Print this page
Saturday, 17 August 2019 14:30

የ RIDE (ራይድ) የ5 ዓመት ጉዞ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 - በ40 ሺህ ብር ካፒታል ተጀምሮ፣ 4 ሚሊዮን ብር ደርሷል
      - ወደ ክልሎችና ምስራቅ አፍሪካ የማስፋፋት ዕቅድ ተይዟል

            በሙያዋ የኮምፒዩተር ፕሮግራመር ናት፡፡ ተቀጥራ ትሰራ በነበረችበት ጊዜ የራሷን ቢዝነስ ለመጀመር በማሰብ ከምታገኘው ደመወዝ ላይ መቆጠብ ጀመረች፡፡ የቆጠበችው ገንዘብ 40 ሺህ ብር ሲደርስላት፣ ‹‹ራይድ›› የተሰኘውን ታክሲና ተሳፋሪን በቴክኖሎጂ የማገናኘት ፕሮጀክት ቀረፀ፣ የዛሬ 5 ዓመት፡፡ ይህን ቴክኖሎጂ ለአሽከርካሪዎችና ለተጠቃሚዎች ለማስለመድና ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደገጠማት ታስታውሳለች:: የ‹‹ራይድ›› መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወ/ት ሳምራዊት ፍቅሩ፡፡
በአሁን ወቅት ከ4 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎችን በ‹‹ራይድ ሥር በማስተዳደር ለአዲስ አበባ ከተማ ደረጃውን የጠበቀ፣ ምቹና አስተማማኝ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ትገኛለች:: የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ “ከራይድ” መስራችና ፈጣሪ ወ/ት ሳምራዊት ፍቅሩ ጋር በቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ በትራንስፖርት አገልግሎት፣ በ “ራይድ” የወደፊት ዕቅድ ዙሪያ አውግተዋል፡፡ ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች፡፡

         የ “ራይድ”ን ጉዞና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ጠቅለል አድርገሽ ንገሪኝ…
በአምስት ዓመት ጉዞ ውስጥ ብዙ ውጣ ውረድ አልፏል። እንደ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅት ብዙ ለፍተንና ዋጋ ከፍለን ነው ለዚህ የደረስነው። ከአምስት አመት በፊት ቢመሰረትም፣ በደንብ መታወቅ የጀመረው ከሁለት ዓመት ወዲህ ነው። ዋናው ፈተና የሆነብን ቴክኖሎጂውን፣ አሽከርካሪው እንዲያውቀውና እንዲያምንበት የማድረጉ ሥራ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ለአንድ አመት ያህል እንደውም በነፃ ስንሰራ ነው የቆየነው። ሌላው ፈተና፣ በመንግስት በኩል የገጠመን ነው፡፡ መንግስት ሲባል በዚህ ዘርፍ ስራችን ይጎዳል ብሎ ያሰበውን አካል ማለቴ ነው፡፡ ሌላው የመሰረተ ልማት ችግር፣ ማለትም የኢንተርኔትና መብራት መቆራረጥና መሰል ችግሮች ናቸው፡፡ ሆኖም እንደ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅት፣ ብዙ ፈተና ሊገጥመን እንደሚችል ገምተን ስለገባንበት፣ በምን መልኩ ችግሩን እንቋቋመዋለን በሚለው ላይ ነበር አተኩረን ስንሰራ የቆየነው፡፡
እንደነገርኩሽ ደሞዜን አጠራቅሜ ነበር ወደ ስራው የገባሁት፡፡ እናም ኢንቨስትመንት ማግኘት ከባድ ነበር፡፡ ብዙ ለፍተን ነው ኢንቨስትመንት ያገኘነው፡፡ በቅርቡ ነው ትንሽ እፎይ ያልነው፡፡ ከዚያ በፊት እጅግ ከፍተኛ ድካም ውስጥ ነበርን ማለት ይቻላል፡፡
በምን ያህል ካፒታል ስራውን ጀመርሽ? አሁን ስንት ደረሰ?
