Saturday, 24 August 2019 14:26

ጥበብን ፍለጋ - ከኢትዮጵያ እስከ ጀርመን

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ተወልዳ ያደገችው ጎጃም ውስጥ ነው፡፡ ትምህርቷን እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በትውልድ ቀዬዋ ከተከታተለች በኋላ ለስነ-ጥበብ ባላት ጥልቅ ፍቅር
የተነሳ፣ እ .ኤ.አ በ 1979 ዓ .ም. ወደ አዲስ አ በባ በመምጣት፣ በጊዜው ‹‹አለ የስነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት››ን የተቀላቀለች ብቸኛዋ ሴት እንደነበረች
ታስታውሳለች፡፡ እውቆቹ የሥነ ጥበብ መምህራን በቀለ መኮንን፣ መዝገቡ ተሰማ፣ ታደሰ መስፍንና ሌሎች ምርጥ የጥበቡ ልሂቃን ለአራት አመታት
አስተምረዋታል - ሰ ዓሊ የእናት ፋንታ አባተ፡፡ በኤችአይቪ/ኤድስ ዙሪያ በወጣ የስዕል ውድድር ማሸነፏን ተከትሎም፣ ወደ በጀርመን ነፃ የትምህርት
ዕድል የማግኘት አጋጣሚን ፈጠረላት፡፡ ከዚያስ? ሰዓሊዋ ትተርክልናለች፡፡ በአሁን ወቅት ኑሮዋን በሀምቡርግ ከተማ፣ ከጀርመናዊው ባለቤቷና
ሁለት ልጆቿ ጋር ካደረገችው እውቋ ሰዓሊ የእናት ፋንታ አባተ ጋር፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ ሰዓሊዋ ለአራተኛው ፕሮጀክቷ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ተመልሳለች፡፡


          በጀርመን አገር የትምህርት ዕድል ያገኘሽው እንዴት ነበር?
የውጭ ዕድሉን ያመጣው አጋጣሚ ከመፈጠሩ በፊት በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጬአለሁ፡፡ ለምሳሌ ገና አርት ስኩል ለመግባት አዲስ አበባ ስመጣ፣ ከቤተሰብ ጀምሮ እንደማይሆንና እንደማይቻል ነበር የሚነግሩኝ፡፡ ያንን ፈተና አልፌ ደግሞ ከክፍለ ሀገር አዲስ አበባ መምጣት ከባድ ነበር፡፡ በሴትነትሽ፣ በወጣትነትሽ ከለመድሽው አካባቢ ወደ አዲስና ትልቅ ከተማ ስትመጭ፣ ሌላ ጫና አለው፡፡ ወደ አርት ት/ቤት ለመግባትም ፈተና ነበረው፡፡  ታደሰ መስፍን ነው ድሮይንግ ሰርቼ እንዳልፍ የረዳኝ፡፡ ትምህርቴን ለአራት አመት ከ14 ወንዶች ጋር ብቸኛዋ ሴት ሆኜ ከተከታተልኩ በኋላ፣ መጨረሻ ላይ አንድ ውድድር መጣ፡፡
ምን አይነት ውድድር?  
እኔ አርት ት/ቤት በነበርኩበት ጊዜ ኤችአይቪ/ ኤድስ በጣም ተስፋፍቶ፣ የዓለም ራስ ምታት የሆነበት ጊዜ ነበር፡፡ እናም ውድድሩ በቀይ መስቀል በኩል መጣ - ዓለም አቀፍ ውድድር ሆኖ:: በዓለም ያሉ ወጣት ሰዓሊያን ኤችአይቪ/ኤድስን እንዴት ይገነዘቡታል? እንዴትስ ይረዱታል? በሚል የምንረዳበትን መንገድ በስዕል መግለጽ ነበር - ውድድሩ፡፡ ስዕሉ በውድድሩ አሸናፊ ከሆነ ደግሞ የኤችአይቪ ማስተማርያ ፖስተር እንደሚሆንም ተነግሮን ነበር፡፡ እኔም ታዲያ ተወዳደርኩና በአጋጣሚ አሸነፍኩኝ፡፡
በውድድሩ ማሸነፍሽ ነው የስኮላርሺፕ ዕድል ያስገኘልሽ?
