Saturday, 24 August 2019 14:03

የቀይ ህንዶቹ መሪ ደብዳቤ

Written by  በተሾመ ገብረ ሥላሴ (ሲልቨር ስፕሪንግ ሜሪላንድ)
Rate this item
(1 Vote)


          “--እኛ የምድሪቱ አካል እንደሆንን ሁሉ እናንተም የምድር አካል ናችሁ። ለእኛ ውድ የሆነችውን ያህል ለናንተም ደግሞ ውድ ናት። በአንድ ነገር እርግጠኞች ነን። ያለን አምላክ አንድ ነው። እርሱ ቀይና ነጭ አይልም። ሁላችንም ወንድማማቾች ነን።”
               
             ስለ ቀይ ህንዶች መሪ ዝነኛ ደብዳቤ ከማውሳታችን በፊት ስለነዚሁ ነባር አሜሪካውያን ጥቂት ነገር ማውሳት አስፈላጊ ነው። ቀይ ህንዶች ወይም የአሜሪካ ነባር ህዝቦች፣ ከ12500 ዓመታት በፊት ከሰሜን ምሥራቅ እስያ ፈልሰው የመጡ የእስያ ዘሮች መሆናቸውን፣ የሥነ-ሰብ ባለሙያዎች፣ የምርምር ውጤቶችን ዋቢ አድርገው ያስረዳሉ። በአርኪዎሎጂ ቁፋሮ የተገኙ ቁሳቁሶች፣ ከዘመናት በፊት የሰሜን እስያ ጎሳዎች ይጠቀሙ ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ሆኖ መገኘቱ የአርኬዎሎጂስቶቹንና የሰውን ዘር ፍልሰት የሚያጠኑ ባለሙያዎችን ግምት ከፍ አድርጎታል። የቋንቋና የዘረ-መል ጥናቶችም የሚያረጋግጡት ይኼንኑ ሆኗል። ቀይ ህንዶች ከአንድ ማዕከላዊ ሥፍራ ተነስተው፣ ከላይ ከአላስካ እስኪሞዎች እስከ ደቡብ አሜሪካ ቺሊ ድረስ በተለያዩ ወቅቶች እየተሰራጩ ቆይተዋል። በዚህም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ነገዶች፣ ጎሳዎች፣ ቋንቋዎችና የባህል ስብጥሮች ተፈጥረዋል።
ቀይ ህንዶች ወይም ነባር ህዝቦች፤ የዳበረ ፍልስፍና፣ ባህል፣ ኃይማኖትና ዕምነት ያላቸውና የአፍአዊ ሥነ-ጽሁፍ (Oral literature) ባለቤቶችም ናቸው። በተለይም የደቡብ አሜሪካ ቀይ ህንዶች ሥልጣኔ በእጅጉ ረቂቅና አሁንም ድረስ እንቆቅልሽን በጉያው የያዘ ነው። የአዜቲኮች ኮከብ ቆጠራና የአስትሮኖሚ ዕውቀት፣ የማያ ፒራሚዶች፣ የኢንካዎች የጦር ቴክኒክና ፈጠራ፤ የማቹ ፒቹ የማይናወጥ የተራራ ጫፍ ኪነ-ህንጻ አሁንም ተጠንተው “ውጤታቸው ይኼው!” ወደሚያስብል ድምዳሜ ያልተደረሰባቸው ናቸው።
“ፍጥረት አንዱ ከሌላው ጋር የተያያዘና የተሳሰረ ነው። የትስስሩ አንዱ ቋጠሮ ሲፈታ ሁሉም ነገር አላግባብ ይተረተርና የህላዌ መጨረሻ ይሆናል።” የሚለው የአሜሪካ ሁሉም ነባር ህዝቦች ፍልስፍና፤ ለበርካታ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች መፈክር ሆኖ ኖሯል። ሣይንሱም ደግፎታል። የክርስቶፎር ኮሎምቦስ አሜሪካንን ከቀሪው ዓለም ጋር ማስተዋወቅ ወይም ማግኘት የነባር አሜሪካውያንን ህይወት አመሳቅሏል። የኃብት ሽሚያው ተፈጥሮን እንዳልነበረ እያደረገና የቀይ ህንዶችን ከተፈጥሮ ጋር የተሰናሰለ ዕምነት ዋጋ እያሳጣ ዘመናትን አስቆጥሯል። ተፈጥሮን ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን የቀይ ህንዶቹንም ህልውና እስከ መፈታተን ደርሷል።
