Saturday, 24 August 2019 13:43

ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግስት እንዲያወያያቸው ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

 ከአገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት እየተገለልን ነው ብለዋል

          በለውጥ ሃይሉ ከተጀመረው የሀገሪቱ የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት እየተገፋንና ከየተገለልን ነው ያሉ 57 የፖለቲካ ድርጅቶች፤ መንግስት በጥያቄያቸው ዙሪያ እንዲያወያያቸው እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች የረቂቅ ህግም በድጋሚ ለፓርቲዎችና ለህዝብ ውይይት እንዲቀርብ ጠየቁ፡፡
‹‹ከአንድ አመት ተኩል በፊት በከፍተኛ መስዋዕትነት የመጣው ለውጥ እንዳይቀለበስና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያለማቅማማትና መጠራጠር ከለውጥ ሃይሉ ጐን ቆመን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ስናበረክት ቆይተናል›› ያሉት ፓርቲዎቹ አሁን ግን ሀሳባችን ተቀባይነት እያጣ፣ መገፋትና መገለል እየደረሰብን ነው ብለዋል፡፡
“የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ህግን በተመለከተ ለመንግስትና ለሚመለከታቸው አካላት በጽሑፍም ሆነ በቃል ያቀረብናቸው የማሻሻያ ሃሳቦች ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት አላገኙም፤ ቀደም ሲል በይፋ ላቀረብነው ቅሬታም እስካሁን ምላሽ አልተሰጠንም” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል - ፓርቲዎቹ፡፡
መንግስትና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ለአቤቱታዎቹ ተገቢውን ምላሽ አለመስጠታቸው በለውጡ ሂደት ላይ እምነት እንድናጣ አድርጐናል ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ለምናቀርባቸው ጥያቄዎችም ምላሽ የሚሰጥም ሆነ ኃላፊነት የሚወስድ አካል ለማግኘት ተቸግረናል ብለዋል፡፡
“ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ህግ፣ በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት የሚቀለብስ፣ ዲሞክራሲያዊ መብትን የሚገድብ፣ የመደራጀት መብትን የሚያፍን እጅግ ኋላቀርና እንከነ ብዙ በመሆኑ፣ በቀጣይ የፖለቲካ ምህዳሩን አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ብለዋል - ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው፡፡ ረቂቅ ህጉ ከመጽደቁ በፊት በድጋሚ ለፓርቲዎችና ለህዝብ ውይይት ክፍት እንዲሆንና በህጉ ረቂቅ ላይ ፓርቲዎች ያቀረቡት የማሻሻያ ሃሳብ በተገቢው መንገድ መካተቱን የሚያረጋግጡበት መድረክ እንዲመቻች እንዲሁም በአጠቃላይ ፓርቲዎቹ አሉን በሚሏቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ግልጽ የውይይት መድረኩ እንዲፈጠር ጠይቀዋል::
የለውጥ ሃይሉ በመነጋገር የሀገሪቱን ሠላምና ዲሞክራሲ ለማጐልበት የገባውን ቃል እንዲያከብር፣ በፓርቲዎች ይደረጋል የተባለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ወደ ተግባር እንዲተረጉም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ጠይቀዋል፡፡ ፓርቲዎቹ ይህ ህግ ባልተስተካከለበት፣ ሀገሪቱ ወደ አስተማማኝ መረጋጋት ባልገባችበት ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ መወሰኑን በመቃወም፣ ምርጫው ይራዘም የሚል አቋም እንዳላቸው አስገንዝበዋል፡፡
መግለጫውን የሰጡት መኢአድ እና ኢህአፓን ጨምሮ 16 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች እንዲሁም የአፋር 2 ፓርቲዎች፣ የኦሮሚያ ክልል 6 ፓርቲዎች፣ በዶ/ር አረጋዊ በርሄ የሚመራው ትዴትን ጨምሮ 3 የትግራይ ፓርቲዎችና ሌሎች የተለያዩ ክልል ፓርቲዎች ናቸው፡፡      

Read 6511 times