በ40 ሺህ ብር ነበር ስራ የጀመርነው፡፡ ከዚያ 600 ሺህ ብር ደረሰ፡፡ ከዚያ ደግሞ 4 ሚ.ብር… እያደረግን ነው ያስፋፋነው፡።
ብዙዎች ከውጭ አገር እንደመጣሽ፣ ውጭ አገር መኖርሽ ለስኬትሽ አስተዋፅኦ ማድረጉን ሲናገሩ  እሰማለሁ፡፡ ውጭ ነበርሽ?
በፍፁም! እኔም ብዙ ሰው፣ አሜሪካ ኖሬ እንደመጣሁ ሲያወሩ ነው የምሰማው፡፡ እኔ አሜሪካ ግን ሄጄ አላውቅም፡፡ አገር በቀል ነኝ። እዚሁ ደመወዜን አጠራቅሜ ነው ስራ የጀመርኩት፡፡ በአገሬ ላይ ኮምፒዩተር ፕሮግራመር ሆኜ ስሰራ ነው የነበረው፡። ከቴክኖሎጂው ጋር ያለኝ ቅርበት ነው ወደዚህ ስራ ያስገባኝ፡፡ ደመወዜንም ያጠራቀምኩት፣ በተለያዩ ቦታዎች ተቀጥሬ እሰራ በነበረበት ወቅት ነው፡፡
ከስራው ጋር ተያያዞ በተለያዩ ጊዜያት ውዝግቦች ንትርኮች ገጥሞሻል፡፡ ድርጅቱ የተፈቀደለት የስራ ዘርፍ ሶፍትዌር የማበልፀግ እንጂ በትራንስፖርት ዘርፍ የመሰማራት አይደለም የሚለው ይገኝበታል… ተሳስቻለሁ?
በጣም የሚገርም ነው! እስኪ ቴክኖሎጂ የሌለበትን የስራ ዘርፍ ንገሪኝ፡፡ ለምሳሌ የፋይናንስ ዘርፍ እንውሰድ፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ያለ ቴክኖሎጂ ምንም ነው። የሽያጭ ዘርፍን ውሰጂ፡፡ የጤናን ዘርፍ እንመልከት፡፡ ያለ ቴክኖሎጂ ማሰብ አይቻልም። አንድ ሰው እቃም ይሸጥ፣ አገልግሎትም ያቅርብ ቴክኖሎጂ ይጠቀማል፡፡ በአጠቃላይ ቴክኖሎጂ የሁሉም ዘርፍ የጀርባ አጥንት ነው። እኛ በቴክኖሎጂ ታግዘን የትራንስፖርቱን ሥርዓቱን አሳለጥን፡፡ እኛ በቀጥታ የትራንስፖርት አገልግሎት አንሰጥም:: ነገር ግን ትራንስፖርት አቅራቢው አለ፡፡ በሌላ በኩል ትራንስፖርት ፈላጊው አለ፡፡ የእኛ ቴክኖሎጂ ሁለቱን ተፈላላጊ አካላት ነው የሚያገናኘው፡፡ ስልክ ደውለው እንደሚገናኙት ሁሉ፣ እኛ ቴክኖሎጂውን አስፍተን፣ አማራጭ ጨምረን አቀረብን፡። በእኛ ቴክኖሎጂ ሥር እንዲገናኙ አደረግን፡፡ ይሄ ጥቅም እንጂ ምን ጉዳት አለው!?
ተመሳሳይ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ቢኖሩም አሉ፡፡ በስፋት የሚታወቀው የእናንተ ነው ልበል… እናንተ ከሌላው በምንድነው የምትለዩት?
