጓዴ ለብሳ
ቢጫ ጽጌ ሆና
ተሸግና ታየች
በቀይ ፀደና፡።
‹‹መፍርህ›› ነሽ እንበላት፣ ‹‹መደንግድ›› ነችና
ታምር ነሽ እንበላት፣ አንች አበባ ለምለም
‹‹የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ
‹‹ቀጠሮ እንዳላቸው›› ታውቃለች መስከረም፡፡
አደይ አበባውንና የአዲሱን ዓመት ልምላሜ፣ ቀለም የተነከረ ውበት፣ ከእንቁጣጣሽ ዜማ አዛንቆ፣ እንደ ታምር ከቆጠራት በኋላ፣ የመንግስቱ ለማን ግጥም፣ በጠቃሽ ዘይቤ ጠቅሶ፣ በዜማ አስዘንጧታል:: ሎውረንስ ፔሪኔ፤ ‹‹ግጥም አያስተምርም፣ ግን ይነሽጣል!›› ያሉት ለዚህ ይሆን!
ውበቷን በዘይቤ ዋንጫ አስጨብጦ፣ ሽፋሏን ኩሎ፣ መስከረምን በአዲስ ዜማ፣ የተስፋ አብሳሪ አድርጓታል፡፡ መስከረም የማትቀሰቅሰው እንቅልፍ - ዜማ የማትነጥቀው ከያኒ የለም፡፡ የአደይ አበባ - የአመት ናፍቆት፣ የወንዞች ዜማ፣ የሰማይ ገፅ - ሁሉም ያጓጓል፡፡ ሁሉም ያባባል፣ ሁሉም ይርባል። ገጣሚውም ይህንን የተፈጥሮ እውነት፤ በጥበብ አድምቆት ብቅ ብሏል፡፡ ዞሮ ዞፎ ሥራው ይሄው ነዋ!
‹‹Art has nothing to do with absolute truth; it shows truth colored by the artist mood;.. ››
‹‹አንድ ዘፈን አለ›› በሚል ርዕሰ ከጻፈው ግጥም አንድ አንጓ ወስጄ፣ በሙዚቃው ስልትና በሀሳቡ አሻራ ብንጫወት ብያለሁ፡-
የወደድሽው ዘፈን፣ የመረጥሽው ዜማ
ዓመታት ቢያልፉትም፣ ለሰው ከተሰማ
የድሮ ቢሆንም፣ ብዙ ዓመት የኖረ
በኔና አንቺ ቤት ግን፣ ሁሌ እንደጀመረ፡፡ አየሽ…
አገሬው አላምጦ የጨረሰው፣ ተደንቆ ያበቃው ዘፈን…፣ ተደምሞ የተወው ስልትና ቃል፣ ለኔና አንቺ እንደ ቀትር ፀሐይ እየሞቀ የሚሄድ፣ እየደመቀ የሚደንቅ ነው ይላታል፡፡ ዓመታት ቢቆጠሩም ለኔና አንቺ ግን ገና ትኩስ፣ መዐዛው ነፍስን የሚነቀንቅ፣ ቀልብን የሚነጥቅ ነው እያላት ነው፡፡ ይህ ሕግ የፍቅር ሕግ ነው፡። ጊዜ ነገሮችን ሁሉ የሚያስረጅበትን ሕግ፤ የፍቅር አጥር አያስገባውም!... ፍቅር ሁልጊዜ አዲስ፣ ሁልጊዜ ብርቅ ነው። ፀሐይ ዘመን ቆጥራ አትሸብትም፣ ጊዜ ሞልታ አትሞትም፡፡ በመንታ ልቦች ላይ የበቀለ ፍቅርም እንዲሁ ነው፡፡ ማልዶ አይጠወልግም፣ ማልዶ አይከስምም፡፡ አድማሱ በሳቅ ጥርሶች እየነደደ ይኖራል እንጂ!
ገጣሚው መዘክር፤  ፍቅርን በውበቱ፣ ፍቅርን በትኩሳቱ፣ ሕይወትን በተስፋው፣ ሀዘንን በጭጋጉ በየመልኩ አስቀምጦታል፡፡ የገጣሚ እጣም ይኸው ነው፡፡

Read 1867 times