Saturday, 24 August 2019 13:47

የኢትዮጵያዊነት ት/ቤት ለማቋቋም ታቅዷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)


· የዶ/ር ዐቢይ መንግስትን ለኢትዮጵያዊነት ባለው አላማ እንደግፈዋለን
· የ17 ዓመቱ የእርስበርስ ደም መፋሰስ በእርቅ እንዲዘጋ እንሰራለን
· መንግስትን በደህንነትና መረጃ ሥራዎች ማገዝ እንፈልጋለን
· የቤተ መንግስቱን ፕሮጀክት፣ በጉልበት ለማገዝ ጠይቀናል


              የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማኅበር በይፋ ተቋቁሞ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ የማህበሩ አላማና ግብ ምንድን ነው? የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደርን በጸጥታና ደህንነት ጉዳዮች በነጻ ማገዝ እፈልጋለሁ ሲል ምን ማለቱ ነው? የኢትዮጵያዊነት ት/ቤት የማቋቋም ዕቅድም አለው፡፡
ኢትዮጵያዊነትን በት/ቤት ማግኘት ይቻላል? የማኅበሩ መስራችና ፕሬዚዳንት የሃምሳ አለቃ ብርሃኑ እምር፣ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ለእነዚህና ሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተውታል፡፡ እነሆ፡-


         የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና የልማት ማኅበር ምን አላማ ይዞ ነው የተመሰረተው?
የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት፣ በመንግስት ለውጥ፣ በ1983 ዓ.ም ከተበተነ ጊዜ ጀምሮ፣ በአልባሌ ስፍራ እንዲሁ ዝም ብሎ የተጣለ፣ ጡረታ እንኳ እንዳይኖረው የተደረገ፣ ብዙ ሰብአዊ በደሎች የተፈጸሙበትና በማኅበራዊ ጉዳዮች የተጎዳ ሰራዊት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር፣ ሰራዊቱ እንደ ዜጋ፣ ለኢትዮጵያዊነት እንደተዋደቀ ሰው፣ የሚኖርበትን ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ማስቻልን ያነገበ ዓላማ ይዘን ነው የተነሳነው፡፡ የህክምና፣ የጡረታና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ማስከበር የመጀመሪያ ዓላማ አናደርጋቸውም፡፡ አሁን የተጀመረው ለውጥ አገራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረና በኢትዮጵያ ጉዳይ አበክሮ የሚሰራ መንግስትም ስለተፈጠረ፣ በመጀመሪያ ይሄን መንግስት በሚገባ መደገፍ አለብን፡፡ ለአገሩ ህልውና የቆመ መንግስት ስለሆነ፣ ይሄን አላማውን በጽናት መደገፍ አለብን የሚል አላማ ይዘናል፡፡ መጀመሪያ አገር ስትኖር ነው ሁሉም ነገር የሚኖረው ብለን ስለምናምን፣ መጀመሪያ መንግስትን በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ መደገፍ እንፈልጋለን፡፡ ይህ ሰራዊት ጡረታ ሲከለከል፣ የመብት ጥሰት ሲፈጸምበት፣ ያን ሁሉ ዋጋ የከፈለው ስለ ኢትዮጵያዊነት ብሎ ነው::  መጽናኛችን ኢትዮጵያ ስለሆነች፣ ያለፈውን ጉዳት በዚህ አልፈነው፣ መንግስትን ለኢትዮጵያዊነት ባለው አላማ እየደገፍን፣ መብቶቻችንን እናስጠብቃለን የሚል አላማ ነው ያለን፡፡
መንግስትን በምን መልኩ ነው ለመደገፍ ያሰባችሁት?
