Saturday, 24 August 2019 13:33

የወሲብ ንግድ በኢትዮጵያ 70 ዓመት ሞልቶታል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

 - በአ.አ የጐዳና ላይ ወሲብ ንግድን የሚከላከል ረቂቅ ህግ ተዘጋጅቷል
                - በመዲናዋ ከ10ሺ በላይ በጐዳና የወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች አሉ
                - በ1930 ዓ.ም በወሲብ ንግድ የተሰማሩ 1500 ሴቶች ነበሩ
                      
             በአዲስ አበባ ከተማ ጐዳናዎች ላይ በወሲብ ንግድ ሥራ የተሰማሩ ወገኖች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን በመበራከቱና ድርጊቱ ለሌሎች ወንጀሎች መስፋፋት ምክንያት እየሆነ በመምጣቱ የከተማው አስተዳደር የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ በዚህ ስራ ላይ እገዳ ለመጣል የሚያስችል ረቂቅ ህግ አውጥቷል፡፡
በረቂቅ ህጉ ላይ ውይይት ከተደረገበትና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ይህ እገዳና ክልከላም በጐዳናዎች ላይ የሚደረጉ የወሲብ ሥራዎችን እንጂ አጠቃላይ የወሲብ ንግድን የሚከላከል እንደማይሆንም ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ጐዳናዎች ላይ በየተሽርካሪው ውስጥ፣ በተሽከርካሪ ማቆሚያዎችና ግልጽ የመናፈሻ ስፍራዎች ላይ የሚከናወኑ የወሲብ ድርጊቶችንና ንግዶችን የመከላከልና የማስቆም ኃላፊነቱ የከተማው አስተዳደር መሆኑ በከተማው ቻርተር ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በዚህ ምክንያትም የከተማው የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ጥናት ካደረገና ችግሮቹን ከመረመረ በኋላ የጐዳና ላይ የወሲብ ንግዶችን ለማስቆም የሚያስችል ረቂቅ ህግ ለማውጣት መገደዱን ገልጿል፡፡  በአገራችን የወሲብ ንግድ ሥራ የተጀመረው በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ሲሆን ሥራው በአብዛኛው ይከወን የነበረው መሳፍንቱና መኳንንቱ በስፋት ይገኙበት በነበረ አካባቢ መሆኑን ዕውቁ የታሪክ ተመራማሪ ሪቻርድ ፓንክረስት ‹‹ሂስትሪ ኦፍ ፕሮስቲቲዩት ኢን ኢትዮጵያ›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ አስፍረውታል፡፡
ዘመናዊ የወሲብ ንግድ ጅማሮም ከከተሞች ማደግና መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚጠቀስ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መንገድ ዝርጋታ ለዚህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ ይነገራል፡፡ ለእዚህ የባቡር ሃዲድ ሥራ ለመጡ ሠራተኞች ምግብና መጠጥ ለማቅረብ በተከፈቱ ምግብና መጠጥ ቤቶች ውስጥ የወሲብ ንግድ ሥራ የሚሰሩ ሴቶችም ብቅ ብቅ ማለት ቀጠሉ:: በወቅቱ ምግብና መጠጥ የሚሸጡ ምግብ ቤቶችን፣ የወሲብ ንግድ ከሚካሄድባቸው ምግብ ቤቶች ለመለየት እንዲቻል ምልክት በራፋቸው ላይ እንዲያንጠለጥሉ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያትም የወሲብ ንግድ የሚሰራባቸው ቤቶች፤ ቀይ የመስቀል ምስል ያለበት ነጭ ባንዲራ ማንጠልጠልም ጀምረው ነበር፡፡ ያ ሁኔታ ግን በአገራችን የቀይ መስቀል ድርጅት ስራ በሚጀምርበት ወቅት እንዲቋረጥ ተደረገ:: ምልክቱ ከቀይ መስቀል አርማ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ በመገኘቱ፡፡
የወሲብ ንግድ ሥራ በእጅጉ መስፋፋት የጀመረው በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ነው:: ለወረራው የመጡት ወታደሮችን በወሲብ ማስተናገድ የሚችሉ ሴቶች ለማግኘት ባለመቻሉ ምክንያት ጣሊያናውያን ሴቶችን ከአውሮፓ ድረስ ማስመጣት ጀምረውም ነበር፡፡ ሁኔታው አዋጪ ባለመሆኑና ወደ አገራችን ለወረራ የገቡት ጣሊያናውያን ቁጥር ከአውሮፓ ከመጡት ሴቶች ቁጥር ጋር ሊመጣጠን ባለመቻሉ፣ የወሲብ ንግድ ሥራ ለመስራት የሚፈልጉ ሴቶች ፈቃድ እንዲያወጡና በየጊዜው ምርመራ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ወጥቶም ነበር፡፡ በዚሁ መሰረትም፤ በጣሊያን ወታደሮች አስገዳጅነት በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለወሲብ ንግድ ሥራ ፈቃድ ተሰጥቷቸውና ምርመራ አድርገው ሥራ ጀመሩ፡፡ እነዚህ ሴቶች ከጣሊያውያኑ ወታደሮችና ባለሥልጣናት ውጪ፣ ከሌሎች ወንዶች ጋር ወሲብን መፈጸም እንዳይችሉም ክልከላ ተጥሎባቸው ነበር፡፡
በ1930 ዓ.ም 1500 ኢትዮጵያውያን ሴቶችና 47 ከአውሮፓ የመጡ ነጭ ሴቶች የወሲብ ንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር፡፡ ከአምስት አመታት በኋላ ግን ይህ ቁጥር እጅግ አስገራሚ በሆነ መጠን አድጎ፣ በወሲብ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ቁጥር 11ሺ ደርሶ ነበር፡፡  

Read 2563 times