Saturday, 24 August 2019 14:31

ጥላ ፍለጋ

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(3 votes)

 የህይወትን ብርታት ሳውጠነጥን እነሆ ዘመናት ተቆጠሩ፡፡ በርግጥ የዛሬው ስሜቴ ይለያል፡፡ ከምጎነጨው ድራፍት ጋር ተዋህዶ ወደ ውስጤ እየገባ ያለውን የነገር ቋት መረዳት አለመቻሌ ነው፤ ክፋቱ፡፡ የሚለቀቀው ሙዚቃ የራሱ የሆነ ሚና ቢኖረውም፤ ህመሜን የማናር እንጂ የመረጋጋት ሀይል አላጎናፀፈኝም፡፡ የሰው ግርግርም፤ እንዲሁ:: የስሜት ንረት ጥጉን ቀድሜ ስለምገነዘብ፣ ምልከታዬ ላይ እየተጨነቅሁ አስታምማለሁ፡፡
የሚገርመው፤ .. “መገፋት ደግ ነው!” ትል ነበር፤ አያቴ፡፡ እንዲያው... በዚህ ሰሞን፣ ከያቅጣጫው የሚወረወረው በትር መብዛቱ::  አህያ አይደለሁ፤ በጅብ ጩኸት የምፈርስ፡፡ እንዲያው ለመሆኑ ውስጥ ውስጡን እየተሹለከለከ፣ ነገር የሚተበትበውን የሰው አውሬ፤ ማለቴ ነው፡፡
ነገርን ነገር ያነሳው የለ ፤ በደርግ ዘመን ነው አሉ!... ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ ኢህአፓ ሆኖ በተጠመቀበት ሰሞን፣ የፓርቲውንም ሆነ የአባላቱን ስም በማጉደፍ ላይ የተጠመዱ የመንደር አለሌዎችና ጠንካራው የደህንነት መዋቅር፣ በፅንፈኞች እጅ ወድቆ ባልተገባ ሁኔታ አገልግሎት ሰጡ፡፡ ይህንን ስውር ደባ ለማምለጥ ሲሉ አባላቱ፣ ለህፃናት በየለቱ የጨርቅ ኳስ እየሰፉ ይሰጧቸው ነበር፡፡ ታዲያ ቀን በቀን አዳዲስ ኳስ የሚያገኙ ህፃናት፣ የትም ምንም ቢላኩ ደስተኞች ነበሩ... ይባላል፡፡ በርግጥ መልዕክቱም፣ የነገ ኳሳችሁን የሚሰጧችሁ አቶ “እገሌ” ናቸው፤ እንደ ልባችሁ ተጫውታችሁ ስትጨርሱ፣ ትሰጧቸውና፣ አዲስ ኳስ ሰፍተው ይሰጧችኋል...ይባላሉ...አሉ:: በፍቅር ያደርጉታል፤ ህፃናቱ፡፡ በዚህ መንገድ የኢህአፓ አባላት በኳሱ ውስጥ ደብዳቤ ይለዋወጡ ነበር፡፡ ሀገር በቀል የመረጃ መረብ እንበለው?
እና’ማ ...ሀገር ለማቆም በስውር ሰሩ፡፡ ለእኔ ግን፤ ሀገር... የኢህአፓን ኳስ ትመስላለች፡፡ ከአባት ለልጅ የምትበረከት ውድ ስጦታ፤ በስስትና በስጋት የተሞሸረች፡፡ በውስጧ ህልውና የቋጠረች:: ስስቱ የሚመነጨው ከሁለቱም ወገን ሲሆን ስጋቱ ግን የአቀባዩ ብቻ ይመስለኛል፡፡ እውን በትክክል ተጫውቶ ለቀጣዩ ያስረክብ ይሆን!!? የሚል የተደበላለቀ ስጋት፡፡  ሀገሬ እንደዚያ ናት፡፡
ሳስበው ...ሳስበው ኳሱዋ ሀገሬ ናት፡፡ ልክ እንደ እንቁላል ውስጧ ህይወት አለ፡፡ እንክብካቤ ትሻለች:: በርግጥ እንቁላሉ ከወደቀ ይሰበራል፤ ሀገርም እንዲሁ፡፡ ኳሷ ግን በእርግጫ ብዛት የበከተች፣ የተበጣጠሰችና የነተበች ብትሆንም፣ የሰው አሻራ ነውና ክብር አላት፤ ምንም ቢሆን:: እናም ሀገሬ ኳሷን ትመስላለች፡፡ ትበክታለች፤ ትታደሳለች፡፡ ውስጧ ግን ሚስጥር  አርግዟል፡፡
አንዳንዴ ሳስባት መንፈስ ትሆንብኛለች፡፡ ከውስጧ የተሸከመችውን እውነት፤ አደራ የቀረፀላት ማነው ??  ኳሷ የኢህአፓን መልዕክት ስትሰንቅ፣ ሀገሬስ የማንን ህልም ይሆን የተሸከመችው???...እላለሁ፡፡
ይገርማል!! የሴራውና የተንኮሉ ብዛት ውስጤን ቢያሳሳውም፣ ኳሷን እመስላለሁ፡፡ የውስጤን ሀቅ አዝያለሁ፡፡ እራሴ እቋጥራለሁ፤ እራሴ እፈታዋለሁ፡፡ ያው...የአለት ያክል ቢበረታም፣ የህልሜ ብርታት ያይላልና አፈራርሰዋለሁ:: ለምን ቢባል፣ ህልም ህይወት ነውና -- ርዕይ፡፡ ህልም፤ ሀገር ነውና -- ሠላም፡፡ ህልም፤ ጉዞ ነውና -- ስንቅ፡፡ ህልም፤ ባህል ነውና  --- ውህደት:: ብቻ ሀገር ህልም ናት፤ የህልምም  ህልም፡፡
የተደበላለቀ ስሜቴን ለመረዳት ያደረግሁት ጥረት፣ ጠንካራ ተብሰልስሎት ውስጥ ዶለኝ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻ ው፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2731 times