በውድድሩ የተነሳ ቀጥታ ስኮላርሺፑን ባላገኝም፣ ማሸነፌ ግን የከፈተልኝ መንገድ ስለነበር ነው ወደ ጀርመን በስኮላርሺፕ የሄድኩት፡፡
ጀርመን ከሄድሽስ በኋላ… ነገሮች ቀለሉሽ ወይስ ከበዱሽ?
ጀርመን እንደገባሁ ወደ ሃይድልበርግ ነው የሄድኩት፡፡ የታወቀ ዩኒቨርሲቲ የሚገኝበት ግዛት ነው፡። ነገር ግን እዚያ አገር በእንግድነት ስትሄጂ፣ ዩኒቨርሲቲ ከመግባትሽ በፊት የደች ቋንቋ መማር አለብሽ፡፡ እኔም ለሁለት ዓመት ተኩል ቋንቋውን ተምሬ ከጨረስኩ በኋላ የማጠቃለያ ፈተና አለ:: ፈተናው አንድ የውጭ ዜጋ ዩኒቨርሲቲ ከመግባቱ በፊት ማሟላት ያለበት ሲሆን ‹‹P and S ›› ይባላል:: እሱን በብቃት አጠናቅቄ በሀምቡርግ ‹‹ሆህ ሹለ ፊወር ቢልደንደ ኩንስት›› ዩኒቨርሲቲ ገባሁ፡፡ የአርት ት/ቤት ነው፡፡ እዚህ ዩኒቨርሲቲ ከመግባቴ በፊት ግን ሁለት የአርት ት/ቤቶች ለመግባት ተወዳድሬ ነበር፡፡ አንደኛው ት/ቤት እዚህ ኢትዮጵያ እያለሁ የተማርኩትን አይነት ትምህርት የሚያስተምር ነው፡፡ ለምሳሌ ግራፊክስ ዲዛይን፣ ሚዩራል፣ አርት ስካልፕቸርና (ቅርጻ ቅርስ) የመሳሰሉት ኮርሶች የሚሰጥበት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ አንድ አርቲስት ተመርቆ ስራ ሲይዝ፣ እንደ ማስታወቂያና ኢለስትሬሽን የመሳሰሉትን የሚሰራበት ዘርፍ ነው፡፡
ሁለተኛው፤ በአርት ብቁና የመጨረሻ ደረጃ የምትደርሺበት፤ አርቲስት የምትሆኝበትን አቅም የሚያስታጥቅሽ ነው፡፡ ከእነዚህ ከሁለቱ በፊት ደግሞ ሀይድልበርግ እያለሁ ለአንድ ዓመት ፔዳጎጂ የሚባል ትምህርት ተምሬአለሁ፡፡ አርትን የማስተማር ዘርፍ ነው፡፡ ግን ይሄ መንገዴ አለመሆኑን ሳውቅ፣ ትቼው ሌሎችን መወዳደር ጀመርኩት፡፡ እኔ በአርት ብቁ ደረጃ ላይ መድረስና መሳል እንጂ የማስተማር ፍላጎት አልነበረኝም፡፡ ስለዚህ ቀደም ሲል ወደ ጠቀስኩልሽ ዩኒቨርሲቲ ሀምቡርግ መጣሁ፡፡ እዚያ ከመጀመሬ በፊት አንድ ፕሮፌሰር አገኘሁና ምን ማድረግ እንዳለብኝ መከሩኝ፡፡ ከዚያ ኮንሴፕቹዋል (Free art) በሚባል ዘርፍ ትምህርቴን ጀመርኩኝ:: የመግቢያ ፈተናውን አለፍኩኝ፡፡ ያለፍኩት ግን ለአንድ አመት ብቻ ነው፡፡   
እንዴት ለአንድ አመት  ብቻ?
