Saturday, 24 August 2019 14:24

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)


                 “ህይወት የምትፈለቀቀው ከጭንቅና ከመከራ ውስጥ ነው”
            
  የነፃነት ሃውልቶች ታሪክ
  አባቶቻችን የገነቡት ነው
  በደም ባጥንታቸው ልክ!
                   

            አንድ የድሮ ቀልድ ነበረች፡፡ ለቁም ነገራችን ማዋዣ የምትሆን፡፡ ዓይናችን ስር ዕውነት ስትሆን ያየናት፡፡ አንድ የቀድሞ የደርግ ባለስልጣን፣ በሰባዎቹ አጋማሽ ላይ፣ አዲስ አበባ ወህኒ ቤት፣ እስረኞችን ለመጐብኘት መጡ፡፡ ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ “መንግስት እንዲያደርግላችሁ የምትፈልጉትን ንገሩኝ” ብለው ፀሐፊያቸው ማስታወሻ እንዲይዝ አዘዙት፡፡ ስለ ት/ቤት፣ ስለ መማሪያ መጽሐፍ፣ ስለ ፍትህ መጓደልና ስለ መሳሰሉት ብዙ ጥያቄዎች ቀረቡላቸው፡፡
ሁሉንም መዘገቡ፡፡ “አይቻልም” ያሉት ነገር ባለመኖሩ፣ ፀሐፊያቸው ተበሳጭቷል፡፡ ወደ መጨረሻው ገደማ አንዱ እጁን አውጥቶ፤ “የመዋኛ ገንዳ ይሰራልን” አላቸው፡፡
“ይሰራላችኋል፡፡ ማስታወሻ ያዝ” አሉት ረዳታቸውን፡፡
ረዳቱ በንዴት ጦፈ፡፡ ይባስ ብሎ ሌላ እስረኛ ደግሞ፡-
“ናይት ክለብ ይቋቋምልን” በማለት ጠየቀ:: እሳቸውም እንደቅድሙ ረዳታቸውን “ጻፈው” አሉት፡፡ በዚህን ጊዜ ረዳታቸው ትዕግሥቱ አለቀና፤ “እንዴት ነው ጓድ? እስረኞች’ኮ ናቸው” ቢላቸው፣ የነቢይ መልስ ነበር የሰጡት፡፡ ምን ይሆን  ያሉት?
***
“…Them, who feared the monuments they left us from which today you can’t tear your gaze”
ከዓይናችን አንነቀል ያሉት
የነፃነት ሃውልቶች ታሪክ
አባቶቻችን የገነቡት ነው
በደም ባጥንታቸው ልክ!
ኤቨርግ ኤሚን
(አርመናዊ ፀሐፊ)
ትላንትናና ያለፉት ቀናት ለአረጋውያን የተሰየሙ ነበሩ፡፡ አንዳንዶች በደንብ አክብረውታል፡፡ ታላላቆችን ማክበር ራስን ማክበር ነው፡፡ የዕድሜ ባለፀጋ ሆኖ መኖር፣ ታላቅ ሆኖ መታየት የማይፈልግ ማን አለ?
ወዳጄ፡- ታሪክ በሰዎች፣ ሰዎች በጊዜ ይሰራሉ፡፡ እንደ ሳሙና ዓረፋ ብልጭ ድርግም ቢል ወይ እንደ ጥፋት ውሃ በአደጋ ቢቆራረጥም፣ ጊዜ እስካልቆመ ድረስ ታሪክ አይስተጓጐልም፡፡ ጊዜ ደግሞ ሰው እስካለ ድረስ አይቆምም፡፡ ጊዜ የሚቆመው “በሰዓት ፍሬም” ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃ ደግሞ ታሪክ፣ ተረት፣ ዕምነት ባህል -- የምንላቸው ተወራራሽ የሃሳብ፣ የዕውቀትና የልማድ ጅረቶች ያለ ማቋረጥ እየፈሰሱ፣ እኛ ካለንበት ትውልድ ደርሰው በማየታችን ነው፡፡
