Saturday, 24 August 2019 13:37

በክረምቱ መጨረሻ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ለጎርፍ አደጋ ይጋለጣሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  1.3 ሚሊዮን ያህል ዜጐች በጐርፍ መጥለቅለቅ ሊፈናቀሉ ይችላሉ


            በዘንድሮ ክረምት የመጨረሻ ሣምንታት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ለከፍተኛ የጎርፍ አደጋ መጋለጣቸውን ያመለከተው አለማቀፉ የድርቅ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ተቋም፤ አገራቱ ለዜጎቻቸው ደህንነት ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳሰበ ሲሆን በነሐሴ አጋማሽና በመስከረም ወር 1.3 ሚሊዮን ያህል ዜጐች በጐርፍ ሊፈናቀሉ ይችላሉ ተብሏል፡፡
በክረምቱ የመጀመሪያ ወራት፣ ሰኔና ሐምሌ  ላይ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አገራት፣ መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ መዝነቡን ያወሳው የተቋሙ ሪፖርት፤ ከነሐሴ ወር ጀምሮ ግን ቀጠናው ከመደበኛ በላይ የሆነ ከፍተኛ ዝናብ እያስተናገደ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በዚህም በቀጣይ ቀሪ የክረምቱ ቀናት በዋናነት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ለከፍተኛ ቅፅበታዊ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ሆነዋል፡፡
በኢትዮጵያ ምዕራብ፣ መካከለኛውና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች፣ በክረምቱ የጣለው ዝናብ፤ ለግብርና ምርት አመቺ ነበር ያለው ሪፖርቱ፤ በአካባቢዎቹ የሚገኙ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችም በቂ የውሃ ክምችት አግኝተዋል ብሏል፡፡
ከነሐሴ ጀምሮ በአፋር፣ በሰሜን ምዕራብ አማራ፣ በጋምቤላና በደቡብ ክልል እያዘነበ ያለው ዝናብ ግን ከመደበኛው በላይ በመሆኑ ቅፅበታዊ ጎርፍ እያስከተለ ሲሆን ከዚህ በኋላም አደጋው የከፋ ይሆናል ብሏል - ሪፖርቱ:: ከነሐሴ አጋማሽ እስከ መስከረም ወር መጨረሻም ክረምቱ በአካባቢዎቹ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡
በአፋር ክልል ከሳምንት በፊት ባጋጠመው ቅፅበታዊ የጎርፍ አደጋ፣ ከ10 ሺህ በላይ በጎችና ፍየሎች የሞቱ ሲሆን በሰዎች ላይ ግን የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በቀጣይ ክረምቱ ተጠናክሮ በሚቀጥሉባቸው የአዋሽ ተፋሰስ፣ ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ጊቤና ዋቢ ሸበሌ፤ የወንዝ ሙላት ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በሱዳን ካርቱም፣ ሲናርና ምዕራብ ዳርፉር አካባቢ፣ ከባድ የጎርፍ አደጋ ይከሰታል ያለው ሪፖርቱ፤ በደቡብ ሱዳንም በሰሜን ባህር ኤል ጋዜልና ጆንግሌ ግዛት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ከባድ የጎርፍ አደጋ ያጋጥማል ብሏል፡፡    
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስጋት አመራር ኮሚሽን በበኩሉ፤ እስካሁን በአዋሽ ተፋሰስ ከ20ሺህ በላይ ዜጐች በጐርፍ ምክንያት መፈናቀላቸውን ገልፆ፤ በቀጣይም በአዋሽ ወንዝና በቆቃ ግድብ ሙላት የተነሳ የጐርፍ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል ብሏል፡፡
የቆቃ ግድብ ሙላንት ለመቀነስ በነሐሴ ወር ለአራት ጊዜያት የማስተንፈስ ስራ ቢሠራም፣ አሁንም ግድቡ በከፍተኛ የውሃ ሙላት መጨናነቁን የጠቆመው ኮሚሽኑ፤ በአካባቢው እየጣለ ያለው ከመደበኛ በላይ ዝናብ ከፍተኛ የጐርፍ አደጋ ስጋት ደቅኗል ብሏል፡፡
በአጠቃላይ በአዋሽ ተፋሰስና በቆቃ ግድብ እንዲሁም በከሰም ግድብ ሙላት የተነሳ በአካባቢው ያሉ 1.3 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ሊፈናቀሉ ይችላሉ ያለው ኮሚሽኑ፤ አደጋው ከማጋጠሙ በፊት ዜጐችን ወደተሻለ ቦታ የማሸሽ ተግባር ከወዲሁ መከናወን አለበት ብሏል፡፡


Read 5910 times