የምንለየው በቴክኖሎጂያችንም በአሰራራችንም ነው፡፡ አሰራራችን ስል… እኛ አላማችን ንፁህ መኪና ማቅረብ፣ በአጭር ደቂቃ ውስጥ ተገልጋዩ እንደጠየቀ መድረስ እንዲሁም ትህትናና ሥርዓት ባለው መንገድ ማስተናገድ ነው፡፡ ይሄንን ሰው ወዶታል:: ቴክኖሎጂውም በጥሩ ሁኔታ እየሰራ ነው፡፡ ለአሽከርካሪዎቻችን በምንሰጣቸው ስልጠና መሰረት ጥሩ አገልግሎት ይሰጣሉ፣ ከጀመርንም ቆይተናል፡፡ ብዙ ጥናቶችን ሰርተን ያለውን ክፍተት አይተናል:: ይሄ በስራችን ውጤታማና ተመራጭ እንድንሆን አድርጎናል ብዬ አምናለሁ፡፡
በስንት አሽከርካሪ ጀምራችሁ አሁን ስንት ደረሳችሁ?
ስንጀምር 20 ተሽከርካሪዎችን ይዘን ነበር:: ከዚያ 100 ደረሱ፡፡ ቀጥሎ 450፡፡ አሁን በሺዎች ይቆጠራሉ፡፡ በትክክል ቁጥሩን ባልነግርሽም በሺዎች የሚቆጠሩ አሽከርካሪዎች ከራይድ ጋር እየሰሩ ነው:: ለብዙ ወጣቶች የስራ እድል ፈጥረናል፡፡ በቀጥታና በተዘዋዋሪ እስከ 100ሺህ ለሚደርስ ሰው እየጠቀምን ነው ብለን እናስባለን፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ወጣት አሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ ወጣት ሆነው በልጅነት አግብተው የወለዱ፣ አባትና እናታቸውን የሚደግፉ፣ አያቶቻቸውን የሚጦሩና እህት ወንድሞቻቸውን የሚያስተምሩ ይገኙበታል፡፡
የከተማውን የትራንስፖርት ችግር ከመቅረፍ አንጻር ምን አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ ብለሽ ታስቢያለሽ? ከከተማው ትራንስፖርት ቢሮ ጋር የገባሽበት እሰጥ አገባስ ከምን ደረሰ?
ከትራንስፖርት ቢሮው ጋር ያለው ጉዳይ በፍርድ ቤት ስለተያዘና እግድ ስለወጣበት አሁን ስለሱ መናገር አልችልም፡፡ የትራንስፖርት ችግርን ከመቅረፍ አኳያ የነበረንን ሪሶርስ ሳንጠቀምበት ዝም ብሎ ቁጭ ያለ ሪሶርስ ነበር፡፡ አብዛኛው መኪና ከቤት ወደ ሥራ፣ ከሥራ ወደ ቤት መመላለሻ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ወደዚህ ሥራ ገብቶ፣ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ ይሄ ማለት ‹‹Shared Economy›› ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ያንን መኪና ቢሮ ከሄደበት በኋላ ሾፌር ቀጥሮ ያሰራበታል፡፡ አንድም ለራሱ ገቢ ያገኛል፣ ሁለትም ለዚያ ሾፌር የስራ እድል ፈጠረ ማለት ነው። በታክሲ ወረፋ ሲንገላታ ለሚውለው ህብረተሰብም አማራጭ አገልግሎት አቀረበ ማለት ነው፡፡ ሌላው በአዲስ አበባ ከሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች አብዛኛው የሚደርሰው ጠጥቶ በማሽከርከር ነው የሚባለው፡፡ የእኛ አሽከርካሪዎች ጠጥተው የሚያሽከረክሩ ባለመሆናቸው፣ አደጋውን ቀንሰናል ብለን እናምናለን፡፡ 24 ሰዓት ነው አገልግሎታችን፡፡ ሰው እንደ ልቡ ስራ ላይም ይሁን ሲዝናና አምሽቶ፣ አገልግሎታችንን ስለሚያገኝ አስተዋፅኦው በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
በ‹‹ራይድ›› ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ፡፡ ከመቶ ብር 17 ብር ኮሚሽን መውሰዳችሁ ውድ ነው የሚሉ አሽከርካሪዎች አሉ፡፡ ተሳፋሪዎች ደግሞ የጥሪ ማዕከላችሁ በቶሎ አይነሳም የሚል ቅሬታ ያሰማሉ፡፡ አንቺ ምን ትያለሽ?