ይሄ ሰራዊት በተለያዩ ሙያዎች ራሱን ያደሰ ሰራዊት ነው፡፡ እንደ ተበተነ ሜዳ ላይ ወድቆ የቀረ ብቻም አይደለም፤ ወታደራዊ ሳይንስን ጠንቅቆ የተማረ ሰራዊት ነው፡፡ ወታደራዊ ሳይንስ ደግሞ ወድቆ መቅረት፣ ተስፋ መቁረጥን የሚያመጣ አይደለም፡፡ ወታደራዊ ሳይንስ በእጅጉ የሞራል ግንባታን የሚፈጥር፣ የሚያበረታ ነው። ብዙዎች በዚህ ብርታት ራሳቸውን አሻሽለው፤ የህክምና ዶክተሮች፣ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች፣ የሂሳብ ሙያተኞች፣ መሀንዲሶች፣ ባለሀብቶች፣ ታዋቂ ነጋዴዎች ሆነዋል፡፡ በዚህ መልኩ ብቁና አገሩን የሚወድ፣ የተማረና ሀብት የያዘ ሀይል አለው:: ይሄን እውቀቱንና ሀብቱን ሳይሰስት ተስፋ ለጣለበት መንግስት ድጋፍ ማድረግ ይፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል፣ በቂ የወታደራዊ ሳይንስ እውቀት ያላቸው አባላት አሉ፡፡ ለነገ ተተኪ የሆኑ ወታደሮችን ማሰልጠን እንችላለን፡፡ ይሄን ስንል እታች እስካለው የአካባቢ ጥበቃና ሰላም ማስፈን ድረስ መሳተፍን ይጨምራል:: የአካባቢ ደህንነትን ከመጠበቅ አንጻር ብዙ አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን፡፡ ይሄ ሰራዊት ደጋግሜ እንዳልኩት፣ በቂ ወታደራዊና የደህንነት ሳይንስ የተማረ እንደመሆኑ፣በየአካባቢው ያለውን ነገር በበቂ መልኩ መፈተሽ ይችላል፡፡ የከፋና አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚፈጠሩ ሰዓት ወታደር በደንብ አድርጎ አካባቢውን ይቃኛል፤ ይገመግማል፤መረጃ አጠናቅሮ ማስተላለፍ እንዴት እንደሆነም ያውቃል፡፡
የደህንነት ሥራ መስራት እንችላለን እያሉ ነው?
አዎ፤በአገር ጥቅም ጉዳይ ላይ፣ ታችኛው ማህበረሰብ ውስጥ በመግባት፣ የደህንነት ሥራና መረጃ፣ ለደህንነት አካላት የማቅረብ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ የአካባቢውን ሰላም በተመለከተ ሰራዊታችን በተለይ በአገሩ ጉዳይ የመጣበትን ማንኛውንም አደጋ በቸልታ አያልፍም። በበቂ መጠንም እንዲሁ ያሉ ችግሮችን አስቀድሞ መረዳት ይችላል፡፡ ተረድቶም ለመንግስት የደህንነት ተቋማት መረጃውን ማቅረብ ይችላል፡፡ መረጃን በማነፍነፍ፣ በማጠናቀርና ለሚመለከተው አካል በማቀበል ደረጃ፣ በአገር ውስጥም በውጭም ስልጠና የወሰዱ በቂ አባላት አሉን፡፡ ከፍተኛ የደህንነት ትምህርት የተማሩ አባላት ስብስብ የያዘ ነው፤ ማህበራችን:: መንግስት በዚህ በኩል እገዛ ከፈለገ፣ ለአገራችን የማናደርገው ነገር አይኖርም፡፡ ሙሉ ፍቃደኞች ነን፡፡
የሰራዊቱ ዓላማ የአገሩን ጉዳይ ማስቀደም ከሆነ፣ ለምን አስካሁን ዘገየ?
በቀድሞ መንግስትም ቢሆን ምንም ነገር ከአገር አይበልጥም ብለው፣ መገፋታቸውን ወደ ጎን ትተው፣ አገራቸውን ያገለገሉ አባላት አሉ፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በርካቶች ተዋድቀዋል፡። ባድመ ላይ ዘምተው ለአገራቸው ሞተዋል፡፡ አገር በተራበች ጊዜ ዝም የሚል ሰራዊት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቀዳሚ አላማው ኢትዮጵያ ናትና፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ የትኛውንም ያህል ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ የሆነ ሀይል ነው፡፡ አሁን በማህበር ለመደራጀት የቻልነው ጊዜው ስለፈቀደልን ነው፡፡ ለመደራጀት መብቱ ስለተሰጠን ነው፡፡
ማኅበራችሁ አሁን ምን ያህል አባላት አሉት? እነማንን ያካተተስ ነው?