ቀጣዩ ደብዳቤ፣ ቀይ ህንዶች ለተፈጥሮ ያላቸውን ፍቅርና በነጩ ሥልጣኔ ላይ ያደረባቸውን ስጋትና ፍርሃት ገላጭ ሲሆን በሰሜን አሜሪካ ሲያትል አካባቢ በነበሩ የቀይ ህንዶች መሪ የተጻፈ ነው። በሥነ- ጽሁፋዊ ዋጋው የከበረ፤ ፍልስፍናን በመግለጽ አቅሙና ኃይሉ በእጅጉ የተደነቀ ተብሎ በአሜሪካ ብሔራዊ ሙዚዬም በክብር ተቀምጧል።
ለዚህ ደብዳቤ መጻፍ ዋናው ምክንያት በወቅቱ የአሜሪካ መንግሥት፣ ቀይ ህንዶቹ ይኖሩበት የነበረውን ሰፊ አካባቢ የሚያቋርጥ የባቡር ሃዲድ መዘርጋት አስፈልጎት ስለ ነበር፣ አሥራ አራተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ፕሪሴ፣ የሃዲዱ መስመር የሚያቋርጣቸውን መሬቶች፣ ከቀይ ህንዶቹ ላይ ለመግዛት ወደ መሪው ሲያትል የላኩት ደብዳቤ ነው።  
ሲያትል በምዕራብ አሜሪካ ዋሸንግተን ግዛት በ1851 ስትመሰረት፣ ስሟን ያገኘችው ከዚሁ የቀይ ህንዶች የጎሳ መሪና ተዋጊ ጀግና ነው። የዚህ ጀግና ሃውልት አሁን በሲያትል ኦሎምፒክ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ቆሞ በብዙዎች ይጎበኛል።  
በዋሽንግተን ያሉት ፕሬዝዳንት መሬታችንን መግዛት እንደሚሹ ገልጸው ቃልዎን ልከውብኛል ግን ሠማይንና ምድርን እንደምን አድርገው ሊገዟቸው ያለዚያም ሊሸጧቸው ይችላሉ? ይህ ሃሳብ ለእኛ ከመርግ የከበደ ነው።
ለስላሳውንና የሚንሸዋሸወውን ነፋስ እንዲሁም የሚንፎለፎለውን ፏፏቴ እንደምን ሊገዙት ይቻልዎታል? የዋጋውስ ተመን ምን ያህል ነው? ሁሉም የምድሪቱ አካላት፣ ከህዝቦቼ ነፍስ ጋር መንፈሣዊ ቁርኝት አላቸው። የእያንዳንዱ ጥድ ዛፍ፣ ውብ ጥላና ቀጫጭን ቅርንጫፍ፤ ትንንሾቹ ነፍሣት በጣፋጩ ህልውና ውስጥ ለመቆየት የሚያደርጉት ውብ ቀዘፋ፤ እኒህ ሁሉ የተቀደሱ ፍጥረታትና ድርጊቶቻቸው በህዝቦቼ ትውስታና ማንነት ውስጥ ህያው ናቸው።
በዛፎቹ ግንድና ቅርንጫፍ ውስጥ የሚመላለሰው የህልውናቸው ወዝና ደም፣ ከእኛው ደም ቅዳና ደም መልስ ወፍራም ሥር ጋር የተሳሰረ መሆኑን ጠንቅቀን እናውቃለን። በዱር ውስጥ የሚደንሱት መዓዛማ አበቦች እህቶቻችን ናቸው። የሚንጎማለለው ግዙፍ ድብ፣ በነጻነት የሚቦርቀው አጋዘን፣ ኃያሉ ንሥር --እነዚህ ሁሉ ወንድሞቻችን ናቸው። የቋጥኛማ ተራሮቻችን ጫፎች፣ በጤዛ ነጠብጣቦች ኅብር የሚያንጸባርቀው ጸዓዳማ መስክ፤ የአፓቼዎች (ድንክዬ ግመሎች) ሙቅ ገላ፣ እኒህ ሁሉ የቤተሰባችን አባላት ናቸው።
በጠዋቱ ጮራ ብርሃን ደምቆ ከጅረቶችና ወንዞች ጋር ሊዋሃድ የሚፈጥነው ፈሣሽ ተራ ውሃ አይምሰላችሁ፤ እርሱ የአያት ቅድመ አያቶቻችን ደም ነው። ምናልባት መሬታችንን ልንሸጥላችሁ እንችል ይሆናል፤ ግን አንድ ነገር መርሳት የለባችሁም። መሬታችን የዕምነታችን እምብርት ነው። ከበረዶ የነጡቱ ነጸብራቃማ ሃይቆች፣ የህዝቦቼን ትዝታና ያለፈ ታሪክ ይዘዋል። የፏፏቴው ጉርምርምታ፣ የአባቶቼ አባቶች ድምጽ ነው። ወንዞቹ ወንድሞቻችን ናቸው - የሥጋና የነፍስ ጥማችን እርካታዎች። ታንኳችንን ይሸከሙና ከሥፍራ ሥፍራ ያጓጉዙናል። ልጆቻችንን ይመግቧቸዋል። ስለዚህ ለማንም ወንድማችሁና አካላችሁ የሆናችሁትን ያህል ለወንዞቻችንም ደግና ርህሩህ መሆን ይጠበቅባችኋል።