ዩኒቨርሲቲውን በመግቢያ ፈተና ስትቀላቀይ፣ ለአንድ አመት የሚቀጥል ፈተና አለ፡፡ ያ ፈተና ምን መሰለሽ? በተለይ ከተለያየ አገር መጥተን በዩኒቨርሲቲው የገባን ተማሪዎች… “ትክክለኛ አርቲስቶች ናቸውን?” ወይስ “በስሜት ተገፍተው ነው?” በእርግጥ “ዝንባሌያቸው ምንድነው?” የሚለውን ለማወቅ በተለያየ መንገድ የሚፈትኑበት ወቅት ነው፡፡ ዝንባሌያችን በደንብ ይጠናል:: ትክክለኛ የአርት ዝንባሌ ሳይኖርሽ እዚያ ዩኒቨርሲቲ ከገባሽ መቀጠል አትችይም፡፡ ይሄ ደግሞ እዚህ ኢትዮጵያ የለም፡፡ አሁንም በአርቲስቱ ላይ የማያቸው ክፍተቶች እነዚህ ናቸው፡፡ ወደ አርት ከመግባት በፊት ትክክለኛ ፍላጎትን ማጤንና መለየት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ እዚያ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ አመት ያሳለፍነውን ብነግርሽ…ከባድ ፈተና የነበረበት ነው፡፡ ድንገት ፕሮፌሰሩ ወደ ክፍል ይገባና ያይሻል:: እውነት አንቺ ትክክለኛ አርቲስት ነሽ? ይህን ዘርፍ የመረጥሽው ለምንድነው? አንቺ የመጣሽው ከአፍሪካ ነው፤ ለምንድነው ህክምና የማትማሪው? እያለ ይጠይቅሻል፡፡ ያኔ በትክክል አርት በውስጥሽ ካለ፣ እነሱ የሚሉት ሳያስከፋሽ፣ ሞራልሽ ሳይነካ በጽናት ትቀጥያለሽ፡፡ ያለዚያ ግን አቋርጠሽ ትወጫለሽ:: ከተለያየ አገር የመጡ፣ ከእኔ ጋር የነበሩ ልጆች ተበሳጭተው፣ ትምህርቱን አቋርጠው የወጡ አውቃለሁ፡፡ “ከደሃ አገር መጥተሽ አርት መማር ቅንጦት አይደለም ወይ?›› አይነት ስነ-ልቦናዊ ጫና ያሳድሩብሻል፡፡ ‹‹እንደውም አስቡበትና እደሩ፤ ይሄ ካልሆነላችሁ ሌላ ትመርጣላችሁ” ይሉን ነበር፡፡
ለእኔ ያ አንድ አመት፣ የአርት ትክክለኛ ፍቅርና ፍላጎት እንዳለኝ ያስመሰከርኩበት ወቅት ነው ማለት እችላለሁ፡፡
ከዚያስ ቀጠልሽ?
ከዚያ በኋላ አንዱን አመት በብቃት አሸንፌ ትክክለኛ ተማሪ ሆኜ ቀጠልኩ፣ አምስት አመት ተምሬም ጨረስኩኝ፡፡ እኔ አገሬ ላይ የነበረኝ መሰረት፣ ጥንካሬ የሰጠኝ ይመስለኛል፡፡ ከዚያ ደግሞ ለማስተርስ ወደ አራት አመት ገደማ ተምሬ ተመረቅኩኝ፡፡
“Free art Felega” የተሰኘውን ወደ ኢትዮጵያ እየመጣሽ የምትሰሪውን ፕሮጀክትም የጀመርሽው እዚያው ሀምቡርግ እያለሽ ነበር… እንዴት ሃሳቡ ተጠነሰሰ?