ይሄን ማኅበር ስንመሰርተው ሀሳቡን መጀመሪያ ያመነጨኹት እኔ ነኝ፡፡ ከዚያ ሀሳቡን ይዤ ወደ ጓደኛዬ፣ የመቶ አለቃ ሰላም አዳሙ (የቱ አር ኤንድ ፈርኒቸር ድርጅት ባለቤት) ጋር ሄድኩ፡፡ ከሱ ጋር ሀሳቡን በሚገባ አብላልተን፣ ሌሎች ጓደኞቻችንን ጨመርንና አንድ ስራ አስፈጻሚ አዋቀርን። ከዚያም መስራች ስብሰባ፣ ጥቅምት 4 ቀን 2011 ዓ.ም እኔ ቤት አደረግን፡፡ ጥቅምት 25 ቀን 2011 ደግሞ የምስረታ ጉባኤውን አካሄድን፡፡ በመጀመሪያ የ21ኛው ተራራ ክፍለ ጦር አባላት ብቻ ነበርን፤ በኋላ ግን ከሁሉም የሰራዊቱ ክፍሎች የተውጣጣ ሀይል ነው የተፈጠረው፡፡ የማደራጀት ፍቃድ ከመንግስት ወስደን ስናደራጅ ነው እስካሁን የቆየነው። አሁን መንግስት ሙሉ እውቅናና ፈቃድ ሰጥቶናል፡፡ ፈቃድ ከመውሰዳችን በፊት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች፣ ወደ 37 ቅርንጫፎችን  አቋቁመን ነበር:: እያንዳንዱ በየክፍለ አገሩ ያለ መሠረታዊ ማኅበር ቅርንጫፍ፣ ቢያንስ በትንሹ ከ1200 በላይ አባላት ነው የነበራቸው፡፡ አሁን በሁለትና ሶስት እጥፍ ጨምሮ፣ በአማካይ እያንዳንዳቸው፣ ከ7 ሺህ እና 8 ሺህ በላይ ደርሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ማኅበራችን አስመራን ጨምሮ 68 ቅርንጫፎች አሉት፡፡
አስመራን ጨምሮ ሲሉን?   
አዎ፤ በኤርትራ አስመራ አባላት አሉን:: ወታደሮች የነበሩ በርካቶች ናቸው፡፡ እዚህ መጥተው ያገኙንና በአባልነት ተመዝግበው የሄዱ አሉ:: የኛ አባላት የነበሩ ወታደሮች ልጆችም አሉ። እነሱም በዚህ ማኅበር ውስጥ እየተሳተፉ ነው፡፡ በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ወደ 845 ሺህ አባላትን መዝግበናል፡፡ አሁንም እየተመዘገቡ ነው:: ይሄ ቁጥር ላይ ብዙዎች ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ ሰራዊት (መደበኛው) ከ3 መቶ ሺህ እስከ 4 መቶ ሺህ የሚገመት ነው፡፡ እኛ 845 ሺህ ስንል፣ የፖሊስ ሰራዊትን፣ ልዩ ሀይል ሚሊሻ ሰራዊትንና በቦርድ የተሰናበተ ሰራዊትን ያካትታል፡፡ በደርግነት የተፈረጀውን ሰራዊት በሙሉ ያካትታል፡፡ የሰራዊቱ ቤተሰቦችም በሌላ ዝርዝር ውስጥ ይመዘገባሉ፡፡
አስመራ ላይ ግን ጽ/ቤት መክፈት ችላችኋል?
የጽሕፈት ቤት መክፈት ጉዳይ ገና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን የሚጠይቅ ስራ ነው። ያንን  ማከናወን ይጠበቅብናል፡፡ ነገር ግን መሰረታዊ ማህበር ግን እዚያም አለን፡፡ አባላቶች አሉን፡፡
ኢትዮጵያውያን ወይስ ኤርትራውያን?