ወዳጄ፡- በዛሬው ዕለት እንኳ በየሆስፒታሉ፣ በየጐጆውና በሌሎች ቦታዎች የተወለዱትን ህፃናት ስናስብ፣ “ወዘተ” እንደምንለው የዓረፍተ ነገር መጨረሻ፣ የትውልድን ቀጣይነት ያረጋግጡልናል:: ታላቁ አርስቶትል፡- “ሰዎች ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ:: ሰው ግን ለዘለዓለም ይኖራል” እንዳለው፡፡ ነገም ተነገ ወዲያም ተመሳሳይ የምጥ ለቅሶዎች ይኖራሉ:: ህይወት የምትፈለቀቀው ከጭንቅና ከመከራ ውስጥ ነው፡፡ እውነትም ከሃሰት የምትለየው በትግል እንደሆነው ሁሉ!!
ስርኑ ውስጥ የተደላደሉት ቆሻሻዎች ካልተጠረጉ አዲስ የተወለደ ልጅ፣ ራሱን ችሎ በነፃነት መተንፈስ ያስቸግረዋል፤ “ዳዴ” ለማለትም ድጋፍ ያስፈልገዋል:: በፊደል ሰሌዳ ላይ “ሀ” ብለን ከጭለማ ለመውጣት ስንውተረተር፣ አጋዥ እንዳስፈለገን ሁሉ፣ እዚህ ያደረሰንን የእውነት ጐዳና ምስጢር ለማስረዳትም የዕውቀት ድጋፍ ያሻናል፡፡
የታሪክ መፃህፍት ከተደበቁበት ወጥተው እንዲነበቡ፣ በህይወት የሚገኙ ታላላቅ ሰዎች ወደ እናት ተፈጥሮ ከመመለሳቸው በፊት ከያሉበት ተፈልገው ምስክርነታቸውንና ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ መወትወት ያስፈልጋል፡፡ የአረጋውያንን ቀን ማክበር አንደኛው የማትጊያ ደወል ነው፡፡
ወዳጄ፡- የትናንት አማጪዎች የዛሬ መጪዎች፣ የዛሬ መጪዎች፣ የነገ አማጪዎች ናቸው፡፡ የዛሬው “ቀን” የተወለደው፣ እነሱ ከሰሩት “ትናንት” ማህፀን ነው፡፡
“ይኼኔ አንድ ቦታ፣ አንድ ሰው፣ ከረዥም ጊዜ በፊት፣ አንድ ቦታ ላይ በተከለው ዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብሏል፡፡” (Someone sitting in the shade today because someone planted a tree longtime ago) ይለናል፤ ዋረን በፌ፡፡ በበጋው ፀሐይ፣ ብሔራዊ ቴአትር መናፈሻ ጐራ ብለን፣ ቡና ስንጠጣ አይቶናል እንዴ?
ወዳጄ፡- አገር መስራት “ሂደት” ነው ሲባል፣ ዛሬ ከትናንትናው፣ ልጅ ካባቱ የተቀበለውን “መልካም ነገር” አሳምሮና አስፋፍቶ፣ “አጓጉሉን” ዳግም አስወግዶ፣ ለመጪው የሚያሳልፍበት የታሪክ ውል፣ በስራ የሚገለጥ የአደራ ጥልፍ ነው፡፡
ስራ መስራት ማለት ጊዜያችንን ከዕድሜአችን ላይ እየቀነስን መስጠት ማለት ነው፡፡ ስራው ደሞዝ ወይም ክፍያ የሚያስገኝ ከሆነ ደግሞ ዕድሜያችንን እየሸረፍን፣ እየሸጥን እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል:: በትንሽ ጊዜ ብዙ ስራ፣ በረዥም ጊዜ ትንሽ ስራ እንሰራ ይሆናል:: የመጠንና የዓይነት፣ ጠቃሚና ርካሽ የመሆን ጉዳይ እንጂ ያለ “ጊዜ” የሚሰራ ስራ የለም፡፡ ጨዋታና ቧልትም ቢሆን፡፡