አንድም የትምህርት ጊዜዬን ያራዘመብኝ ይህንን ፕሮጀክት ትምህርት ላይ እያለሁ መጀመሬ ነው:: የመጀመሪያውን ‹‹ፍሪ አርት ፍለጋ›› የጀመርኩት በ1996 እ.ኤ.አ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት የተጀመረው እዚያው ተማሪ እያሉ በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ላመጡ የውጭ አገር ዜጎች በሚሰጥ እድል ነው:: በእነሱ ቋንቋ ‹‹ዲትስ ኢሽቲፍቱንግ›› ይባላል፡፡ ይህን የፕሮጀክት ዕድል ተጠቅሜ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ማሰቤን ሲሰሙ፣ ቅድም የጠቀስኩልሽና ሌሎችም መምህሮቼ ጉጉትና ፍላጐት አደረባቸው:: እኔ እዚያ የተማርኩትን ከእዚህ አገር የአርት ተማሪዎች ጋር በፎቶና በቪዲዮ… የልምድ ልውውጥ ማድረግ ጀመርን፡፡ በአገራችን አርት ተስፋና ተግዳሮቶች  ዙሪያ ከተማሪዎችና ከመምህራን ጋር ተወያየን፡፡ እዚህም ያለውን ልምድና እውቀት ወሰድኩኝ፡፡ አውሮፓ በአርት በኩል የት ደረሱ? የአፍሪካ አርቲስቶችስ? የሚለውን በደንብ ተወያየንበት፡፡ የልምድ ልውውጡም ‹‹በአለ የስነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት›› ነበር የተካሄደው፡፡ ይህንን ውይይትና የልምድ ልውውጥ ወደ ጀርመን ይዤው ሄድኩና፣ ጀርመን ላሉ መምህሮቼ በትልቅ ፕሮጀክተር  አጠቃላይ ሂደቱን አስቃኘኋቸው። ከዚያ በኋላ ‹‹አሃ አርት ት/ቤትም አላችሁ ማለት ነው?›› አሉ፡፡ ይህንን ሲያውቁልኝ እኔም ደስ አለኝ፡፡ ምክንያቱም እነሱ ኢትዮጵያን በአብዛኛው የሚያውቋት በድህነትና በረሃብ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ሲያዩ እንድቀጥልበት አደረጉ፡፡
ሁለተኛውን ‹‹ፍሪ አርት ፍለጋ›› ከጎተ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ነበር ያካሄድሽው…
ትክክል ነው፡፡ የመጀመሪያውን ፕሮጀክት ጎተዎች ሲሰሙ በጣም ነበር የተደነቁት፡፡ ‹‹ከአሁን በኋላ አንቺ ነሽ ድልድያችን›› አሉ፡፡ ስለዚህ እኔ እዚያ ኤግዚቢሽን የማዘጋጅበትን የራሴን ጥቅም እየተውኩ፣ ወደ አገሬ ነበር የምመጣው፡፡ እናም በአንደኛው ‹‹ፍሪ አርት ፍለጋ›› ላይ የአርቲስቶቻችንን ብቃትና እውቀት አየሁ፤ ግን ደግሞ ቀለም፣ ብሩሽ፣ ሸራ የላቸውም፤ የተመቻቸ ነገር አልነበራቸውም፡፡ አይቼ ነበር የሄድኩት፡፡ ስለዚህ ለሁለተኛ ጊዜ ስመጣ ቀለም፣ ብሩሽ፣ ሸራ፣ ፍሬምና መሰል ቁሳቁሶችን በኮንቴይነር አስጭኜ መጣሁ፡፡
እንደነገርኩሽ አለ የስነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ልናካሂድ ስንል፣ ጎተዎች ሰምተው ‹‹እባካችሁ እኛ ጋ አድርጉት›› አሉን፡፡ ያን ጊዜ የጎተ ኢንስቲትዩት መክፈቻ ሥነ ሥርዓትም ነበር፡፡ ስለዚህ እነሱ ጋ አዘጋጀን፡፡ በርካታ ሰዓሊያን ነበሩ የተሳተፉበት:: ተመዝግበው ለሌላ ጊዜ ያቆየናቸውም ነበሩ - በቦታ ጥበት፡፡ ስኬታማ ፕሮጀክት ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ እነዚህ አርቲስቶች ያንን ቀለምና ብሩሽ ተካፍለው፣ ማቴሪያል ሳይገድባቸው ነፃ ሆነው፤ በስዕል ሀሳባቸውን እንዲቀልፁ ነበር አላማችን:: ከብሩሽና - ከቀለሙም ባሻገር እኔ የምማርበት አገር ያሉ ትልልቅ ሰዓሊያንን ታሪክ ይዤ ነበር የመጣሁት:: ከየት ተነስተው በምን አይነት ጥረት የት ደረሱ? የሚለውንም