በፊት ለኢትዮጵያ የተዋደቁ አሁን ኤርትራውያን የሆኑ አባላት ናቸው ያሉን፡፡ ከኛ ጋር አብረው የተዋጉ፣ የኛ አባላት የነበሩ ሰራዊት ናቸው፡፡ ማዕረግተኞችም አሉ። አሁን መጥተው አግኝተውናል፡፡ ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል፡፡
ኤርትራ ላይ ማኅበሩን ማደራጀት ምንድን ነው ትርጉሙ?  
እኛ ራሳችንን የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት ነው ያልነው፡፡ የአሁኑን አይጨምርም ማለት ነው፡፡ የአንድነት ዘመናችንን፣ ወዳጅነታችንን፣ ጓደኝነታችንን፣ ለአንድ ጉዳይ ተሰልፈን እንደነበር ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በቀጣይ ግን ኤርትራውያን ስለ አገራቸው፣ ስለ ራሳቸው፣ እኛ ኢትዮጵያውያኑም ስለ አገራችን ስለ ራሳችን መሰለፋችን እንዳለ ሆኖ፣ በጋራ የምንመራበትም ሁኔታ ይኖራል የሚል ታሳቢ ነው ያለው፡፡ የኛ ልጆች ኤርትራ አሉ፤ አባቶቻቸው እዚህ አለን፡፡ ዋናው ይሄን ማቀራረብ ነው፡፡ በሂደት አብሮነትን፣ አንድነትን ማምጣት የሚቻልበት ግንኙነትም ይሆናል፡፡
ማኅበራችሁ ‹‹የድጋፍ እና የልማት›› ነው የሚለው፡፡ የድጋፍ ሲባል ምን ማለት ነው?
ሰራዊቱ ወትሮም ቢሆን አንድ ኮዳ ውሃ እየተካፈለ፣ እየተዛዘነ፣ እየተረዳዳ የሚኖር ነው:: ይሄ የወታደሩ ባህሪ ነው። እስካሁንም በግል በተቻለን አቅም የተጎዱትን እየደገፍን ቆይተናል:: ለወደፊት ግን ማህበራችን፣ ይህን ተቋማዊ የሚያደርግ የፕሮጀክት ንድፍ አለው፡፡ የተለያዩ የስራ መስኮችን ለመዘርጋት እቅድ አለን፡፡ እቅዱ በባለሙያዎች የተሰራ ነው፡፡ እጃችን ላይ ሲደርስ የምንገልጸው ይሆናል፡፡ የጡረታ ጉዳይም እንዲከበር ለወደፊት ጥረት እናደርግበታለን፡፡ አሁን የማደራጀት ጊዜያችን ነው፡፡ በቀጣይ አመት የማኅበሩ የሕግ ክፍል አተኩሮ ከሚሰራባቸው አንዱ የሰራዊቱ የጡረታና የህክምና ጉዳይ ይሆናል:: መታወቅ ያለበት ግን ይሄ ሰራዊት፣ ስለ አገር አንድነት በነፃ የተዋደቀ መሆኑን ነው:: ስለ አገር ሲል የተራበ፣ የታረዘ ሰራዊት ነው:: ይህ ሰራዊት ዛሬ አገሩ ላይ ቀና ብሎ እንዲራመድ መደረጉ ብቻውን ለኛ ትልቅ ነገር ነው፡። ዶ/ር ዐቢይ የሚመሩት መንግስት ክብር ሰጥቶናል፡፡ ለኛ ይሄ በራሱ በቂ ነው። የእውቅና ሰርተፊኬታችንን እንኳ ሲሰጡን፣ እንደ ቀድሞ የደርግ ሰራዊት የሚል ማጠልሸት ውስጥ አልገቡም፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት ብለው ነው እውቅናና ሠርተፊኬት የሰጡን:: በዚህ ሁልጊዜ ምስጋናችን አይቋረጥም:: ይሄን ላደረጉ የለውጡ ሃይሎች በሙሉ ትልቅ ምስጋና አለን፡፡ ሠራዊታችን አሁንም ሀገሩን በነፃ ለማገልገል ዝግጁ ነው፡፡ በሚችለው መጠን ሀገሩን በነፃ ያገለግላል፡፡
በሀገር አንድነት ጉዳይ ላይ ሠራዊቱ አሁንም ጽኑ አቋም ያለው ነው ይላሉ?
