Saturday, 31 August 2019 12:40

መኢአድ ከ60 በላይ ፓርቲዎችና ምሁራን የሚሳተፉበት ጉባኤ ያካሂዳል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

መኢአድ ያለፈውን አንድ አመት የሚገመግምና የወደፊቱን የሚተልም፣ ከ60 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶችና ምሁራን የሚሳተፉበት ጉባኤ፣ ጳጉሜ 3 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ ያለፈው አንድ አመት የሀገሪቱ ፖለቲካ ጉዞና የወደፊቱን አቅጣጫ በተመለከተ በታዋቂ ምሁራን ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ይደረጋል  ተብሏል፡፡
በዋናነትም ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ስለ ሀገራቸው ያላቸውን ግንዛቤ እንዴት ማስፋት ይቻላል፣ ለትውልድ ምን እናውርስ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይትና ምክክር እንደሚካሄድ የመኢአድ አመራርና የፕሮግራሙ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል አቶ ሙሉጌታ አበበ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የሀገር ሽማሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች  ይገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በመድረኩ መሳተፍ የሚፈልጉ አካላትም መገኘት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ ሂደቶች ላይ ከሚመክረው ጉባኤ ጐን ለጐንም፣ የኪነጥበብ ስራዎች እንደሚቀርቡ አቶ ሙሉጌታ ጠቁመዋል፡፡  

Read 6254 times