ምናልባት መሬታችንን ከሸጥንላችሁ በአንክሮ ልታስታውሱት የሚገባው አየራችን ለእኛ ከምንም በላይ ውድ ነገር መሆኑን ነው። መንፈሱን እያጋራን በየዕለቱ እንቅስቃሴያችን ሁሉ ይራዳናል። ቅድመ አያቶቻችን መጀመሪያ የተቀበሉትን እስትንፋስና የመጨረሻ ረጅም ትንፋሻቸውን ከእኛ ጋር ያስተሳስራል። በተጨማሪም ለእምቦቃቅላዎቻችን ውቡንና ጠንካራውን የመኖር መንፈስ ያቀብላል። እንግዲህ ምናልባት መሬታችንን ከሸጥንላችሁ እኒህን መንፈሳዊና ልዩ ነገሮቻችንን ማክበርና መጠበቅ ይኖርባችኋል። ያለንበት ምድር ነፋስ በምድር አበቦች መዓዛ የጣፈጠ መሆኑን ለአንድ አፍታ ምጋችሁ፣ ከነፍሳችሁ ጋር በማዋሃድ ልታረጋግጡ ይገባል።
ለህጻናቶቻችንን የምናስተምራቸው ይህንን ነው። እናንተስ ይህን ለልጆቻችሁ ታስተምራላችሁ? ምድር እናታችን መሆኗን? በምድር ላይ የመኖር አጋጣሚውን ያገኘ ሁሉ የምድሪቱ ልጅ መሆኑን?
እኛ አንድ ነገር እናውቃለን። የሰው ልጅ የምድሪቱ ቅዱስ ኃብት እንደሆነና ምድር ግን የሰው ልጅ ንብረት እንዳልሆነች። ሁሉም ነገሮች እንደ ደም ሥር የተሳሰሩና የተጣመሩ ናቸው። የሰው ልጅ የህይወትን ድር ሊሸምን አይችልም። እርሱ ራሱ እንዲሁ ዝም ብሎ ከህይወት ክሮች መካከል እንደ አንዲት ቁጢት ነው። ምንም ነገር ማናቸውም ነገሮች የዚህ ግዙፍ ድር አካል ናቸው።
እኛ አንድ ነገር እናውቃለን። የእኛ አምላክ የእናንተም አምላክ መሆኑን። ምድር ውድ ነገሩ ስትሆን እርስዋን የሚጎዳ ሁሉ እርሱን እንደሚያስቀይም እናውቃለን። የእናንተ ጉዞና የህልማችሁ መዳረሻ ለእኛ ስውርና ምስጢራዊ ነው። ጎሾቻችንን ሁሉ ድንገት ታርዱብን ይሆን? የዱር ፈረሶቻችን ለማዳ እንዲሆኑ ታስገድዷቸው ይሆን? በደኖቻችን ምስጢራዊ ኩርባዎች ከባድ የባቡር ጢስ ጠረን ይናኝ ይሆን? ወይስ ኮረብቶቻችን ላይ በተንደረከኩ ፍራፍሬዎች አናት ላይ የቴሌግራም ሹክሹክታዎችን ታጓጉዙብን ይሆን? የቁጥቋጦና ዋሻዎቻችን እጣ ፈንታ ምን ይሆን? ንሥሮቻችን ምን ይሆኑብን ይሆን? ከእኛ ይኼዳሉ? ፈጣኗንና ድንክዬዋን አፓቼ፣ እንደምን እንሰናበታታለን? አደኑንስ? የአንዱ ህይወት ማክተም ለሌላው ህላዌ ጅማሮ ነው።
የመጨረሻው ቀዩ ሰው ከነበረኸኛነቱና ዱር አደግነቱ ጋር ጨርሶ ከምድረ ገጽ ይጠፋና ትውስታዎቹ በደመናው ጥላ ውስጥ የሣሩን መስክ ሲያቋርጡት ይኖራሉ። በዚህ ሁሉ ውስጥ እነዚህ የባህር ዳርቻዎችና ደኖቹ ጸንተው ይቆዩ ይሆን? የህዝቦቼስ መንፈስ?
አራስ ልጅ የእናቱን የልብ ትርታ የሚወደውን ያህል ይህችን ምድር እንወዳታለን። ምናልባት መሬታችንን እንሸጥላችሁ ይሆናል። መሬታችንን እኛ የምንወዳትን ያህል ውደዷት። እኛ የምንጠነቀቅላትን ያህል ተጠንቀቁላት። የምድራችንን ትዝታዎችና ትውስታዎች አብራችሁ ተቀበሉ። እግዚአብሔር ሁሉንም እንደሚወድ እንዲሁ። እኛ የምድሪቱ አካል እንደሆንን ሁሉ እናንተም የምድር አካል ናችሁ። ለእኛ ውድ የሆነችውን ያህል ለናንተም ደግሞ ውድ ናት። በአንድ ነገር እርግጠኞች ነን። ያለን አምላክ አንድ ነው። እርሱ ቀይና ነጭ አይልም። ሁላችንም ወንድማማቾች ነን።

Read 890 times