8294 አይነሳም ለተባለው ተጠቃሚያችን ብዙ ስለሆነ፣ የማዕከሉ አስተናጋጆች አንዱን አስተናግደው እስኪጨርሱ ትንሽ የመጠበቅ ጉዳይ አለ፡፡ ተራቸው እስኪደርስ ሙዚቃ እየሰሙ ይቆያሉ፡፡ ያ እንግዲህ በሰው ሀይል ውስንነትና በቴክኖሎጂ አለመስፋት የተፈጠረ በመሆኑ፣ የሰው ሀይል እስክንጨምርና ቴክኖሎጂያችንን እስክናሰፋ በደንበኞች ላይ ለደረሰው መጉላላት እናዝናለን፡፡ ነገር ግን አሁንም እናዝናለን ብቻ ብለን አልተቀመጥንም፡፡ ቴክኖሎጂያችንን አስፍተናል። የሰው ሀይላችንንም አሳድገናል፡፡ አንድ ሰው በጥሪ ማዕከሉ ደውሎ 23 ሰከንድ ነው የሚጠብቀው፡፡ ቢበዛ 48 ሰከንድ ነው፡፡ አሁን የጥሪ ማዕከላችንን ወደ አራት እጥፍ አሳድገናል:: የሰው ሃይላችንን በ50 በመቶ አሳድገናል፡፡
17 በመቶ ኮሚሽን ትወስዳላችሁ የተባለው ስህተት ነው፡፡ የምንወስደው 12 በመቶ፣ 15 በመቶና 17 በመቶ ነው የምንወስደው፡፡ ልዩነታቸው ምንድነው ካልሽኝ፣ ለምሳሌ በወር 120 እና ከዚያ በላይ ምልልስ (ትሪፕ) ለሰራ ሰው፣ ማለትም በቀን 4 እና ከዚያ በላይ ለሰራ አሽከርካሪ 12 በመቶ ነው የምንወስደው። በቀን ሁለት ወይም በወር 60 ምልልስና ከዚያ በላይ ለሰራ 15 በመቶ እንወስዳለን:: በቀን አንድ ለሰራ ወይም ምንም ለማይሰራ ማለትም በወር 30 እና ከዚያ በታች ለሚሰራው 17 በመቶ እንወስዳለን፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡን በደንብ የሚያገለግል 12 በመቶ ነው የሚቆረጥበት፡፡ ይሄ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ በርትቶ ከሚሰራው ላይ ትንሽ ኮሚሽን ነው የምንወስደው፡፡ ያልበረታውን አናበረታታም፡፡
የተገልጋዩን እርካታ በምንድነው የምትለኩት? እስከ ዛሬ በአሽከርካሪዎች ላይ የቀረበ ቅሬታ አለ?
