Saturday, 24 August 2019 13:28

ናሽናል አቪየሽን ኮሌጅ በተለያየ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ ያስመርቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 የናሽናል አየር መንገድ እህት ኩባንያ የሆነው ናሽናል አቪየሽን ኮሌጅ፣ በተለያየ የትምህርት ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ ከጠዋቱ 2፡00 ጀምሮ፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) አዳራሽ በልዩ ስነ ሥርዓት ያስመርቃል፡፡
የኮሌጁ ሀላፊዎች ከትላንት በስቲያ ሀሙስ ረፋድ ላይ በኢሲኤ አዳራሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ኮሌጁ ከአለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA) እና እንግሊዝ አገር ከሚገኘው ኢንስቲትዩት ኦፍ ኮሜርሽያል ማኔጅመንት  (ICM) ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን 131 እጩ ተመራቂዎች ጨምሮ 71 በመጀመሪያ ዲግሪ እንደሚያስመርቅ አስታውቀዋል፡፡
 ኮሌጅ ለስድስተኛ ጊዜ ዛሬ የሚያስመርቃቸው ተማሪዎች በትራቭል ቱሪዝም፣ በበራ መስተንግዶ  (ሆስተስ)፣ በፍላይት ኦፕሬሽን፣ በሆቴልና ካጸሪንግ ሱፐርቪዥን፣ በትኬቲንግና ሪዘርቬሽን እንዲሁም በሆቴል ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ የሰለጠኑ ናቸው ተብሏል፡፡
ናሽናል አቪየሽን ኮሌጅ የናሽናል አየር መንገድ እህት ኩባንያ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ከሚንቀሳቀሱ የግል አየር መንገዶች መካከል ግንባር ቀደም መሆኑንም የኩባንያው ሀላፊዎች ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ናሽናል አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት አስማማኝ የበረራና የካርጎ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን አየር መንገዱ በአገራችን በፍጥነት እያደገ የመጣውን የአቪዬሽንና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ቀጣይነት ለማረጋገጥ፣ ተወዳዳሪነቱን ማሳደግ ይችል ዘንድ ቁልፍ የሆነውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅን በማቋቋም የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በዛሬው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰረተ ልማት አማካሪ አቶ ጀንጥራር አባይን ጨምሮ በአየር ትራንስፖርትና በቱሪዝም ዘርፎች የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡  


Read 702 times