እንዲያውቁ ተወያየንበት፡፡ በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነው ያሳለፍነው፡፡ በሶስተኛው ‹‹ፍሪ አርት ፍለጋም›› የአገሬ አርቲስቶች የማቴሪያል ጥረት ሳይገድባቸው፣ በአገራቸው በሚገኝ ቁሳቁስ እንዴት አርትን መስራት ይችላሉ የሚለው ላይ ነው ያተኮርኩት፡፡ ምክንያቱም ሁልጊዜ ቀለም፣ ብሩሽ፣ ሸራና ፍሬም ከጀርመን መጥቶ አይቻልም፤ አይሆንምም፡፡ ስለዚህ ምን ማድረግ አለብን? የሚለውን አስበን፣ ከአስተባባሪዋ ጋር ሆነን መርካቶ ምናለሽ ተራ ሄድን፡፡ እዚያ ስንሄድ ለአርት የማይሆን ነገር የለም፡፡ ለቅርጽ ስራ፣ ለፎቶግራፍ፣ ሁለገብ የሆነ ብዙ ቁሳቁስ አገኘን፡፡
ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ‹‹ፍሪ አርት ፍለጋ››ን ለማዘጋጀት ነው የመጣሽው፡፡ (ቃለ ምልልሱ ከሁለት ሳምንት በፊት ነው የተደረገው) በዘንድሮው ላይ ‹‹ማንነት›› የሚል ሃሳብ ተጨምሮበታል፡፡ ከውይይቱና ከኤግዚቢሽኑ ባሻገር ደግሞ በመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የጀመርሽው ነገር እንዳለ ሰምቻለሁ…
መልካም! ‹‹ፍሪ አርት ፍለጋ ሶስት›› ካለቀ በኋላ ብዙ በአዕምሮዬ የሚመላለሱ ነገሮች ነበሩ:: ከመጀመሪያው እስከ ሶስተኛው ባካሄድነው ‹‹ፍሪ አርት ፍለጋ›፤ የአርቲስቶቹን አጠቃላይ ሁኔታ ስገነዘብ፣ ብዙ የማንነት መዛባቶችም ተመልክቼ ነበር፡፡ እና እንደገና ሀላፊነት ተሰማኝ፡፡ እነዚህ ልጆች ማንነታቸውንና መንገዳቸውን መያዝ አለባቸው:: አዲሱ ትውልድ መንገዱን እንዲይዝ ደግሞ እኛ ሀላፊነታችንን መወጣት አለብን በሚል ነው - ‹‹ፍሪ አርት ፍለጋ ማንነት›› ያልነው፡፡ ውይይቱ በጎተ ኢንስቲትዩት ሀምሌ 30 የተካሄደ ሲሆን የተሳታፊዎች የስዕል ኤግዚቢሽን ደግሞ በሳምንቱ ማክሰኞ ነሐሴ 7 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ አለ የስነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ተካሂዷል፡፡
የመቄዶኒያን በተመለከተ አርት ቴራፒ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው፡፡ አርት የአዕምሮንም ሆነ የአካልን ህመም ማከም ይችላል የሚል እምነት አለኝ:: ስለዚህ ባለፈው አንድ ወር ገደማ፣ በመቄዶኒያ ከአለ የአርት ተማሪዎች ጋር በመሆን ስልጠና ስንሰጣቸው ነበር፡፡ አሁን የሚሰሩትን ብታይ ማመን ያቅትሻል፡፡ ‹‹እኛም እንችላለን›› የሚል መንፈስ አሳድሮባቸዋል፡፡   በሌላ በኩል፤ በማዕከሉ ትልቅ አዳራሽ ለኤግዚቢሽን ስለተሰጣቸው፣ በመቄዶኒያ ለመጀመሪያ ጊዜ አርት ኤግዚቢሽን ይካሄዳል:: ብሩክ የሺጥላና እስራኤል የተባሉ ጎበዝ አካል ጉዳተኛ አርቲስቶችንም አካትተናል፡፡ ይሄ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ለትንሽ ጊዜ በወሰዱት ስልጠና ያሳዩትን ፍላጎትና ብቃት ስመለከት ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ አርት ማከም እንደሚችል ያስመሰከረ ነው፡፡ ኤግዚቢሽኑ በሜቄዶኒያ ነሐሴ 12 ቀን 2011 ተካሂዷል፡፡
140 የዓለም ሰዓሊያን አገራቸውን የሚወክል ስዕል ሰርተው፣ ስዕላቸው ዓለምን እየዞረ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ ከእነዚህ አርቲስቶች መካከል አንዷ ደግሞ አንቺ ነሽ፡፡ እንዴት ተመረጥሽ?