ጊዜ ዕድሜም ጉልበትም ነው፡፡ አእምሯችን የሚያመነጨው የማሰብ ሃይል ጉልበት ሆኖ፣ በህዋሳቶቻችን በኩል በተለያየ ስሜትና መንገድ ይገለጣል፡፡ በስራ፣ በሳቅ፣ በለቅሶ፣ በጨዋታ፣ በጠብ፣ በፀሎት፣ በፍቅር በዕውቀትና በመሳሰሉት:: ብቻውን ለረዥም ጊዜ የሚቆይ፣ ሱባኤ የገባ ወይ ቅብዓ ቅዱስ ተቀብሎ አርፎ የተቀመጠ ሰው እንኳ ቀኑን ሙሉ ተቆጥቦ ከዋለው ወይም እንዳያደርግ ከተከለከለው ነገር ለተመልካቹ የራቀ ይመስለዋል እንጂ ሰውየው “እስካሰበ” ድረስ ኢነርጂው፣ ሌሊትም ቢሆን፣ በህልሙና በቅዠቱ ውስጥ መገለጡ   አይቀርም:: ይህ ካልሆነ ሰውየው “ሞቷል” ማለት ነው፡፡ እንደ አሮጌ ባትሪ ድንጋይ ወይም እንደተቃጠለ አምፖል ይጣላል፡፡
ወዳጄ፡- የዕድሜን ጉዳይ ያነሳነው የመጀመሪያው ሃሳባችን ወደ ሆነው የአረጋውያን ጉዳይ እንዲመልሰን ነበር፡፡ አረጋውያኑ አገር ሰጥተውናል፤ት/ቤት ሰርተውልናል፤በፍቅር በመቻቻልና በመተጋገዝ የደረጀ ማህበራዊ ኑሮ አውርሰውናል፤ ዛፎች ተክለውልናል፡፡ ዛሬ ላይ ያሉት እነሱ ግን ተቸግረዋል::ሔሪተጅ የተባለ ድርጅት ባጠናው ጥናት፤ ከ10 ሚሊዮን በላይ ዐቅመ ደካማ አረጋውያን በአገራችን ይገኛሉ:: ከነዚህ ውስጥ “እዚህ ግባ” የማይባል ጡረታ የሚከፈላቸው 17% ያህሉ ናቸው:: ሌሎቹ በምፅዋትና እንደ ሜቄዶኒያ ዓይነት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በሚያደርጋቸው ሰብዓዊ ድጋፍ የሚተነፍሱ ናቸው፡፡ ጥሪው፡- ለነዚህ አረጋውያን የምንሰጠው ክብርና ምስጋና እንዳለ ሆኖ፣ ከንፈር ከመመምጠጥ ባሻገር ዐቅም የፈቀደውን ዕርዳታ እናክልበት፤ ችግሩን ከተሸከሙት ጥቂት ሰብዓውያን ግብረሰናይ ድርጅቶች ትከሻ ላይ ቀለል እናድርገው የሚል ነው፡፡ “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው…” እንደሚባለው፡፡
***
ወደ ቀልዳችን ስንመለስ፡- የሊቀ መንበሩ ረዳት፣ ሰውየው የተጠየቁትን ሁሉ “እሽ ይሟላል” በማለታቸው ተናዶ፣ “እንዴት እንዲህ ይሆናል? እስረኞች’ኮ ናቸው” ሲላቸው፣ የመለሱለት ምን መሰላችሁ?
 “ማን ያውቃል? እኛም እንገባበት ይሆናል” ብለው ነበር፡፡
“አረጋውያንን እናግዝ” ስንል፣”ነግ በኔ” ማለታችን እንደሆነ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ አገር ካደገ ከቢጤዎቻችን በስተቀር ማን ቁጭ ብሎ ያጫውተናል?
እናም ወዳጄ፡- “Action speaks better than words” መባሉን ታውቃለህና አስብበት!!
ሠላም!!

Read 1057 times