የተገልጋዩን እርካታ የምንለካው በሁለት መንገድ ነው። አንደኛው ጥሪ ማዕከላችን ላይ ደውለው አስተያየት ይሰጣሉ ወይም በኢ-ሜይል አድራሻችን ይልኩልናል፡፡ እሱ ላይ አይተን ቶሎ ቶሎ ምላሽ እንሰጣለን፡፡ ችግር እንኳን ቢኖር በ24 ሰዓት ውስጥ መፍትሄ እንሰጣለን፡፡ እስካሁን ከሰው የምናገኘው ግብረ መልስ በጣም ደስ የሚል ነው፡፡ ጥቃቅን ስህተቶችን ሲመለከት ተገልጋዩ ቶሎ አስተያየት የሚሰጠው፤ ይሄንን አገልግሎት እንዳናጣ በሚል ስስት ነው፡፡
አንድ የራይድ አሽከርካሪ ቀኑን ሙሉ በደንብ ቢሰራ ምን ያህል ገቢ ያገኛል? ጥናት መቼም ትሰራላችሁ ብዬ ነው፡፡…
ይሄንን ባልናገር እመርጣለሁ፡፡ አሰራሩን ከካሽ ውጭ የሆነ ሲስተም ውስጥ እስክናስገባው ባልናገር ጥሩ ነው፡። ከዚህ በፊት አንድ ሬዲዮ ላይ ተናግሬ የተወሰኑ የራይድ አሽከርካሪዎች ዝርፊያ ተፈፅሞባቸዋል፡፡
አንድ ቱሪስት አገር ውስጥ ሳይገባ በፊት አገልግሎታችሁን ማግኘት ቢፈልግ ያመቻቻችሁት ነገር አለ? ከአዲስ አበባ ውጭስ ምን አስባችኋል?
ዛሬ አዲስ አበባ ላይ እንጀምር እንጂ ወደ ክልል ከተሞች የማስፋት እቅድ አለን፡፡ ክልል ብቻ ሳይሆን ወደ ምስራቅ አፍሪካም እንሄዳለን:: መጀመሪያ ግን የአዲስ አበባውን በደንብ እንስራው፡፡ ከዚያ ወደ ክልልም ሆነ ወደ ምስራቅ አፍሪካ እናሰፋዋለን። ምስራቅ አፍሪካ ስንሄድ ለማኔጅመንትም ሆነ ለተለያዩ ስራዎች የራሳችንን ሰዎች ነው የምንወስደው። ከተቻለም ክፍያውን በዶላርም ሆነ በራሳቸው ምንዛሪ ሲከፍሉን፣ በራሳችን ባንኮች በኩል ወደ አገራችን እንዲመጣ ለማድረግ፣ ባንኮችም ይዘን የመሄድ እቅድ አለን፡፡ በሀዋሳ ባህርዳር፣ ጎንደርና መሰል ከተሞች ሥራውን የማስፋት እቅዳችን እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡ ቱሪስቶችን በተመለከተ አሁን ላይ አገልግሎቱን ያውቁታል:: አፕሊኬሽኑን (መተግበሪያውን) በደንብ ይጠቀሙበታል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ ሆነው ቅድመ ትዕዛዝ፣ በአፕልኬሽኑ ላይ ስላለ፣ እሱን ተጠቅመው ያዝዛሉ። እኛ ሹፌሮችን እንመድብና ኤርፖርት ሄደው ይቀበሏቸዋል፡፡ ስለዚህ ቱሪዝሙን በማዘመን ረገድ የበኩላችንን እየተወጣን ነው፡፡
በሌላ በኩል ከትንንሽ መኪናዎች በተጨማሪ ወደ አውቶቡሶችም እንገባለን፡፡ አሁን ቴክኖሎጂው አስፈላጊ ነው። ሰው አንድ ቦታ ተሰልፎ አውቶቡስ ይጠብቃል፡፡ አውቶቡሶች አንድ ቦታ ተከማችተው ያለ ስራ ይቆማሉ፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ወደ አውቶቡሶች ፊታችንን እናዞራለን፡። ይሄም በቅርብ ዕቅዳችን ውስጥ የተካተተ ነው፡፡
ለእናንተ ሥራ በጣም ወሳኙ ኢንተርኔት ነው፡፡ ኢንተርኔት ሲቋረጥ ምን ታደርጋላችሁ? በዚህ ጊዜ በስራችሁ ላይ ምን ያህል ኪሳራ ይደርሳል?