በፈረንጆች ሚሊኒየም ወቅት ጀርመን ያዘጋጀችው አንድ አለም አቀፍ ፕሮግራም መጣ:: ከዚያ ‹‹አገራችሁን የሚወክልና ዓለምን የሚዞር ሥራ ስሩ›› ተብለን በኤምባሲ በኩል ተጠየቅን፡፡ እያንዳንዱ ኤምባሲ የራሱን አገር አርቲስት ወከለ:: ጀርመን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም እኔን ወከለኝ ማለት ነው፡፡ ያኔ እኔ ተጠይቄ ስሰራ 120 አገራት ብቻ ነበሩ የተወከሉት፡፡ አሁን 140 ደርሰዋል። ከእንግሊዝ፣ ከአሜሪካ፣ ከካናዳ፣ ከአፍሪካም ሁሉ ተሳትፈዋል፡፡ ስዕሉ በዓለም ሲዞር፤ እንዴት ነው ኢትዮጵያን የሚገልፅልኝ የሚለው ጉዳይ ከፍተኛ ሀሳብ የሚጠይቅ ነበር፡፡ ሀሳቡ ከባድ ስለሆነ፣ እሺም እምቢም ለማለት ተቸግሬ ነበር፡፡ ለውጤት ያበቃኝ ቆራጥነት ነው፡፡ የተጠየቅኩት በአገሬ ኤምባሲ በመሆኑ መጨከን አለብኝ አልኩኝ፡፡ የከበደኝ ለምን መሰለሽ? እኔ ስማርም ስሰራም የነበረው ነፃ አርት ነው፡፡ የመጣልኝን ሀሳብ ነው በስዕል የምገልጸው እንጂ በትዕዛዝ መስራት ብዙም አላውቅም ነበር:: ነገር ግን እኔ ካልሰራሁት ማን ሊሰራልኝ ነው አልኩኝ፡፡ ኤምባሲም በኋላ ይቆጭሻል አሉኝ፡፡ ሁለተኛ ሥዕሉ ጀርመን ውስጥ አይቀርም፤ አለምን ከዞረ በኋላ መጨረሻ ላይ ኒውዮርክ ሄዶ፣ በጨረታ ተሸጦ ለዩኒሴፍ ገቢ ይሆንና ለሕጻናት መርጃ ይውላል ሲባል፣ ዓላማው ይበልጥ አነሳሳኝ፡፡ አገሬን ይወክላል ያልኩትን ስዕል፤ ጀርመኖችን የሚወክለው የድብ ምስል (ቢር) ላይ ሳልኩኝና አሁን አለምን እየዞረ ነው፡፡ በእኛ ሚሊኒየም ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል ተብሎ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ብዙ ነገሮች ሳይመቻቹ ቀሩ፡፡ እስካሁን አውሮፓን እየዞረ ነው:: በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል፡፡  በነገራችን ላይ የኢትዮጵያንና የጀርመንን የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ ከምኒልክ ዘመን ጀምሮ የሚያሳይ ስዕል እዚሁ ድብ ላይ ሰርቼ፣ አሁን ጀርመን ኤምባሲ ውስጥ ይገኛል:: እስካሁን አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያና ሌሎችም ትልልቅ ሰዎች ጎብኝተውታል፡፡ ግን ብዙ ሰው ስለዚህ ሥዕል አያውቅም፡፡

Read 1451 times