እኛ ለሀገራችን ስንዋደቅ ብሔራችንን አናውቅም ነበር፡፡ እከሌ ጉራጌ፣ እከሌ ኦሮሞ፣ እከሌ ትግሬ፣ እከሌ አማራ እያልን አንተዋወቅም ነበር፡፡ አሁንም ይህ ሠራዊት በዚያ መንገድ ነው ያለው፡፡ ብሔሩን አይተዋወቅም፤ ብሔር የለውም፤ ዘር ይኖረዋል፤ ግን መገለጫው ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው፡፡ ይሄ ሠራዊት፣ ከኢትዮጵያዊነት ውጪ ሌላ አያውቅም:: ለዚህ ነው መሣሪያ ይዞ፣ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ምግብና ውሃ ይለምን የነበረው፡፡ ጠመንጃ ዘቅዝቀን ወደ ቤታችን የገባነው፣ ጨዋነት ስላለን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ በነፃ ዋጋ የሚከፍል ሠራዊት ነው ዛሬም ያለን፡፡ ሁሉም ማጠንጠኛው ኢትዮጵያ ነች፡፡ አሁንም በዚህ መንፈስ ውስጥ ነው ያለው፡፡ የትኛውም የቀድሞ ሠራዊት፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ አይደራደርም፡፡ ስለ ዘሩና ብሔሩ አይገደውም፡፡ ይሄን ማንም ማረጋገጥ ይችላል፡፡ ተፈጥሮው ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡
መንግስት በፈለገን መልኩ ድጋፍ ልናደርግ ዝግጁ ነን ብላችኋል፡፡ ከመንግስት ያገኛችሁት ምላሽ አለ?
አሁን የለውጥ ሃይሉን የምናመሰግነው፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ክብር እንዲያገኝ በማድረጉ ነው፡፡ መንግስት በእርግጥ እኛን እየደገፈን ነው፡፡ እኛ ግን መንግስትን ለመደገፍ ገና የሚቀሩን ነገሮች አሉ፡፡ ያንን ድጋፍ ለማድረግ ከኛ የሚጠበቅብንን በቅድሚያ ማከናወን አለብን:: ከዚያ ተደራጅተን ፕሮጀክታችንን እናቀርባለን፡፡ እስከዚያው ግን በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ለመሳተፍ ጠይቀናል፡፡
በምን ዓይነት ፕሮጀክቶች ለመሳተፍ ጠየቃችሁ?  
ለምሣሌ በቤተ መንግስቱ ውስጥ የሚከናወን ፕሮጀክት አለ፡፡ በክቡር ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሚመራ ፕሮጀክት ነው፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ላይ ለመሳተፍ በደብዳቤ ጠይቀናል:: በቀን ከ100 እስከ 200 ሰዎች በነፃ በጉልበት ሥራ እንዲሳተፉ ነው የጠየቅነው፡፡ ሌሎች ሀብት ያላቸው በገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ እኛ ግን ያለን አቅም ጉልበት ስለሆነ፣ በጉልበት በፕሮጀክቱ ላይ ለመሳተፍ ጠይቀናል፡፡ ለደብዳቤው መልስ እየጠበቅን እንገኛለን፡፡ ለአዲስ አበባ ክቡር ም/ከንቲባውም እንዲሁ እሳቸው በፈለጉን ቦታ በነፃ የጉልበት ስራ ለማገልገል ፍላጐት እንዳለን በደብዳቤ ገልፀንላቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ የለውጥ ሃይሉን እንደግፋለን፡፡ መንግስት ፍቃድና እውቅና እንደሰጠን ሁሉ፣ ጠ/ሚኒስትራችን ስለ ቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አንዲት ቃል ቢናገሩልን በእጅጉ ደስ ይለናል፡፡ ይሄ ሠራዊት ለርዕዮተ አለም ውግንና የሞተ አይደለም፤ ሀገርህ ልትበታተን ነው ሲባል ለሀገሩ አንድነት የተዋደቀ፣ ከምንም በላይ ሀገሩን የሚያስቀድም ሠራዊት ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትራችን፤ ስለ ቀድሞ ሠራዊት አንዲት ቃል ቢናገሩ፣ ለኛ ትልቅ የሞራል ካሣ ይሆነናል፡፡
በ17 አመቱ የእርስበርስ ጦርነት፣ ብዙ ደም መፋሰስ ተከስቷል፡፡ ይሄ  እንዴት ነው የሚሽረው?