በቅርቡ እንኳን ሲቋረጥ ኪሳራውን አላሰላነውም እንጂ በደንብ ጎድቶናል፡፡ ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም:: በማኑዋል የተወሰነ ያህል ለመስራት ሞክረናል፡፡ ለምሳሌ የዱቤ አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞቻችን ስለነበሩ፣ መኪና መድበንላቸው እንዲጠቀሙ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ በጣም ደንበኛ የሆኑት ደግሞ ሲደውሉ መኪና እየመደብንላቸው ሲጠቀሙ ነበር፡፡ ነገር ግን በደንብ ጎድቶናል፡፡ በአገር ኢኮኖሚም ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ ይሄን ያህል ገንዘብ አጥተናል ብለን ግን በሂሳብ ደረጃ አልሰራነውም፡፡
የእናንተ አሽከርካሪዎች ከሌሎች የዘርፉ አሽከርካሪዎች ደብደባ፣ የመኪና መሰበርና መሰል ጥቃቶች ይደርሱባቸው እንደነበር ሰምተናል፡፡ አሁን ለአሽከርካሪዎቹ የምትሰጡት የደህንነት ጥበቃ ወይም ከለላ አለ?
አሁን በሕግ እግድ አውጥተናል፡፡ አሽከርካሪዎቹ ላይ ምንም አይነት ጥቃት እንዳይደርስባቸው ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል በየፖሊስ ጣቢያውም እየዞርን ‹‹ራይድ›› ህጋዊ እንደሆነ አሳውቀናል፡፡ ‹‹ራይድ ሕገ ወጥ ነው›› ብሎ ከገለፀው አካል ጋር ጉዳያችን ፍርድ ቤት እንዳለ ገልፀናል፡። እርግጥ ነው የተወሰኑ አሽከርካሪዎች መኪኖቻቸው ላይ ጉዳት ደርሷል:: በዚህ አጋጣሚ ሌሎች አሽከርካሪዎችም ቢሆኑ እኮ ወደዚህ ሲስተም መግባት ይችላሉ፡፡ እኛም መኪናቸውን እንዲቀይሩ የባንክ ብድር አመቻችተን፣ የተወሰነ ክፍያ ቅድሚያ እየከፈሉ፣ ብድራቸውን ለባንኩ በመክፈል የ‹‹ራይድ›› ቤተሰብ መሆን ይችላሉ፡፡ የተወሰኑትንም በዚህ መልኩ እንዲሰሩ አድርገናል፡፡ ሌሎቹም ይህን እድል ተጠቅመው፣ ከኛ ጋር መስራት ይችላሉ፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ሀሳብ፣ አዲስ ፈጠራ ይዞ ኢንቨስት ማድረግ ምን ያህል ፈታኝ ነው?
እውነት ለመናገር ከምነግርሽ በላይ ከባድ ነው፡፡ በሌላ በኩል መንግስት ቴክኖሎጂን እናበረታታለን፣ ወጣቱ ቴክኖሎጂ እንዲፈጥር እንፈልጋለን ይላል:: ነገር ግን በተለይ ፕሮግራሚንግ ላይ ስንመጣ የሚያስፈልገው ነገር በጣም ቀላል ነው፡፡ ላፕቶፕ፣ እውቀትና ኢንተርኔት ካለሽ በቂ ነው፡፡ ብዙ ወጣቶች ኢንተርኔት ላይ ያነባሉ፡፡ እውቀታቸው የትና የት ደርሷል፡፡ ከአሁን በኋላ የሚፈጥሩት በሕግ ማዕቀፍ የሌለ ነገር ይሆናል፡፡ ስለዚህ መንግስት ወጣቱን የሚደግፍ፣ የሕግ ማዕቀፍ ከስር ከስር እያወጣ ካልደገፋቸው የሚገጥማቸው እንቅፋት ለአገር ጠቃሚ ቴክኖሎጂ እንዳይፈጥሩ ያደርጋቸዋል:: የሚገፉ ከሆነ ወደ ውጭ ሄደው ተከብረው ይሰራሉ፡፡ አገሪቷ እውቀት ያላቸውን ሰዎች ወደ ውጭ መላክ የለባትም፡፡ ይሄ ራሱ ኪሳራ ነው፡፡ አገር የራሷን ኤክስፐርቶች ለመጠቀም በሯ ክፍት መሆን አለበት፡፡ ፖሊሲ ነው የሚያስፈልግህ? ምንድነው የምትፈልገው? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ኢኮኖሚ የያዙት የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ናቸው፡፡ እነ ማይክሮ ሶፍት… እነ ፌስቡክንና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህ ዘርፍ በአገራችን ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ሁኔታዎች ብዙም አበረታች አይደሉም፡፡ ይሄ መቀየር አለበት፡፡
የዛሬ 5 ዓመትና 10 ዓመት ‹‹ራይድን›› የት ማድረስ ነው የምትፈልጊው?
እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ራይድ›› እንዲህ ሆነ፣ እንዲህ አደረጉት የሚለውን እንደ ትንሽ ጫጫታ ነው የምቆጥረው። በእኔ ስራ ላይ የሚመጣውንም ችግር ወደ ጥሩ አጋጣሚ ነው የምቀይረው፡፡ ኢትዮጵያ የምትታወቀው በረሃብ ነበር፡፡ በጥሩ ጎኑ ደግሞ በሩጫ ትታወቃለች፡፡ በቴክኖሎጂ በራሷ ልጆች ትልቅ ሥራ ሰርታ ካደጉት አገራት ተርታ ተሰልፋ ማየት ነው፤ የኔ ራዕይ። እንደገና በ‹‹ራይድ›› ስር የሚሰሩ ቤተሰቦች፤ ኑሯቸው ተቀይሮ፣ ልጆቻቸው የተሻለ ዕድል አግኝተው ማየት እሻለሁ:: በጎ ማህበራዊ ተፅዕኖም ማምጣት እንፈልጋለን። ከፍተኛ ውጤት ላመጡት ‹‹የራይድ›› ቤተሰብ ልጆች፣ ነፃ የትምህርት ዕድል እየፈለግን፣ በውጭ ተምረው ለአገራቸው እንዲጠቅሙ የማድረግ ዕቅድ አለን፡፡ በአሁኑ ወቅትም ብዙ ማህበራዊ ተሳትፎ እናደርጋለን። ምጥ የያዛትን ሴት በነፃ ሆስፒታል እናደርሳለን። ገላን ከተማ ላይ ባለፈው አራት ሄክታር መሬት ወስደን፣ ከ10 ሺህ በላይ ችግኝ ተክለናል፤ ለመንከባከብም ሀላፊነቱን ተረክበናል:: ብዙ ሺህ የ‹‹ራይድ›› ቤተሰቦች በተከላው ላይ ተሳትፈዋል። ከተከላው በኋላ አንድ ሳምንት ሳይሞላ አጥር አጥረናል፡፡ ጥበቃም ቀጥረናል፡፡ የከተማው ከንቲባም የምስጋና የምስክር ወረቀት ሰጥተውናል፡፡ ያንን ትልቅ ደን ማድረግ እንፈልጋለን። አዲስ አበባም ቦታ ከተሰጠንም ይህንን መድገም እንፈልጋለን፡፡
እስካሁን በገንዘብ ጉዳይ ላይ በደንብ አላወራንም:: በዚህ ዓመት ለመንግስት ምን ያህል ግብር  ከፈልሽ?
እኛ እስከ ጥቅምት መጨረሻ ገና ሂሳባችንን እያሰራን ነው፤ ነገር ግን በአሽከርካሪዎች በኩል ለመንግስት የተከፈለው ግብር 50 ሚ ብር ነው፡፡
በዓል ሲመጣ ለደንበኞችሽ የትራንስፖርት ፓኬጆችን በነፃ ታቀርቢያለሽ፡፡ ለአዲስ አመትስ ምን አቅደሻል?
በአዲስ አመት ያሰብነው ትልቅ ነገር አለ፡፡ በመስቀል አደባባይ የሚደረግ ነው፡፡ ቀኑ ሲቀርብ ነው የምገልጸው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡


Read 4351 times