Saturday, 31 August 2019 12:42

ኢዜማ በአዲስ አበባ የመጀመሪያ ህዝባዊ ስብሰባውን ዛሬ ያካሂዳል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 በአዲስ አበባና በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያወያያል

            ኢዜማ በአዲስ አበባ የመጀመሪያ ህዝባዊ የወጣቶች ስብሰባውን በዛሬው እለት የሚያካሂድ ሲሆን በስብሰባውም በአዲስ አበባና በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያይ ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ በሚካሄደው በዚህ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ እስከ 1500 የሚደርሱ ወጣቶች ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ የፓርቲው መሪዎች ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ አንዷለም አራጌና አቶ የሸዋስ አሰፋ ስብሰባውን እንደሚመሩ የኢዜማ ስራ አስፈፃሚ አባልና የወጣቶች ጉዳይ ተጠሪ ቴዎድሮስ አሰፋ ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡  
ኢዜማ ከተመሠረተ ወዲህ በአዲስ አበባ የመጀመሪያው በሆነው በዚህ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ በዋናነት ወጣቶች እንደሚሳተፉና በመድረኩ ላይ ጥሪ የቀረበላቸው ምሁራን እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡ በዚህ መድረክ ይገኛሉ ተብለው ከሚጠበቁት መካከልም ዶ/ር ምህረት ደበበ፣ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ ኡስታዝ አቡበከር ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የህዝባዊ ስብሰባው ዋነኛ አጀንዳ፣ አጠቃላይ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ መሆኑን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፤ በአዲስ አበባ ወቅታዊ ጉዳይ እንዲሁም በቀጣዩ ምርጫ ዙሪያ ከመዲናዋ ነዋሪ ወጣቶች ጋር ውይይት ያደርጋል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ፓርቲው በዛሬው ዕለት በምዕራብ አርሲ ዞን ህዝባዊ ስብሰባ የሚያካሂድ ሲሆን በነገው እለት ደግሞ በደሴ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባውን እንደሚያካሂድ ተጠቁሟል:: በቅርቡም በመቐሌ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ማቀዱን ኢዜማ አስታውቋል፡፡ 

Read 6821 times