እውነት ለመናገር ሁለታችንንም ያደባደበን የአመለካከት ልዩነት ነው፡፡ የርዕዮተ አለም ልዩነት፣ ወንድማማቾችን ያደባደበበት ዘመን ነው፡፡  እንዳለመታደል ሆኖ ግን በመጨረሻም፣ የአሸናፊና ተሸናፊ ትርክት ተፈጥሮ፣ ባለፉት አመታት ጠላት ስንባል ቆይተናል፡፡ አሁን የመሸናነፉን ጉዳይ ለታሪክ ትተነው፣ እርቅ ያስፈልገናል፡፡ የሠላምና የእርቅ መድረክ ተፈጥሮ፣ ቀጣዩ ትውልድ እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ ስለ ሀገሩ የሚቆምበትን መንገድ እውን ለማድረግ በኛ በኩል እቅድ አለን፡፡ ጠላትና ወዳጅ በሚል አዕምሮ መቀጠል አንፈልግም:: ይሄ እንዲሽር የእርቅ መድረክ ያስፈልገናል፡፡ በዚያ ጦርነት አዕላፍ ኢትዮጵያውያን ወድቀዋል:: እነዚያን በእኩል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ የሠላምና የእርቅ ጉዳይ፣ የስፖርት ፌስቲቫል የማዘጋጀት እቅድ ጭምር አለን:: በዚያ መድረክ የጠላትና ወዳጅነት እሳቤ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲዘጋ እንፈልጋለን፡፡
ማህበሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያከናውናቸው ያቀዳቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
በአጭር ጊዜ ውስጥ ከምንሰራቸው አንዱ፣ የኢትዮጵያዊነት ት/ቤትን ማቋቋም ነው፡፡ አሁን የዚህ ት/ቤት ዲዛይን አልቋል፤ የመሬት ጥያቄም ለመንግስት ቀርቧል፡፡ የኢትዮጵያዊነት ት/ቤት በባህሪው፣ የኢትዮጵያዊነት እሣቤ በትምህርት መልክ የሚሰጥበት የግብረ ገብነት ት/ቤት ነው:: ሁሉም የእምነት ተቋማት ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚያስተምሩበት ነው:: ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ የራሱ ስርአተ ትምህርት ያዘጋጃል:: ግብረ ገብነትን በዋናነት ያስተምራል፡፡ የኢትዮጵያን መንፈስ የምንጋራበት፣ ትውልድ በኢትዮጵያዊነት የሚታነጽበት ት/ቤት ነው፡፡ ፕሮጀክቱን የነደፉት አካላት ወደፊት ዝርዝር ማብራሪያ ይሰጡበታል፡፡
መደበኛ ት/ቤት ነው?
መደበኛ ሳይሆን የግብረ ገብነት ስልጠና ማዕከል ነው የሚሆነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የራሱ ት/ቤት እንዲኖረው እንፈልጋለን፡፡ የማህበራችን የመጀመሪያ እቅድ ይሄ ት/ቤት ነው፡፡ ትውልዱ እንደ ገበቴ ውሃ ወዲያ ወዲህ እየሰፈፈ ነው ያለው፡፡ ት/ቤቱ ትውልድን በኢትዮጵያዊነት የሚያፀና እንዲሆን ነው እቅዳችን፡፡

Read 1646 times